>

አያያዝ አለማወቅ ጭብጦ ያስነጥቃል!!! (ደግፌ አስረስ)

አያያዝ አለማወቅ ጭብጦ ያስነጥቃል!!!
ደግፌ አስረስ
ዐብይ መለስን እንዲሆን፣ ኦሮሞን ብቻ እንዲያስቀድም ካልሆነ ደግሞ ኦሮሞም ሆኖ ያብይ ጠላት መሆን ወያኔያዊ ሞትን ያመጣል
በአለም ላይ ያለን የፖለቲካ ሀይል ምን ዘንበል እንደሚያደርገው ማንም አያውቀውም። የሀይል ወይም የእውቀት የበላይነትም አይደለም። ዘንበል ካለ ማንም እንደበፊቱ አርጎ አያቃናውም። በኢህአዴግም የሆነው ይሄ ነው። ምንም ተአምር ወደቀደመው ሊመልሰው በማይችለው መልኩ ዘንበል ብሎ ወያኔን ደፋ አድርጓታል።
ይሄን ያመጣው ጉልበት አይደለም። የሚመለክን ንጉስ የጣለው ደርግ በአንድ ካርባይን ጠብመንጃና በአንድ ወታደር እየተጠበቀ ነበር። ደርግ ሲወድቅ ኤርትራ ብቻ አንድ መቶ ሰማንያ ሺ ተዋጊ ሀይል ነበር። ወያኔ ጀኔራሎቹን በሙሉ ከብብቱ ማውጣቱ ሀይል ሆኖ አላዳነውም።
አሁን ያለው መንግስት በእድሜው ጩጬ ቢሆንም በቀናም ይሁን በተንኮል የተወሰነ ርቀት መሄድ ይችላል። አሁን ያለው መንግስት በጎላ መልኩ የአማራንና የኦሮሞን ህብረት ስለያዘ፣ ይህም ህብረት ያገሪቱን ልእል አብላጫ ስለሆን አሁንም የተወሰነ ርቀት ሊሄድ ይችላል። ሂዶ ሂዶ ግን ድንገት ከወደቀ ውድቀቱ አነስተኛ (minority) የህዝብ አካል ወክለው ከገዙት ህወሀቶች አወዳደቅ የከፋ ይሆናል። የታላቅና የታናሽ አወዳደቅ አበሳ ካስከተለ አበሳው የሚከፋው በታላቁ ላይ ነው። የዐብይ መንግስት መውደቅና የመለስ ሀይለማርያም መንግስት መውደቅ ውርደት ካስከተለ ውርደቱ የሚከፋው በአብይ መንግስት ላይ ነው። እንደ ህዝብ ኦሮሞንና አማራን አከርካሪው ጡንቻውና ልቡን ያደረገ መንግስት አወዳደቅ ካላማረ የዚህ ህዝብ አመራር እንዳላማረ ይወሰዳል።
ጊዜው የዘር ሆነና በዘር ለሚያስቡት፣ በዘራቸው ጥንካሬ ወይም ብዛት ለሚመኩት ይህን እላለሁ። ፖለቲካን ጉልበት ቢወስነው ኑሮ ዛሬ ዐብይ መሪ አይሆንም ነበር። የት ነበር የሚባል ሰው ስልጣን ላይ እየወጣ ሲወርድ እድሜያችን አሳይቶናል። ዐብይ መለስን እንዲሆን፣ ኦሮሞን ብቻ እንዲያስቀድም ካልሆነ ደግሞ ኦሮሞም ሆኖ ያብይ ጠላት መሆን ወያኔያዊ ሞትን ያመጣል። በሽራፊ ሰከንድ ወያኔያዊ ባለስልጣኖች ራሳቸውን መቀሌ ያሰሩት ትምሕርት ሊሆነን ይገባል። አያያዝ ማወቅ ጭብጦን ከመነጠቅ ይሻላል። ያካፈሉት ጭብጦ ከተነጠቁት ጭብጦ ይሻላል። ግፈኝነት ጭብጦን መነጠቂያው ዋናው መንገድ ነው።
በምን ጥበብ ነው ሀይለስላሴን መንግስቱ፣ መንግስቱን መለስ፣ መለስን ሀይለማርያም፣ ሀይለማርያምን ዐብይ እንደሚተካ ማወቅ የሚቻለው?
ዐብይ ጭብጦን መካፈል እንደሚገባ ማመኑና ለዚያ መትጋቱ የኦሮሞውና የአማራው ፓለቲካ መላቁንና ኢትዮጵያዊ ፖለቲካ መሆኑን ያሳያል። ዐብይ ኦሮሞም አማራም መሆኑን መዘንጋት ሳይገባ ለአብዛኞች ገዥነት(majority rule) እንትጋ!
Filed in: Amharic