>
6:13 pm - Wednesday November 30, 2022

ጳውሎስ ኞኞ ለደርግ ጽ/ቤት የጻፈው ታሪካዊ ማመልከቻ!!! (ኤልያስ በላይ)

ጳውሎስ ኞኞ ለደርግ ጽ/ቤት የጻፈው ታሪካዊ ማመልከቻ!!!
ኤልያስ በላይ
 
ለኩራዝ ድርጅት በታህሳስ ወር 1978ዓ/ ም መጽሀፌን ለህትመት ሰጠሁ። በኋላ ምን እንደደረሰ ብጠይቅ “የበላይ አካል ወሰደው” አሉኝ። ‹‹ማነው የበላዩ አካል?›› ብዬ ደጋግሜ ብጠይቅ “ታስበላናለህ እና አርፈህ ተቀመጥ” እባል ጀመር። “ንገሩኝና ልበላ” ብልም የሚነግረኝ አጥቼ ለፍቼ ባዶ እጄን ቀረሁ!!!
ደራሲ እና ጋዜጠኛ የጳውሎስ ኞኞ ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ በአገር ውስት እና በውጭ አገራት የተፃፃፏቸውን ደብዳቤዎች በመሰብሰብ እና በማሳተም ሂደት ውስት ከፍተኛ ችግር ገጥሞት እንደነበር ይነገራል። ለዚህም እንደ ማሳያ፣ ጳውሎስ ኞኞ የሚከተለውን ደብዳቤ ለደርግ አባል ለሆኑት ለተስፋዬ ወልደስላሴ ፅፎ ነበር። ይህ ደብዳቤ በመስከረም 13ቀን 1979 ዓ/ም ተፃፈ።
ለጓድ ተስፋዬ ወልደስላሴ
የኢሠፓ ማእከላዊ ኮሚቴ የፖለቲካ ቢሮ ተለዋጭ አባልና የአገር እና ህዝብ ደህንነት ጥበቃ ሚኒስትር
አዲስ አበባ፤
—-
ደብዳቤዬ የህይወት ውሳኔ ጉዳይ ስለሆነ ስራ እንደሚበዛቦት ባውቅም እስከመጨረሻው እንዲያስቡልኝ በታላቅ ትህትና እለምናለሁ።
ዋናው ቁም ነገር፤ አገሬን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ጠልቼ ሳይሆን በደረሰብኝ የግል በደል ከኢትዮጵያ ምድር ለመውጣት ስለፈለኩኝ የመውጫ ፍቃድ እንዲሠጠኝ ለመለመን ነው።
በእኔ እምነት፤ እያወቅሁ በኢትዮጵያ ላይ ክፉ ነገር አልሰራሁም። በአገሬ አስተዳደርም ላይ እያወቅሁ የሰራሁት መጥፎ ስራ የለም። ይሄ እንግዲህ በኔ እምነት ነው። መጥፎ ነገር ብሰራ ኖሮ መንግስት ከራስ ፀጉሬ አንዲቱን እንኳን ሳይነካ በሰላም እና በክብር አያኖረኝም ነበር።
አሁን ከፋኝ። የከፋኝም በሶስት ነገሮች ነው።
፩ኛ) ለአዲስ አበባ ከተማ መቶኛ አመት መታሰቢያ መፃፍ እንዳዘጋጅና ለአንዳንድ ወጪዎች የሚረዳኝ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እርዳታ እንዲያደርግልኝ የዛሬ አራት አመት ጠይቄ አምስት ሺህ ብር እርዳታ ሊሠጠኝ ተዋውለን ገንዘቡን ተቀበልኩ። በውላችን መሰረት የማዘጋጀውን መፃፍ የማሳተሙ ቅድሚያ የማዘጋጃ ቤቱ ሆኖ ማዘጋጃ ቤቱ ባያሳትመው እኔ እንዳሳትመው ተዋውለን ነበር። ስራውን ጨርሼ በውላችን መሰረት እንዲፈፀም ደጋግሜ ለማዘጋጃ ቤት ብፅፍም መልስ አጣሁ። አሁን በመጨረሻው፤ “መፅሃፉ በግለሰብ ስም መታተም አይገባውም ተብሎ ተወሰደብህ” የሚል ወሬ ሰማሁ። ከ 300 ገፆች በላይ የሚሆነውን መፅሃፌን ማን መሆኑን የማላውቀው የበላይ ወርሶኝ ያጠራቀምኳቸውን 500 ያህል ፎቶግራፎቼን ታቅፌ ቀረሁ።
፪ኛ) ቀድም ብሎ በጓድ ፍሰሃ ደስታ፣ በኋላም በጓድ ፍቅረስላሴ ወግደረስ ፍቃድ የዳግማዊ አጤ ምኒሊክ መዝገብ ቤትን እንዳጠና አስፈቅጄ በእረፍት ጊዜዬ እየሰራሁ የዳግማዊ አጤ ምኒሊክን ደብዳቤዎች ገልብጬ ወሰድሁ። ደብዳቤዎቹን ከፋፍዬ የስምና የቦታ ማውጫ ሰርቼ፣ ታይፕ አስመትቼ ፳፪፻፵፭ (2245) ደብዳቤ ያህል ያሉበትን ያንደኛውን መፅሃፌን እንዲታተም ለመነጋገር ለኩራዝ ድርጅት በታህሳስ ወር 1978ዓ/ ም ሰጠሁኝ። በኋላ ምን እንደደረሰ ብጠይቅ “የበላይ አካል ወሰደው” አሉኝ። ‹‹ማነው የበላዩ አካል?›› ብዬ ደጋግሜ ብጠይቅ ታስበላናለህ እና አርፈህ ተቀመጥ እባል ጀመር። “ንገሩኝና ልበላ” ብልም የሚነግረኝ አጥቼ ለፍቼ ባዶ እጄን ቀረሁ።
፫ኛ) በዚህ ላይ እንዳለሁ አንድ ቀን የማስታወቂያ ሚኒስትራችን ከቢሮአቸው ጠርተውኝ “ብዙ የታሪክ ፅሁፎችን፣ ማስረጃዎች እና ደብዳቤዎች አሉዎት?” ቢሉኝ ለስራ የተጠየቅሁ መስሎኝ “አዎን ያቅሜን ያህል ያጠራቀምኳቸው አሉኝ” አልኳቸው። “ያለዎትን ማንኛውንም የታሪክ ማስረጃ ለመንግስት እንዲያስረክቡ ታዘዋል” ቢሉኝ፤ “ማነው ያዘዘው?” አልኳቸው። “የበላይ አካል ስላዘዘ በአስቸኳይ ያስረክቡ” አሉኝ። “ለዚህ ከሆነ የለኝም” ብላቸው፤ “ቤትዎ ይፈተሻል” ብለውኝ እስካሁን ሳላስረክብ አለሁ።
እኔ የኢትዮጵያ ህዝህ የሚበደልበትን ልስራ አላልኩም። ታሪኩን እንዲያውቅ ያቅሜን ያህል እየፈላለግሁ የችሎታዬን ያህል ልስራለት ነው የምለው። አሁንም የጀመርኩት እንደ አልማናክ ወይም እንደ ኢንሳይክሎፒዲያ መሳይ የኢትዮጵያ ታሪክ መፅሃፍ አለኝ። በስራዬ ተስፋ ባልቆርጥም፤ “ከደሞዜ እየተበደርኩ በከባድ የኑሮ ችግር እየኖርሁ ታይፕ ካስመታሁ በኃላ ያ የማይታወቅ የበላይ አካል ቢወርሰኝስ?” እያልኩ አስባለሁ። ስለዚህ በረጋ ህሊና ስራዬን ለመጨረስ ከኢትዮጵያ ምድር ለመውጣት አሰብሁ።
ከኢትዮጵያ ምድር ልውጣ ስል አገሬን ከድቼ አይደለም። ግን ይሄን እኔ ሳላውቀው የሚወርሰኝን የበላይ አካል የሚባለውን ስም ጠልቼ እና ፈርቼ ነው። ታላላቆቹ የበላዮች ይሄን እንደማይሰሩ አውቃለሁ። በዚህ በኩል ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የለኝም። ለዚህም ያለኝ ማስረጃ ታላላቆቹ የበላይ አካሎች በኔ ላይ መጥፎ አስተያየት ቢኖራቸው ኖሮ ለህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን አባልነት በበላይ አካል ተመርጬ ባልገባሁ ነበረ። እኔን ግራ ያጋባኝ በበላይ አካል ስም የግል ስራዬን ያውም ድርሰት መወረሴ ነው።
አገሬን ብቻ ሳይሆን መንግስቴንም እወዳለሁ፣ አከብራለሁ። የምወደውና የማከብረውም በአፌ ሳይሆን ከልቤ ነው። ይህም በመሆኑ ነው እንደሌላው ሳልጠፋ በህጋዊ መንገድ ከኢትዮጵያ ምድር ለመውጣት የፈለግሁት።
ከኢትዮጵያ ምድር ወጥቼ ወዴት እንደምሄድ አላውቅም። በአሳቤ ያለው የአማርኛ የህትመት ፊደል ካለበት አገር ሄጄ የማውቀውን የኢትዮጵያን ታሪክ እያሳተምሁ ለመኖር ነው። ድግሜ የምናገረው ያደግሁበትንና የኖርኩበትን አገሬን፣ የምወደውንና የሚወደኝን የኢትዮጵያን ህዝብ ከድቼ አይደለም። ስራዬን ከማልወረስበት አገር ሰርቼ ካልሞትሁ ለመቀበር ወደ አገሬ የምመለስ ሰው ነኝ።
እንኳን ከኢትዮጵያ ውጪ ከአዲስ አበባ ደብረ ዘይት የምሄድበት ገንዘብ የለኝም። ጥረቴ መፅሃፍ በመግዛትና ይህን በመሳሰለው ስለነበረ ኑሮዬም የተመሰቃቀለ ነው። ስለዚህ ጓድነትዎን የምለምነው ሶስት ነገሮችን ነው፤
፩ኛ) የሚወዱኝን ኢትዮጵያውያንን የመሳፈሪያ ገንዘብ እንድለምንና እንዳጠራቅም እንዲፈቀድልኝ ነው። ይህን ሳላሳውቅ ልመናዬን በሚሥጥር ባደርገው የመንግስቴን ስም ለማጥፋት የተነሳሁ ስለሚመስልብኝ እንደዚያ አይነቱን ነገር አልፈለግሁም። አላደርገውም። የሚቻል ቢሆን በጋዜጣም ሆነ በቃል ለመለመን እንድችል የፈቃድ ወረቀት እንዲሠጠኝ፣ በወረቀት መፍቀዱ የማይቻል ከሆነ ግን ልመና ለመጀመር መነሳሳቴን መስሪያ ቤቱ አውቆ በቃል እንዲፈቀድልኝ ነው።
፪ኛ) የምሄድበትን አገር ርቀት የሚወስነው በልመና የሚገኘው ገንዘብ ልክ በመሆኑ ልመናዬን ስጨርስ በህጋዊ መንገድ የመውጫ ፍቃድ እንዲሠጠኝ።
፫ኛ) በምወጣበት ጊዜ ያሉኝን የኢትዮጵያ ታሪክ መፅሃፎቼንና አንዳንድ ጥርቅምቅም ማስረጃዎቼን ይዤ እንድወጣ እንዲፈቀድልኝ በማክበር እለምናለሁ።
ይህን ደብዳቤ ሥጽፍ፤ “ይበላሃል” የሚባለው የማላውቀው የበላይ አካል እንደሚበላኝ እጠረጥራለሁ። አንዳንድ ወዳጆቼም ነገሩን በሚስጥር እንዳደርገው መክረውኝ ነበር። እኔ ግን በአገሬ ላይ የማውቀው ወንጀል ያልሰራሁ ሰው በመሆኔ እንደሌባ ከኢትዮጵያ ወጥቼ ያልበደለኝም ያገሬን መንግስት ስም ለማሳማት አልፈለግም። በዚህ ምክንያት፤ ያ በይ የተባለው ህቡዕ አካል ቢበላኝም ካለሁበት የብስጭት ኑሮ የማይቀረውን ሞት ብሞት ይሻላል በማለት በግል ውሳኔዬ ይህን ደብዳቤ ፅፌሎታለሁና በሚያደርጉልኝ ከፍተኛ እርዳታ ደስ እንደሚያሰኙኝ ተስፋ አለኝ።
ይህን ደብዳቤዬን ለጏድ ሊቀመንበር መንግስቱ ሃይለማሪያም ዓልጻፍኩም። ነገሩን አስቤው ስራ ስለሚበዛባቸው በአንድ ፣መልኩም የግል ጉዳይ አላደክማቸውም በማለት ነው። ግን ለሁለት ሰዎች ያህል እንዲረዱኝ በማለት ግልባጩን መስጠቴን ይወቁልኝ።
ጨርሰው ስላነበቡልኝ እግዚአብሄር ይሥጥልኝ። በቅርብ ጊዜ ተስፋ ያለው ደስ የሚያሰኝ መልስዎን እንደማገኝም ተስፋ አለኝ።
=====
ምንጭ:
አጤ ምኒሊክ በአገር ውስጥ የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች – በጳውሎስ ኞኞ
Filed in: Amharic