>
5:13 pm - Sunday April 19, 5615

ማነው ባለዕጣ? ማነሽ ባለሣምንት!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ማነው ባለዕጣ? ማነሽ ባለሣምንት!!!
አሰፋ ሀይሉ
መቼም በጆሮ የማይገባ ነገር የለም በዘንድሮ ዘመኑ የፖለቲካችን ሞቃታማ አየር። ባለፈ ሰሞን በትግራይ ክልል በሙስና የተጠረጠሩ ሰዎችን ሊያስሩ በአውሮፕላን ወደመቀሌ የሄዱ የፌዴራሉ መንግሥት ፖሊሶች ራሳቸው ታስረው ከቀናት ቆይታ በኋላ በመጡበት አኳኋን በደብረዘይት የአየር ኃይል ፌርማታ እንዳራገፏቸው ሠማን። ጉድ አልን። አወራን። አጣራን። ግን ጉድ አንድ ሰሞን ነው። እና ያ ጉድ በዚያው ሰሞን በረደ።
በረደ ስንል ግን ከሠመ ማለታችን አይደለም። የበረደው እኮ የፖለቲካው ሐሩር ነው። እንጂማ ተረኛ የመታሠር ዕጣው በየትኛው የኢህአዴግ ቱባ ባለሥልጣን ላይ እንደሚወጣ እኮ ሰው ሞቅ አድርጎ ያወራል። ያስተነትናል። ይተነብያል። ይከራከራል ጎራና ጎሣ ለይቶ። አብዛኛው የሰዉ ወሬ ቀጣዮቹ የመታሠር 1ኛ ባለዕጣዎችን ይደረድርልሃል።
ከእነዚህ “እጩ” (“እጩ ታሣሪዎች”) መሐል ሁሌም ከሰዉ አፍ የማይጠፉ ወፋፍራም የፓርቲው ሰዎች አሉበት። ከእነርሱ መካከል ለምሣሌ… የእኛ ሰው በደማስቆ (ማለቴ ራሳቸውን ከመንበራቸው ያገለሉት የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ)፣ የቀድሞዋ ቀዳማይት እመቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ መጤው ፖለቲከኛ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ቀድሞ አቶ መለስን ይቅር-በለኝ ብለው በመፀፀታቸው እንደነ አቶ ስዬ ከመታሠር ዕጣ ፈንታ ለጥቂት የተረፉት አቶ አባይ ፀሐዬ፣ ሥልጣን በቃን ብለው ከቲቪ ምስሎቻቸውን ገለል ያደረጉት እነ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ እነ ጄ/ል (ወይም አቶ) አባዱላ ገመዳ፣ አሁን በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉት ሚኒስትር (የቀድሞው የፖሊስ ኮሚሽነር) እነ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፣ ….. ኧረ የስንቱን የሰው አፍ፣ የስንቱን ሰው ስም አስታውሰን እንዘልቀዋለን…?! (እዚያው በፀበላቸው!)
አሁን ደሞ ሌላ የሰዉ አፍ አስቀድሞ የለበለበውን የሌላ አንድ ሰው ስም ስንት ከተተነበየለት የታሣሪነት ዕጣ ፈንታ 2ኛውን ዕጣ አፈሱት የሚል ዜና እየሰማን ነው። አሁን – በሰው አፍ ብቻ ሣይሆን – በአካል በአምሳል – የመታሠር ዕጣ ተራው ፊቱን ወደ ልበ ደንዳናው የኢህአዴግ አድራጊ ፈጣሪ ባለሥልጣን ወደ አቶ በረከት ስምዖን የዞረ ይመስላል።
ትናንት – በኤርትራዊ ደሜ ተለይቼ የዘረኝነት ሰለባ ሆኜያለሁ ብለው የዘረኝነትን አጉል ጠንቅ ሊያስረዱን መከራቸውን ሲበሉ የተስተዋሉት እኚህ የደረቅ ፖለቲካ ደራሲና የቀድሞ የኢሕአዴግ መንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ሚኒስትር – አቶ በረከት ሥምዖን – ራሳቸው ጠፍጥፈው በጋገሩት የኢህዴን (የተከታዩ ብአዴን ወይም የአሁኑ አዴፓ) ኢህአዴጋዊ ፓርቲ በሚተዳደረው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፀጥታ ፖሊሶች –  ዛሬ ላይ – በቦሌ ጃፓን ኤምባሲ (ጎን!) ከሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው – እርሳቸውም እንደ ተራ (ተረኛ) ሰው – “ቅደሙ ወደክልልዎት!” ተብለው – ወደ ባህርዳሩ መታሠሪያ ጣቢያቸው መወሰዳቸውን – ይኸው ዛሬ በጆሮአችን ሠማን።
ጉድ ነው ዘንድሮ አልኩ። ዘንድሮ የሰው አፍ ጠብ ማለቱን አቁሟል ማለትም ነው መሠል። ዕድሜ ብዙ ያሣየናል። ከሰነበትን ገና ብዙ እናያለን። እውነት እያደር ገና ትጠራለች። እና ትጣራለች። የመንግሥትን ሀብት እንደ ጓሮ እርሻው የቀጠፈውም፣ የዜጎችን ህይወት እንደ ጥቅምት አበባ የቀጠፈውም፣ እውነትን ከሕዝብ ሸሽጎ በአደባባይ የቀጠፈውም፣ ….ሁሉም ቀጣፊ – በየፊናው – በያይነቱ የሚጠብቀው – ባለዝሆኑ ዕጣ ያለ ይመስላል።
ትናንት – የትናንቱ ሥርዓት – የብዙ አነጋጋሪ የትናንት ባለዕድለኞችን እስሮችን በየዓይነቱ አሣይቶን እንዳለፈ መቼም ምንም ነጋሪ አያሻውም። ከጠንቋዩ አባባ ታምራት እስከ አስደናቂው ተዋናይ ዶ/ር ኢንጂነር ሣሙዔል ዘሚካኤል እስር፣ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ከእነ አቶ እስክንድር ነጋ እስከ እነ ዶ/ር መረራ ጉዲና እስር፣ ከሥኳር ባለሥልጣናቱ ከእነ አቶ ጠ/ሚ ታምራት ላይኔ እስከ እነ አቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረዋህድና እስከ መከላከያ ሚ/ሩ አቶ ስዬ አብርሃ እስከ ድረስ ሁሉንም ዓይነት እስሮች በያይነቱ አሳይቶን አስተምሮናል። እና እስር ብንሰማ አይገርመንም ብለን ነበር። ያልን ካለን ልክ አልነበርንም። እያንዳንዱ ዕጣ የራሱ ትርክት፣ የራሱ ግርምት፣ የየራሱ ልዩ ነገር አለውና። እና ተገረምኩ ዛሬ። ሣልወድ። በግድ።
እና እስር ብርቁ አትሁን። ይልቅስ ሕዝቡ የሚያወራውን አድምጥ። እና ነገ የማን ተራ ይሆን…?! እያልክ የሚሆነውን ጠብቅ። እውነት ትዘገያለች እንጂ ተቀብራ አትቀርምና። በዘንድሮው የሀገራችን የፖለቲካ ትኩስ አየር – ምንም የማይሆን ነገር የለም። ሁሉም ሰዓቱን ጠብቆ ይሆናልና። ማነው ባለተራ? ማነው ባለሣምንት?
እስሩስ በየሣምንትም ቢሆን ባልከፋን። መታሠር እኮ ህጋዊ ሂደት ነው። ከታሠርክ በህግ እጅ ነህና ህግ ነው የሚዳኝህ። ሃቅህ ነው የሚያድንህም የሚያስኮንንህም። ግን ይህ የሚሆነው ፍትህ በተረጋገጠበት ሀገር ላይ ነው። በነፃ የዳኝነት አካል ፊት ብቻ ነው። ፍትህ በሌለችበት መስክ ላይ የጉልበተኛው ማንነት ቢቀያየር የሚፈይደው አዲስ ነገር አይኖርም። ለውጥ የለሽ ለውጥ ብቻ ይሆናል። ነገር ግን በፍትህ የሚደረግ ከሆነ ለውጡ ትልቅ ለውጥ ሆነ ማለት ነው። ትናንት ፍትህን ከብዙዎች ላይ ለቀሙ ሁሉ ታላቁ የህሊና ቅጣት ቀማኞቹን በፍትህና በፍትህ መንገድ ብቻ መጠየቅና መዳኘት ብቻ ነው።
በተረፈ ግን በሀገራችን የአንዱ ክልል ፍ/ቤት ከሌላ ክልል ሰው እየታሠረ እንዲመጣለት የሚጠይቅበት ህጋዊ ሥርዓትና አግባብ ስላለው ያ በጥብቅ ቢተገበር፣ ህግና የዳኝነት ተቋማት የፖለቲካ ግቦች ማስፈፀሚያ መሣሪያ ሆነው እያገለገሉ ያለመሆናቸው ሁልጊዜም በሠከነ ህጋዊ አግባብ በየደረጃው የሚፈተሽበት ጥብቅ ሀገር-አቀፍ አሠራር (ወይም ሥነሥርዓት) በፍጥነት ተግባራዊ ቢደረግ በሀገራችን የፍትህ መስክ ሊከሰቱ የሚችሉ ብዙ የወደፊት እንዘጭ እንቦጮችን ከወዲሁ ለማስቀረት ይቻላል ብዬ አበቃሁ።
ፍትህ ለሁሉም!
እምዬ ኢትዮጵያ ፍትህን ለልጆቿ ሁሉ በፍትህ-ርትዕ ሚዛን እያርከፈከፈች፣ በዜጎቿ ፍቅር-ኅብረት አምራና ደምቃ፣ ለዘለዓለም በብልፅግና ትኑር።
ፈጣሪ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ።
Filed in: Amharic