>

ኦነግና ምዕራብ ኦሮሚያ ከየት ወዴት? (ኢትዮጲስ)

ኦነግና ምዕራብ ኦሮሚያ ከየት ወዴት?
ምዕራብ ወለጋ
በኢትዮጲስ ዝግጅት ክፍል የተጠናከረ
 
ምዕራብ ወለጋ የምንለው አካባቢ ነባር ስም “ቢዛሞ” ይባል እንደነበርና፣ በኋላም በኦሮሞዎች በተሰጠው ስም ቄለም ተብሎ እንደሚጠራ፤  የታሪክ ምሁራኑ ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ መስሪያ ቤት እ.ኤ.አ በ2007 ባወጣው መረጃ መሰረት፣ የምዕራብ ወለጋ የሕዝብ ብዛት 1,350,415 ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 671,538ዎቹ ወንዶች፤ 678,877ዎቹ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ 96% የሚሆነው የምዕራብ ወለጋ ሕዝብ ኦሮሞ ሲሆን፣ 1.45% የማኦ ጎሳዎች፣ 1.2 % የአማራ ብሄር ተወላጆች እና፣ 0.63 % የሚሆኑት ደግሞ የሌላ ብሄር ተወላጆች ናቸው፡፡ የሃይማኖት ስብጥራቸውም ሲታይ፣ 59.55 % ፕሮቴስታንት፣ 20.19 % ኦርቶዶክስ፣ 19.66 % እስልምና ናቸው፡፡
ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ውስጥ ባቦ ጋምቤላ፣ ቤጊ፣ ቦጂ ቾኮርሳ፣ ቦጂ ዲርማጂ፣  ጊምቢ፣ ጉሊሶ ከተማ፣ ጃርሶ፣ ቆንዳላ፣ ላሎ አሳቢ፣ ማና ሲቡ፣ ኖሌ ካባ፣ ሳዮ ኖሌ፣ ሀሩ፣ ሆማ፣ ዩብዶ፣ ነጆ፣ አይራ፣ ገንጂ፣ ኪልቱ ካራ የተባሉ ወረዳዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ደምቢ ዶሎ፣ ጊምቢ የተባሉ ከተሞችም አሉት፡፡
ምስራቅ ወለጋ
ምስራቅ ወለጋ የምንለው አካባቢ ነባር ስሙ “ዳሞት” ይባል እንደነበርና፣ በኋላም በኦሮሞዎች በተሰጠው ስም “ሌቃ” ተብሎ እንደሚጠራ የታሪክ ምሁራኑ ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ መስሪያ ቤት እ.ኤ.አ በ2007 ባወጣው መረጃ መሰረት፣ የምስራቅ ወለጋ የሕዝብ ብዛት 1,213,503 ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 606,379ዎቹ ወንዶች፤ 607,124ዎቹ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ 87.74% የሚሆነው የምስራቅ ወለጋ ሕዝብ ኦሮሞ ሲሆን፣ 10.89 % የአማራ ብሄር ተወላጆች እና፣ 1.37 % የሚሆኑት ደግሞ የሌላ ብሄር ተወላጆች ናቸው፡፡ የሃይማኖት ስብጥራቸውም ሲታይ፣ 48.42 % ፕሮቴስታንት፣ 37.04 % ኦርቶዶክስ፣ 12.09 % እስልምና ናቸው፡፡
ከምስራቅ ወለጋ ዞኖች ውስጥ ጂማ ሆሮ፣ ማና ሃሬና፣ ሲናና ዲንሾ፣ ዋሊሶና ጎሮ፣ ዋና ቦናያ፣ ያያ ጉለሌና፣ ሙላና ሱሉልታ፣ ሃዋ ውለሌ፣ የተባሉ ወረዳዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ነቀምት ትልቋ ከተማ ነች፡፡
ኦነግና ወለጋ
‹‹ኦነግ ስንት መልክ አለው?›› በሚል ከቃሊት የግል ማስታወሻው ቆንጥሮ የጻፈ ያዕቆብ ሻገላ የተባለ ሰው፣ ‹‹የቃሊቲ ቋንቋ የወለጋ ኦሮምኛ እና በጥቂቱ የአምቦ ኦሮምኛ ሆኗል ቢባል እውነታውን ይገልጻል። ይህንንም ዞን ሦስት እና ዞን ሁለት በታሰርኩባቸው ጊዜያቶች ያረጋገጥኩት ሃቅ ነው። ይህን በተመለከተ በኦነግ ምክንያት ከታሰሩ ግለሰቦች እንደተረዳሁት፣ እዚህ እስር ቤት ብቻ ሳይሆን፣ ኬኒያ ስልጠና ላይ በነበሩ ጊዜ የነበረው ከዚህ የተለየ አልነበረም። ኬኒያ ወታደራዊ ስልጠና ወሰዶ የተመለሰ የኦነግ አባል የነበረ ጓደኛዬ እንዳጫወተኝ፣ ኬንያ በሰለጠንበት ጊዜ በሥልጠናው የነበሩ በብዛት የወለጋ ኦሮሞና በተወሰነ ደረጃ ደግሞ የአምቦ ኦሮሞዎች ሲሆኑ፣ በጣት የሚቆጠሩ ደግሞ ከሸዋ እና ቦረና ኦሮሞዎች እንደነበሩ አውግቶኛል”  ሲል ፅፏል፡፡ ይህ ማስታወሻ በገሃድ ያለውን እውነታ በትክክል ያስቀመጠ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
የኦነግ ክፍፍል
ኦነግ አሁን ባለው ሁኔታ አምስት ቦታ ተከፋፍሎ ይገኛል፡፡ ይኸውም፣ በዳውድ ኢብሳ የሚመራው -ኦነግ ሸኔ፣ በገላሳ ዲልቦ የሚመራው-የሽግግር አካል ኦነግ፣ ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ ጎንፋ የሚመራው የኦነግ ክፋይ (በሌላ ስም) ፣ በጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦነግ ክፋይ( በሌላ ስም) ፣  በሌንጮ ለታ የሚመራው የኦነግ ክፋይ (በሌላ ስም)  ናቸው፡፡   ከእነዚህ መካከል፣ ትክክል ሆነም አልሆነም፣ የዳውድ ኢብሳ፣ የገላሳ ዲልቦ፣ የሌንጮ ለታ በዋናነት የወለጋ ተወላጆች የሚሳተፉባቸው እንቅስቃሴዎች እንደሆኑ ይታመናል፡፡ በአንፃሩ፣ በከማል ገልቹ የሚመራው ክፍያ የአርሲዎች ድጋፍ እንዳለው ይወራለታል፡፡  በአንዳንዶች ግምት፣ የእነ ዳውድ ኦነግ  ከክፍፍሉ በፊት ከነበረው  የኦነግ ኃይል (ደጋፊዎቹን ጨምሮ) 90 ከመቶውን፣ ቀሪዎቹ 10 በመቶውን ብቻ የያዙ ናቸው፡፡ በዚህ ስሌት፣ ኦነግ ከውጭ የሚገመተውን ያህል አልተከፋፈለም፤ ዋናው ኃይል በእነ ዳውድ ዙሪያ እንደተሰባሰበ ነው፡፡
በጥቅሉ፣ ካሉት የኦነግ ክፋዮች መካከል ትልቁ ነው ተብሎ የሚታመነው በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ መሆኑ ብዙም አያከራክርም፡፡  ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ የተደረገለት ግዙፍ አቀባበል ይህን የብዙዎች ግምት የሚያረጋግጥ ሆኗል፡፡ ገዢ ፓርቲ የሆነው የእነ ዐቢይ አህመድ ኦህዴድ/ ኦዴፓም፣ የእነ ዳውድ ኦነግ በህዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከፍተኛ መሆኑን በተቀበለ መንፈስ አስመራ ድረስ ሄዶ አነጋግሮታል፤ የሰላም ስምምነት የተፈራረሙትም እዚያው አስመራ ውስጥ በተደረገ ትልቅ ስነ ሥርዓት ነው፡፡  አሁን እየታየ እንዳለውም፣ ከኦነግ ክፋዮች መካከል የኦህዴድ/አዴፓን ስልጣን እየተግደራደረ የሚገኘው ይኸው በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ሆኗል፡፡ ይህም ለብዙዎች ትክክለኛው የኦነግ መገለጫ ሆኖ እንዲታያቸው ተጨማሪ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡
ኦነግና ኦህዴድ/ ኦዴፓ
በኦነግና በኦህዴድ/ ኦዴፓ መካከል ያለውን ግንኙነት ከኦህዴድ ምስረታ አንስቶ የተበላሸ ሆኗል፡፡ በኦነግ እይታ፣ የኦህዴድ ምስረታ ህወሓት በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ እጅን ለማስገባት የፈጠረው አሻንጉሊት ድርጅት ነው፡፡  ኦህዴድ በበኩሉ፣ ለምስረታው እንደ ምክንያት የሚያነሳው ኦነግ ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ ለመነጠል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመቃወም መሆኑን ከመጀመሪው አንስቶ ተናግሯል፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ኦህዴድ በህወሓት ጥላ ስር ቢቋቋምምና የፖለቲካ ተቀባይነቱም ውስን የነበረ ቢሆንም፣  ከኦነግ ጋር መሰረታዊ የሆነ የፖለቲካ ልዩነት አለው  ማለት ነው፡፡ ይህ ልዩነት ሁለቱ ድርጅቶች በሁለት ጎራ ተሰልፈው ለሦስት አስርት ዓመታት እንዲፋለሙ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ ሂደት አንዱ በሌላው ላይ ያስከተለው ቁስል በቀላሉ የሚሽር ሊሆን አልቻለም፡፡
በዚህም መሰረት፣ የእነ ዳውድ ኦነግ በኦሮሚያ ክልል ከወረዳ ጀምሮ ያሉ አመራሮችን በመግደልና በማፈን፣ ከታች ያለውን የመንግስት መዋቅር የማዳከም ስራ ለ6 ወራት ሲያከናውን ቆይቷል በማለት ኦህዴድ/ ኦዴፓ መግለጫ ለማውጣት ብዙም ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ከዚያ ጊዜ አንስቶ፣ መወነጃጀሉና አለመተማመኑ እየሰፋ በመሄድም ላይ ይገኛል፡፡
የኦህዴድ/ ኦዴፓ መሪዎች እንደሚሉት፣ ኦነግ በሶስት አካባቢዎች የማሰልጠኛ ካምፖችን በመክፈት ወታደሮችን እያሰለጠነ ነው። የኦሮሞ ወጣቶችን በብዛት ወደየካምፖቹ እያስገባ እንደሆነም ይነገራል። ከየመንደሩ ህጻናት ወታደሮችን ጭምር (እድሜያቸው ከ18 ዓመታት በታች የሆኑ) እንደሚመለምል የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል። በዚህ ሁኔታ፣ ከ1ሺህ የማይበልጥ ታጣቂ ይዞ የገባው የእነ ዳውድ ኦነግ፣ የሰራዊቱን ቁጥር በ10ሺዎች ለማሳደግ ተግቶ እየሰራ ይገኛል። አደጋው የታየው ኦህዴድ/ ኦዴፓም፣ ሂደቱን ከወዲሁ ለመግታት ወታደራዊ ዘመቻ ጀምሯል፡፡
በዚህ ድባብ በገላሳ ዲልቦ የሚመራው ኦነግ መግባቱ ለዳውድ ኢብሳ ጥሩ ምልክት አልሆነም።  አቶ ገላሳ  ዲልቦ መንግስታዊ ለሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ‘’ለውጡ የኦሮሞ ህዝብ የተዋደቀለት በመሆኑ ልንከባከበው ይገባል፣ ልንቀሳቀስ የሚገባውም በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው’’ ማለታቸው ለእነ ዳውድ የተላለፈ መልዕክት መሆኑን ብዙዎች ገምተዋል፡፡  የገላሳ ዲልቦ ኦነግ የዳውድን ኦነግ ምን ያህል በፖለቲካ እንደሚፎካከረው ግልፅ አይደለም፡፡ ሆኖም፣ እንዳንዳዶቹ ግምት እነ ገለሳ በምስራቅ ወለጋ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የፖለቲካ አማራጭ ሆነው ሊወጡ የሚችሉበት ሁኔታ አለ፡፡
 
የኦነግ እንቅስቃሴ በምዕራብ ኦሮሚያ 
የኦነግ እንቅስቃሴ በስፋት የሚታየው በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ በቀጠናው የሚደረጉ መንግስታዊ እርምጃዎችን በሚመለከት በተደጋጋሚ መንግስትን ይወቅሳል፣ የማስጠንቀቂያ መግለጫዎችም ይሰጣል፡፡ ኦነግ ወደ ሰላማዊ መድረኩ ከተመለሰ ጊዜ አንስቶ በአካባቢው ያለው ሁኔታ መረጋጋት ተስኖት  ለወራት ከቆየ በኋላ፣ ከህዳር አጋማሽ ጀምሮ  እየተባባሰ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በኅዳር ወር አጋማሽ በምዕራብ ወለጋ ማንነታቸው በውል ያልታወቀ፣ በደፈናው ግን የኦነግ ናቸው ተብለው የሚታመኑ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት፣ የፖሊስ አባላትን ጨምሮ የበርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል።  ከዚህ ቀደም ብሎም፣ በምዕራብ ወለጋ ማኅበረሰብ ዘንድ ታዋቂ የሆኑ አቶ ስሜ የተባሉ ባለሀብት ተገድለዋል፡፡ ይኼንን ተከትሎ ክልሉን የሚያስተዳድረው ኦህዴድ/ ኦዴፓ አስቸኳይ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አካሂዶ ባወጣው መግለጫ፣ በአካባቢው  የኦነግ ታጣቂ ኃይሎች እንቅስቃሴ መኖሩንና፣ ይህም የኦነግ ታጣቂ ኃይል ትጥቅ ፈትቶ በካምፕ እንዲቀመጥ ከተደረሰው ስምምነት ውጭ ነው ብሏል፡፡
ኦነግ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ በኩል እየደረሰ ያለው ጥቃት በታጣቂ ኃይሎች መሆኑን፣  በአካባቢው በሚገኙት ኦሮሞዎች ላይ እየተካሄደ ያለው የግድያ ዘመቻ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን፣ እስካሁን ግን የችግር ምንጭ ናቸው የተባሉትን ለሕግ በማቅረብ ችግሩን ለመፍታት ኦህዴድ/ ኦዴፓ በቂ ዕርምጃ አልወሰደም በማለት ወንጅላ ሰንዝሯል። ይህም በመሆኑ፣ “ባለን ራስን የመከላከል መብት ተጠቅመን፣ እንደ ብሔር እየተፈጸመብን ያለውን ግድያና ማንኛውንም ችግር መከላከል የሕዝባችን መብትና ግዴታ መሆኑን እናሳስበለን” በማለት ደምድሟል፡፡
ትጥቅ የማስፈታት እንቅስቃሴ 
የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊቱ ከጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በምዕራብና በምሥራቅ ወለጋ አካባቢዎች መሰማራት ጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ ሠራዊቱ ወደ አካባቢው  እንደሚሰማራ ቀደም ሲል መረጃ የነበራቸው  ወጣቶች የተቃውሞ ሠልፎችን አድርገዋል፡፡ እነዚህ ወጣቶች የመከላከያ ሠራዊቱ በአካባቢያቸው እንዳይሰማራ መንገዶችን በመዝጋታቸው፣ ወታደሩ መንገዶችን በኃይል ለማስከፈት በመሞከሩ በጦር መሣሪያ የታጀበ ግጭት አጋጥሞታል፡፡ ከመካከላቸው የታጠቁ ወጣቶች ለኃይል ዕርምጃው የአፀፋ ምላሽ እየሰጡ በማፈግፈግ አንዳንዶቹ ወደ ማኅበረሰቡ ውስጥ፣ የተቀሩት ደግሞ ወደ ጫካ ገብተዋል።
 ከዚህ በመቀጠል፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የአካባቢውን አመራሮችንና ሽማግሌዎችን በማስተባበር ትጥቅ ለማስፈታት ቤት ለቤት በመዞር ጥረት ቢያደርጉም፣ መሽገው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች መንገድ በመዝጋትና ድንገተኛ ጥቃቶችን በመሰንዘር ፋታ ነስተዋቸዋል፡፡ በዚህ ሂደት፣ አይራ ጉሊሶ በሚባል አካባቢ መንገድ በመዝጋት የሠራዊቱን እንቅስቃሴ ለመገደብ በሞከሩ ታጣቂዎች ላይ  በተወሰደ የኃይል ዕርምጃ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ፤ በደምቢዶሎ አካባቢ ደግሞ፣ በመንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎች ላይ በተሰነዘረ የቦምብ ጥቃት በሦስት ወታደሮች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሷል።
የኦነግ ሠራዊት ራሱን እንዲከላከል መታዘዙ
ነገሮች በዚህ መልክ እየተባባሱ ሄደው፣ ገዢው ፓርቲ ኦህዴድ/ ኦዴፓ በቀጣይነት ባወጣው መግለጫ፣ በኦሮሚያ በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች ላይ ማንኛውም ዓይነት ዕርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑን ተናግሯል፡፡ ቃላቱንም ከረር በማድረግ፣ “በሰላማዊ መንገድ ትልግ ለማድረግ የገቡትን ቃል አፍርሰውና ለኦሮሞ ሕዝብ የሚያደርጉትን ትግል ክደው፣ (ለሕወኃት) መጠቀሚያ የሆኑ የኦሮሞ ድርጅቶች አሉ” ብሏል፡፡ በመግለጫውም፣  በፈንጂ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች መኖራቸውን፣ ሴቶች መደፈራቸውን፣ ንብረት እንደወደመና የሕዝቡ የመንቀሳቀስ መብት እንደተገደበ አትቷል፡፡ የኦህዴድ/ ኦዴፓ አመራሮችና የኦሮሚያ ፖሊስ አባላትም በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው ማለፉን ገልጿል፡፡
ከዚህ በመቀጠል፣ የእነ ዳውድ ኢብሳ ድርጅት በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹ከፍተኛ የሆነ የመንግሥት ሠራዊት በሰላሌ፣ በባሌ፣ በጉጂና በወለጋ ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀምሯል፤  ሠራዊታችን ጥቃት አይፈጽምም፣ ራሱን ግን እንዲከላከል ትዕዛዝ ተሰጥቶታል›› ብሏል፡፡ ከዚህ በኋላ፣ ሁለቱ ድርጅቶች ወደ አልታወጀ ጦርነት ውስጥ ገብተው ይገኛሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳል፣ የእነ ዳውድ ስራ አስፈፃሚና አባልና  የፖለቲካ ኃላፊ የሆኑት አቶ ጋሹ ለሜሳ በቀጣይነት በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹አስመራ ላይ በተደረገው ስምምነት ብዙ ነገሮች ነበሩ፤ ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሚሟሉ ማለት ነው። አንድ፣ በሰላማዊ መንገድ ለአገሪቱ የሚስማማውን የፖለቲካ ሂደት ማካሄድ ነው። ሁለተኛው ደግሞ፣ በ1992 (እአአ) ከአገር ስንወጣ የተዘረፉ የኦነግ ንብረቶች ባግባቡ እንዲመለሱ፤ የ”ኦሮሞ ሪሊፍ አሶሴሽን” የሚባል ሰብአዊ ድርጅት ተመዝግቦ በሥራ ላይ እንዲሰማራ ነበር የተስማማነው። እነዚህ ሁኔታዎች እስካሁን ድረስ  አልተሟሉም።  ጉለሌ ያለ ቢሮ ብቻ ከፊሉ ተመልሷል፤ ሌላው  አልተመለሰም›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ እንፍታ ነው  የተባለው፣  በመንግሥት በኩል ተመልሶ አላስፈላጊ ጦርነት የመቀስቀስ ሁኔታ ይታያል፤ በየከተማው በየገጠሩ ማስፈራራት፣ ጦር ማስፈር ይታያል›› ብለዋል።
በኦነግ ታጣቂዎችና በጸጥታ ኃይሎች መካከል ውጊያ ስለመኖሩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽም፣ “እኛ  የሰማነው (ውጊያ መኖሩን)  ከሚዲያ ነው፡፡ በእኛ በኩል የተኩስ ልውውጥ የተደረገበት ቦታ የለም።  የእኛ ሠረዊት አላግባብ የተኩስ ልውውጥ የሚያደርግበት ቦታ አይደለም ያለው። ነገር ግን፣ አሁንም በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ኦነግ የሚንቀሳቀስ ሠራዊት አለው፤ የታጠቀ የኦነግ ኃይል ምዕራብ ኦሮሚያ ላይ አለ፡፡  ምዕራብ ኦሮሚያ ላይ በጣም ትኩረት ተደረገበት እንጂ፣  የታጠቀ የኦነግ ሠራዊት ያለው ምዕራብ ኦሮሚያ ብቻ አይደለም ። በደቡብም አለ፣ በመሐልም አለ፣ በምሥራቅም አለ። በሁሉም የኦሮሚያ ቦታዎች እየተንቀሳቀሰ ነው። ግን ዋንኛው ትኩረትና የፖለቲካ ውጥረት ያለው በምዕራቡ ላይ ነው፡፡ ሠራዊቱ አሁንም ልክ እንደ ሽምቅ ተዋጊ ሆኖ ነው ያለው፤ ያላግባብ ጦርነት፣ ውጊያና ግጭቶችን እየቀሰቀሰ አይደለም። ነጻ ባወጣቸው መሬት ላይ ሰፍሮ ነው ያለው። አስመራ ላይ በተስማማነው ውል፣ የሠራዊቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንዴት እንደሚሆን በሂደት ላይ ነው ያለው” ብላዋል፡፡ መሬቶቹን ከማን ነጻ እንዳወጧቸው ሲናገሩ፣ ‹‹ከወራሪ መንግሥት፤ ወይም ከወራሪ ሠራዊት ነው ነጻ ያወጣነው። እኛ  ወይም ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት ብለን ከምንፈርጃቸው ከወያኔ ወራሪዎች ነጻ አውጥቶ ነው በአካባቢው አሁን ሰፍሮበት ያለው›› ብላዋል።
በኦህዴድ/ኦዴፓ በኩል ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት ያለው ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ብዙዎች ግን ይሳካል የሚል እምነት የላቸውም፡፡
Filed in: Amharic