>

አርበኛ ሌፍተናንት ጄነራል ጃገማ ኬሎ  የበጋው መብረቅ!!! (ከፍቅረማርቆስ ደስታ) 

አርበኛ ሌፍተናንት ጄነራል ጃገማ ኬሎ  የበጋው መብረቅ!!!
ከፍቅረማርቆስ ደስታ
ጃገማ ኬሎ አጀሴ ገላ
ኦፍጀጁ ባንደ ቀዌን ኦሼ ላማ
ጃጋማን ዱላ ኤፍኬሌቲ ገሌ
ኤቦደን ቀዌ በጅኤ ገሌ
ባንዳ እሼ ገንቱ ኮኬ እሼ ቀሌ
ጃጋማ አካም ጀርተሬ ሌንጫ ጅባት ወለካ 
ሳቦንቲቻ ኦሮሞ የእሰ ሌሊ በከካ።
በ1913 ዓ.ም ማክሰኞ ማታ በጥር 20 ምሽት በጅባትና ሜጫ ወረዳ፤ በድንዲ ወረዳ ዮብዲ የሚባል ቦታ ጀግናው ጃገማ ኬሎ ከአባታቸው ከኬሎ ገሮ እና ከእናታቸው ደላንዱ ተወለዱ።
አባታቸው ትልቅ ሠው ስለነበሩ ካላቸውም ሃብትና ንብረት ብዙውን ያወረሱት ለጃገማ በመሆኑ በተጨማሪም አባታቸው ከሰጧቸው ትልቅ ቦታ በመነሳት “አባቱ የመረጠው” በሚል ገና በለጋ እድሜያቸው ለዳኝነት መቀመጥ፣ በገዳ እርከን ፎሌ ደረጃ (ዕድሜያቸው ከሃያ አምስት እስከ ሠላሳ ሁለት) ከደረሱ ወጣቶች ጋር ፈረስ ግልቢያ፣ ጦር ውርወራ፣ ጋሻ አነጋገብና ምክቶሽ፣ ውሃ ዋና ረሃብና ጥም መቋቋምን እየተማሩ በጥሩ ስነምግባር አደጉ።
ፋሺስቱ የጣሊያን መንግሥት በ1928 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በመውረር አዲስ አበባን ሚያዚያ 27 ቀን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ ምዕራቡ የአገሪቷ ክፍሎች በመስፋፋት ጭልሞና ጋጂ አካባቢን ተቆጣጥሮ ይዞታውን ለማስፋፋትና ለሚያደርገው ሙከራ የመሸጋገሪያ ምሽግ ጊንጪ አካባቢ በመሥራት ለመጠቀም ሙከራ ሲያደርግ የነበረ ቢሆንም፣ አርበኛው ጃግማ ኬሎ የመሸጋገሪያ መሥመሮችን በመዝጋትና የደፈጣ ውጊያ በማድረግ የጠላትን ጦር በእንቅስቃሴ ሲገቱ ቆይተዋል፡፡
የበጋው መብረቅ በጦር ሜዳ ውሏቸው በፋሺስቱ የጣሊያን ወራሪ ጦር ላይ ካገኙት አንፀባራቂ ድል አንዱ በኅዳር ወር 1933 ዓ.ም. የተገኘው ነው፡፡ ይህም የአዲስ ዓለምን ጽዮን ማርያም ምሽግ በመሰበር 70 የጣሊያን ወታደሮችን በመግደል፣ 1,500 ጠመንጃ በመማረክ፣ እንዲሁም 80 የወገን እስረኞችን በማስፈታት ከፍተኛ ወታደራዊ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡
በመጋቢት 1933 ዓ.ም. በጭልሞ ምሽግና ጊንጪ አካባቢ በተደረገ ከፍተኛ ውጊያም የጠላት ጦር ቅስሙ ስለተመታ መኪና ያገኙት ወደ አምቦ ሲሸሹ ሌሎች ወደ አዲስ ዓለም የሸሹ ሲሆን የሸሹትን እግር በእግር መከታተል፣ በየመንገዱ በመቁረጥና በመበተን የጠላት ጦር ከጥቅም ውጭ አድርገዋል።
የአርበኛው የጦር ሜዳ ድል አድራጊነት ዝነኝነት በአገር ሁሉ እየናኘ የመጣ ሲሆን፣ በዚሁ በ1933 ዓ.ም. ወደ ጅማ ከዘመተው የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጦር ጋርም  ወታደራዊ ቅንጅት በመፍጠር በደቡብ ምዕራብ የመሸገውን የፋሽስት ጦርን መውጪያና መግቢያ አሳጥተዋል፡፡
በፋሺስት ላይ የፈጸሙት የላቀ ጀብዱና ታላቅ ገድላቸው ‹‹የበጋው መብረቅ›› የሚል የጀግንነት ስያሜ የተሰጣቸው ጄኔራል ጃገማ አገሪቷ ነፃ ከወጣች በኋላና አፄ ኃይለሥላሴ ከእንግሊዝ ስደት እንደተመለሱ ከፍተኛውን ሚና ከተጫወቱት ድንቅ አርበኞች መካከል ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡
የጃገማ ፉከራ
 
ገዳይ በልጅነቱ
ዶቃ ሳይወጣ ከአንገቱ
ጃጌ ጃገማቸው
እንደገጠመ የሚፈጃቸው
በአባት በእናቱ ኦሮሞ
ፍዳውን አስቆጠረ ከምሮ ከምሮ 
ጃገማ አንድ ወንድና አምስት ሴት ልጆች፣ አምስት የልጅ ልጆችና አራት የልጅ ልጅ ልጆችን አፍርተዋል፡፡ መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።
መስዕዋትነት ከፍለው ነፃ ሃገር ስላስረከቡን ሁሌም ስንዘክርዎት እንኖራለን።
እንኳን ተወለዱልን ጀግናው አባታችን
Filed in: Amharic