>

የቀን ጅቡን አከራካሪ ከወዲሁ ስለመስበር!!! (መስቀሉ አየለ)

የቀን ጅቡን አከራካሪ ከወዲሁ ስለመስበር!!!
መስቀሉ አየለ
እንደ መነሻ፤
የደርግ ዋነኛው ሜካናይዝድ ሃይል የነበረው በኤርትራ ግንባር ነው። በመንግስቱ ሃይለማርያም ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እስከተደረገበት አስራዘጠኝ ሰማኒያ አንድ ድረስ የሻቢያ አስመራን የመቆጠጠር ህልም የህል እንጀራ ነበር ማለት ይቻላል። ይልቁንም የሻቢያ የውስጥ ግምገማ መረጃ እንደሚያሳየው ይኽ መፈንቅለ መንግስት ከመካሄዱ ጥቂት ወራት በፊት ሻቢያ ሊበተን ጫፍ ላይ ደርሶ ነበር።
ነገር ግን እንደ ለገሰ አስፋው ባሉ ሚሊሻ ካድሬዎች  ወታደሩ ትግራይ ለቆ እንዲወጣ የተሰጠው ትእዛዝ በኤርትራ የነበረውን ዋነኛ የሃገሪቱን መከላከያ ሃይል ስሩ የተቆረጠ ዋርካ አደረገው።
፩ኛ ከብዙ የወረዳ ከተሞች ተፈናቅለው በአስመራ ከተማ የተቀመጡ የፋብሪካ ሰራተኞች፣ መምህራንና የመንግስት ሰራተኞችን ያለስራ ደመወዝ የሚከፍለው ደርግ ነው።
፪ኛ አነሰም አደገም ወደ ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ገደማ ለሚገመተው የኤርትራ ህዝብ ጤፉንም፣ በርበሬውንም፣ስኳሩንም፣ ዘይቱንም የማቅረብ ግዴታው አሁንም የደርግ ነበር።
፫ኛ ወደ ሶስት መቶ ሽህ ለሚገመት የመከላከያ ሃይል ስንቅና ትጥቅ የማቅረብ ግዴታም እንዲሁ።
ይኽ ሁሉ የሚመላለሰው ደግሞ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ በትግራይ-ኤርትራ ድንበር በኩል መሆኑ እየታወቀ ዋነኛ የደም ስር የሆነውን ይሕንን ክፍለሃገር በቀላጤ ውስኔ ጦሩ ለቆ ይውጣ ሲባል ኤርትራ ውስጥ የነበረውን ትግል እንዴት እንዳሰቡት ለማንም የሚገባ አልነበረም።
ኢትዮጵያን በምታክል ደሃ አገር በወቅቱ በነበሩዋት ውሱን ቦይንግ አውሮፕላን ወንበራቸው እየታጠፈ ከባህርዳር አውሮፕላን ማረፊያ በሚነሳ በረራ ሙሉ ቀን እና ሌሊት የጦር መሳሪያ፣ ዘይትና ዱቄት ጭምር ማመላለስ ተጀመረ። ነገር ግን ጥረቱ ከጉሮሮ ጠብ የሚል አልነበረም። እንዲሁ አባይን በጭልፋ ነበር ማለቱ ይቀላል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ይኽ የአገሪቱ ዋነኛ ሃይል እንደጥሬ ቆሎ ተበተነ ማለቱ ይቀላል።
ከዚህ ምን እንማራለን፤
የአብይ አስተዳደር ሃይሉን አጠናክሮና ፓራለል የሆነ ሃይል ፈጥሮ ፊቱን ወደመቀሌ ከማዞሩ በፊት በርካታ መሰናክሎችን ማለፍ ይጠበቅበታል።በኦነግና፣ ቤንሻንጉል መሰል አካባቢዎች ያለውን ጎሰኛ ሃይል ከማጽዳት ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የመንግስት መዋቅር የተሰገሰጉትን የተበላሹ አመራሮች ልካቸውን እንዲያውቁ ለማድረግ በርካታ ታክቲካልና ስትራቴጅካል የሆኑ እቅዶች(the Devil is in the detail) በየደረጃው መፈጸም አለባቸው። ስለዚህ ኤርትራን ጨምሮ በጎንደር፣ በአፋርና ወሎ አካባቢ ያሉ የአፋርና የአማራ ተጋድሎ ወጣኒያን   በተቀናጀና ቀጣይነት ባለው መልኩ የቅድመ መንገድ ጠረጋውን ስራ ሊሰሩ ይችላሉ። ይኸውም የተጀመረን መንገድ የመዝጋት ዘመቻ አጠናክሮ መቀጠል ነው።”አንድ ሚሊዮን ያህል ሚሊሻ አስታጥቄያለሁ” እያለ ለሚደነፋው የቀን ጅብ አንድ ጥይት ሳይተኮስ ለተወነሰ ግዜ በረሃብ መቅጣት ከተቻለ እንደ እስራኤል ዘጸአት መና ከሰማይ አውርዶ ውሃ ከጭንጫ ላይ አፍልቆ አርባ ዘመን የሚመግብ ሙሴ ከተረገመው የትግራይ መሬት ይወጣል ብሎ ማሰብ አይቻልምና እንደ እንቧይ ካብ ከውስጥ መፍረስ እንደሚጀምሩና እንደፊኛ እንደሚተረሹ ጥርጥር የለውም።
Filed in: Amharic