>

" ጦርነት መፍትሄ ስለማይሆን የታጠቀው ሀይል ወደ ካምፕ ይግባ"  የኦነግ ም/ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ

” ጦርነት መፍትሄ ስለማይሆን የታጠቀው ሀይል ወደ ካምፕ ይግባ”
 የኦነግ ም/ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ
(ኢ.ፕ.ድ)
 ሰላማዊ ትግል ለማድረግ በመወሰን ወደ ሀገር ከገባን በኋላ ወደ ትጥቅ ትግል የሚመልሰን ምክንያት የለም አሉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ።
አቶ አራርሶ ቢቂላ ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት፥ ኦነግ ያለፈውን እና ወደፊት የሚያጋጥሙትን እድሎች በማገናዘብ የትጥቅ ትግል ምእራፍን በመዝጋት ሰላማዊ ትግልን መርጧል፤ ይህንን ደግሞ የድርጅቱ አባላት፣ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ሀይል እና ደጋፊዎች አክብረው መቀበል አለባቸው ብለዋል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከኤርትራ ወደ ሀገር ሲመለስም በታላቅ እምነት ራሱን ለመንግስት አሳልፎ በመስጠት ነው ሲሉም አቶ አራርሶ ተናግረዋል።
ኦሮሚያ ውስጥ በምንቀሳቀስበት ወቅትም ችግር አጋጥሞን አያውቅም ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፥ መንግስት ሀላፊነቱን ሙሉ በሙሉ እየተወጣ እንደነበረም ገልፀዋል።
ከኤርትራ የተመለሰው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጦር አርዳይታ እንዲያርፍ ከተደረገ በኋላ በአሁኑ ወቅት ስልጠና በመውሰድ ላይ ይገኛል።
በጫካ ውስጥ ታጥቆ ያለው የኦነግ ሀይል አርዳይታ ገብተው የነበሩ የኦነግ ጦር አባላት አያያዝ ላይ ጥያቄ ነበራቸው ያሉት አቶ አራርሶ፥ ወደ ማሰልጠኛ ካምፕ ከገባን በኋላ አያያዛችን መልካም ካልሆነስ የሚል ጥያቄ እንደነበረም አስታውቀዋል።
ይህ ጥያቄም መንግስት እና ኦነግ ባዋቀሩት የጋራ ኮሚቴ አማካኝነት የኦነግ ታጣቂዎችን ወደ ካምፕ ለማስገባት እየተደረገ የነበረው እንቅስቃሴ እንዲጓተት እና ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።
መንግስትም የሰጠው ጊዜ በመጠናቀቁ እና ከዚህ በኋላ አልታገስም በማለት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የፀጥታ ሀይልን በማሰማራቱ የተፈጠረው ግጭት እስካሁን እንዲቆይ አድርጓልም ብለዋል አቶ አራርሶ።
በግጭቱ ጫካ ውስጥ ያሉ የኦነግ ታጣቂዎች፣ በህዝቡ እንዲሁም የኦሮሚያ እና የፌደራል መንግስት የፀጥታ ሀይሎች ህይወት መጥፋት እንዳልነበረበት እና ሁኔታው የሚያሳስባቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።
የኦሮሞ ሀይሎች አንዱ አንዱን ለማዳከም የሚያደርጉት ጉዞ ጠላትን የሚያስደስት በመሆኑ ለችግሩ ትኩረት በመስጠት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ለመቅረፍ እንደሚሰሩም ነው ምክትል ሊቀመንበሩ የተናገሩት።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወደ ሀገር የተመለሰው ጦርነት ለመክፈት አይደለም ያሉት አቶ አራርሶ፥ አሁን የትግል ምእራፍ ተዘግቷል፤ በጫካ ያለ የኦነግ ሀይል ወደ ካምፕ አንዲገባ እንፈልጋለን ብለዋል።
እርስ በእርስ መጋጨት፣ መካሰስ፣ መወነጃጀል እና መተኳኮስ ቀርቶ አሁን የተገኘው ለውጥ መሬት መያዝ አለበት፤ ስለዚህ ችግሮቻችንን በውይይት እንፈታለን ሲሉም አስታውቀዋል።
ህዝቡ በተደጋጋዊ በኦዲፒ እና በኦነግ መካከል ያለው ግጭት እንዲቆም ሲጠይቅ ነበር ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፥ አሁንም ቢሆን ጠላት እንደሚፈልገው ኦሮሚያ የጦርነት እውድማ ትሆናለች በሚለው ስጋት ሊገባን አይገባም ብለዋል።
ትልልቅ ችግሮችን እየፈታን መጥተናል፤ ሁለታችንም ለአንድ ህዝብ የታገልን በመሆኑ የቀሩ ትናንሽ ችግሮችንም በውይይት እንቋጫለን ሲሉም ተናግረዋል።
ስምምነታችን ስራ ላይ ውሎ በሁሉም አቅጣጫ የሚንቀሳቀስ የታጠቀ የኦነግ ሀይል ከምፕ ይግባ ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፥ እንደ ድርጅት ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወስነን የመጣን በመሆኑ ማንኛውም አይነት ጥያቄ ካላቸው ካምፕ ከገቡ በኋላም ማቅረብ ይችላሉ ብለዋል።
አቶ አራርሶ ቢቂላ አክለውም፥ “የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኦነግን አናግረው ወደ መንግስት በመሄድ አንድ ላይ ሊያገናኙን እቅድ ይዘዋል፤ ውይይቱም እንደሚሳካ እምነት አለን፤ የሚያሳልፉትን ውሳኔም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንቀበላለን” ብለዋል።
ከዚህ በኋላ ከሰላማዊ ትግል እና ውይይት ውጪ የታጠቀ ሀይል ጫካ ተቀምጦ ድንጋይ እየተንተራሰ የዛፍ ፍሬ እና ስር እየተመገበ መኖር መቆም አለበት፤ አንዱ አንዱን ማዳከምም አማራጭ አይሆንም ሲሉም ተናግረዋል።
በአንድነት በመሆን አሁን የተገኘውን ለውጥ ወደ ትክክለኛ የዴሞክራሲ ምእራፍ ማሻገር የሁላችንም ድርሻ ነው ሲሉም አቶ አራርሶ ቢቂላ ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኤፍ ቢሲ ነው።
Filed in: Amharic