>

ከደርግ  መስራቾች አንዱ የነበሩት ሻምበል ለገሰ አስፋው በ76 አመታቸው አረፉ!!!

ከደርግ  መስራቾች አንዱ የነበሩት ሻምበል ለገሰ አስፋው በ76 አመታቸው አረፉ!!!
ጴጥሮስ አሸናፊ
* ” ሀውዜን የምትባል ቦታ አላውቅም። ወደፊት የትግራይ አስተዳዳሪ ካደረጋችሁኝ ላውቃት እችላለሁ”
 
ሻምበል ለገሰ አስፋው “ሀውዜንን አስደብድበዋል ወይ ?” ተብለው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለተጠየቁት ጥያቄ የሰጡት መልስ
በቀድሞው መናገሻ አውራጃ ባጫ መድኃኔዓለም መስከረም 21ቀን 1935 ዓ.ም የተወለዱትና ከደርግ መስራች 108 አባላት ውስጥ አንዱ የነበሩት ሻምበል ለገሰ አስፋው አርፈዋል።
ሀውዜን ላይ በአውሮፕላን ከተፈፀመው ደብደባ ጋር ለረጅም ጊዜያት ስማቸው ተያይዞ የሚነሳው ሻምበሉ ክስ ተመስርቶባቸው ከ20 ዓመት እስራት በኋላ በምህረት መፈታታቸው ይታወሳል።
ለመሆኑ ሃውዜንን ማን አስደበደበ?
የቀድሞው የህወሀት ሊቀመንበር አቶ ስብሀት ነጋ የህወሀትን 40ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ወደ ትግራይ ለተንቀሳቅሱት ጎብኝዎች የደርግ 604ኛ ኮር የተደመሰሰበትን ወታደራዊ ሳይንስ አስመልክቶ በሽሬ ከተማ በተሰናዳ መድረክ ላይ ባደረጉት ገለጻ ደርግ ሃውዜንን የደበደበው በእስራኤል መንግስት መሪነትና አስታጣቂነት መሆኑን ተናግረው ነበር።
“እስራዔል ደርግን ማስታጠቅ ጀምራ ነበር፤ ደርግም የታጠቀውን ክላስተር ቦንብ እኤአ ሰኔ 22 ቀን 1988 ሃውዜን በገበያ ቀን ህዝቡ ላይ አዘነበው። በጥቃቱ ከ2 ሺ 500 በላይ ህዝብ አለቀ። “
“ይህ ሁሉ የህዝብ እልቂት በእስራኤል አስታጣቂነት የተፈጸመ ነበር” ማለታቸው አይዘነጋም።
የቀድሞው የህወሀት አመራር አቶ ገብረመድህ አርአያን ጨምሮ በርካታ ድርጅቱን የከዱ አመራሮች ፤ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የድጋፍ መጠየቂያና የትግራይን ህዝብ ለትግል ማነሳሻ እንዲሆን በህወሀት ሰዎች በከፍተኛ ዝግጅት በዘመናዊ ካሜራ ለተቀረጸው የሀውዜን ጭፍጨፋ ዋነኛው ተጠያቂ የህወሀት አመራሮች እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲከሱ ቆይተዋል።
ለኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ባላቸው ቅርበትና ታማኝነት የሚታወቁት ለገሰ ፤ ሃውዜን ላይ ለተፈፀመው እልቂት ህወሀት የትግራይን ህዝብ “የደርግ አየር ኃይል ጨረሰህ ” ለሚለው ፕሮፓጋንዳዊ ቅስቀሳዋ ስማቸው ተለይቶ ተጠቃሽ እንዲሆን ያደረገች ሲሆን፤ በደርግ በኩልም ለ604ኛው ኮር ትግራይ ላይ መሸነፍ ተጠያቂ ተደርገውም የሚብጠለጠሉ ነበሩ።
ጥር 3 ቀን 1999 ዓ.ም. የፌዴራሉ የከፍተኛ ፍርድ ቤት በዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥረው በነበሩት የደርግ ባለሥልጣናት ላይ ውሳኔ ለመስጠት ተሰይሞ በነበረው ችሎት ዓቃቤ ሕግ ካቀረባቸው 21 የደርግ ባለሥልጣናት ውስጥ በ20ዎቹ ላይ ሞት ሲፈርድ፣ በአንዱ ላይ የከፍተኛ ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቶ የነበረ ሲሆን፤ በሞት እንዲቀጡ ተወስኖባባቸው የነበሩት ፣
1) ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣
2) ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ፣
3) ሌ/ኮሎኔል ፍሰሃ ደስታ፣
4) ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ፣
5) ሻምበል ለገሰ አስፋው፣
6) ጄኔራል ተስፋዬ ገ/ኪዳን፣
7) ካሳሁን ታፈሰ፣
8 ) ሻለቃ ታዴ ተድላ፣
9) ሌ/ኮሎኔል እንዳለ ተሰማ፣
10) ሻምበል ገሰሰ ወ/ኪዳን፣
11) ሜ/ጄኔራል ውብሸት ደሴ፣
12) ሻለቃ ካሳዬ አራጋው፣
13) ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ፣
14) ሻምበል በጋሻው አታላይ፣
15) መቶ አለቃ ስለሺ መንገሻ፣
16) ሌ/ኮሎኔል ናደው ዘካሪያ፣
17) ም/መቶ አለቀ አራጋው ይመር፣
18) ሻለቃ ደጀኔ ወ/አገኘሁ፣
19) ም/መቶ አለቃ ደሳለኝ በላይ እና
20) ሻለቃ ሐዲስ ተድላ ነበሩ።
ከነዚህ ውስጥ ካሳሁን ታፈሰ በማረሚያ ቤት ሕይወታቸው ስላለፈ ውሳኔው ያልተላለፈ ሲሆን፣ በመቶ አለቃ አክሊሉ በላይ ላይ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰነውን የዕድሜ ልክ እስራት ውሳኔ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አፅንቶባቸው ነበር።
በመስከረም 2004 ዓ/ም በዘር ማጥፋት ወንጀል ከተከሰሱት ከፍተኛ የደርግ ባለሥልጣናት መካከል 20 ዓመት በእስር ያሳለፉት 16 ባለሥልጣናት በአመክሮ ተፈትተዋል፡፡ የተፈቱት ባለሥልጣናት :
የደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ፣
ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ፣
ሻምበል ለገሰ አስፋው፣
ኮሎኔል እንዳለ ተሰማ፣
ሜጀር ጀነራል ውብሸት ደሴ፣
ሌተና ኮሎኔል ናደው ዘካሪያስ፣
መቶ አለቃ ጴጥሮስ ገብሬ፣
መቶ አለቃ ስለሺ መንገሻ፣
ሻለቃ ደጀኔ ወንድማገኘሁ፣
አቶ እሸቱ ሸንቁጤ፣
አቶ ልሳኑ ሞላ፣
ብርጋዴር ጄነራል ለገሰ በላይነህ፣
አቶ ገስግስ ገብረ መስቀል፣
አቶ አበበ እሸቱ፣
አቶ በሪሁን ማሞና
መቶ አለቃ ደሳለኝ በላይ
የነበሩ ሲሆን ከባለሥልጣናቱ መካከል በደርግ ዘመን የደኅንነት ሚኒስትር የነበሩት ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ በወህኒ ቤት እንዳሉ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል፡፡
ሻምበል ለገሰ አስፋው ያረፉት በ76 ዓመታቸው ነው።
ጥቂት ስለ ደርግ 
ደርግ ከሰኔ 21 1966 እስከ 1979 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሰፍኖ የነበረ የወታደራዊ አገዛዝ ስርዓት አይነት ነበር። ደርግ የሚለው ቃል ከግዕዝ የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜውም ቡድን ወይንም ኮሚቴ ማለት ነው። ይህን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ለስርዓቱ  መገለጫነት የተጠቀሙት ግለሰብ ሻለቃ ናደው ዘካሪያስ ሲሆኑ ይኸውም ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም. ነበር። በዚህ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የአራተኛ እግረኛ ክፍለ ጦር መምሪያ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ መለዮ ለባሾች በየካቲት ወር ስለፈነዳው አብዮት ከሰኔ 19 ጀምሮ ውይይት የሚያካሂዱበት ጊዜ የነበር ሲሆን፤ ሻለቃ ናደው የዚህ ኮሚቴ ማስታወቂያ ጉዳይ ሠራተኛ ነበሩ። ደርግ በዚህ ሁኔታ በዝቅተኛ መኮንኖች (ከኮሎኔል ማዕረግ በታች) ከተመሰረተ በኋላ በዚያው ቀን ሻለቃ መንግስቱ ኃይለማርያም የደርግ ሊቀመንበር በመሆን ተመርጦ እስከ ስርዓቱ ማብቂያ (1979) ድረስ በዚያ ስልጣን አገልግሏል።
በነገራችን ላይ የደርግ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት የኤርትራው ተወላጅ ጄኔራል አማን አንዶም ነበሩ።
Filed in: Amharic