>

የምክትል ከንቲባው ነገር...  !!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

የምክትል ከንቲባው ነገር…  !!!!
አቻምየለህ ታምሩ
 
ታከለ ስለኛ ሳይሆን ስለ ዐቢይ ያጠፋው ነገር ቢኖር ዐቢይ ቲያትረኛነቱን ተጠቅሞ  በብልጠት አሳካዋለሁ ብሎ ያሰበውን  የኦሮሙማ ግብ ታኬ  የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል እንደሚባለው  በጊዜያዊ ስልጣን በአንድ አመት ውስጥ ከዉኖ የዐቢይን ቡራኬ ለመቀበል መጣደፉ ብቻ ነው!!
ነገሩ የሆነው በ1847 ዓ.ም. ጎጃም ውስጥ ነው። ታሪኩ የተፈጸመው ልጅ አዳል ተሰማ [የኋላው ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት] ከዘመዱና ከዝነኛው የጎጃም መስፍን ከደጃች ተድላ ጓሉ ቤት ያድግ በነበረበት ወቅት ነው። ደጃዝማች ተድላ ጓሉ ወደ ዘመቻ ሲሄድ የጉ ርምስና እድሜ ላይ የነበረው ልጅ አዳል የደጃች ተድላን እቁብ ወይዘሮ ጉዳይን ይገናኛት ነበር። ልጅ አዳል የመጀመሪያ ልጁን ራስ በዛብህን የወለደው  ከደጃች ተድላ እቁብ ከወይዘሮ ጉዳይ ነበር። የልጅ አዳልንና የወይዘሮ ጉዳይን ግንኙነት፤ የራስ በዛብህንም መፀነስ የሰማው ደጃች ተድላ ጓሉ ልጅ አዳልን ሊያጠፋው ተነሳ። ልጅ አዳልም የአሳዳጊውን የደጃች ተድላን መቆጣት ሰምቶ ኖሮ አሉላ ተሰማ፣ መሸሻ እንግዳ፣ መርሻ ፀዳሉና ዓፅቁ ደረሰ የሚባሉ ረዳቶቹን ይዞ ወደ ጠለዛሞ ሸሸ። በዚያም ሌት ሌት ከወዳጁ ቤት፤ቀን ቀን ከዱር ተሸሽጎ ተቀመጠ።
ደጃች ተድላም ልጅ አዳልን በእግር በፈረስ ይፈልግ ያስፈልገው ጀመር። ልጅ አዳል የደጃች ተድላን ወደ አዴት መዝመት ሰምቶ ጠለዛሞ ከተደበቀበት ረዳቱን አሉላ ተሰማ ወደ ደብረ ማርቆስ በመላክ የደጃች ተድላን ቤት አቃጥሎ ወይዘሮ ጉዳይን ይዞ እንዲመጣ አደረገው። የቤቱን መቃጠልና የወይዘሮ ጉዳይን መወሰድ የሰማው ደጃች ተድላ እነ ልጅ አዳል ሳይሰሙ ከአዴት ተነስቶ  ወደተደበቁበት ዱር ዘመቻ አደረገ። ልጅ አዳልና ወይዘሮ ጉዳይ ሲያመልጡ የልጅ አዳል ረዳት አሉላ ተሰማ ተማረከ። ደጃች ተድላም አሉላ ተሰማን ይዞ ቤቴን ባቃጠልህበት፤ እቁቤን በወሰድህበት ተፋረደኝ ብሎ ተፈረደበት። ያን ጊዜ ዋናው ባለጉዳይ ልጅ አዳል ቀርቶ ጉዳይ አስፈጻሚው አሉላ ተሰማ የልጅ አዳልን ቅጣት ሲቀበል ያየች አንድ አዝማሪ፤
ደግሶ አላበላኝ፤ ከጠጁ አላጠጣኝ አላውቀው አያውቀኝ፣
አሉላ ተሰማ ቢቀጣ ጨነቀኝ። አለች።
በዚህ ጊዜ ደጃች ተድላ ባልሽ ነወይ? ቢላት አይደለም፤ እንዲያው ልጅ አዳል ባጠፋ አሉላ ተሰማ መቀጣቱ ሲያሳዝነኝ ነው አለች።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ተደርጎ በዐቢይ አሕመድ የተሾመው ተከለ ኡማ እንደ አሉላ ተሰማ የሆነ ይመስለኛል። ታኬ የዐቢይ አሕመድ ተሿሚ እንደሆነ ብዙ ሰው ያውቃል። ዐቢይ አሕመድ የወያኔውን የስዬ ሕግ አይነት አዲስ ደንብ አመንጭቶ ከንቲባ የሚሆን የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ሳይታጣ ታከለ ኡማን ከአዲስ አበባ ውጭ አምጥቶ ለአዲስ አበባ ከንቲባነት የሾመው ታከለ ዛሬ እየሰራው ያለው ሁሉ እንዲያስፈጽምለት ነው። ታኬ ተጠሪነቱ ከንቲባ አድርጎ ለሾመው ለዐቢይ አሕመድ እንጂ ላልመረጠውና ላልተመረጠበት የአዲስ አበባ ምክር ቤት ወይንም ለአዲስ አበባ ሕዝብ አይደለም።
ታዲያ ታከለ ኡማ በከንቲባነቱ እያስፈጸመ ያለው ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ አምጥቶ አዲስ ሕግ አመንጭቶ ምክትል ከንቲባ አድርጎ የሾመውን የዐቢይ አሕመድን ፍላጎት ሆኖ ሳለ ታከለ ዛሬ እየሰራው ያለውን ስራ እንዲሰራ የሾመው ዐቢይ አሕመድ ከእግዜር የተላከ መላዕክት ተደርጎ እየቀረበ በሱ ላይ ግን የሕዝብ ተጠያቂነትና ተጠሪነት እንዳለበት ተደርጎ ነገር ሲጠናበት እያየን ነው።
ታኬ የገጽታ ግንባታ ለማድረግ ያልሞከረው ነገር የለም። ወጣቶችን ሲያጎርስ፣ ስቴዲዮም ሲታደም፣ ዳግማዊ ምኒልክ ለራስ ጎበና ዳጨ የጫኑላቸው  የራስ ወርቅ አስሮ አድዋን ሲያከበር ታይቷል። ከነዚህ በተጨማሪ የከተማ አውቶቡስ ውስጥ ገብቶ ባዶ ወንበር በግራና በቀኙ እየታየ ቁሞ ሲጓዝ ፎቶ ተነስቶ ቢለጥፍ፤ በአገዛዙ ቤታቸው ፈርሶ የጎዳና ተዳዳሪ የተደረጉ አዲስ አበቤዎችን ምግብ አበላ እንዲባል ከጀርባው ባዶ እጃቸውን ይዘው የቆሙ ጎረምሶች እየታዩ እሱ ግን ሁለት እጆቹ እስኪዝሉ ድረስ በሁለትም እጆቹ ምግብ የተሞሉ ሳህኖች ተሸክሞ በአገዛዙ ጎዳና ተዳዳሪ ለተደረጉት ድሆች ምግብ ሲያቀርብ የሚያሳይ ፎቶ ቢለጥፍም ከመሾሙ በፊት ስለአዲስ አበባ የተናገረው ስላልተረሳለት አልያም እንደኔ ነገር ስለሚጠናበት ትወናው የዐቢይ አሕመድን ያህል አልተሳካለትም።
ታኬ ምክትል ከንቲባ ተደርጎ የተሾመው ጊዜያዊ ስልጣን [mandate] ተሰጥቶት ነው። ይህም ጊዜያዊ ስልጣን የውክልና እንጂ ፍጹም አይደለም። ጊዜያዊ mandate ያለው ሰው ደግሞ በውክልና የስልጣን ዘመኑ ሊያከናውነው የሚችለው ነገር ቢኖር ውዝፍ ስራዎች ካሉ እነዚያን ውዝፍ ሥራዎች ባለው የሕግና የአሰራር አግባብ ባግባቡ ማጠናቀቅ ነው።
የዐቢይ አሕመድ ተሿሚው ጊዜያዊው ከንቲባ ታከለ ኡማ ግን ሲያደርግ የከረመው ነገር ሁሉ የጊዜያዊ ምክትል ከንተባ ሥልጣንና ኃላፊነት የሚፈቅደውን ሳይሆን በሕዝብ የተመረጠና ፍጹም ሥልጣን ያለው ከንቲባ እንኳ ከሚያደርገው በላይ ነው። ጊዚያዊው ከንቲባ ታከለ ኡማ ዘላቂ ተጽእኖ የሚያስከትል ሕግ የማውጣትና አዲስ ሕግ የማምንጨት ሥልጣን የለውም። ሕግ ማውጣትና ሕግ መሻር የጊዜያዊ ከንቲባ ሥልጣን [mandate] አይደለም። ታካለ ኡማ ግን በጊዚያዊ ሥልጣን የተከማዋን የትምህርት ቋንቋ [medium of instruction] መቀየርን ጨምሮ ቀላል የማይባሉ አዳዲስ ሕጎችን አውጥቷል። ታኬ ይህን ሁሉ ጉልበት ያገኘው በጊዜያዊ ምክትል ከንቲባነቱ  ሳይሆን በዐቢይ አሕመድ ከተሰጠው ሥልጣን ነው።
ታከለ ስለኛ ሳይሆን ስለ ዐቢይ ያጠፋው ነገር ቢኖር ዐቢይ ቲያትረኛነቱን ተጠቅሞ  በብልጠት አሳካዋለሁ ብሎ ያሰበውን  የኦሮሙማ ግብ ታኬ  የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል እንደሚባለው  በጊዜያዊ ስልጣን በአንድ አመት ውስጥ ከዉኖ የዐቢይን ቡራኬ ለመቀበል መጣደፉ ብቻ ነው።
ታኬ ወደፊትም እስካሁን ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ በአዲስ አበባ ሕዝብ ገንዘብ ዐቢይ አሕመድ በሰጠው ሥልጣን ለአዲስ አበባ ሕዝብ ሳይሆን በቅድሚያ የዐቢይ አሕመድን እቅድ፣ ቀጥሎ ደግሞ የተከታዮቹን አጀንዳና ፍላጎት ለማስፈጸም ፍጹም ሥልጣን ካለው ከንቲባ በላይ ሕግ እያወጣ ያሻውን ለማድረግ እንደቆረጠ ባለፈው ሰሞን ለተከታዮቹ ተደብቆ[በኦሮምኛ] ባስተላለፈው መልዕክቱ አስታውቋል።  ታኬ ለተከታዮቹ ተደብቆ መልዕክት ማስተላለፍን የተማረው ከዐቢይ አሕመድ ነው። ዐቢይ አሕመድም የማንከተታተለው እየመሰለው ተመሳሳይ መልክዕቶችን ተደብቆ  ሲያስተላልፍ ከርሟል፤ አሁንም እያስተላለፈ ነው። ሆኖም ግን ታኬ እንደኔ ነገር ሰሚጠናበት ነው መሰለኝ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ የሰለበተው  እሱ ተደብቆ ያስተላለፈው መልክዕት ብቻ ነው።
እና እባካችሁ ነገር በልኩ እንዲሆን አሕያውን ፈርቶ ዳውላውን እንደተባለው ዐቢይ አሕመድ የሰጠውን አጀንዳ ስላስፈጸመ እንደ ዐቢይ አሕመድ የተዋጣለት ተዋናይ ባለመሆኑ ብቻ በታኬ ላይ ነገር አታጥኑበት! ታኬ እንደ አሉላ ተሰማ  እድለኛ ባለመሆኑ በዚህ ዘመን እንደ ደጃች ተድላ ዘመኗ አዝማሪ  አስተዋይ ጥበበኛ ስለሌለች  ታኬ እያደረገው ያለውን እንዲያደርግ የሾመው ዐቢይ አሕመድ እየተመለከ  የዐቢይ ጉዳይ አስፈጻሚው ታኬ እንደ አሉላ ተሰማ መሆኑ ደግ አይደለም  ብላ የምታዝንለት  አስተዋይ እንኳ ያገኘ አይመስልም! መልካም ቀን!
Filed in: Amharic