>

አንባገነናዊነትን እያስታመሙ መቅበርም ይቻላል!!! (ያሬድ ኃይለማርያም)

አንባገነናዊነትን እያስታመሙ መቅበርም ይቻላል!!!

ያሬድ ኃይለማርያም

* የአቶ በረከት እስር ይዛሬ ስምንት ወር ሰኔ 6፣ 2018 እ.አ.አ የጻፍኳትን ጽሁፍ አስታወሰችኝ ወቅቱን እና ሁኔታውን ገላጭ ናትና ድጋሚ ለጠፍኳት

የአንባገነናዊ ሥርዓት ሞት ሁለት መልክ ያለው ነው። አንደኛው ከሱ የፈረጠመ ጡንቻ ባለው ወይም በሕዝባዊ አመጽ ድባቅ ተመቶ በሱ መቃብር ሌላ ጉልበተኛ ወይም ሕዝባዊ መንግሥት የሚሾምበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው። ሁለተኛው ሞት ደግሞ እያዋዛ እና ረዥም ጊዜ የሚወስድ በረዥም ጣርና የስቃይ ጉዞ ውስጥ የሚመጣ ሞት ነው። በሰው ብንወስደው የመጀመሪያው በድንገተኛ አደጋ ወይም በቀናቶች ህመም የሚሞት ሰው ሲሆን ሁለተኛው ሞት ደግሞ እያንዳንዱ የሰውነት ክፍሉ አንድ በአንድ እየከዳውና ከጥቅም ውጭ እየሆነ በስቃ ውስጥ ለተራዘመ ጊዜ ወይም ለአመታት ቆይቶ የሚሞት ሰው ነው።

የአንድን አንባገነናዊ ሥርዓት የሞት ፍጥነት የሚለካው ለሥርዓቱ መሞት ምክንያት በሆነው ገፊ ኃይል መጠንና ፍጥነት ነው። አዝጋሚና ደክም ያለ ግፊት ሲሆን ሥርዓቱን መግደሉ ባይቀርም ሞቱን አዝጋሚ ያደርገዋል። በተቃራኒው ግፊቱ ፈጣን እና ከተገፊው ሥርዓት አቅም ጋሪ ሲነጻጸርም እጅግ የገዘፈ ከሆነ የተገፊው ሥርዓት ሞት ፈጣን ይሆናል። ለዚህም በቅርቡ በአንዳንድ የአረብ አገሮች የታዩ ሥር ነቀል ለውጦች ጥሩ ምስክሮች ናቸው።

በአገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ የታዩትን መንግስታዊ ለውጦች የተመለከትን እንደሆን ሥር ነቀል ስለሆኑ በአንዱ ሥርዓት መቃብር ሌላው እየተተካ ነው የመጣነው። በእነዚህ ለውጦች አገርን የበደሉ ብቻ ሳይሆኑ ለአገር መልካም የሰሩ በርካቶች ጭምር የለውጦቹ ሰለባ ሆነዋል። ሂደቱም ሥርነቀል የአንባገነኖች መተካካት ነው የሆነው። በቅርቡ በአገራችን እየታየ ያለው የመንግስት ሳይሆን የፖለቲካ ለውጥ ይህን አዙሪት የሰበረ ይመስላል። ምንም እንኳን የለውጥ ግፊቱ የመጣው ከሕዝብ ቢሆንም የለውጡን ሂደት ሊቆጣጠር የሚችልና በቂ አቅም የገነባ የተደራጀ የፖለቲካ ኃይል ባለመኖሩ የተነሳ የለውጥ ሂደቱን የተቆጣጠረው እራሱ የአገዛዝ ሥርዓቱ ነው። ይህ ደግሞ ስር ነቀል በሆነ ለውጥ በሌላ የለውጥ ኃይል የመተካት እድሉ እንዲጨናገፍ ተደርጓል። ስለዚህ ለውጡ የሥርዓት ሳይሆን ፖለቲካ ብቻ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ የፖለቲካ ለወጥ የሥርዓቱን አንባገነናዊ ባህሪ እያስታመሙ በሂደት እንዲሞት እና በሚደረጉትም ለውጦች በአንባገነናዊነት ቦታ ዲሞክራሲያዊነት እንዲያብብ ማድረግ ነው።

አንድ አንባገነናዊ ሥርዓት በሕዝብ ግፊት እራሱን እንዲያርቅ ሲገደድ እና የመጣውን የሕዝብ ግፊት ተቋቁሞ በሥልጣን መቆየት ሲችል ሁለት እድሎች ይኖሩታል። አንደኛው እራሱን አርቆና አስተካክሎ ሕዝብ በሚፈልገው መልክና ቅርጽ በማስተካከል በቀጣዩ የአገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ዋና ተሳታፊ መሆን ነው። ሁለተኛው ደግሞ Aristotle ከብዙ አመታት በፊት እንዳለው “. . . tyranny can also change into tyranny. . .” ሥርዓቱ ወደ ከፋ አንባገነናዊነት በመቀየር የሕዝቡን ግፊትና የለውጥ ተነሳሽነት ማጨናገፍና ማዳፈን ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ አንባገነናዊ ሥርዓትን እያስታመሙ መቅበር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ የወሰዷቸውን እርምጃዎች ከስሜታዊነት በጸዳ በጥንቃቄ የታዘብን ከሆነ ይህንን ነው የሚያሳየው። ጠ/ሚኒስትር አብይ የተጋፈጡት የ27 አመት የወያኔን አንባገነናዊነትን ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ውስጥ ለዘመናት ከአንዱ አንባገነን ወደ ሌላኛው አንባገነን እየተሸጋገረ ከመጣው የፈላጭ ቆራጭነት አስተሳሰብ ግር ጭምር ነው። ብዙ ተቺዎቻቸው ይህን ይህን አላክናወኑም እያሉ ሲዘረዝሩ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ እስከ አሁን ያከናወኗቸውን ሁሉ በዜሮ እያባዙ ድካማቸውን መና ለማስቀረት ሲሞክሩ ይስተዋላል። እንዳንዴም የተወሰኑትን ለውጦች በመቀብለ ይልቅስ የለውጡ ባለቤት እኔ ወይም እኛ ነን ሲሉም የሚስተዋሉ አሉ። ለማንኛውም ጠ/ሚኒስትሩ የሚመሩት አስተዳደር ከዚህ የሚከተሉት አንኳር ለውጦችን አስመዝግቧል። እያንዳንዱ ለውጥ ለአገር ሰላም፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ለኢኮኖሚ መሻሻል እና ለአገር አንድነት ያለውን ፋይዳ መመዘን ይቻላል። ለአሁን የታዩትን አንኳር ለውጦች ልጥቀስ።
– የፖለቲከኛ እስረኞች መፈታት፣
– በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በተለይም በመከላከያ እና በደህንነት ተቋማት ውስጥ እየታዩ ያሉት ለውጦች፣
– ሥርዓቱ ለአፈና መዋቅሩ እና ለምዝበራ ይጠቀምባቸው የነበሩ ትቋማትን ማጽዳት እና አንዳንዶቹንም በከፊልም ቢሆን በግል ባለኃብቶች እንዲያዙ መወሰናቸው፣
– ከኤርትራ ጋር ያለውን ፍጥጫ ለመቋጨት ለረዥም ጊዜ በህውሃት ተዘግቶ የነበረውን የእርቅ መንገድ መክፈታቸው፣
– ጎምቱ የሚባሉ የህውኃት የጦር ጀነራሎች እና የደህንነት አመራሮች ሂደቱን እንዳያደናቅፉ ከመንገዳቸው ላይ ገሸሽ ማድረጋቸው፣
– የወያኔ ጥርስ ውስጥ የገቡና በመፈንቅለ መንግስት ተጠርጥረው የታሰሩ የጦር ጀነራሎችን በምህረት ለቆ፣ ማእረጋቸው እንዲመለስ እና ጡረታቸው እንዲጠበት ማድረግ፣
– ዋና ዋና ለሚባሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች የድርድር ጥሪ ማቅረባቸው እና
ሌሎች እየወሰዷቸው ያሉ ተመሳሳይና ቀላል ግምት የማይሰጣቸው እርምጃዎች ሥርዓቱ ውስጥ ቀንድ ያበቀለውን አንባገነናዊነት ቀስ በቀስ እየገደሉ ለመሆኑ ከበቂ በላይ ማሳያዎች ናቸው።

አንባገነናዊነትን አንዴ መግደል እንጂ ማስታመም ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። ይህ አይነቱ ሥር ነቀል ለውጥ በምኞት አይገኝም። እጅግ ከፍ ያለ የሰው ሕይወት እና የአገር ሃብት ያስከፍላል። በቃኝ የማያውቅ የአገዛዝ ሥርዓት ሽንፈትን የሚቀበለው ሲሞት ብቻ ነው። ያ ባይሆን እማ ጋዳፊ እና ሳዳም ሁሴን የአውሬ ሞት ባልሞቱ ነበር። አገራቸው ወድሞና ሕዝባቸው ተሰዶ የወንበዴዎች መፈንጫ ባልሆነ ነበር። ከአንባገነኖች ጋር አብራ የምትሞት አገር እንድትኖረው የሚፈልግ ሰው ያለ አይመስለኝም። ስለዚህ እያስታመሙም ቢሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አንባገነናዊ ሥርዓትን ከኢትዮጵያ ለመሸኘትና ታሪክ ሆኖ እንዲቀር ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ስህተታቸውን እያረሙም በጀመሩት የለውጥ ጉዞ እንዲገፉበት ከማበረታታት የተሻለ አማራጭ ያለ አይመስለኝም።

የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰር እና የአልበርት አንስታይን የምርምር ተቋም መስራች የሆነው Gene Sharp “From Dictatorship to Democracy” (1993) በሚለው ድንቅ መጽሐፉ ውስጥ አንባገነናዊነትን በሂደት እያስታመሙ ስለመግደል ያሰፈረውን ነገር ጠቅሼ ጽሑፌን ልደምድም

“No one should believe that with the downfall of the dictatorship an ideal society will immediately appear. The disintegration of the dictatorship simply provides the beginning point, under conditions of enhanced freedom, for long-term efforts to improve the society and meet human needs more adequately. Serious political, economic, and social problems will continue for years, requiring the cooperation of many people and groups in seeking their resolution. The new political system should provide the opportunities for people with varying outlooks and favored measures to continue constructive work and policy development to deal with problems in the future.”

Filed in: Amharic