>
7:15 am - Tuesday December 6, 2022

የአፄዎቹ ሿሿ (ታምሩ ተመስገን)

የአፄዎቹ ሿሿ
ታምሩ ተመስገን
…… አንዳንዴ ዝም ብየ ሳስበው ከጎጃም ኮብልየ አዲስ አበባ ከኖርኩባቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥ በተደጋጋሚ ዘግናኝ ሿሿ የሚካሄድብኝ የአፄዎቹን ታሪክ እንዳስታውስ ይመስለኛል፡፡ ሿሿ ጥንትም ነበረ ዛሬም አለ ወደፊትም ይኖራል፡፡ ስንቶቻችሁ ትሆኑ አፄ ምኒልክ ንጉሥ ተክለሃይማኖትንና አፄ ዮሃንስን ሿሿ እንደሰሯቸው እምታውቁ? (የስልጣን ሿሿ)
1870 ዓ.ም
…… የደርቡሽ ወታደር ኢትዮጲያን ሲያስጨንቅ በጊዜው ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ዮሃንስ በኤርትራ ነበሩና የጎጃሙን ንጉሥ ንጉሥ ተክለሃይማኖትን “እኔ እስክመለስ ድረስ ተነስተህ ተዋጋ፡፡” ይሏቸዋል፡፡ ታሪክ እንደሚነግረን በመጀመሪያው ጦርነት ንጉሥ ተክለሃይማኖት ደርቡሽን ድል ማድረግ ችለው ነበር፡፡ ነገር ግን ከድል መልስ ሳር ውሃ የሚባል አካባቢ እንዳረፉ ግን የደርቡሽ ጦር ዳግም አገግሞ ገጠማቸው፡፡ በዚህኛው ግን ተሸነፉ፡፡
ይህ ከተፈፀመ ከ3 ዓመታት ገደማ በኋላ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ለሶስተኛ ጊዜ ወደ መተማ እንዲዘምቱ በአፄ ዮሃንስ ታዘዙ፤ ቀደም በደርቡሽ የተጠቃው የጎጃም ጦር ያ ገና አላገገመም ነበር፤ ስንቅም ትጥቅም ማዘጋጀት ተስኖታል፡፡ ንጉሥ ምኒልክ (የሸዋው ንጉሥ)፣ ይህን ያጤኑ ይመስላል፣ ንጉሥ ተክለሃይማኖትን አግባብተው ሁለቱ ንጉሦች አንድ ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ ስምምነቱም ለንገሠ ነገሥቱ ላለመገዛትና ጎጃምን የወረረ እንደሁ ንጉሥ ምኒልክ የአፄ ዮሐንስን ጦር በጀርባው በበጌምድር በኩል በመምጣት ከጎጃሙ ንጉሥ ወግነው ሊወጉ ነበር፡፡ ግና ተክለሃይማኖት በዚህ ስምምነት ቀላል ተሸወዱ እንዴ! የአፄዎቹ ሿሿ ልትለው ትችላለህ፡፡
አፄ ዮሃንስ ሊወጓቸው መጡ፡፡ ንጉሥ ተክለሃይማኖት በስምምነታቸው መሰረት የጠበቁት የንጉሥ ምኒልክ ጦር ሳይደርስላቸው ቀረ፡፡ ያኔ በስምምነቱ እንደተፎገሩ ሲረዱ ስንቃቸውን ሰንቀው መኳንኖታቸቸውን ሰብስበው ምሰኪኑን የጎጃም ህዝብ ፎጨጭ አድርገው ለወራሪ ጦር አጋፍጠው ከደብረ ማርቆስ በስተደቡብ ወደ ‘ሚገኝ ጅበላ እና ሞተራ ወደ ‘ሚባል አምባ ሸሹ፡፡
ንጉሡና መኳንንቶቻቸው እዚህ አንባ ላይ መሽገው ቺላክስ ሪላክስ ክላክስ ሲያደርጉ መካቹ ጥሎት የኮበለለው የጎጃም ህዝብ ግን ከነሃሴ 1880 ዓ.ም እስከ የካቲት 1881 ዓ.ም ያለርህራሄ ተደበደበ ተበዘበዘ ብዙ ስቃይ ሆነበት፡፡
እንደውም ስቃዩ ያንገፈገፋት አንዲት ሴት ፈጣሪን ከዚህ ሰቆቃ አድነኝ ብላ ብትለምነውም ሊታደጋት አልቻለምና እንዲህ ስትል ገጠመች
“አገርን ገረመው፣ እኔንም ገረመኝ፣
ዮሐንስ እግዜርን ገደለው መሰለኝ፡፡”
ሌላዋም ድሆች እኛ ምን አደረግን እና ነው የምንጨፈጨፈው ብላ የሚከተለውን ስንኝ ወረወረች፤
“ይገለኛል፣ ይሰቅለኛል ብሎ፣ አንድ ሰው በሸሸ፣
መላው የጎጃ ሕዝብ፣ እንደጭቃ ታሸ፡፡”
የጎጃምን ሕዝብ ጥጋብ ለማብረድ በሚል ስሌት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ዮሃንስ ከብቱ ወደ ጎንደር እንዲነዳበት አደረጉ፡፡ የሚጠጣው ወተት የሚበላው ስጋ እና ቅቤ እንዲሁም የሚያርስበት ከብት ያጣው የጎጃም ህዝብ ለከፍተኛ ርሀብ ተጋለጠ፤ ይሄን ጊዜ
“እስቲ ትንሽ ቅቤ፣ የቁስል፣ የቁስል፣
ከብቱ ጎንደር ገባ፣ የሚካን ይመስል፡፡”
አለች አንድ ተቆርቋሪ፡፡ በጊዜው የጎጃም ዲያቆናት ለመካን (ካህን ለመሆን) ወደ ጎንደር ነበር የሚጓዙት፡፡ በመጨረሻ ግን አፄ ዮሃንስ ጎጃምን በመበደላቸው ተፀፅተው ዲማ ጊዮርጊስ ድረስ ሄደው ንስሃ ገብተው ወርቅ ጫማ እና የነሃስ ቁር ለቤተክርስቲያኑ አበረከቱ፡፡ ከዚያም ከጦርነት ስመለስ ጎጃምን ተመልሼ አለማዋለሁ፡፡
ኋላም መጋቢት 1881 ንጉሥ ተክለሀይማኖት አማላጅ ይዘው (የአርባ አራት ቤተክርቲያን ታቦቶችን እና ካህናት ይዘው ነበር ንጉሠ ነግሥቱን የተማጠኑ ይባላል፡፡) አፄ ዮሐንስን ይቅርታ ጠየቁ፡፡ አፄ ዮሐንስም በዚያን ጊዜ ስለተደረገው ግፍ በጸጸት ላይ ስለነበሩ ይመስላል፣ ለንጉሥ ተክለሀይማኖት ይቅርታ አደረጉላቸው፤ ብሎም እርቅ ሰፈነ፡፡
በመጋቢት መጀመሪያ 1881 ዓ.ም አፄ ዮሃንስ በደርቡሽ መገደላቸውን ምክንያት አድርገው አፄ ሚኒልክ የሸዋ ንጉሥ መሆናቸው ቀርቶ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጲያ ለመሆን በቁ፡፡ እዚህች ጋር ሁላችንም አንድ ጊዜ ሿሿ እንላለን፡፡
.
… እና ምን ለማለት ነው፣ ወዳጄ በዝሆኖች ጠብ ሁሌም የሚጎዳው ሳሩ ነው፡፡ ዛሬ አለሁልህ ና አብረን እንጎንጥ የሚሉ ሁሉ ነገ ላይ አሳልፈው እንደሚሰጡህ እመን ምክንያቱም ማንም ቢሆን ከራሱ ደህንነት የሚያስቀድመው ሊኖረው አይችልምና፡፡ ይህ ሰዋዊ ባህሪ ነው፡፡ የኋላ የኋላም በአንተ መቃብር ላይ ቆመው እነርሱ ለእርቅ እንደሚጨባበጡ እመን፡፡ አብዛኞቹን የሀገራችን የንግሥና ታሪኮችን ብትታዘብ ይህን ያረጋግጡልሃል፡፡ ህዝብ ይጋደላል ኋላ መሪዎች ይታረቃሉ፡፡ ምን በወጣህና ሌላው ሊነግሥ አንተ ትሞታለህ! ታሪክ ባትሰራ እንኳን ከታሪክ ተማር እንጂ፡፡ ስለዚህ አንዳንዴ ከመጎነጥህ ጌት ኦፍ ኖ ሪተርን ላይ ከመድረስህ በፊት እና ነገ ላይ እምትፀፀትበትን ውሳኔ ከመወሰንህ በፊት ወደኋላ ለጠጥ ብለህ ተቀመጥና ቆንጆ ቡና ምናምን እየቀማመስክ ትንፋሽህን ወስደህ የከበበህን ለመረዳትና ሚዛን ላይ ለማስቀመጥ ሞክር፡፡ መሪ ከመሪ እንጂ ህዝብ ከህዝብ ጠላትነት የለውም፡፡
ኢትዮጲያዊነት ይፋፋምብን
Filed in: Amharic