>

አገር ወዳድ ሁሉ ከሙስጠፋ ዑመር ጎን ሊቆም ይገባል!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

አገር ወዳድ ሁሉ ከሙስጠፋ ዑመር ጎን ሊቆም ይገባል!!!
አቻምየለህ ታምሩ
ባለፈው ሰሞን ስለ ሙስጠፋ ዑመር ቃለ መጠይቅ አስተያየት  ለመጻፍ ፈልጌ ነበር። ሆኖም ግን ያገራችን ፖለቲከኞችና ጎሰኞች  የሚገዙበት ቋሚ  መርህና ሀሳብ ስለሌላቸው፤  ዛሬ የተናገሩትን ነገ ባፍጢሙ እየደፉ የደገፋቸውን ሁሉ ስለሚያሳፍሩና አንገት ስለሚያስደፉ  ለሙስጠፋ  ጥሩ ሀሳብም ያለኝን  ድጋፍ  በይፋ  እንዳልገጽል አድርጎኝ ቆይቷል።
ከሰሞኑ እየሰማነው ያለው የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ሙስጠፋን ለማስወገድ  እያካሄደው ያለው ሴራ ግን ስለ ሙስጠፋ ዑመር በቃለ ምልልሶቹ ወቅት  የታዘብሁትን የዘገየ  አስተያየት ጭምር  ለመሞንጨር እንድነሳ አድርጎኛል።
የጅግጅጋው ልጅ  ሙስጠፋ ዑመር የሐሳብ ጥራት ያለው ሰው ነው። ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ እንደ ሙስጠፋ ዑመር የሐሳብ ጥራት ያለው ሰው አላጋጠመኝም። ኢትዮጵያን መምራት ያለበት እንደ ዐቢይ አሕመድ አይነት ጎሰኛ ሳይሆን እንደ  ሙስጠፋ ዑመር አይነት የሀሳብ ጥራት ያለው ፖለቲከኛ ው። ሙስጠፋ  ከየት ተነስቶ የት እንደሚደርስ አሻግሮ የሚያይና በሀቅ ላይ የተመሰረተ እውነታ ያለው ሰው ነው።
በእኔ እምነት በአገራችን ውስጥ ካለፉት ዘጠኝ  ወራት ወዲህ ወደፊት ከመጡት የአካባቢ ገዢዎች ሁሉ  መሪ መሆን የሚያስችል ሀሳብ ያለው ብቸኛው ፖለቲከኛ ሙስጠፋ ዑመር ብቻ ነው። ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ [ለማ ይሻለኛል] ሌሎቹ  የአገዛዙ ኮልኮሌዎች የመንደር ጎሰኞች [Ethnic Entrepreneurs]  እንጂ ፖለቲከኞች አይደሉም።
ፖለቲካ ማለት በእውቀትና በአስተሳሰብ የተሻሉ ሰዎች ሕዝብን ለማገልገል ያስተሳሰብና የተግባር ፉክክር በማድረግ በጥላቻ የፈረሰው የአገር  ሞገስ ተመልሶ የሚገነባበት፤ በሞራል ስልጣኔ የጸና የሲቪል ፍኖት ነው። ፖለቲከኞች ይህንን ፍኖት የሚያራምዱ ናቸው። ጎሰኛነት ሀሳብ የሌለበት፤  የነገር  ዓለሙ ሁሉ  ማያ መነጸር ጎሳ የሆነበት ነው። ጎሰኛነት ጎሰኞች  ጎሳችን የሚሉትን የኅብረተሰብ ክፍል  ስሜት እየኮረኮሩ ሰለባ አድርገው  የህመማቸው ቁራኛ  የሚያደርጉበት የእእምሮ በሽታ ነው። እንደ ፋሽስት ወያኔና ኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች በጎሰኛነት በሽታ ለሚማቅቁ ሰዎች የሳይኮ አናሊሲስ  ሕክምና እንጅ ፖለቲካ  የህመማቸው ፈውስ ሊሆን አይችልም።
ባጭሩ ጎሰኛነት እንደ ፖለቲካ አልፋና ኦሜጋ የሚቀበል አንድ ሰው የተስተካከለ እሳቤ ያለው አይደለም። ሙስጠፋ ፖለቲካ የሀሳብ እንጂ የነገድ ወይንም የጎሳ ከሆነ አገር ያፈርሳል ያለው የሐሳቡን ጥራት የሚያሳይ ነው።  ጎሳችን የሚሉትን በጨለማ ውስጥ አስገብተው ጎሰኛነትን እየጋቱ ለዘላለም በባርነት ሊያኖሩት  ላይ ታች የሚወርዱ ተንጋደው የተፈጠሩና ሀሳብ የሌላቸው  የአገዛዙ ባላደራዎች የሆኑት የኦሕዴድ የድንቁርና በሽተኞች በሙስጠፋ ዑመር ላይ መነሳታቸውን እየሰማን ነው።
ለጎሰኞች  ፖለቲካ ማለት ከተቻለ ሁሉን ወደ ዞምቢነት መቀየር፤ ካልተቻለ ደግሞ አሳዶ ማሳደድ ነው፤ ምክንያቱም እነሱ የእድገት ተስፋቸውን ያቆራኙት የአዕምሮ የበላይነት ካላቸው ሰዎች ውድቀት ጋር ነውና የጎሰኞች ፓርቲ የሆነው አገዛዙ  የጠራ ሀሳብ ያለው ሙስጠፋ ቢያሰጋው የማይጠበቅ አይደለም!
ነገር ግን ጥራት ያለው ሀሳብ፤ ራዕይ ያለው ፖለቲከኛ፤ ብሩሕ አእምሮ ያለው መሪ የሚሻ አገር ወዳድ ሁሉ ከምስራቁ ፈርጥ ከሙስጠፋ ዑመር ጎን ሊቆም ይገባል!
Filed in: Amharic