>
3:58 pm - Thursday May 19, 2022

ኢትዮጵያ ግን የማን ናት?:-   የከምባታ እና የጉራጌ ማህበረሰብ ተረኛ የመከራዉ ገፈት ቀማሽ ሆኗል!!! (ሸንቁጥ አየለ)

ኢትዮጵያ ግን የማን ናት?:- 
 የከምባታ እና የጉራጌ ማህበረሰብ ተረኛ የመከራዉ ገፈት ቀማሽ ሆኗል!!!
ሸንቁጥ አየለ
ሀገረ እግዚአብሄር ኢትዮጵያ በምናምንቴዎቹ የኢትዮጵያ ምሁራን ተክዳለች!!
 
በደቡብ ኢትዮጵያ ምን እየተካሄደ ነዉ? ኢትዮጵያ ግን የማን ናት? በከምባታ ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ የመፈናቀል እና የግድያ ወንጀል በከፋ ዞን እንዲህም በአርሲ አዋሳኝ ስፍራዎች ዉስጥ እየተካሄደ ነዉ::
እስካሁን እስከ 30,000 የከምባታ ማህበረሰብ አባላት መፈናቀቸዉ : ህጻናት የገቡበት አለመታወቁ እና እና በርካቶች መገደላቸዉ ተዘግቧል::
ይሄ ዘግናኝ ሁኔታ ሳይቆም ሰሞኑን ደግሞ በጉራጌ ማህበረሰብ ላይ በአዋሳ ከፍተኛ ሌላ ዙር ከከተማዉ የማስወጣት ስራ እየተከናወነ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነዉ:: “ጉራጌዎች እቃችሁን አውጡ ቦታው ለሲዳማዋች ሊሰጥ ነው” የሚል ቀጥተኛ መመሪያ ከአክራሪ የሲዳማ ባለስልጣናት እየተሰጠ መሆኑ እየተዘገበ ነዉ::ባለፈዉ ከመቶ በላይ የንግድ ቤቶች በነዚሁ አክራሪ የሲዳማ ባለስልጣናት እንዲቃጠሉ መደረጉ ይታወሳል::
ይሄ ሁሉ እየተከናወነ ያለዉ ያትዉልድ በሚባለዉ ምሁራን በተዘራዉ እርኩስ አስተምህሮት መሆኑ ነዉ:: ኢትዮጵያዉያን ምሁራን በኢትዮጵያዊነት ላይ ክህደት ፈጽመዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ወደ ተሳሳት አዙሪታማ ቀለበት ዉስጥ ከተዉት ቁጭ ብለዋል::
ከወያኔ ጋር አንሶላ በመጋፈፍ እና የወያኔን ሀሳብ በምን አለበት ያስፈጸሙ እንዲሁም ከወያኔ በላቀ ዘረኝነትን ለሰላሳ አመታት ያቀነቀኑ ኢትዮጵያዉያን ምሁራን ቁጥራቸዉ እጅግ ብዙ እና ብዙ ነዉ::በዚህ ሁሉ ሰይጣናዊ ክህደት ደግሞ የመጨረሻዉ ተጠቂ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆነ::
ለሰላሳ አመታት አማራዉ በአባቶቹ ሀገር መጤ ነህ እየተባለ በልዩ ልዩ ስፍራዎች ሲታረድ ሌላዉ ኢትዮጵያዊ ነገድ ዝም እናዳለዉ አሁን ደግሞ ከምባታዉ: ሲዳማዉ: ሀመሩ: ኮሬዉ እንዲሁም በሌሎችም ነገዶች ላይ በአባቶቻቸዉ ሀገር መጤናችሁ እየተባሉ ከፍተኛ መከራ ሲደርስባቸዉ ሌላዉ ኢትዮጵያዊ ዝም ብሏል::
ኢትዮጵያ አዚም ወድቆባታል::የየነገዱ ፖለቲከኞች የሚጮሁት ከነሱ ነገድ የሆነ ወገን ሲሞትባቸዉ ብቻ ነዉ::
ኢትዮጵያዉያን በልባቸዉ ኢትዮጵያዊነትን ክደዉ ነገዳዊ ማንነታቸዉን አግንንነዋል እና የእርስ በእርስ ወገናዊነታቸዉ ተኖ ጠፍቷል::
ከዚህም የከፋዉ አክራሪ እና ምናምንቴ ሰዎች የወረዳዎችን: የዞኖችን:የክልልሎችን እና የፌደራሉን ቁልፍ ቁልፍ ስልጣኖች አንቀዉ ይዘዋል:: ኢህአዴግ አሁንም የነገድ ፖለቲካዉን ወደ ከፍታ ማማ ላይ ሰቅሎታል::
የኢህአዴግ ደናቁርት ደጋፊዎችም በሚሊዮን ከመቆጠር አልፈዉ ወደ አስር  እና በሰላሳ ሚሊዮኖች ወደሚቆጠር ደርጃ አሻቅበዋል::ኢትዮጵያን የኢህአዴግ ስፍልስፍና እስኪያጠፋት ድረስ ኢህአዴግ ሽህ አመት ንገስልን እያሉ ነዉ::እነሱ ቀዳሚዎቹ ጠፊዎች መሆናቸዉ ከቶም ትዝ አይላቸዉ::
ኢትዮጵያዊነትን ወያኔ/ኢህአዴግ  እንዲሁም ተባባሪዎች ሁሉ በመቃብር አትመዉታል::የባርነት ስነልቦና በታላቅ እና በሚያስፈራ ሁኔታ በኢትዮጵያዉያን ምሁራን ልቦና ዉስጥ ሰፍኗል::
ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ግን ከፍተኛ ጥፋት ሳይከሰት ንጹሁን ኢትዮጵያዊነት ፈልገዉ በእዉነተኛ ወኔ እና ፍቅር እስኪያገኙት መከራዉ እንዲህ በቀላሉ አይቆምም::
ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ያስባት
Filed in: Amharic