>
5:13 pm - Wednesday April 19, 1189

".ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ የኢሕአፓ መሪና ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ!!!" (በየነ ጂ ተስፉ)

“.ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ የኢሕአፓ መሪና ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ!!!”
ከታሪክ ማህደር፣
በየነ ጂ ተስፉ
ከስር የምትመለከቱት #ያ ትውልድ# በሚል ስም የሚታወቅ ተቋም የዶክተር ተስፋይ ዳባሳይ 36ኛ የሙት ዓመት ለማስታወስ በሚል ዶክተር ተስፋይን በቅርበት የሚያውቁት ሰዎችን በመጠየቅ የፃፈው የዶክተር ተስፋይ ዳባሳይ የህይወት ታሪክ ነው። ዶክተር ተስፋይና መሰሎቹ የ1960ዎቹ ትግል ሲመሩ የነበሩና ዛሬ በህይወት የሌሎ ታዋቂ ሰዎች ማንነት ወጣቱ ትውልድ ማወቅ አለበት ከሚል መሰረታዊ እምነቴ በመነሳት፣ ይህ ያ ትውልድ ተቋም ስለ ዶክተር ተስፋይ ያዘጋጀው የህይወት ታሪኩ በእስካሁን ስለሱ ከተፅፉት የበለጠ ዶክተር ተስፋይን ይገልፅዋል ብዬ ስላመንኩ፣ ተቋሙን ከልብ እያመሰገንኩ ታሪኩን ጀባ ልላችሁ ፈለግኩ።
ዝክረ ዶክተር ተስፋዬ ደበሳይ፣  
ከያ ትውልድ ተቋም
 በሀገራችን ኢትዮጵያ ሰሜን ምሥራቅ ትግራይ ክፍለ ሀገር፤ በአጋሜ አውራጃ፤ በኢሮብ ወረዲ እምትገኝ፤ ዓሊተና እምትባል መንደር በጣም ደሀ ከሚባለ ቤተሰብ ክፍል ከአባቱ ከአቶ ደበሳይ ካሕሳይና ከእናቱ ከወ/ሮ ምህረታ ዓድዐማር በ1933 ዓ.ም. ሕፃን ተስፋዬ ተወለደ። ለአባትና እናቱ ብቸኛ የበኩር ወንዴ ልጃቸው ሲሆን ከሱ በኋሊ የተወለዱት ስድስቱም ሴቶች ናቸው። ተስፋዬ ደበሳይ ዕዴሜው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ በተወለደባት መንደር ዓሊተና ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ለመማር የነበረው ዕድሉ እጅጉን የጨለመ ነበር። ቀረብ ያለ ትምህርት ቤት በጊዜው የነበረው ከዓሉተና 35 ኪሎ ሜትር ገደማ እርቀት ላይ አዱግራት ከተማ ውስጥ ነበር። በዚህ ምክንያት ሕፃኑ ተሰፋዬ ዕዴሜው ለትምህርት እንደደረሰ ትምህርት ሉያገኝ ባለመቻሉ ወሊጆቹን ትምህርት ወደሚገኝበት ቦታ ወስደው ወደ ት/ቤት እንዱያሰገቡት ሌት ተቀን ይጨቀጭቃቸው እንደነበር ወላጆቹና ጎሮቤቶቻቸው ይመሰክራሉ። ወደ ሌላ ቦታ ወስደው ት/ቤት እንዲያስገቡት ግና በጣም ድሆች ነበሩ። ስለዚህ ተሰፋዬ ለመማር የነበረው ዕድሉ በጣም የተወሰነ፤ የመነመነ ነበር።
ተስፋዬ ገና በልጅነቱ ለመማር ከነበረው ጉጉት የተነሳ ውትወታውን ሳያቋርጥ ሉገኝ የሚችለውን አማራጭ ሁሊ ያሰሊስል ነበር። ተስፋዬ ዕዴሜው አሥር ዓመት ገደማ ሲሆነው በሌላ አከባቢ ይኖሩ የነበሩ፤ ከወላጆቹ ሻል ያለ ኑሮ የነበራቸውና የራሳቸው ልጆች ወዳልነበራቸው አክስቱ ሄዶ ለትምህርት የነበረውን ፍላጎት ገልጾ፤ ወላጆቹ ግና ከዴህነታቸው የተነሳ ለት/ቤት ሉከፍሉለት እንደማይችሉ በማስረዲት ያስተምሩት ዘንድ ተማጸናቸው። የተስፋዬን የትምህርት ፍላጎትና ጉጉት የተገነዘቡት አክስቱ ያለምንም ማመናታት የሚከፈለውን ከፍለው በዓዱግራት ከተማ በሚገኝ የካቶሉክ ት/ቤት አስገቡት።
 በተፈጥሮው ለየት ያለ ባህርይ እንደነበረው የሚነገርለት ተስፋዬ በአገኘው ዕድል በመጠቀም እርሳስና ደብተሩን ታጥቆ ለትምህርት ተነሳ። ጊዜም ሳይወስድ በገባበት የካቶሉክ ት/ቤት የሚመሰገን ጎበዝና ምርጥ ተማሪ ሆነ። በዓመት አንዴ ሳይሆን ሁለት ክፍልችን መዝለል ለተስፋዬ የተለመደ ነበር። ተስፋዬና ትምህርት፣ ትምህርትና ተስፋዬ ገና በለጋ ዕድሜው የተዋሃዱ መሆናቸውን በችሎታውና በጉብዝናው አስመሰከረ። ተስፋዬ የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዛው በካቶሉክ ት/ቤት እጅግ በጣም ጥሩ ውጤት በማምጣት ጨረሰ።
 በዓዱግራት የምትገኘው የካቶሉክ ት/ቤት የተመሠረተችበት ዋና ዓሊማ ተማሪዎቹዋን ለመንፈሳዊ ትምህርት ማዘጋጀት ስለነበረ የትምህርት ሥርዓትዋ ረዘም ላለ ጊዜ ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሥርዓት ጋር ሳይስተካከል ቆይቶ ነበር። ስለዚህ ለመጀመርያ ጊዜ ተማሪዎቿ በመንግሥት በሚሰጡ ብሔራዊ ፈተናዎች እንዱሳተፉ የፈቀደችው በአጋጣሚ ተስፋዬ በ8ኛ ክፍል በነበረበት ጊዜ ነበር። ይህም ቀደም ብሎ የታሰበበት ጉዲይ ሳይሆን ውሳኔው የተደረገው እነ ተስፈዬ 8ኛ ለመጨረስ ጥቂት ወራት ሲቀራቸው ነበር። ስለዚህ ያኔ በዛች ት/ቤት በስምንተኛ ክፍል የነበሩ ተማሪዎች ለብሔራዊ ፈተና በሚገባ ሳይዘጋጁ ነበር በከተማዋ ወደሚገኝ የመንግሥት ትምህርት ቤት (አግአዚ) ተወስደው በፈተናው የተሳተፉት። ተማሪዎቹ በፈተናው የተሳተፉት በድንገት በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ በመሆኑ ለሎች በሙለ ሲወድቁ ወጣቱ ተስፈዬ ግን ብቻውን አመርቂ ውጤት በማምጣት አለፈ፤ ለዚህም አመርቂ ውጤት ያበቃው ከልጅነት ጊዜ ጀምሮ ጥሩ አንባቢና አጥኚ ስለነበረ ነበር።
ታዲጊ ወጣቱ ተስፋዬ በትምህርት ቤቱ የሚታወቀውና የሚደነቀው በፈተናዎች በሚያመጣው ነጥብ ወይም የክፍል ውጤት ብቻ ሳይሆን፤ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና አስተማሪዎች በተሰፋዬ የሚደነቁት ወደር የሌለው አንባቢ በመሆኑም ጭምር ነበር። ትምህርት ቤቱ መጻህፍት ቤት (ሊይብረሪ) አልነበረውም።  በዛን ጊዜ ላይብረሪ የሚባል ነገር በከተማዋ ፈጽሞ አይገኝም። ሆኖም ተስፋዬ ከአስተማሪዎችና ከሌሎች ምሁራን እየተዋሰ ሁሌ ጊዜ መጻሕፍትና መጽሔቶችን ሲያነብ ይታያል፣ ይስተዋላል። አንዲንዴ ሥነ ጽሑፍ ከየት እንደሚመጣለት ተማሪዎች ብቻ ሳንሆን መምህራን ሁሉ ሳይቀሩ ይገርማቸው ነበር በማለት በወቅቱ በትምህርት ቤቱ የነበረ ተማሪ ይመሰክራል። በወቅቱ፤ በ1950ዎች አከባቢ የማይገኙና ያልተለመዱ ‘ታይም መጋዚን’ (Times) እና ‘ንዩስ-ዊክ’ (News Week) መጽሄቶችን ይዞ ይታይ ነበር።
‚አንድ አቶ አሰፋ ሱባ የሚባሉ በዛ ትምህርት ቤት የአማርኛ ቋንቋ አስተማሪ የነበሩ በጣም አዋቂ ሰው ‚ይህ ብርቅ ተማሪ (ተስፋዬ) የት እንደሚደርስና ለወደፊቱ ምን እንደሚሆን ለማየት ያለኝን ጉጉት ልቆጣጠረው አልችልም‛ ሲሉ አስታውሳለሁ ይላል‛ አቶ ግርማይ ተስፋ ጊዮርጊስ የድክተር ተስፋዬ አብሮ አደግ ጓደኛ ፣ በመቀጠልም ‚አንዲንዴ በዛን ጊዜ፤ ምንም ዓይነት መገናኘ ብዙሃን የማይደርሱበት አከባቢ ከመጀመርያ ደረጃ ተማሪ የማይጠበቁ ጠባዮች ይታዩበት ነበር። ጊዜው ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ከባዕዴ አገዛዝ ነፃ የሚወጡበት ጊዜ ስለነበረ ዜናውን እየተከታተለ ለሌሎች ተማሪዎች እንዱያውቁት ያደርግ ነበር። ከትምህርት ነፃ ስንሆን እሱ ወዲለበት እየሄዴን ከበብ አድርገነው ጥያቄዎች ስናቀርብለት ትዝ ይለኛሌ። ስለ ጋናና ሌሎች አዱስ ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገሮች፣ በተለይ ስለ አልጀርያ ህዘብ የነፃነት ትግሌ ወዘተ ቆሞ በማራኪ አንደበቱ ሲገልፅልን የነበርንበትን ቦታ ሳይቀር አስካሁን አስታውሳለሁ። ስለ አልጀርያ ህዝብ ትግሌ ሲገልጽ በዛ አጋጣሚ የፈረንሳይ አብዮትን በሚመለከትም መግለጫ ሰጠን። እኔ ለመጀመርያ ጊዜ ስለ ፈረንሳይ አብዮት የሰማሁት ያኔ ከሱ ነበር። ገና የስምንተኛ ክፍሌ ተማሪ እያለ የተስፋዬ ሁኔታ አስተማሪ እንጂ ተማሪም አይመስሌም ነበር ይላል አቶ ግርማይ ተስፋገርግስ።‛
ተስፋዬ በስምነተኛ ክፍሌ የሚሰጠውን ብሔራዊ ፈተና እንዳለፈ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መቀሌ ውሰጥ ወደሚገኝው ዮሐንስ አራተኛ ሄዶ የዘጠነኛ ክፍሌ ያጠናቀቀው እዛ ነበር። ያኔ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መቀሌ በስተቀር በላልች የትግራይ ከተሞች አልነበረም። ከዝግ ካቶሉካዊ ትምህርት ቤት ወጥቶ በመቀሌ የተማረበት ጊዜ ተሰፋዬ ከብዙዎች ለህዝባቸውና ለሀገራቸው ከሚቆረቆሩ መምህራንና ተማሪዎች የመተዋወቅ ዕድል እንዲገኘ ይናገር ነበር። ከተለያየ ገጠር የመጡ ድሃ ተማሪዎች ለቤት ኪራይና ኑሮ አየከፈሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለመቀጠል የነበረባቸው ችግር ምን ያህል አስቸጋሪና አሳዛኝ መሆኑን በዚሁ የመቀሌ አንድ ዓመት ቆይታው ግንዛቤ ሉያገኝ አስችሎታል። ተስፋዬ ደበሳይ በመቀሌ ያሳለፈውን የሕይወት ውጣ ውረድና ችግር ከተገንዘበና የወደፊት ዕድለንም በውጭ አገር ለመማር ከነበረው ፍሊጎት በመነሳት፤ ለዚህ አማራጩ በፊት ወደ ነበረበት የካቶሉክ ትምህርት ቤት መመለሰ ለትምህርት ወደ ውጭ አገር የመሊክ ዕድሉን ከፍ ሉያደርገው እንደሚችል በመረዲት ካቶሉካዊቷ ትምህርት ቤት፡ ዓዱግራት ተመለሰ።
እንደገና ወደ ዓዱግራቷ ካቶሉካዊት ት/ቤት ተመሌሶ እንደገመተውና ተስፋ እንዳደረገው ወደ ጣልያን አገር እስከተላከበት ጊዜ ድረስ ትመህርቱን የቀጠለው እዛው ዓዲግራት ነበር። እንደ አቶ ግርማይ አባባል ‚በዚያን ጊዜ ከመቀሌ የተመለሰበት ቀን በትምህርት ቤቱ አለቃ አሰባሳቢነት በአንድ ትልቅ ክፍል ተሰብስበን ቆይተን ተሰፋዬን ተነስተን በጭብጨባ ስንቀበለው ትዘ ይለኛል። በክፍሉ ያንድ ሀገር መሪ የገባ ነበር የሚመሰለው። የተስፋዬ ወደ ካቶሉክ ትምህርት ቤቱ መመለሱ የትምህርት ቤቱ አለቆችን፣ አስተማሪዎችንና ተማሪዎችን እጅግ በጣም ነበር ያስደሰተውና የተደረገለት አቀባበል እስካሁን ድረስ ይገርመኛሌ ይላል ግርማይ።‛
ተስፋዬ በዓዱግራት በምተገኘው ካቶሉካዊት ት/ቤት በኩል ወደ ሮም Urbaniana University ተልኮ በፍሌስፍና ጥናቱን በመከታተሌ በከፍተኛ ማዕረግ የዩንቨርስቲ ዶክተሬቱን እስኪያገኝ ድረስ ተማረ። ተሰፋዬ በዶክቶሪያሌ ድግሪ የተመረቀበት ጊዜ…‛ ይላል አቶ ግርማይ ‚…እኔም እሱ በተማረበት ዩንቨርስቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ስለነበርኩ ለዱግሪ ማሟያ የፃፈውን ፅሑፍ (ዱዘርተሽን) ያቀረበበት ቀን ተገኝቼ ነበር። ዱዘርተሽኑን ሲጽፍ የተከታተለው ዋና አስተማሪውና (Advisor) ላልች ብዙ የፍሌስፍና ፋክሌቲ አስተማሪዎች በተለያየ መልክ የቀረቡለት ጥያቄዎች በማስረጃዎች የተዯገፈ በቂና አስደሳች መልስ ስለሰጠ ከትልቅ ምስጋና ጋር ‚ Magna Cum Laude ( ማኛ ኩም ሊውደ ) ‛ የልቅነት ማዕረግ ሲቀበል ተገኝቼ  ነበር።‛
ዶክተር ተሰፋዬ ትምህርቱን እንደጨረሰ ወዱያውኑ ሀገሩን ለማገልገል፡ ለሕዝቡ ለመሥራት ወደ ሚወዳት ሀገሩ፡ ኢትዮጵያ ተመለሰ። ዶክተር ተስፋዬ ሥራ በሚፈሌግበት ጊዜ ማንም የሚረዲው ሰው አልነበረውም። ከአንድ ዘመድ ወይም ጓደኛዬ… ጋር ኣልስተዋውቅህ፣ ወደዚ ሂድና እገሌ ልኮኛሌ በለው/በላት ሊለው የሚችል ዘመድ ወይም ጓደኛ፣ ወይም ረዳት አልነበረውም። ስለዚህ ባከማቸው ትልቅ ዕውቀት የቀረቡለት ጥያቄዎችንና ቃለ መጠይቆችን በሚገባ ለመመለስ በመቻሉ በችልታው በማሰታወቅያ ሚኒስቴር ሥራ አገኘና በስነ ጽሑፍ ክፍሌ ተመድቦ ሠራ ———–ጀመረ ። ዋና ሥራውን ምርምር እያደረገ ለፕላኒንግ መሥሪያ ቤትና ለሌሎች ክፍልች ጥናት ማቅረብ ነበር። እንዱሁም የአንዳንዴ መጻሕፍትን ፍሬ ነገር (Summary) በአሕጽሮት እየጨመቀ ያቀርብ ነበር። በምርምር ክፍል ሲሠራ አንዳንዴ ግኝቶችን በመጽሔትና ዕለታዊ ጋዜጦች ለማውጣት ይሞክር ነበር። ሥርዓቱን የሚነኩ ከሆኑ አይታተሙለትም ። አንዳንዴ ሥርዓቱን በሚመለከት ትችት የማያደርጉ ጽሑፎች ግን አልፎ አልፎ ታትመውለታል። ለምሳሌ በፈረንጅ አቆጣጠር በMarch 1970 ገደማ Ethiopian Herald ላይ ‚Zera-Yaqob the Philosopher and not the Emperor‛ በሚል አርዕሰት ያወጣው መጣጥፍ ነበር።
ዶክተር ተስፋዬ በተባለው መሥርያ ቤት በሠራበት ጊዜ የተለያዩ ሚንስትር መሥሪያ ቤቶችን የምሰጢር መዛግብት ለመመርመር ልዩ ፈቃዴ ተሰጥቶት ስለነበር አጋጣሚውን በመጠቀም የሀገራችን የፖለቲካ ሥርዓትና ቢሮክራሲው ምን ያህል የተበላሸ እንደነበረ በሚገባ የመታዘብና የመመልከት ዕድል ያገኘው።  በዚሁ ጊዜ ዶክተር ተሰፋዬ በተጨማሪ በአባዲና ኮለጅ የማታው ክፍለ ጊዜ ፍልስፍና ያስተምር ነበር።
ዶክተር ተሰፋዬ በአዱሰ አበባ በሥራ ዓለም በቆየበት ጊዜ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ተራማጅ ምሁራን ጋርና የተማሪ ንቅናቄ መሪዎች ጋር፣ እንዱሁም ማታ የፍልሰፍና ትምህርት ለመከታተል ከሚመጡ የወታደርና የፖሊስ መኮንኖች ጋር ለመተዋወቅና አሰፈሊጊ ግንኙነቶችን ለመመሥረት ቻለ። ይህም በኋሊ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ምሥረታና ማደራጀት ውስጥ ለተጫወተው ትልቅ ሚና አስተዋጽዎ ነበረው። በተለይ ኢሕአፓን ካቋቋመው ተራማጅ ትውልድ ጋር ፅኑ ትውውቅ ሊገነባና ለድርጅቱ ምሥረታ ወሳኝ የነበረ ግንኙነት ሊፈጥር የቻለውም በነዚህ ዓመታት ውስጥ ነበር።
ዶክተር ተስፋዬ በ1964 ዓ. ም. እንደገና ወደ አውሮጳ (ስዊዘርሊንዴ) ሄደ። በዚህ ጊዜ ወደ ውጭ ሀገር የሄደው በኢትዮጵያ መካሄድ የነበረበትን አብዮት በሚመለከት በተለያዩ የወጭ አገሮች ከነበሩ ተራማጅ ኢትዮጵያውያን ጋር የትግሌ ዕቅድችን ለመመካከርና ለመቀየስ ነበር። በኢትዮጵያ፣ በአውሮጳና አሜሪካ እየተመላለሰ በየአህጉሩ ተደራጅተው የነበሩ ቡዴኖችን በማቀነባበር በኋላ ኢሕአፓ የተባለ በ1964 ዓ. ም. በሃገረ ጀርመን በርሊን ከተማ የተመሠረተውን የኢትዮጵያ ህዝቦች አርነት ድርጅት (ኢህአድ) በመመስረት ትልቅ ተጫውቷል። እንዱሁም በውጭ አገሮች የድርጅቱ የድጋፍ መሠረት የነበረው የኢትዮጰያ ተማሪዎች ማሕበራት በፌደራሊዊ ቅርጽ ተደራጅተው ትግላቸውን እንዱያስተባብሩ፤ እንዱያቀናጁ በማዴረግም ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
የ1966ቱ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት ወቅት ጊዜ ዶክተር ተስፋዬና ሌሎች ኢሕአፓን የመሠረቱ ተራማጆች የዓፄ ኃይሇሥላሴን መንግሥት ለመለወጥ የትጥቅ ትግልን የጨመረ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነበሩ። የ1966ቱ አብዮት እየተጧጧፈ በነበረበት ወቅት ከኤውሮጳ እንደገና ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የሃገርቤቱን ትግል ሲመሩ ከነበሩ አንዱና ዋናው ነበር። በዛን ጊዜ ዶክተር ተስፋዬ በፃፈው የድርጅቱ መግለጫ ውስጥ እንደ አቶ ግርማይ አባባል የሚከተለው ይገኛሌ ‚ዝግጅታችን በግድ ለሕጋዊም፣ ከሕግ ውጭ ለሚደረገው ትግሌ ጭምር መሆን አለበት፤ የሕገ መንግሥቱ ለውጥ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሕጋዊ ትግሌ የሚፈቅድ ከሆነ በሕግ እንታገላለን፤ ካልፈቀደ ግን በሕግ የተሰየመውን አመጽ በእውነተኛው ሕግ፤ በሕዝብ ሕግ ለመተካት እንታገላለን።‛
በአብዮቱ እንቅስቃሴ በአስተባባሪ ኮሚቴነት ሲሰራ ቆይቶ እራሱን እያጠናከረ ብቅ ያለው ወታደራዊ ደርግ በአዋጅ የተመሠረተበትና በግልፅ በመውጣት በዓፄው አገዛዝ ተጠያቂ ያላቸውን ሚንስትሮች፣ ከፍተኛ መኮንኖች፣ ባላባቶችንና መኳንንቶችን የሚያሥርበት ወቅት ነበር። በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ አቶ አክሉለ ሀብተወልድን ተክተው ጠቅላይ ሚንስተር ተሹመው የነበሩ ልጅ እንዳልካቸው መኯንን በልጅ ሚካኤሌ እምሩ የተተኩበት ጊዜም ነበር። ልጅ ሚካኤሌ በስዊዘርሊንዴ የኢትዮጵያ ልዐክ በነበሩበት ጊዜ ዶክተር ተስፋዬ ጋር ተዋውቀው ስለነበር ዶክተር ተስፋዬ ወደ አገር ቤት እንደገባ ፈላልገዉ አገኙትና የመሬት ይዞታ ሚንስትር እንዲሆን ጠየቁት።  ዶክተር ተሰፋዬ ግን የራሱ ስራና እቅድ ስለነበረው ምክንያት ፈጥሮ በከበሬታ የምንስተር መዓርጉን ሳይቀበላቸው ቀረ። ሆኖም ግን በመሬት ይዞታ ውስጥ ተመድቦ በትግራይ ክፍለ ሀገር እንድሠራ ከተፈቀደለት ለመሥራት ዝግጁ እንደሆነ ነገራቸው። እርሳቻውም ሀሳቡን ተቀበለት፣ አፀደቁለት። ዶክተር ተሰፋዬም መሬት ይዞታ ስራውን ምክንያት በማድረግ በትግራይ የድርጅቱን ስራ እንደልብ ለመስራትና ለማደረጀት ጥሩ አጋጣሚ ሆነለት። በተልይ ከ1964 የኢህአድ ምስረታ በኋላ በትግራይ ዓዲ ኢሮብ እንዲጀመር ተወስኖ ለነበረ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን ወደ አከባቢው ለመቀበል ሲደረግ የነበረውን ዝግጅት በቅር ሆኖ ለመምራትና ለለከታተል ትልቅ ዕድል አገኘ።
አንድ ዓመት የሚሆን ጊዜ በመሬት ይዞታ መስሪያቤት በተሰጠው የሥራ መስክ አየሠራና በሀገሪቷ ከአንድ ቦታ ወደ ላሌ ቦታ በሕግ እየተዘዋወረ ከሌሎች ጓዶቹ ጋር በሕቡእ ህዝቡን በኢሕአፓ ጥላ ሥር በማደራጀትና ትግለን በመምራት ላይ እያለ የዶክትር ተስፋዬ ማንነትን የሚያውቁ ከትጥቅ ትግል ጀመሪ አባላት የነበሩ 8 ሰዎች ከሜዳ ከድተው ለደርግ እጃቸውን ስለሰጡና የተስፋዬ የኢህአፓ መሪነት ስላጋለጡ እንደ ጥሩ ሽፋን ሲጠቀምበት የነበረ የመሬት ይዞታ መ/ቤት ሥራ ትቶ ህቡእ በመግባት ሙሉ ጊዜውን ለድርጅት ስራ በመስጠት መስጠት፤ ‚የትግሉ ነው ሕይወቴ‛ በማለት ኢሕአፓን የማደራጀትና የመምራት ኃላፊነቱን በሕቡእ ያከናውን ያዘ።
‚ዶ/ር ተስፋዬን የማውቀው ወደ ሠራዊቱ አሲምባ ሲመጣ ነው።‛ ያሉት የኢሕአፓ/ኢሕአሠ መሥራች አባል አቶ ፀሐዬ ረዳ ‚በመጀመሪያ የመጣ ወቅት ቤተሰቦቼን አያለሁ በማለት የመንግሥት መኪና ይዞ እስከ ዓሊተና እንደመጣ አስታውሳለሁ።
በዚህ ጊዜ አመጣጡ ኢሕአፓን ለማወጅ ሊደረግ ለታሰበው ኮንፈረንስ ብርሃነ መስቀል ረዲን ከአሲምባ ለመውሰድ በመምጣቱ የነበርነውን ጥቂት የሠራዊት አባላት ለማወያየት ጊዜም አልነበረውምና ለሁለተኛና ሦስተኛ ጊዜ አሲምባ ሲመጣ ነው በሚገባ የተወያየነውና ባህሪውንም በመጠኑ ለማወቅ የቻልኩት‛ ይላል አቶ ፀሐዬ በመቀጠል ‚ተስፋዬ ከጅምር እንጠቀምበት የነበረውን የሠራዊቱን ሕግና ደንብ በመጠኑም ቢሆን እንዲሻሻል ያደረገና ሠራዊቱን በጋንታ በጋንታ በማወያየትና የሠራዊቱንም አዛዥ ክፍሌ (Command Unit) ያዋቀረና ያጠናከረ ብቃት ያለው መሪና አመራር ሲጪ ጓድ ነበር።‛
‚ዶ/ር ተስፋዬ ከሻዕቢያ ጋር የተደረገውን ስብሰባ ለመምራት ለሦስተኛ ጊዜ ወደ አሲምባ መጥቷል። በዚህ ስብሰባ ላይ ሻቢያ ውይይቱን ከመደበኛ አካሄዴ ውጭ በጥያቄ መልክ በማካሄደ ይቀርቡ ለነበሩ ጥያቄዎች ዶ/ር ተስፋዬ እንደ ቡድኑ መሪነት እኔ ልናገር ባይ አልነበረም።
ይቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎችን በወቅቱ አብረን ለሄድነው ልዑካን ለእኔ፣ ለፀጋዬ ደብተራው፣ ለጋይምና ግሩም እንድንመልስና ማብራሪያ እንድንሰጥ በመጋበዝ ምን ያህል እራሱን ከፍ ከፍ የማያደርግና ሊታይ ሊታይ የማይታይበት እጅግ በጣም ዴሞክራቲክ ባህሪ የነበረው የኢሕአፓ መሥራች አባልና ከምሥረታው ጀምሮ የፓርቲው ፖሉት ቢሮ አባል፤ ችሎታና ዕውቀቱን ለሀገርና ሕዝብ የሰጠ የያ ትውልድ አባል ነበር ይላሉ አቶ ፀሐዬ ረዳ
ኢሕአፓ የፖለቲካ ፕሮግራሙን በነሐሴ 27 ቀን 1967 ዓ.ም. ለሕዝብ በማሳወቅና እራሱን ይፋ በማውጣት የደርግን ፋሽስታዊ አገዛዝ በሁለገብ ትግል በመታገል ለማስወገደና በሀገሪቷ ከሁለም የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት በመመስረት የሕዝቡን በሀገሩ ገዳይ የመወሰን ዴሞክራሲያዊ መብቱን በማወቅ ለሀገር ልማትና ዕዴገት መሠረት የሆነ ሕዝባዊ ሥርዓት ለመመስረት የታገለ የመጀመሪያው ቀዲሚ የሕዝብ ፓርቲ ነበር። የደርግ አገዛዝ የኢሕአፓን ሕዝባዊ መሠረት ሊያናጋ እንቅስቃሴውንም ሊያጨልም የሚችለው በየትኛውም የሀገሪቷ ክልል ዘርና ሃይማኖት፣ ዕዴሜና ፆታ ሳይለይ ያሳተፈና ለትግሉ ከዳር እስከዳር ያንቀሳቀሰን ፓርቲ ማንንም ሳይለዩ በጥርጣሬ፣ በመሰለኝ፣ በቅናት፣ በቂም በቀል ወዘተ. የታገዙ ግድያዎችን ‚በማር‛ በተለወሱ መርዘኛ አዋጆችና መግለጫዎች ግድያን በዘመቻ ለማካሄድ፡ ነፃ የመግደል መብትን በአጠገቡ ለተኮለኮሉት ቡድኖችና በየቀበሌው ያደራጃቸው የአብዮት ጥበቃዎች በመስጠት በሞላ ሀገሪቷ ላይ ነፃ እርምጃና ቀይ ሽብር በማወጅ አንድ ትውልድን ያለምንም ሕግ ያጠፋ አገዛዝ ነበር።
 ለዚህም ደርግ በ1969 ዓ.ም. ለተጀመረው የቤት ለቤት የአስሶ መደምሰስ ዕቅደ የሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽ/ቤትን በጉያው በተወሸቀው ሞላው ኢትዮጵያ ሶሻሉስት ንቅናቄ (መኢሶን) የበላይ ተቆጣጣሪነት በአዋጅ በማቋቋም ሦስት አሰሳዎችን አካሂዷል። የመጀመሪያው ህዲር 1969 ዓ.ም. ሲሆን ሁለተኛው ለሦስት ቀን የተካሄዯው መጋቢት 14 ቀን 1969 ዓ.ም. የተካሄዯው ሲሆን ሶስተኛውና የመጨረሻው ሚያዝያ 1969 የተካሄደውና መኢሶንም እራሱ የወጠነው ጥቃት ሰለባ የሆነበት አሰሳ ነበር።
የሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽ/ቤት እና መኢሶን የአስሶ መደምሰስ ዘመቻ በተግባር ለመተርጎም ሁሉተኛው የቤት ለቤት አሰሳ መጋቢት 14 ቀን 1969 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተጀመረ። የአብዮት ጥበቃ አባላት፣ ጦር ሠራዊቱ፣ ቀበሌዎች፣ የሕዝብ ድርጅት ጽ/ቤት በተለይም መኢሶንና ሌሎች በደርግ ዙሪያ የተሰበሰቡ ቡድኖች አባላት በቤት ለቤት አሰሳው ተካፋለዋል። ለሶስት ተከታታይ ቀናት የተካሄደው አሰሳ ሕዝቡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ፈፅሞ እንዲይንቀሳቀስ በወጣ የደርግ ተከታታይ መግለጫ የታገዘ ነበር።
ከኢሕአፓ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ወጣቶችና ሠራተኞች ሁሉ በጅምላ ታሰሩ። በ1969 ዓ.ም. በየካቲት ወር መጨረሻ አካባቢ በርካታ የኢሕአፓ አመራር አባላት አዱስ አበባን ለቀው መውጣታቸው ቢታወቅም ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ የአዲስ አበባው የኢሕአፓ መዋቅር ውስጥ የነበሩ አባላትን በእንዱህ ያለ ቀውጢ ጊዜ ትቶ መሄደ ለሕሊናው ስለከበደው ለሀገሩና ለሕዝቡ ብሎም ለትግሉ የሰጠውን ሕይወቱን፤ በፍጹም እምነቱ ሊተገብር፤ ማንኝውንም መከራና ስቃይ እራሱን ከፍ ሳያርግና ሳያስቀድም እንደ ሌሎች የኢሕአፓ አባላት አብሮ ሊመክትና ሊታገል ወሰነ።
እንደ አቶ ክፍለ ታዯሰ «ያ ትውሌዴ» ቅጽ II ገለጻ ‚መጋቢት 15 ቀን 1969 ዓ.ም. ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይና ጓደኛው በሪሁን ማርዬ የደርግ የቤት ለቤት አሰሳ መስሪያ ቤቶች ላይ ትኩረት ስላላደረገ አምባሳደር ትያትር አጠገብ ወደሚገኘው የኪዲኔ በየነ ሕንጻ አመሩ።
ሕንጻውን የመረጡት የበሪሁን ባለቤት የምትሰራበት ቢሮ በመሆኑና እዚያ በመሆን አሳሹን ቡዴን ለማሳለፍ በማቀድ ነበር። ዶ/ር ተስፋዬ በዕለቱ ይጓዝባት የነበረችው መኪና በተክለ ሃይማኖት አካባቢ ስታልፍ የመኢሶን አባላት በወቅቱ አሰሳ ያደርጉ ስለነበር መኪናው ውስጥ ዶ/ር ተስፋዬን መለየት እንደቻሉና መኪናውን መከተል ይጀምራሉ።‛ ይላል።
ተስፋዬና በሪሁን የሚከተላቸውን ሳይጠራጠሩ ወደ ሕንጻው ውስጥ እንደገቡ ተስፋዬ በመኢሶን አባልነት የሚጠረጠር አንድ ሰው ስላየ ሕንጻውን ለቆ ለመሄድ ወዱያው ወሰነ። ዶ/ር ተስፋዬ የሕንፃውን ደረጃዎች ወርዶ መሬት ሲደርስና የመኢሶን አሳሽ ቡድን ወደ በራፉ ሲጠጋ አንድ ሆነ። ወዱያውም አሳሹ ቡድን ተኩስ በመክፈት ከፊት ለፊት ይመራ የነበረውን በሪሁን ማርዬን ከመቅጽበት ገደለው፣ ዶ/ር ተስፋዬም አቆሰሉት። እንደቆሰለም ፊቱን አዙሮ የፎቁን ደረጃዎች በሩጫ በመውጣት ስድስተኛው ፎቅ እንደደረሰ ባለው መስኮት ቁልቁል ወደ መሬት ራሱን በመወርወር ተፈጥፍጦ ሞተ።
 ‚ቢወቀጥ አጥንቴ ቢንቆረቆር ደሜ ለአዱስ ሥርዓት ልምላሜ፣ ፍጹም ነው እምነቴ ለትግሉ ነው ሕይወቴ‛ ን     በደሙ ጻፈ።
 ልጆቹን ያስዘመራቸውን ‚ለዘመናት የሚለው የኢህአፓ ብሄራዊ መዝሙር በተግባር ራሱ ውድ ህይወቱን በተግባር በመክፈል አሳያቸው። ‚በመስዋዕቱ ትግሉን ቀጥሉ አታቁሙ!  አላቸው!
‚ልጓዝ በድል ጎዳና፣ በተሰዉት ጓድች ፋና‛ በተግባር አሳያቸው።
 ዶ/ር ተስፋዬን ፈለግ በመከተል በመኢሶንና ደርግ ገዳዮች እጅ ከመውደቅ ይልቅ ሕይወታቸውን ለትግሉ በመስጠት አኩሪ ጀግንነት አስመዝግበው እስከወዲያኛው ያሸለቡ የኢሕአፓ ሰማዕታት በርካታ ናቸው። እንደ አቶ ክፍሉ መጽሐፍ ያ ትውሌዴ ቅጽ II አገላለጽ ‚የተስፋዬ ሞት፡ በኢሕአፓ ሊይ ብቻ ሳይሆን በመላው የኢትዮጵያ መሠረታዊ ለውጥ ደጋፊ ትውልድ ላይ መኢሶን ከደርግ ጋራ በማበር ያሳረፈው ዱላ ካባድ፣ ክፉና ትግሉን ገዳይ በትር ነበር።‛
ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ፤ በዓፄነታቸው ሳይኮፈሱ፡ ዳር ድንበርን ብለው፡ ለሀገር አንድነትና ክብር ከድርቡሽ ወራሪ ጋር ሲፋለሙ የተሰዉት ዓፄ ዮሐንስ፣
 እጅህን ስጥ አለኝ…ለጠላት? ለወራሪ? ለእንግሉዝ? ብለው ለሀገር ክብር እራሳቸውን በመሰዋት ታሪክ አስመዝግበው ያለፉት ዓፄ ቴዎዴሮስ፣
 ለጣሉያን ፋሺስት ወራሪ ሕዝቡ እንዳይገዛ ገዝተው የሀገራቸውን ክብር በደማቸው የፃፉት አቡነ ጴጥሮስ፣ ወዘተ አርአያ በመከተል ለሀገርና ለሕዝብ መብት የሚደረግ ተጋድሎ መስዋዕትነት ሊከፍል ዝግጁ በሆኑ አመራርና አባላቱ ጽናት መሆኑን አካሉን የከሰከሰ፡ ደሙን ያፈሰሰ ጀግና የኢሕአፓ መሪና ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ ነበር ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ።
ዶ/ር ተስፋዬ የፓርቲው የርዕዮተ ዓለም ግንባር ቀደም አራማጅ፣ አደራጅ፣ የፖለቲካ ጠቢብና መሥራች አባትም ነበር። ለዝናና ለታዋቂነት ቁብ ያልነበረው ተስፋዬ፤ በሌላው ቀርቶ በኢሕአፓ አባላት እንኳን በጥቂቶች ነበር የሚታወቀው። ይሁንና በቅርብ በሚያውቁት ጓድቹ መካከል ከማንም በላይ የሚከበር ነበር። ተስፋዬ ብዙ አይናገርም፡ መናገር ሲጀምር ግን በአካባቢው ያለና የሚሰሙት ሁለ ከአንደበቱ የሚወጣውን እያንዳንደን ቃል እንዱያደምጡ የማስገደድ ኃይል የተላበሰ ነው። ተስፋዬ በማኅበራዊ ሕይወቱ እውነተኛ፣ ግልጽና ትሁት ሰው ነበር። ጥልቅ የዳሞክራሲና የፍትህ ስሜት የተዋሃደው ሰውም ነበር። በፖለቲካ አስተሳሰቡ ውስብስብና የረቀቀ ከመሆኑም ሌላ፡ ከማንም በላይ ሩቅ ሀሳቢ እንደነበር የሚያውቁት ሁላ ይመሰክራሉ። ‚ማንም ሰው አይናገረው እንጂ፤…‛ እንደ ያ ትውልድ ቅጽ II አባባል‚ማንም ሰው አይናገረው እንጂ፤ ከተስፋዬ ሞት በኋላ ኢሕአፓ የወትሮው ኢሕአፓ እንደማይሆን አውቆታል። ኢሕአፓ በተስፋዬ ሞት፤ ሕይወትና ግርማ ሞገስ የሚያጎናጽፈውን መንፈሱን አጣ። ከማንኛውም ጊዜ ይልቅ ጥብቅ መሪውን በሚፈልግበት ጊዜ፤ እንደ ተስፋዬ አርቆ አስተዋይና መንገድ አመላካች ሰው በሚሻበት አስቸጋሪ ወቅት ኢሕአፓ መሪውን አጣ።‛
ከድሀ ቤተሰብ ተወልዶ፤ በጠበበች ዕድል ተጠቅሞ የዘመናዊ ትምህርት ዕድልን በማግኘት በፍልስፍና የዶክተሬት ማዕረግነት የተጎናጸፈው ዶ/ር ተስፋዬ ዕወቀቱን ለሀገሩና ለድሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕድገትና ብልጽግና የዘረጋውን ምኞቱንና ተስፋውን ሳያይ በጅምር ተቀጨ። ‚የተስፋዬ ዛፉ፤ ሲከረከም ቅርንጫፉ‛ እንዲለው ገጣሚ የተስፋዬ ተስፋ በተስፋ ቀረ። ብርሃን ዓይኑን ከደነ። በአጭር ተቀጨ፣ ተቀበረ።
ዶ/ር ተስፋዬ ባለትዳርና የአንዱት ሴት ሌጅ (ሐምራዊት) አባት ነበር። ሐምራዊት የአባቷን ጣዕም ሳታውቅ በሕጻንነታቸው ደርግ ወላጆቻቸውን ከበላባቸው፤ የአባት ወይም የእናት ወይም የሁለቱንም ጣዕም ሳያጣጥሙ፣ ሳያውቁ ካደጉት፤ የወላጆቻቸው አኩሪ ታሪክ እንኳ ያልተዳሰሰላቸው በርካታ የትላንት ሕፃናት የዛሬ ወጣቶችና ጎልማሳዎች ውስጥ ከሚመደቡት አንዷ ናት።
«ያ ትውልድ ተቋም» ከተነሳበት ዓላማ አንደ የዚያን ትውሌዴ ሰማዕታት መዘከርና ታሪካቸውን ለትውልድ ማስተላለፍ በመሆኑ የዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይን 36ኛ የሙት ዓመት መዘክር ስናስታውስ በጥሌቅ ሐዘን ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልና ኢሕአፓ አንድ ሁነኛ መመኪያውንና መሪውን ያጣበት ቀን መጋቢት 15 ቀን 1969 ዓ.ም.። ኢትዮጵያ ሀገራችን አንድነቷን ጠብቃ የልጆቿ መብት የተከበረባትና ለሀገር ብልጽግናና ለልማት የተከፈለው የያ ትውሌድ ሰማዕታት ደም ከንቱ እንደማይቀርና ሁሌም በትውልዴ ሲዘከር፡ ሲታወስ እንደሚኖርና የትግላቸውም ፍሬ ኢትዮጵያ ሀገራችንንና ልጆቿን ከፍ ከፍ እንደሚያደርጋት እምነታችን የጸና ነው።
‚ዶ/ር ተሰፋዬን የማውቀው በሶሰት የተለያዩ አጋጣሚዎች ነው።
መጀመርያ፦ በዓዲግራት ካቶሉካዊት ት/ቤት እኔ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪ ሁኜ እሱ ደግሞ የመካከለኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖ፤ ሁለተኛ፦ በጣሉያን አገር እኔ የመጀመርያና የሁለተኛ ዓመት የዩንቨርስቲ ተማሪ ሁኜ ዶ/ር ተሰፋዬ ደግሞ የድረ ምረቃ (Post Graduate) ተማሪ ሆኖ፤ ሶስተኛ፦ በአዱሰ አበባ በሥራ ዓለም ቆይቶ እንደገና ወደ አውሮጳ በተመለሰ ጊዜ‛ ያሉን አቶ ግርማይ ተስፋ ጊዮርጊስ፡ የዶ/ር ተስፋዬን 36ኛ ዓመት የሙት ዓመት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ ይህን አጭር የሕይወት ታሪኩን ለማዘጋጀት ላደረጉልን ከፍተኛ ትብብር «ያ ትውሌዴ ተቋም» የከበረ ምስጋናችንን እያቀረብን ሌሎችም የአቶ ግርማይን አርአያ በመከተል በምታውቁት ታሪክ ላይ ትብብራችሁ ቀና ይሆን ዘንድ በዚህ አጋጣሚ «ያ ትውልድ ተቋም» መልዕክቱን ያስተላልፋል።
ይህንን የዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይን የሕይወት ታሪክ በመጠኑም ቢሆን ለመጻፍና ማንነቱን ለመግለጽ ላደረግነው ጥረት ከፍተኛ ትብብር ያደረጉልንን አቶ ግርማይን እንዳመሰገንን፤ ለዚህም ስኬታማነት በሩን የከፈቱልንን ባለቤቱ የነበሩትን ወ/ሮ ፍቅርተ ገ/ማርያምንና ብቸኛ ልጁን ወ/ሪት ሐምራዊት ተስፋን በያ ትውልድ ወገኖቻችን፡ በኢትዮጵያ ሀገራችንና ሕዝባችን እንዱሁም በ«ያ ትውሌዴ ተቋም» ስም ከፍተኛ ምስጋናችን ይድረሳችሁ።
በመጨረሻም ከኢሕአፓ መስራች አባላት አንድ የነበሩትና በተለይ የኢሕአሠ ጥንስስ መሠረት ለመጣል የመጀመሪያው የሠራዊቱ መሥራች አስኳል አባል የነበሩት አቶ ፀሐዬ ረዲ፡ ስለ ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ያላቸውን እውቅናና በተለይ በአሲምባ ያላቸውን ትዝታ በማውሳት ላደረጉልን ቀና ትብብር «ያ ትውሌዴ ተቋም» ወደር የሌለውን ምስጋናውን ያቀርባሌ።
የዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ በተለይ በኢሕአፓ ውስጥ የነበረው ሚና፣ እስከ ዕለተ ህልፈቱ ያበረከተውን አስተዋጽዎና የትግል ተሳትፎ በተመለከት መረጃ እንዲሰጡን ከሌሎች ትብብር ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባለመሳካቱ የተሰማንን ቅሬታ እየገለጽን አሁንም በድጋሚ የኢሕአፓና ዛሬ በህይወት የሌሉ እንደ ዶ/ር ተስፋዬ ዓይነት መሪዎቹ ታሪክ የሀገርና የሕዝብ እንደመሆኑ ጽፈው ሉያስነብቡ ፈቃደኛ ባልሆኑ፡ ሌሎች ሲጽፉም ጸጉራቸው በሚቆመው ‚እኛ ብቻ‛ ባዮች ታሪክ ብቻ እንዳልሆነ «ያ ትውሌዴ ተቋም» በድጋሚ ኢያሳውቅና ሊያሰምርበት ይወዳል።
ያ ትውልድ ተቋም፣ መጋቢት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ።
ዋቢ ጽሁፎች • ቃለ መጠይቅ፡ ከአቶ ግርማይ ተስፋ ጊዮርጊስ ጋር • ቃለ መጠይቅ፡ ከአቶ ፀሐዬ ረዲ የኢሕአፓ መሥራች አመራር አባል• «ያ ትውልድ» ቅጽ ሁለት ክፍለ ታደሰ፤ 1991 ዓ.ም.
Filed in: Amharic