>

ስለተፈናቀሉት ጦቢያውያን.....

ስለተፈናቀሉት ጦቢያውያን…..
ሙሉነህ 
አቶ ፍስሃ በህይወቴ እጅግ ከማከብራቸው ጥቂት የሚናገሩትን ከሚኖሩ ሰዎች አንዱ ናቸው። አቶ ፍስሃን ለማታውቁ ሰዎች ስለእሳቸው ጥቂት ቃላት አስቀምጬ ወደ አስተያየታቸው እንዳሻግራችሁ ፍቀዱልኝ። አቶ ፍስሃ ስለቀረጥ፤ ስለትራንስፖርት፤ ስለሳፕላይ ቼይን ብዙ እውቀት ካላቸው አዋቂ መሆናቸውን ሳይሆን ብዙ የማያውቁት ነገር እንዳለ ከሚያውቁ ሰዎች አንዱ ናቸው።
አቶ ፍስሃ አቶ መለስ ዜናዊ ሊዘረጋው ላሰበው የዘረፋ ስርዓት እንቅፋት ሊሆንብኝ ይችላል በሚል በጊዜ ከመንግስት ሃላፊነት ያስወገዳቸው ሰው ናቸው። አቶ ፍስሃ የጉሙሩክ ባለስልጣንን ጨምሮ ሌሎች ተቋማትን በሃላፊነት መርተዋል። የጉሙሩክ ስራ አስኪያጅ በነበሩበት ጊዜ አቶ መለስ ብቻ ሳይሆኑ የሻቢያም ሰዎች እንዳልወደዷቸው አንድ ከእርሳቸው ጋራ የሰራ ስለእሳቸው አውርቶ የማይጠግብ ባልደረባቸው አጫውቶኛል። ወደፊት ስለእሳቸው ብዙ የምለው ይኖረኛል። Fiseha Letta አስተያየታቸው እነሆ፦
ወዳጄ ሙሉነህ! እነዚህን በቁጥር የምንገልጻቸውን እናቶችና  አባቶች (ወንድሞችና እህቶችን አልረሳሁም) አክብረን መብታቸው ሳይገፈፍ እንዲኖሩ ማስተማር የሚበረታታ የዜጎች ሁሉ ጥሪ ነው:: ይህ ጉዳይ የህዝብ ንቅናቄመሪ ነን ከሚሉ ከፖለቲከኞች እጅ ወጥቶ የባለጉዳዩ ነፃ ፈቃድ ካልሆነ: እርሻን ማረስ ቤትንመሥራት ልጅ ማሳደግ እና የመሳሰሉት የግለሰብ ዓርነት ጥያቄዎች ለግለሰቡ ካልተመለሱ በቀር: አሁን በህዝብ ስም ተደራጅተው የቆጡን የባጡን የሚቀባጥሩ ሰዎች አንዳች መፍትሄ አይሰጡንም:: መቼም ድንቁርና እንደ ዘንድሮ በእግሯ በመከከላችን የተመላለሰችበት ጊዜ የለም:: እንግዲህ ወዳጄ! እንደ ጀመርከው ይህንን የህዝብ ቁጥር ወደ ስብዕና ለውጠህ ትውልድ መንደሩን ባይጨንቀው ጥሎ እንደማይሰደድ ጨምረህ: በሄደበት ቢያገኝ ወይ ቢያጣ መርምሮ ሊሰነብት ወይ ቀድሞ ቄዬው ሊመለስ ማንም እጁን እንዳይሰነዝርበት: ፀሐዩ መንግሥትም ሁሉ በሁሉ መሆኑ ተሽሮ በዜጎች ህይወት ጣልቃ እንዳይገባ ህግ እንዲያግደው: የህዝብ ተወካይነትም ባለ ክብርና ማዕረግ እንዲሆን ውክልናን ለሚያውቅና ለሚያከብር እንጂ ለማናቸውም መንገድ ተላላፊ (የድርጅት አባል ነኝባይ) እንዳይሆን አበክረህ አሳስብ:: አታውቀውም ብዬ አይደለም:: እንደምታውቀው ግልፍ ይልብኛል አንዳንዴ ሲበዛብኝ:: ማህበራዊ ቀውስን እንደ ማህበራዊ ዋስትና አርገው የቆጠሩ ሰዎች እየተሞገሱ በያደባባዩ ይናገራል:: አደባባዩ የዋልጌ መዋያ ሆነ:: የመንግሥትን ሥልጣን ተገን አድርገው በሕዝብ ላይ የሚደረግ ሙከራ አልሠራም: በላቸው:: ወደፊትም አይሠራም:: ሥልጣን ካልተረከብን እያሉለሚቸኩሉም ሌላ ማስጠንቀቂያ የለኝም:: ውጤት ቢኖረውም ባይኖረውም የማያስጠይቅ አሠራር እኔው ራሴ የወደድኩትን ያለ አንዳች አስገዳጅ ሁኔታ ስመርጥ ነው:: ስው ቦታ ሲጠበው ሪሱ ይውጣና ይተንፍስ! አትከልክሉ: በልልን:: በሄደበት ሲወድ ከምባታነቱን ያጎላል:: ከመሰለውም አካባቢው ጉድፈቻ ያደርገዋል:: የፈቃድ የምርጫ እንጂ የክልል አስተዳደር ግዴታ አይሁን:: ደግሞስ ይሁን ብለን አዳመጥን እንጂ ምን ቋንቋ እንደምናገር: የት መሬት ላይ እንደምኖር የዕለት ምርጫዬ ነው:: የጎረቤቴን ቋንቋ ሳላውቅ መክረም ብችል እናንተን ምን ገዷችሁ:: ካልመሰለኝ ተነስቼ ልብረር:: አትያዙኝ: አታስገድዱኝ:: መሬት ቢጠብ ሰበብ ነው:: ውጤቱ የእያንዳንዱ ሰው የቤቱ ጥያቄ ነውና ተቀምጬ ከመሰሎቼ ጋር ብመክር: እምቢም ብዬ በቅሎዬን ብጭን ወይም ዱላዬን በጫንቃዬ ባንገዋልል ማንን ይመለከታል:: እስኪ አታናግሩን:: ዝምታው ብሶት ወልዶ አወቅን ያሉትን ባዶአቸውን እንዳያስቀራቸው እዛው ምከርልን: ወዳጄ ሙሉነህ!! ያለ ምክንያት እንዲህ ያለ ስም አላገኘህም::
በቅድሚያ ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሚከተለው ማስቀመጥ ይቻላል፦
1. ተፈናቃዮቹ ከከምባታ ጠንባሮ ዞን በሰፈራ ወደ ከፋ ዞን ተወስደው የሰፈሩ ናቸው፤
2. ለሰፈራው ምክንያት የሆነው በከምባታ ጠንባሮ ዞን የነበረው የህዝብ መጨናነቅ (population density)እንደነበር፤
3. ይሄ የህዝብ መጨናነቅ የከምባታ ጠንባሮ ዞን ብቻ አለመሆኑንና መላ ሊበጅለት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን፤
4. ሰፈራ በሚካሄድበት ጊዜ ለሰፋሪዎቹ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ሳይሟሉ እንደተከናወነና በዚህም ምክንያት በሰፈራ እያሉም ሆነ በተፈናቀሉበት ወቅት በህይወታቸውና በንብረታቸው ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሰን አንስቼ ነበር።
በጽሁፉ ላይ ብዙ ሰዎች አስተያየት የሰጡ ቢሆንም በሁለቱ ላይ ብቻ ጥቂት ብዬ ወደዛሬው ክፍል አመራለሁ። የመጀመሪያው አስተያየት ክቡር አቶ ፍስሃ ደጀኔ Fiseha Letta የሰጡት ነው። የእሳቸው አስተያየት የህዝብ እድገት ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ይቀበላል። መፍትሄም ሊፈለግለት የሚገባ መሆኑንና በነካ እጄ ዳር እንዳደርስ የሚያሳስብ ነው። ሰፈራን በሚመለከት ግን መንግስት ምን አግብቶት ነው ዜጎችን ከአንድ ቦታ አንስቶ በሌላ ቦታ የሚያሰፍረው? ሲሉም ይጠይቃሉ። እንደእሳቸው ከሆነ ዜጎች ካንድ አካባቢ በግልም ሆነ በቡድን ሆነው ለእነርሱ ያዋጣናል ባሉበት ቦታ ሲሻቸው የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን እየተነጋገሩበት፤ አሻፈረኝ ያሉ እንደሆነ ደግሞ መርጠው በሄዱበት ቦታ ላይ የሚኖረው ሰው የሚነጋገርበትን ቋንቋ ተምረው ህይወታቸውን መምራት የግለሰቦቹ ምርጫ እንጂ መንግስት ምን አግብቶት እንዲህ ያለውን ስራ ይሰራል ይላሉ። የህዝብ እድገት ምጣኔን በሚመለከት ለጊዜው እንደአንድ ዜጋ ከዚህ በላይ ምን ልሰራ እንደምችል እንዳስብ እንዳደረጉኝ አምናለሁ።
ሰፈራን በሚመለከት ግን መንግስት ስራው አይደለም ይልቅስ መንግስት የዜጎችን የህይወት፣ የንብረትና የነጻነት መብት ማስከበር ላይ ብቻ ያተኩር በሚለው ሀሳባቸው አልስማማም። ይሄ ሀሳብ የመንግስት ስራ ምንድነው? መንግስት እራሱ ምንድነው? መንግስት ሲጀመር ለምን ያስፈልገናል? ደስ ያለን ቦታ ላይ እንዳሻን መኖር ስንችል መንግስት የሚባል ደንቃራ ስለምን ያሻናል? በሚሉና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች ላይ ለዘመናት በተለያዩ አስተምህሮዎች ውስጥ ሆነው ልሂቃኑና ፈላስፋዎቹ የተነታረኩበት ጉዳይ በመሆኑ ለምን መንግስት ስራው እንደሆነ ልከራከር እንደምፈልግና ከእርሳቸው ጋራ በዚህ ጉዳይ ወደፊት ዱላ ቀረሽ ሙግት ልገጥም ፈቃዴ መሆኑን ገልጬ ለዛሬው ይለፈኝ ብያለሁ። አንባቢዎቼ እንድትረዱልኝ የምሻው አቶ ፍስሃ የውስን መንግስት (limited government)እሳቤ አራማጅ ሲሆኑ እኔ ደግሞ እሳቸውን መሰል ሰዎች እንደሚጠሩን የትልቅ መንግስት (big government) እሳቤ አራማጅ ነኝ።
ሁለተኛው አስተያየት ሰጪ ደግሞ አቶ ከበደ ሞላ Kebede Mrg Mola ይባላሉ። እሳቸው የህዝብ እደገትን እንደችግር ተመልክቼ መላ ሊፈለግለት ይገባል ማለቴ ትክክል እንዳልሆነ አስረድተዋል። በሁለት ምክንያት፦ አንድም የህዝብ እድገት ከኢኮኖሚ እድገት ጋራ በራሱ ጌዜ እየቀነሰ የሚሄድ በመሆኑ አንድም ያደጉት ሀገሮች ከኢኮኖሚ እድገታቸው ጋራ የህዝባቸው ቁጥር እየቀነሰ ሄዶ አሁን የገቡበት ችግር ውስጥ እንዳይከተን በመፍራት፤ ለዚህም እንደአብነት ሲውዲንን አንስተዋል።
እርግጥ የእርሳቸው መነሻ እውነትነት አለው፤ ኢኮኖሚ እያደገ ሲሄድ የህዝብ እድገት ምጣኔ ይቀንሳል። ስዉዲንም ከሌሎች ሀገሮች ሰዎችን ለማምጣት የሚገደዱበት ሁኔታ ትፈጥሯል። ይሄ ምልከታ ግን ሁለት ነገር ይጎድለዋል፤ አንድም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት የህዝቡን ፍላጎት የሚሸፍን ባለመሆኑ ለረሃብና ለማህበራዊ ቀውስ የሚዳርግ መሆኑን በመዘንጋቱ፤ ሁለተኛ የሳይንስና የቴክኖሎጂ እድገት አቅጣጫ የሰውን ጉልበት የማይሻ ምናልባትም ዛሬ የሰው ልጅ የሚሰራቸውን ጥቃቅን ነገሮች ሳይቀር በሮቦቶች የሚተካ እየሆነ እንደሚሄድ በመሆኑም እነስውዲን አሁን የገቡበት ችግር ጊዜያዊ መሆኑን የዘነጋ ይመስለኛል።
እንደውም የአለም አካሄድ ማሽንና ሮቦት የሰውን ስራ እየቀሙ የሚሄዱበት ይመስላል። ለዚህ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ በሰፈሬ ያለው ዎልማርት ካሉት ሃያ አንድ የሂሳብ መክፈያዎች ግማሽ የሚሆኑት ሰው አልባ ሂሳብ መቀበያዎች ሆነዋል። ሌላም ልጨምር ከጥቂት ቀናት በፊት አምፖል ልገዛ ሆምዲፖ የሚባል ሱቅ ገብቼ የምፈልገውን አምፖል ከተደረደሩ አምፖሎች መካከል አንስቼ ሂሳብ መክፈያ ዘንድ ስቃረብ ራስህን አስተናግድ (self check)የሚል አመላካች ተጥፎበት አይቼ ወይ ጉድ ብዬ ራሴን አስተናግጄ ወጣሁ። ምንም እንኳን አለም የሰውን ጉልበት በማሽኖችና በሮቦቶች ለመተካት ረዥም ጊዜ እንደሚያስፈልገው ባምንም አቶ ከበደ ወደፊት የሰው ጉልበት እጥረት ገጥሞን እንቸገራለን ሲሉኝ እኔ ደግሞ የሰው ጉልበት በርክቶ የምንቸገር ስለመሰለኝ ነው። የወደፊቱን ለጊዜው አቆይተን አሁን ግን እኛ በምግብ ራሳችንን ያልቻልን ተመጽዋቾች መሆናችንን እንመን፤ ስለሆነም በኢኮኖሚያችን እድገት ራሳችንን መመገብ እስከምንችለው ድረስ መመገብ ያልቻልናቸውን ህጻናት ወደዚህ ምድር አምጥተን በረሃብ ተሰቃይተው ህይወታቸው እንዲቀጭ ልናደርግ አይገባም ብዬ ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልዝለእ።
በመጀመሪያ ጥሁፌ እንዳነሳሁት በኢትዮጵያ ሰፈርህ/ሽ እዚህ አይደለም፤ መጤዎች ናችሁ እየተባለ መፈናቀል አዲስ አይደለም። ለከምባታና ጠንባሮ ህዝብም አዲስ አይደለም። ወያኔ ሲገባ የሆነውን የምናስታውሰው ነው። እኔው እራሴ ከምዕራብ አርሲ ከከምባታና ሃዲያ የመጡ ገበሬዎች ሲፈናቀሉ አክስቴ ቤት እኖር ስለነበር መፈናቀልንና ከዚያ ጋራ ያለውን ውጣውረድ በግሌ አውቀዋለሁ። ሁላችንም ተራ በተራ ደርሶናል።
ከከፋ ዞን ከዴቻ ወረዳ የተፈናቀሉት የከምባታና ጠንባሮ ዞን ተፈናቃዮች ጉዳይ ከሌሎች ተፈናቃዮች የሚለይ ባይሆንም በአንድ ጉዳይ ግን በእጅጉ እንደሚለይ አይቻለሁ፤ ምንድነው የተባለ እንደሆነ ጉዳዩ እውቅና አግኝቶ የሚመለከታቸው አካላት እርምጃ እንዲወስዱ ግፊት ለማድረግ የተሞከረው እንቅስቃሴ የሚዲያ ሽፋን ይጎድለው ስለነበር የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልተቻለም ነበር። እንደውም አንድ ዶ/ር አቢይ ያማልዳሉ ማለት ብቻ የሚቀረው ደጋፊያቸው ሳይቀር “የስንት ከምባታ ሞት ነው የአንድ ኢትዮጵያዊ ሞት ተደርጎ የሚቆጠረው?” ሲል እንዲጠይቅ እንዳደረገው ተመልክቼአለሁ። እኔም በአቅሜ ሚዲያዎች እንዲዘግቡ ለማድረግ የአቅሜን አድርጌአለሁ። በዚህም የጉዳዩን አሳሳቢነት አስረድቼ የዘገቡትን የሚዲያ ተቋማት ሁሉ አመሰግናለሁ፤ ነገር ግን የህዝብ መፈናቀል መኖሩን ለማስረዳት ብዙ ጥረት ማድረግ ያለብን እኛ ሳንሆን ሚዲያዎቹ መሆን ይገባ ነበር፤ በዚህም ድክመት እንዳለባቸው መታዘቤን በግል የገለጽኩላቸው ቢሆንም በአደባባይም ሳልገልጽ ማለፍ አልሻም።
በመንግስት በኩል የተወሰደው እርምጃ እጅግ አሳፋሪ እንደነበር ሳልገልጽ ማለፍ አልፈልግም። መንግስት ስል የምገልጸው የደቡብ ክልልን መሆኑን ልብ ይሏል። የደቡብ ክልል የጸጥታ ቢሮ ችግሩ መከሰቱ ሲነገረው በብዙ ጉትጎታ 9 የልዮ ፖሊስ አባላትን ብቻ መላኩ እንዳያማ ጥራው እንዳይበላ ግፋው የሚባለውን ተረት እንዳስታወሰኝ አልሸሽግም። ይህ እውነት መሆን አለመሆኑን ለማጣራት የክልሉን የጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ወንድሙን በተደጋጋሚ እኔም ሆንኩ ዘገባውን የሰሩ የሚዲያ ተቋማት ለማግኘት ሞክረን አልተሳካልንም። በአስር ሺዎች ዜጎችን ያፈናቀለን ክስተት ለማስቆም 9 ፖሊስ መላክ ምን ይባላል? ወይስ የደቡብ ክልል ልዩ ሀይሎች እንደሸዋዚንገር አንዱ ሺ ገዳይ ነው?
በዚህ አጋጣሚ በደቡብ አፍሪቃ ያሉ ጦቢያውያንን በተለይ ደግሞ ከከምባታና አካባቢው የተሰደዱ ጦቢያውያን እንደኮራሁባቸው መግለጽ እፈልጋለሁ። በሰሜን አሜሪካም በአውሮፓም ያላችሁትን እንዲሁ። በተለይ ከሰሜን አሜሪካ አቶ ለማ ለዕመንጎን አለማመስገን አይቻልም። የከምባታ ዞንን የአቅሙን ለማድረግ እንዳልሰነፈ ምስክርነቴን እሰጣለሁ። በተለይ ለዞኑ ሃላፊ ዶ/ር ታከለ ነጬ ባርኔጣዬን አንስቼአለሁ። ሀገራችንን ኢትዮጵያን ዜጎች የማይፈናቀሉባት ሰላማዊ ሀገር እንዲያደርጋት ለልጆቿ የሚያስተውል ልቦናን እንዲሰጠን አምላኬን እማጸናለሁ። ቸር ያሰማን!
Filed in: Amharic