>

የመንፈስ ልዕልና ማሳያው  ፕሮፌሰር !!!  (እስክንድር ከበደ )

የመንፈስ ልዕልና ማሳያው  ፕሮፌሰር !!!
እስክንድር ከበደ
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በ “መዝናኛ” ቻናሉ “ፕሮፌሰሩ ገበሬ ” በሚል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባረሩ 40 ፕሮፌሰሮች አንዱ የሆነው  የፕሮፌሰር ምንዳርያለው ዘውዴ የሚገርም ገጠመኝ አቅርቧል:: ቴሌቪዥኑ የፕሮፌሰሩን   የ25 አመት የስራ ዋስትና እጦት አቅርቦ ነበር::
ይህ ዶክመንተሪ የሰራው ጋዜጠኛ አድናቆቴን ብገልጽም ፤ይህ በመዝናኛ የሚቀርብ ተራ ጉዳይ አይደለም :: የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “የዜና ” ቻናል ጨምሮ በሌሎችም መተላለፍ ያለበት “ምርጥ የበደል ማሳያ ” ዘጋቢ ፊልም ነው::
የፕሮፌሰሩ የቋንቋ አጠቃቀም፤ በዚህ ሁሉ በደል አልፈው ለበዳዮቹ የሰጡት “ይቅርታ” ከፍ ያለ የሞራል ልእልና ብርቅዬ  ነው :: ስም ላለመጥራትና ሰዎች ላለመጉዳት የደረጉት ትህትና ተሞላበት ማብራሪያ የሚያስደምም ነው:: ከጣቢያው ድረ ገጽ አውርዳችሁ ብትመለከቱት ሰብአዊ መብት ጥሰት መግረፍ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ዜጋ የስራ ዋስትና ማሳጣት እንዲሁም የስነልቦና  ጠባሳ ማድረስ ቂመኛ አካሄድ ” መቼም መቼም እንዳይደገም !” ሊባል ይገባል::
ያንን ወቅት መለስ ብለን እናስበው:-
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ውስጥ አንድ ምሽት ድንገተኛ የተማሪዎች ስብሰባ ተጠራ::በዘመኑ ፌስቡክም ሆነ ሞባይል አልነበረም ::በጩኸትና በዶርሙ ተንኳኩቶ የወጣው ተማሪ ከየጥናቱ ተነስቶ መኮንን አዳራሽ ፊት ለፊት ተሰበሰበ:: ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው አጀንዳውን ባለማወቁ እርስበእርስ መሸኳሾክ ጀመር:: በወቅቱ የተማሪዎች  መማክርት የሚባል አካልም አልተመሰረተም::  በህንጻው ደረጃ ዳርና ዳር በተቀመጡበት  የሚያምሩ  ውብና ራቁት ጌጠኛ ሀውልቶች ማህል የቆመው የመጨረሻ አመት የፖለቲካና አለምአቀፍ ግንኙነት  እጩ ተመራቂ ተማሪው ጋሻው ነበር::
ስብሰባው በዛ ምሽት በድንገት የተጠራበትን ምክንያት መናገር ጀመሩ ::በወቅቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የነበሩት ግብጻዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ በቀጣዩ ቀን አዲስ አበባ እንደሚገቡ  ገለጸ:: ግብጻዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ መሆናቸው ከቀጣዩ የኤርትራ ሪፈረንደም የተሻለ ነገር እንደማይመጣ አብራራ::
ዋና ጸሀፊው  ኢትዮጵያ እንደትዳከም የግብጽን የቆየ ሴራ  እንደሚያሳኩና ድርጅቱን እንደ መሳሪያ ይጠቀሙበታል  የሚል የስጋት ትንታኔ ሰጠ:: ጋሻው ረጋ ብሎ እና ምክንያታዊ ማብራሪያዎችን ከአፍሪካ ቀንድን ሁኔታ ጋር አስተሳስሮ አብራራ:: በወቅቱ የኤርትራ ሀርነት ግንባር አስመራን ቢቆጣጠርም ፤ ሪፈረንደም አልተካሄደም  ነበር::
በዛ ዘመን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “ብሄር” አጥሮችና “በመንጋ” ተነድቶ ትምህርት ማቋረጥ  አይታወቅም ነበር:: ተማሪው የልምድና እውቀት እጥረት ቢኖርበትም፤ በደቦ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ዝምብሎ ዘው ብሎ የመግባት አዝማሚያ አይታይበትም ነበር :: “ለምን? እንዴት ? …” የሚሉ ጥያቄዎችን አንስቶ መተማመን ይፈልጋል::
 በድንገት የተማሪዎች መሪ ሆነው መድረክ ላይ የወጡት ተማሪዎች  “በቀጠዩ ምን ይደረግ ?”  እድሉን በዛ ምሽት ለተሰበሰበው ተማሪዎች ሰጡ ::
ሀሳብ ሰጪዎች ከትምህርት ዳራቸው ጋር እያዛመዱ ትንታኔ ያቀርቡ ነበር::
አንዱ የኤርትራ መገንጠልን እውን ለማድረግ  ግብጽን ሴራ ሲተነትን ፤ሌላው ደግሞ ወደብ አልባ ሀገራት ታሪክ በመዘርዘር ቀጣዩ ጊዜ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጨፍጋጋ ገጽ ይናገራል::
የቲያትር ተማሪው አጠር ማብራሪያ ሰጥቶ ፤ የሼክስፒርን “ማክቤዝ ” የተወሰነ ትእይንት መነባብ  አቅርቦ ተጨበጨበለት:: ሌሊት ላይ ተማሪው የዋና ጸሀፊውን ተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ለማሰማት ውሳኔ ተላለፈ::ያልተፈቀደ ሰልፍ በመሆኑ እንዴት ሰላማዊ ይሁን ብዙ አከራከረ :: አንድ የህግ ተማሪ ” እንደ ጋንዲ ቢመቱንም ፤ምንም ጥፋት ሳንሰራ መውጣት እንችላለን !” ብሎ የሙያውን መከረ ::
ሌሊቱን መዝሙርና መፈክር ሲዘጋጅ አድሮ ፤በማግስቱ ቅልጥ ያለ ሰልፍ ተጀመረ :: ከግቢው ብዙ ሳይርቅ በኃይል የተበተነው ይህ ሰልፍ ተማሪዎች የሞቱበትና የተጎዱበት አስደንጋጭ ድርጊት ሆኖ አለፈ::
በወቅቱ የመምህራን ማህበሩ ሊቀመንበርና የፖለቲካል ሳይንስና አለምአቀፍ ግንኙነት መምህርና የትምህርት ክፍሉ ሊቀመንበር የነበሩት ዶክተር ታዬ ወ/ ሰማአት በተወሰደው እርምጃ  በማህበሩ ስም የሚያወግዝ መግለጫ አወጡ:: በዛ ዘመን በአብዛኛዎቹ የትምህርት ክፍሎች  የሚገኙ መምህራን  በክፍል ውስጥ መንግስት ላይ የሰላ ትችት ያቀርቡ ነበር::
ከሰልፉ በኋላ የተማሪ መሪዎችና ዶክተር ታዬ  በልደት አዳራሽ ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸው  እዲመለሱ ለማሳመን ሞከረው ነበር::ዶክተሩ በአንድ ወቅት የእንግሊዝ የሰራተኞች ማህበር መሪዎች ያነሷቸው ጥያቄዎች እንዴት በመከፋፈል እንደተዳከመ በምሳሌ በማቅረብ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርቱ እንዲመለሱ ቢወተውቱም ፤ተማሪዎቹ በእምቢታ ጸኑ :: በዚህ ምክንያት ዩኒቨርሲቲው ለሶስት ወራት እንዲዘጋ ተደርጎ ፤ ከመጀመሪያ አመት እስከ ተመራቂ ተማሪዎች የድጋሚ ምዝገባ ሆነ:: ዳግም ምዝገባው “ረብሻ ውስጥ አልሳተፍም ” ከምትል ብጣሽ ፎርም በመፈረምና የድሮው መታወቂያ ተመልሶ  አዲስ መታወቂያ ተሰጠ::
ከዛ በኋላ 42 የዩኒቨርሲቲው መምህራን በድንገት መባረራቸው ተሰማ:: የተቋረጠው ትምህርት ክረምትን ጨምሮ ማካካስ በሚል ጥድፊያው ቀጠለ :: በሽግግር መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ደብዳቤ ቀደም ብሎ በመንግስት ይካሄድ የነበረው የተመራቂዎች የስራ ምደባ መቋረጡ ተነገረ :: በወቅቱ ተመራቂዎች የነበሩ ተማሪዎች ተቃውሞ በእነ አበበ ገላው ተጀመረ ::እንደበፊቱ ጠንካራ ሊሆን አልቻለም ::
ከ25 አመታት በፊት ተባረሩት 42 የዩኒቨርሲቲ መምህራን እንዲመለሱ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶክተር አብይ አህመድን ውሳኔ ትልቅነት መረዳት የሚቻለው “ፕሮፌሰሩ ገበሬ ” ማየት ይበቃል::
 በመምህራን ስብሰባ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ 42 መምህራን “ይቅርታ ብለው ይመለሱ !” በሚል ሲያቀርቡ ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ” እኛ ነን ይቅርታ መጠየቅ ያለብን  ብለዋል::
ከዚህ ሁሉ አመታትና ልኬት አልባ በደል በኋላ የፕሮፌሰሩን የመንፈስ ከፍታ  አስገራሚ ነው ::ይህ ውሳኔ ሲወሰን የሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር 17 አመት ቢሆናቸው ነው::በሳቸው ዘመን የወሰዱት ውሳኔ  ምንጊዜም አድናቆት የሚቸረው ይሆናል::
ልዩነት ያመጣል….
አዛውንቱ በውቅያኖስ ዳርቻ እየተዘዋወሩ ነበር፡፡ አዛውንቱ አንድ ወጣት አንድ ነገር ወደ ውቅያኖሱ ደጋግሞ በመወርውር ተጠምዶ ያዩታል፡፡ቀረብ ብለው ልጁ የሚያደርገውን ሲከታተሉ ውቅያኖስ ማዕበሉ ደጋግሞ የተፋቸውን እና አሸዋ ላይ የቀሩትን Star fish – ስታር ፊሽ(ኮከብ ቅርፅ ያላቸው የአሳ ዝርያዎች) በመባል የውሃ ፍጥረታት ወደ ውቅያኖሱ መልሶ እየወረወራቸው ነበር፡፡ የውቅያኖሱ ማዕበል በሃይል እየገፋ የሚያወጣቸውን ወጣቱ ልጅ “ስታር ፊሾቹን” ሳይሰለች አንድ በእንድ እየለቀመ መልሶ ወደ ውቅያኖሱ መመለሱ የሚመለከቱት አዛውንት ድርጊቱ ገረሟቸው ጠየቁት፡፡
“ልጄ ምን እያደረክ ነው?” ብለው ጠየቁት
“ስታርፊሾቹ በውቅያኖስ ዳርቻ ባለው አሸዋ ላይ ከቆዩ ፀሃይ ስትወጣ ሊሞቱ ይችላሉ” ብሎ መለሰ ልጁ፡፡
” ይህ አስቂኝ ነው፡፡ሞኝነት ነው፡፡ በሺዎች ማይሎች በሚሸፍነው በዚህ የውቅያኖስ ዳርቻ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስታርፊሾች ወደ ውቅያኖሱ በመመለስ እንዴት ትዘልቀዋለህ? የቱንም ያህል ቁጥር ወደ ውቅያኖሶች ብትመልስም ምንም ዋጋ የለውም፡፡ልዩነት አያመጣም፡፡”
“ለዚህ ግን ዋጋ አለው ” አለ ልጁ አንድ ስታርፊሽ ወደ ውቅያኖሱ ማዕበል እየወረወረ፡፡
“ለኔ ዋጋ ባይኖረውም ለዚህ አሳ ግን ልዩነት ያመጣል !” አለ መልሶ ሌላ ስታርፊሽ ወደ ውቅያኖሱ እየመለሰ፡፡
Filed in: Amharic