>

40/40/20 የአፓርታይድ ሥርዓት በድሬደዋ!!! (ዘመድኩን በቀለ)

 40/40/20 የአፓርታይድ ሥርዓት በድሬደዋ!!!
ዘመድኩን በቀለ
* ቀጣዩ የኢትዮጵያችን ስጋት በድሬደዋ እየታየ ነው።
 
አመፁ አፓርታይድን ለማስወገድ ስለሆነ አይደለም ድሬዎች የዓለም ህዝብ ከድሬዎች ጎን መሰለፍ አለበት። 
ህወሓት ድሬደዋን በቁሙ ነው ጉድጓድ ቆፍራ የቀበረችው።
 
~ በድሬደዋ እየተካሄደ ላለው አመጽ ለመንስኤው የትኛውም ዓይነት የዳቦ ስም ቢሰጠውም የአመጹ መነሻ ግን የተጠራቀመ በደልና መገፋት ነው። በተለይ 40/40/20 ። 
 
እንደ መግቢያ።
 
•••
ባለፈው ዘመን በዘመነ ህውሓት ማለት ነው በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ ጭቆና የነበረ ቢሆንም የድሬደዋን ያህል በቁሙ መንምኖ እንዲሞት የተፈረደበት ከተማ ግን ተፈልጎ አይገኝም።
 —
ህወሓት መጀመሪያ የኢትዮ ጂቡቲን የባቡር መንገድ ዘጋችውና የድሬደዋን የኢኮኖሚ ደም ስር በጠሰችው። እንቅስቃሴ ቆመ። መጀመሪያ ሽባ ሆነች ቀጥሎ ድሬ አልጋ ላይ ዋለች። ድሬደዋ ፈውስ አጥታ እንደመጻጉ አልጋላይ ከዋለች ይኸው 27 ዓመታት ተቆጠሩ። በዚህ ምክንያት ብዙ የድሬደዋ ልጆች ድሬን ለቀው በየሀገሩ ተሰደዱ። ድሬ ትንሿ ኢትዮጵያ በመባልም የምትታወቅ ከተማ ነበረች። የዘር ዓይነት ተደባልቆ እንደሠርገኛ ጤፍ ተደባልቆ ያለልዩነት ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚኖርባት የፍቅር ከተማም ነበረች። ወደ ከተማዋ የመጣ ሁሉ አብረሃም ቤት እንደገባ እንግዳ የሚስተናግድባት፣ ዘር፣ ቀለም ሃይማኖት ሳይለይበት በእኩልነት በስምምነት እየበለፀጉ የሚኖሩባት ከተማም ነበረች። ይሄን የፍቅር፣ የአንድነትና የመተሳሰብ ከተማ ነው እንግዲህ ህውሓት መጥታ አፈር ከድሜ ያበላችው። 
 
•••
ይባስ ብሎ በድሬደዋ የደቡብ አፍሪካውን የአፓርታይድ ሥርዓት በገይልፅ በይፋ ተግባራዊ አድርጋ አፓርታይድን በመንግሥት ደረጃ ተግባራዊ ያደረገች የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አፍሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ ሆና አረፈችው። ዐማራ፣ ጉራጌ፣ ከምባታ፣ ሀዲያ፣ ወላይታ፣ አፋርንና ሌሎችን በድሬደዋ የሚኖሩ ነገዶችን ለመጨፍለቅ ሲባልም። 40/40/20 የሚል ቀመር ተዘጋጀ። በድሬደዋ ሥልጣን፣ ሀብት፣ የሚያገኙት 40%ሶማሌዎች፣ 40% ኦሮሞዎች ሲሆኑ ቀሪዋን 20 % ለሌሎቹ ብሔሮች እንደ ታማኝ አሽከርነታቸው ሻሞ ተብሎ ይሰጣቸው ዘንድ በሕግ ተደነገገ። አሁን በድሬደዋ ለተነሳው መቆሚያ አልባ መነሻው ይሄው የአፓርታይድ ሥርዓት ይወገድልን። ዜጎች በእውቀታቸው፣ በችሎታቸው እንጂ በዘራቸው የተለየ መብት በኢትዮጵያ ማግኘት የለባቸውም የሚል ልክ የሆነ ጥያቄ ነው።
 
•••
ህወሓት ዐማራን ጫካ የገባች ዕለት ነው ለማጥፋት ተማምላ ሥራ የጀመረችው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንረርት የነበሩ፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ አውጥታ አንቱ ያሰኘቻቸው 42 ዓለምአቀፍ ምሁራንን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስታስወግድ ቅሽሽ እንኳ አላላትም። አምቦ፣ ጋይንት፣ አና ሐረር ደግሞ ህወሓትን ገትረው ስለተወጉ 27 ዓመት ሙሉ ተቀጥተዋል። አምቦ በመሠረተ ልማት፣ ጋይንትም እንዲሁ መብራትና የመብራት ዘርን ባለማሳየት፣ ሐረርንም በውኃ ጥም ነው አጅሪት ህወሓት የቀጣችው። ድሬደዋ ደግሞ ፍቅሯ ህወሓትን ረበሻት፣ የሰዉ ደግነት ረበሻት፣ ትንሿ ኢትዮጵያ፣ የብልጽግና፣ የመረዳዳት፣ የመከባበር ሀገር መሆኗ እንቅልፍ ነሳት፣ እናም ሰይጣኗ ህወሓት ድሬደዋን ሲኦል አስመሰላት አረፈችው። 
 
•••
የአሁኑ የጠብ መነሻ ምክንያት የተደረገው በቃና ዘገሊላ የጥምቀት ማግሥት ሰኞ ዕለት የእግዚአብሔር አብ ታቦትን አንግሠው በሰላም እየዘመሩ ከቤተክርስቲያን ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ባነበሩ ምእመናን ላይ የሶማሌ ጎሳ ወጣቶች ድንጋይ በመወርወራቸው ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል። ኦርቶዶክሳውያኑም የአፀፋ ምላሽ በመስጠት የተደራጁትን የሶማሌ ወጣቶች ልክ አግብተው ቢያስተነፍሷቸውም በሁኔታው ግን ” እስከመቼ በዚህ መልኩ እንቀጥላለን?” በማለት የተጠራቀመውን በደል ከኋላ ኪሳቸው በመዋጥት ወደነፃ መውጣት ዘመቻና ትግል ተሸጋግረዋል።  
 
•••
አመፅ ሲነሳ እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ድንገት ቱግ አይልም። አመፅ የቆየ፣ የተጠራቀመ በደልና ብሶት ቆስቁሶ እንደ ቤንዚን ይጠቀምና ነው ከች የሚለው። ባለፈው ጊዜ በመላ ኦሮሚያ አመጽ ሲነሳ እንደ መነሻ ምክንያት የተጠቀመው፣ እንደ ቤንዚን ማለት ነው የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ነበር። እሱ ነው መነሻ ሆኖ የባሌን ኦሮሞ፣ ከመቱ በደሌ ኦሮሞ ደምቢዶሎ ሀረር ካለው ኦሮሞ ጋር እንዲነሳሳ እንዲያብር ያደረገው። ጊንጪ አብዮቱን አቀጣጠለች መላ ኦሮሚያ ተናጠ፣ በመጨረሻም የሆነው ሆነ።
 
•••
የኢትዮጵያን ፖለቲካ የለወጠው የጎንደሩ አብዮት መነሻው በኦሮሚያ የሚደረገው ግድያ ይቁም የሚል ነበር። የኦሮሞ ደም ደሜ ነው በማለቱ ጎንደርና ጎጃም በህወሓት ሠራዊት በአደባባይ በሺዎች የሚቆጠሩ በኃይለማርያም ደሳለኝ ትእዛዝ ተረሸኑ። እናም ደም መቃባት ሲጀመር ህውሓት ካልተወገደች ወደ ቤቴ አልገባም የሚለው በዝቶ ደጅ ውሎ በማደር አሁን ያለው ለውጥ የሚመስል ለውጥ ለመታየት በቃ። 
 
•••
በቱኒዝያ አንድ ዲግሪውን ይዞ ሥራ በማጣቱ በጎዳና ላይ ንግድ በተሰማራ ወጣት ላይ በፖሊሶች በተፈፀመ ግፍ ምክንያት ወጣቱ በአደባባይ ራሱን በቤንዚን በማቃጠሉና በመሞቱ ምክንያት አመፅ ተነስቶ ቱኒዝያን ከናጠ በኋላ፣ ሊቢያን አፍርሶ፣ ሶርያንና የመንንን ደርምሶ፣ ግብፅን አናወጦ፣ ሱዳንን አድቅቆ፣ አረቦችን አደብ አስገዝቶ አልፏል። የረሃብ አመጽ ከባድ ነው። መመለሻ የለውም። ዝም ቢልም በረሃብ፤ ቢያምጽም በጥይት መሞቱ ስለማይቀር ዐይኔ እያየ በረሃብ ከምሞት ለለውጥ ታግዬ በጥይት ብሞት ይሻለኛልም የሚለው ይበዛል። ሐዋርያትም በረሃብ ከመሞት በሰይፍ መሞት ይሻላል ብለው ያስተማሩት ለዚህ ነው።
 
•••
አሁን በኢትዮጵያ ከዘመነ ህወሓት ወደ ዘመነ ኦህዴድ፣ ከዘመነ ትግሬ ወደ ዘመነ ኦሮሞ መሸጋገራችን እውነት ነው። ሥልጣኑንም፣ ኢኮኖሚውንም በስግብግብነት ኦሮሞዎቹ በሽሚያ እየተቆጣጠሩት መሆናቸው እየታየ ነው። ጠሚዶኮ ዐብይ በዙሪያው ለዐመል ታህል እንኳ ትግሬና ዐማራ ይዞ መንቀሳቀስ ካቆመ ቆየ። ይሄ ደግሞ የኋላ ኋላ አደጋ አለው። ያውም ከባድ አደጋ።
 
•••
በድሬደዋ የተነሳው ዐመጽ በድል ከተጠናቀቀ ህወሓትና ኦህዴድ በጋራ ይሸነፋሉ። ኦህዴድ ህወሓት የመሠረተችውን 40/40/20 ይዞ መቀጠል ነበር የፈለገው። ነገር ግን የድሬ ህዝብ ትእግስቱ ከጫፍ ስለደረሰ፣ ሞልቶም ገንፍሎ ስለፈሰሰ ላይመለስ አደባባይ ወጥቷል።
 
•••
ምን አለ በሉኝ የድሬደዋው ችግር በአጭሩ ካልተቀጨና መፍትሄ ካልተሰጠው በቀጣይ በመላ ሀገሪቱ የኢኮኖሚና የዘር መድልዎ አሠራሩ ብቻ ለሌላ ዙር ምስቅልቅል እንደሚዳርገን ሳይታለም የተፈታ ነው። አሁን ህዝቡ እየራበውም ቢሆን የዐቢቹን መንግሥት በተስፋ እየጠበቀው ነው። ነገር ግን የአቢቹ መንግሥትም እንደ መለስ ዜናዊ መንግሥት በአፉ ኢትዮጵያ እያለ በልቡ ለኦሮሞ የሚሠራ ከሆነ አይሰነብታትም። በቀይ መስቀል መኪኖች እደላና በኢንዱስትሪ መንደር ግንባታ የሚታየው ኦሮሚያ ላይ ብቻ የማተኮር ነገር ሌሎችን ለምን የሚል ጥያቄ ያስነሳልና ቢታሰብበት መልካም ነው።
 
•••
ድሬደዋ ለእኔም  ሀገሬ ናት። አየሯ ተስማሚ ህዝቧ እንግዳ ተቀባይ ነው። ታናሽ እህቴ መስከረም በቀለ ከነልጆቿ፣ ታናሽ ወንድሜም አሸናፊ በቀለ የሚማረው የሚኖረውም በድሬደዋ ነው። የፍቅር፣ የደግነት፣ የቅንነት፣ የነፃነትና የእኩልነት ምድር ናት ድሬደዋ። በንግድ ሥራ አንቱ የተባሉ ባለፀጎችን ያፈራች ናት። በሙዚቃ እንደነ አሊቢራ፣ በእግር ኳስ እንደ እነሉቺያኖ፣ጀማል ሮጎራ፣ የተካበ ዘውዴ፣ የአሰግድ ተስፋዬ፣ የስምኦን ዓባይና የዮርዳኖስ አባይ፣ የእነ አሸናፊ የእነ መሐመድ ሚግ ሀገር ናት። 
 
•••
ድሬደዋ እነ ነጋድራስ ገ/ህይወት፣ አግላን ዚያድ፣ ብርሃነ ዴሬሳ፣ መሐሙድ ድሪር ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶለሳን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች ተወልደው ያደጉባት ሀገር ናት። የአሁኑ የጅቡቲ ፕሬዝደንት ኢስማኤል ጌሌም እትብት የተቀበረባት ሀገር ናት ድሬ። እነ ደምሴ ዳምጤ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የኖሩባት ሀገር ናት ድሬ። 
 
•••
ከዚራ፣ ኮኔል፣ አምስተኛ፣ ግሪክ ካምፕ፣ ለገሃሬ፣ ደቻቱ፣ ጊንፊሌ፣ አዲስ ከተማ፣ ፓሊስ መሬት፣ ነምበር ዋን፣ አሸዋ፣ ሳቢያን፣ ጎሮ፣ መልካ የሚባሉ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ የምንሰማቸውና ለማየት የሚያጓጉ ሠፈሮች ባለቤት ናት።
 
•••
አንድ ጸሐፊ እንዳለው አሁን የድሬ ደዋ ጥያቄ “It is not about the Mayor. It is not about the cabinet. It is about the racist TPLF strategy. Devide and rule! Not more not less. How could the sprite of love and liberty goes with the TPLF design? Not at all! That is where your essence put in to grave Dire Dawa.
 
••• መልካሙ ነገር እስከ አሁን ባለው አመፅ የቆሰሉ ሰዎች እንጂ የሞት ዜና ሲዘገብ አልተሰማም። መከላከያ ሠራዊት እያሳየ ያለው ትእግስት ገራሚ ነው የሚሉም ተሰምተዋል። ከከተማዋ ፖሊስ ጋርም መከላከያ አለመግባባት እየፈጠረ ነውም ተብሏል። በጎንደር ትእግስት የሚያጣው መከላከያ ድሬደዋ ላይም የሌለ ፀባየኛ ሆኖ ህዝባዊነቱት እያስመሰከረ ነው ተብሏል። ነገ ተቀይሮ አውሬ ትሁን ወይም በዚሁ ጠባዩ ይቀጥል አይቀጥል ግን የታወቀ ነገር የለም።
 
•••
የራበው ሰው ቤተመንግሥት ገብቶ መሪውን ይበላል። ማርክ ማይወርድ አሉ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና። እናም አሁንም የድሬ ደዋ የግጭቷ መነሻ የእግዚአብሔር አብ ታቦት ሽኝት ምክንያት በተነሳ ግጭት አይደለም። እሱ ምክንያት ነው። ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው ነው ነገሩ። እንኳንም እናቴ ሙታ እንዲሁም አልቅስ አልቅስ ይለኛል ነው ነገሩ። አሁን ወደ መፍትሄ።
 
•••
መፍትሄውም አንድና አንድ ብቻ ነው። ያውም 40/40/20 የተሰኘውን የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት አስወግዶ ድሬደዋን ለድሬዎች ማስረከብ። ለዚህ ሁሉ ግርግር መነሳት ከጀርባ ሆኖ የሚቆሰቁስ ነው የተባለውን የከተማዋን ከንቲባ ማስወገድ ብቻ ነው። ማርክ ማይወርድ አለ ኦባማ። አከተመ ። ሌላ ምንም አማራጭ የለም። ይኸው ነው። 
ድሬ አንቺ የፍቅር ሀገር። አቦ ወለበል፣ ምንድነው ሳ ባይዋ ጭንቅ አይገቤ የምሥራቅ ጮራዋ የደጎች ሀገር ድሬዳዋ ሆይ የሰላሙን ያውርድልሽ ። ድል ለተጨቆኑ ህዝቦች ሁሉ ይሁን።
—-
በፎቶው ላይ ስለምታይዋቸው ባለ ገጀራዎቹ የዘር ፖለቲካ ትሩፋቶች ጥቂት ልበል:-
የዘር ፖለቲካ ውጤቱ መተራረድ መጠፋፋትና መጨረሻም ሀገር አልባ መሆን ነው
እነዚህ ምስሉ ላይ የሚታዩት የዘር ፖለቲካ ትሩፋቶች ሲሆኑ ለጊዜው ከስር ምስላቸው የሚታየውን ወጠጤዎች ማንነታቸውን ባላውቅም ህወሀቶች ኦነጎች አብኖች ኤጀቶዎች ወይ አብዲ ኢሌ ካደራጃቸው ዘረኛ ወሮበሎች የአንዱ ድርጅት አባል ወይ ደጋፊ ሊሆኑ ይችላሉ::
የሆነ ሆኖ ነባር ዘረኞችም ሆኑ አዲስ ለመቀፍቀፍ የሚዳክሩ ዘረኞች ህዝባኝችንን በማፋጀት ከወያኔ ስርአት እጅግ ወደ ከፋ የወሮበሎች ስርአት ሊዘፍቁን እየጣሩ ስለሆነ ሀገርህንና ወገንህን የምትወድ ሁሉ ለዘረኞች ፊት በመንሳት አንድነታችንን እናጠናክር::
ከርእሴ ሳልወጣ ታዋቂው የኢሳት ፖለቲካ ተንታኝ 
ኤርሚያስ ለገሰ በአንድ ወቅት ዛሬ ላይ ድሬደዋ የሚመጣባትን አደጋ ታሳቢ በማድረግ መድረክ ላይ ያቀረበውን ንግግር ሊንኩን አያይዣለሁ
🚫40%40%20%🚫
ኤርሚያስ ለገሰ
*     “ደግሜ ደጋግሜ ማሳሰብ የምፈልገው፣ ስለ ድሬ ዳዋ ማልቀስ አለብን የምር። ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ እንኳን መኼድ ያልቻለባት ከተማ ናት!
Filed in: Amharic