>

የአላሙዲና የአየር መንገዱ ጉዳይ! (ሀይለገብርኤል አያሌው)

የአላሙዲና የአየር መንገዱ ጉዳይ!
ሀይለገብርኤል አያሌው
እውነት ወዴት ናት? መርሃችንስ ምንድን ነው?
ሕግ የጣሰ በሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ : የሃገርን ሃብት የዘረፈ የተፈጥሮ ሃብትን ያወደም : ሕዝብ ላይ ግፍ ሲፈጽሙ ከነበሩት ጋር የተባበረ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የሕግ ጥሰት ፈጽሟልና በፍርድ መጠየቅ ይኖርበታል:: ይህ ስርአት ነው:: ማንም ይሁን ማን ሹም ይሁን ጭፍራ መጠየቅ ባለበት መጠየቅ ይኖርበታል:: ፍርድ ያጏደሉ ድሃ የበደሉ ከግፈኞች ጋር የተባበሩትን ስልጣንና ብሄርን መሰረት አድርጎ መሸፋፈን ከፍ ሲል ወንጀል ዝቅ ሲል የሞራል ውድቀት ነው:: በታሪክም የሚያስጠይቅ ታላቅ ነውር ነው::
የሕግ ሚዛናችን ተሰብሮ ዘውግ ሆኗል መለኪያው: የሞራል መሰረታችን ላልቶ ለመንጋ ፍርድ  ማጎብደድ ጎልቶ መታየት ጀምሯል:: በሃገራችን የፖለቲካ የትግል ሂደት ውስጥ እንደአቅማችን ጥረት ስናደርግ የቆየንው ባለፉት አመታት ስለነበሩት ውጣ ውረዶች ስለ ቡድኖች አሰላለፍና ስለሹማምንቱና ስለከበርቴዎች የፖለቲካ አቋም በግርድፉም ቢሆን በቂ ግንዛቤዎች አሉን::
ትላንት የዘውግና የድርጅት ድንበር ሳያግደን በጋራ ያወገዝናቸውን ተቋማትና የረገምናቸውን ግለሰቦች እንዴት ዛሬ ተነጣጥለን ለማወደስና ለማውገዝ በቃን:: በምን መርሕ በየትኛውስ ውሃ የሚቋጥር ምክንያት ተለያይተን ቆምን:: በሃቅና መርሕ ወይስ በዘውግ የመንጋ   ፍርድ ::የምንሄድበት ሁኔታ ያሳፍራል::
ሰሞኑን በአላሙዲ መፈታትና: በአየር መንገዱ ስራ እስኪያጅ ላይ የሚታየው የተምታታና የተሳከረ የአቋም መጣረስ ከያቅጣጫው እናያለን:: እስኪ ሁሉንም ነጠል አድርገን እንመልከት::
አላሙዲ ከሕዝብ ነበር ወይስ ከአገዛዙ?
ቢሊየነሩ ከበርቴ ሼክ መሃመድ አላሙዲ ምንም ትውልደ ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም በዜግነት ሳውዲአረባዊ በመሆናቸው በኢትዮጵያ በሕግ የሚከለከሉትን የቢዝነስ  ሴክተሮች ለግዜው ትተን የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ  የመሳተፍ ሕጋዊ መብት ባይኖራቸውም የሕወሃት ደጋፊ በመሆን በአደባባይ በ97ቱ ምርጫ ወቅት  ባሳዩት የማይገባ ድርጊት ከሕዝብ ጋር በከባዱ ተቆራርጠው ቆይተዋል:: ከዚህም በላይ በሰሜን አሜሪካ ለዘመናት የቆየውን የስፖርት ፌዴሬሽን በገንዘባቸው አቅም ለመበተን ያም ሳይሳካ ሲቀር ለመከፋፈል የሄዱበትን አስነዋሪ እንቅስቃሴ በተባበረ የሕዝብ ሃይል  እንደከሸፈ ይታወቃል::
ይህና ብዙ ሊዘረዘሩ የሚችሉ ምክንያቶች እንደነበሩ  ተዘንግቶ ከአንድ አመት እስር በሗላ ሲፈቱ እየታየ ያለው ዘውግ ተኮር ድጋፍና ተቃውሞ እጅግ ያሳፍራል:; በአንዳንድ የኦሮሞ አክቲቪስቶች የቀረበው የተፈጥሮ ሃብት ውድመት እና ያን ተከትሎ በዜጎች ላይ ደረሰ የሚሉት የጤና ችግር የሃብት ብዝበዛና  የተጠቃሚት ጥያቄ ማስረጃ አለን ብለው ሲቃወሙ የኛ ብሄር ስለሆኑ ነው የሚል  ተከላካይነት አማራ ነን ከሚሉት ሰምተናል:: ሼኩን ከአማራ ብሄርተኝነት ጋር ሊያያይዝ የሚችለው ትርክት መነሻው በራሱ  ከየት እንደሆነ ግልጽነት ይጎለዋል::
ከበርቴው በእርግጥ ከአማራ ቤተሰብ ወሎ ውስጥ ቢወለዱም ለሳቸው ግን ቅርብና ወዳጅ ሆኖ የኖረው የአማራው የሕልውና ጠላት ሕወሃት ነው:: ይሄ ሃቅ ብዙ ምርምር የሚጠይቅ ሳይሆን ትላንትና ስንኖረው በነበረው የጭለማ ዘመን ውስጥ ያየነው የአደባባይ ሚስጥር ነው:: ከዚህ በላይ ግዜ ለመቆጠብ ብዙ ማለት አልፈልግም:: ወደ ሌላው ልለፍ::
የዶር አብይ የአየር መንገዱ ጉብኝት ንግግር የፈጠረው እንድምታ!
ባለፉት 27 አመታት በሕወሃት ሙሉ ቁጥጥር ስር እንደወደቀ ሲነገርለት የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትንሿ ትግራይ እስከመባል የደረሰ በትግራይ ተወላጆች ከላይ እስከታች መሞላቱን ሂያጅና መጪው ሲያወራው የነበረ ነው:: የተቋሙ ሰራተኛ የስራ መመሪያው የደረጃ እድገቱና በስራ የመቀጠል ዋስትናው የሕወሃት ሰዎች ቀና ፍቃድ ብቻ እንደሆነ ከሻንጣ ተሸካሚ እስከ ዋና አብራሪ በየሚድያው ሲናገሩት እኛም ስንሰማው  ኖረናል:; አየርመንገዱ ካለው የዘመናት ዝና በላይ በአለም ያስተዋወቁት የፖለቲካ ጫናው አስመርሯቸው የሚያበሩትን አውሮፕላን ጠልፈው ጥገኝነት የሚጠይቁ ፓይለቶች : ከሚጭኑት ሻንጣ ጋር አብረው ተጭነው ከሃገር በወጡ የአገዛዙ ምሬተኞች ጭምር ነው:: ከዛም በላይ አሰልጥኖ ወደ ስራ ያሰማራውን የተማረ ፓይለት በብሄር ማንነቱና በፖለቲካ አመለካከቱ አባሮ አራሽ ገበሬ ማፍራት የቻለ ባለ ትንግርት ተቋም ነው::
ስለአየርመንገዱ የግፍ ሰለባዎች ብንዘረዝር መጽሃፍ ስለሚወጣው እንለፈው:: ግዜ ታሪክ ወደፊት በሰፊው ያሳየናል::
የሚገርመው ግራ የሚያጋባው የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር መወደድና መከበር ያገኙ መሪ ስንሰማውና ስናየው የኖርነውን እውነት አሉባልታ ነው አሉት:: የሕወሃት ተሿሚ የድርጅቱ ተጠሪ የሆነው ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ምስጉን  ታታሪና ድርጅቱን የመምራት ብቃት ያለው በሚል በጠቅላይ ሚንስትሩ ተሞካሽቷል:: የተወነጀለውም በሃሰት አስተዳደሩም ጠንካራና ስልጡን ነው ተብሎ ተነግሮለታል:: እንግዲህ በግፍ ተባረርን የሚሉትን ፓይለቶች የአስተዳደር ባለሙያዎች የአቬሽን ኤክስፐርቶች እና የተለያዪ ስራተኞችን እንመን ወይስ ጠቅላይ ሚንስትሩን:: ግራ አጋቢና የተወሳሰበ ነገር ነው::
በጣም የሚያነጋግር በታሪክም በሕግም የሚያስጠይቅ የትርክት ተቃርኖ ይታያል:; ወይ የሰራተኞቹ ክስ አለያም የጠቅላይ ሚንስትሩ ምስክርነት ይዋል ይደር እንጂ መገለጡ አይቀርም:: ግዜ ለኩሉ….:: ከሕዝብ አይን የማይታዉቅ የተሸፈነ የማይታይ የተደበቀ ነገር አይኖርም::
የጠቅላይ ሚንስትሩን ውዳሴና ሙገሳ ያገኙት የአየር መንገዱ ዋና አስኪያጅ አቶ ተወልደ በፖለቲካው ውስጥ ያለውን የዘውግ እሰላለፍ በመረዳት ይመስላል የኦሮሞ ሚድያ ኔትወርክ ስራ እስኪያጅ : ቄሮም አባገዳም መንግስትም ነኝ የሚለውን እንደልቡ ጁሃር መሃመድን እንደ አንድ ከፍተኛ የመንግስት ተጠሪ ወይም እንግዳ የተደረገለት ኦፊሴላዊ ጉብኝት አንድምታው የሃይል ሚዛን ጥበቃና አጋር የማድረግ አካሄድ ነው የመሰለው:: ይህ ጎረምሳውን በዛ ደረጃ በአየር መንገዱ ማስተናገዱ ለኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞች መንበርከኩንና በራሱ ይቀርብበት የነበረውን አማራውን የማግለል  የብሄር ጭቆና ክስ ሊመልስ የማይችልበት ሁኔታ እንዳለ ገላጭ ነው::
በአጠቃላይ በመደመር ፍልስፍና : የሕግ ልዕልና ይደፍጠጥ የሚል አቅጣጫ ያለ አይመስኝም:: የመደመሩ ጽንሰ  ሃሳብ ያጠፋ በህግ እንዲዳኝ አለያም በይቅርታ እንዲታለፍ እንጂ እውነትን ቀብሮ ሃሰትን ማንገስ አይደለም::በዘልማድ ሰዎችን ለማስታረቅ መዋሸት ጥበብ ቢሆንም : ሃገርና ሕዝብን ግን ዋሽቶ በማስማማት እረጅም እርቀት መውሰድ አይቻልም :; ለግዜው አቅም  በማጣት ለመሪው ካለው ፍቅርና ክብር እያወቀ ቢያልፈው ዘግይቶ አያነሳውም ማለት አይቻልም:; ስለሆነም  አበው አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ እንዲሉ  እንዳይሆን የሕግ ዋጋው ታውቆ ሊከበር:: የሞራል ልዕልናዋ ሲጠበቅ  ከመርሕ አልባ የመንጋ ፖለቲካ ወጥተን በሕግ በስርዓት በሞራልና በእውነት ላይ መመስረት ሲችል ነውየለውጡ ዑደት ስሉጥና ሰላማዊ ወደ ሆነ ግብ የሚያደርሰው::
እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን!!!
Filed in: Amharic