>

አርባ አራቱ ታቦት የሚለው ታሪክ መነሻው ምንድን ነው ? (መ/ር ታሪኩ አበራ)

በሙሴ ዘመን የነበረው ታቦት አንድ ነው፤ አሁን ለምን በዛ???
መ/ር ታሪኩ አበራ
አርባ አራቱ ታቦት የሚለው ታሪክ መነሻው ምንድን ነው ?
 
 ጎንደር በኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ከአክሱምና ላሊበላ ቀጥሎ ታላቋ የመንግሥት ማዕከል ነበረች፡፡ በመንግሥት ማዕከልነት የተቆረቆረችው በአፄ ፋሲል (1624-1660 ዓ.ም) ነው፡፡ ጎንደር የመንግሥት ማዕከል ብቻ ሳትሆን በጊዜው የመንፈሳዊ ትምህርት ማዕከልም ነበረች፡፡ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የመጻሕፍት ትርጓሜና የአቋቋም ትምህርት/ዜማ/ ይበልጥ የተስፋፋውና በየሀገሩ ያሉ ሊቃውንት በመናገሻ ከተማዋ ጎንደር በነገሥታቱ አማካይነት በመሰባሰባቸው ሲሆን ከዚያን  ዘመን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ መንፈሳዊ ትምህርት በስፋት የሚሰጥባት የትምህርት ማዕከል ለመሆን ችላለች፡፡
በአሁኑ ሰዓት በሰሜን ጎንደር በሚገኙ 21 ወረዳዎች ከ2117 ያላነሱ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ሲኖሩ በዋና ከተማዋ ደግሞ ከ92 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ በአብነት ት/ቤት ረገድም የመጻሕፍት ጉባዔያት፣ የአቋቋም ምስክር፣ የቅኔ አብያተ ጉባዔያት እንዲሁም የዜማ ት/ቤቶች በከተማዋ እና በዙሪያዋ በሚገኙ ወረዳዎች ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ ከ92 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም በአብዛኛው ስማቸው ደጋግሞ የሚነሳው የ44ቱ ብቻ ነው፡፡
አንዳንዳን ሰዎች  በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙት የአብያተ ክርስቲያናት ታቦታት ስያሜ ብዛት ሲመስላቸው ሌሎች ደግሞ በጎንደር በጥምቀት በዓል ወደጥምቀተ ባህር የሚወርዱትን ብቻ ሲሉ ይደመጣሉ፡፡አርባ አራቱ ታቦታተ ጎንደር ከቤተ መንግሥቶቹ በተጨማሪ ታሪካዊዋ ጎንደር የምትታወቅበት ቅርስ ነው፡፡ ጎንደር ከተማ በአፄ ፋሲል የመንግሥት ከተማ ከመሆኗ አስቀድሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ተክለዋቸው የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ቀሐ ኢየሱስ፣ አርባዕቱ እንስሳ፣ አበራ ጊዮርጊስ በምሳሌነት ይጠቀሳሉ።
ጎንደር የመንግሥት ከተማ ከሆነችበት እስከ ጎንደር ዘመን ማክተሚያ ፈፃሜ መንግሥት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ (1772-1777) ድረስ 18 ነገሥታት የነገሱ ሲሆን እነዚህም አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተዋል፡፡ እንግዲህ 44 የሚባሉት አብያተ ክርስቲያናት ጎንደር የመንግሥት ከተማ ከመሆኗ አስቀድሞ የተተከሉበትን ጨምሮ እስከ ፈፃሜ መንግሥት ተክለ ጊዮርጊስ (1772-1777) ድረስ የተተከሉትን ብቻ ሲሆን ቁጥራቸውም 44 ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ከዘመነ መሳፍንት እስከ አሁን የተተከሉ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም ከ44ቱ የሚቆጠሩ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ አርባአራቱ ታቦታተ ጎንደር በጎንደር ዘመን በጎንደር ከተማና አካባቢው የሚገኙና የነበሩ 44 አብያተ ክርስቲያናት ጥቅል ስም ነው፡፡
ስለዚህ አርባ አራቱ ታቦት ሲባል ይህን ታሪክ ተከትሎ የመጣ ስያሜ እንጂ በቤተክርስትያናችን ስፍር  ቁጥር የሌላቸው ታቦታት ነው ያሉት! ምክንያቱም ሁልጊዜም አዲስ ቤተ ክርስቲያን በሚሰራበት ጊዜ ታቦት ተቀርጾ በላዩ ላይ ” ኢየሱስ ክርስቶስ አልፋ ኦሜጋ ” ተብሎ ይጻፍበታል። ኢየሱስ ፊተኛውና ኃለኛው፤ መጀመሪያውና መጨረሻው ማለት ነው ፡፡ ይህ ቃል ከተጻፈበት በኋላ በሊቀ ጳጳስ እጅ ተባርኮና ሜሮን ተቀብቶ በመንበሩ ይሰየማል (ይቀመጣል) ፣በቅዳሴም ጊዜ ሕብስቱና ወይኑ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ቄሱ ሥርዓተ ቅዳሴውን የሚያከናውነው ሕብስቱን ሥጋ መለኮት ፣ ወይኑን ደመ መለኮት ወደ መሆን የሚለውጠው በዚህ በታቦቱ ላይ አክብሮ በሚጸልየው ጸሎት ነው ፡፡ሥጋዬን ብሉ ደሜንም ጠጡ እያለ ያመኑትን ሁሉ የሚጠራበት የምሕረት ምሥዋዕ (መሠዊያ) ነው ፡፡ ታቦት በሐዲስ ኪዳን እውነተኛው የሕይወት ምግብ የክርስቶስ ሥጋና ደም የሚቀርብበትና የሚፈተትበት መሠዊያ ነው።
ስለዚህ ታቦት  በአርባ አራት ቁጥር ብቻ የሚወሰን ሳይሆን እልፍ አዕላፍ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል! “ለሚጠይቋቹ ጥያቄ ሁሉ እንዴት መልስ መመለስ እንዳለባቹ ታውቁ ዘንድ ንግግራቹ ሁል ጊዜ በጨው እንደተቀመመ በፀጋ ይሁን” ቆላስይስ 4:6
ብዙ ጊዜ ከኦርቶዶክስ እምነት ውጪ ያሉ ሰዎች የሚያነሱት ጥያቄ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን ጽላት እንዲያስቀምጥበት ሥራ ያለው ታቦት አንድ ብቻ ነው ዛሬ ግን በጣም ብዙ ነው ለምን ይሄ ሆነ ? ይላሉ። ለዚህ ጥያቄ ምላሻችን ሁለት ነው። አንደኛ እግዚአብሔር በሙሴ ዘመን ሰጥቶት የነበረው ጽላት በጊዜው ለነበረው ሕዝብ ማምለኪያ ነው።በአንድ በተወሰነ ቦታ ተሰብስቦ በሙሴና በአሮን  መሪነት ያመልክ ለነበረው  የተወሰነ ሕዝብ አንድ ታቦት በቂው ነበር ።ሕዝብ ሲበዛና እግዚአብሔርን የሚያመልከው አማኝ  በየቦታው ሲሰፋ ግን ጽላቱን ማብዛት የግድ ነው።ለዚህም ነው እግዚአብሔር ለሙሴ እኔ የሰጠሁህን ዓይነት ጽላት ቅረጽ ብሎ ፈቃድ የሰጠው ዛሬም እንደ ሙሴ ያሉ የሃይማኖት አባቶች ይህንን ቅዱስ ንዋይ ያዘጋጃሉ።
” ጽላቶቹም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቶች ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ።”
(ኦሪት ዘጸአት 32:16)
” እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እንደ ፊተኞች አድርገህ ጥረብ።”
(ኦሪት ዘጸአት 34:1)
ሁለተኛው ምክንያት፤ ታቦታትን ማብዛት መጽሐፍ ቅዱስን ከማብዛት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ነው።መጽሐፍ ቅዱስ ጥንት ሲዘጋጅ አንድ ብቻ ነበር።ዛሬ ግን በቢልየን ደረጃ ያውም በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ በዓለም ዙሪያ ተባዝቶ ይገኛል። መጽሐፍ ቅዱስ ለምን በዛ ? የሚል ጠያቂ ካለ መልሱ አጭርና ግልጽ ነው።እግዚአብሔርን የሚያመልከው ሕዝብና በቃሉ ሕይወት ማግኘት ያለበት አማኝ ስለበዛ መጽሐፉም ተባዝቷል። ይህንን ማድረግ ደግሞ ምንም ስህተት የሌለበት የተቀደሰ ተግባር እንደሆነ ሁሉ።ታቦታት ቢብዙና እግዚአብሔርን የሚያመልከው ሕዝብ ባለበት፣አብያተ ክርስቲያን በታነጸበት ቦታ ሁሉ ቢቀመጥ ስህተት አይደለም።ታቦት አይመለክም የምናመልከውና የምንሰግደው በታቦቱ ላይ ለተጻፈው አልፋና ኦሜጋ ለሆነው በደሙ ቤዛ ለሆነን ጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው።ክብር ለስሙ ይሁን።
(ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች ምዕ. 2)
———-
10፤  በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥
11፤ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።”
በተጨመሪ ስለ ታቦት  በስፋት ለመረዳት ከዚህ ጽሑፍ በፊት በዚሁ የፌስ ቡክ ገጼ ላይ የተጻፉትን ሁለት  ጽሑፎች በደንብ ይመልከቱ።
ወገኖቼ መንፈሳዊ ትውፊታችንን፣ታሪካችንና ሃይማኖታችንን አጥብቀን እንያዝ። ዛሬ በአውሮፓና በአሜሪካ ሰለጠንን፣ ወንጌል በራልን፣ብለው ሲመጻደቁ የነበሩና መንፈሳዊ ትውፊታቸውን አራግፈው የጣሉ የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች የአምልኮ መቅደሶቻቸውን ዘግተው ወደ ዓለማዊነትና ወደ ለየለት የክህደት ዓለም ውስጥ ገብተዋል። ቤተመቅደሶቻቸውን ቡናቤት፣ልብስ መሸጫ ቡቲክና፣የመኖሪያ አፓርትመንት አድርገውታል።ዛሬ ሃይማኖት የለሽ ትውልድ ፈጥረው ወጣቶቻቸው የሰይጣን እምነት
ተከታዮች፣ሰዶማውያን፣የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞች፣ዘወትር የጌታ ስቅለት የሚታሰብበትን ዕለተ አርብ በስካርና በጭፈራ የሚያነጉ የርኩሰት ተባባሪዎች ሆነዋል።በአጭሩ ታቦትን ሲቃወሙ የነበሩ የፕሮቴስታንት  ፓስተሮቻቸውና ተከታዮቻቸው በአብዛኛው ሃይማኖት የለሾች  ከሃድያን/ATHEIST/ ሆነው ቀርተዋል።
ወገኖቼ ኢትዮጵያውያን እባካችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አጥባቃችሁ ያዙ ትውልዱን ከክርስቶስ ጋር በፍቅር አጣብቃ ፣በምግባርና በሃይማኖት ይዛ የቆየች ወደፊትም የምትኖር ብቸኛዋ የክርስቶስ ሙሽራ ይህችው እናት ቤተክርስቲያን ነች።ዛሬ በሐሰተኛ ነቢይትና በአጭበርባሪ ፓስተሮች በስሜት የሚነዳው ሕዝብ ለጊዜው ነው ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ሁሉ ነገራቸው እያስጠላው፣ሌብነታቸው እያንገፈገፈው ሲመጣ አንቅሮ ይተፋቸዋል፤ የሚያሳዝነው ግን ከቤተክርስቲያንም ወጥቶ ኦርቶዶክስን እየረገመ ስለኖረ ተመልሶ መምጣት ስለሚከብደው ጨፋሪና ዘማዊ፣በፍልስፍና ልቡ የተጠለፋ ከሀዲ ትውልድ ሆኖ ይቀራል።እባካችሁ ከቤተክርስቲያን ኮብልላችሁ የወጣችሁ ኦርቶዶክሳውያን አገልጋዮችና ምዕመናን ወደ  እናት ቤተክርስቲያናችሁ ተመለሱ።የሚያብረቀርቅ ሁሉ ወርቅ አይደለም ።ኢየሱስ፣ ኢየሱስ ያለ ሁሉ ኢየሱስ የሚያውቀው አይደለም ከቶውን አላውቃችሁም የሚባሉ በጣም ብዙ ናቸው።
ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ላለመመለስ የካህናቱን ድክመትና፣የመሪዎቹን ስንፍና አትመልከቱ የተሰቀለውን ክርስቶስ ብቻ ተመልከቱ።ቤተክርስቲያኒቱ ላይ ጣት ከመቀሰርና ከማጥላላት ይልቅ ዶግማዋ ምን እንደሆነ በጥልቀት መርምሩ፣በነገረ መለኮት ዙሪያ ያላት ጥልቅ አስተምህሮ ምን እንደሆነ ሊቃውንቱን ቀርባችሁ ጠይቁ።የዶክትሪን መጻሕፍቷን መርምሩ።በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ብቻ ቤታክርስቲያኒቱ ላይ ዘለፋ አትናገሩ።የእውቀት ደረጃዬ ምን ያህል ነው ብላችሁ በመጀመሪያ ራሳችሁን ፈትሹ።ምን ያህል መጻሕፍቶቿን አንብቢያለው ብላችሁ አዕምሯችሁን መዝኑ።ቤተክርስቲያኒቱ እንኳን አንብበን ቆጥረን የማንጨርሰው እልፍ የምስጢር መጻሕፍት ያላት ታላቅ መንፈሳዊ ሀገር ነች።ሁሉ በፍቅርና በትህትና ይሁን።
” እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”
(1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5:5)
ለበረከት ሁኑ
Filed in: Amharic