>
10:31 pm - Tuesday July 5, 2022

የመጀመሪያዋ አጭር ልቦለድ ደራሲና አርበኛ ተመስገን ገብሬ ህይወት!!!

የመጀመሪያዋ አጭር ልቦለድ ደራሲና አርበኛ ተመስገን ገብሬ ህይወት!!!
መጽሀፍት ለሁሉም
በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ግንቦት 15 ቀን 1901 ዓ.ም ጎጃም ውስጥ ደብረማርቆስ ከተማ አንድ ድንቅዬ ደራሲና አርበኛ ተወለደ። ተመስገን ገብሬ ይባላል። በ1929 ዓ.ም ኢጣሊያ ኢትዮጵያን እንደምትወር ቀድሞ ያወቀና የነቃ ሰው ነበር። በየቦታው እየተዘዋወረ ንግግር ያደርግ ነበር። ዛሬ ሐገር ፍቅር ቴአትር ቤት በሚባለው፣ በቀድሞ ስሙ የሃገር ፍቅር ማህበር ቴአትር ቤት ውስጥ ታዋቂ ንግግር አድራጊ ነበር። ‹‹ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ልትወር ነው፤ ለጦርነት እንዘጋጅ›› እያለ ዲስኩር የሚያሰማ ንቁ ኢትዮጵያዊ ነው።ተመስገን ገብሬ  የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ጭፍጨፋ ሲደረግ ጣሊያኖች ሊይዙት የሚፈልጉት ዋነኛው ተጠርጣሪ ነበር። ግራዚያኒ ላይ በአብርሃም ደቦጭ እና በሞገስ አስገዶም አማካይነት የተወረወረ ቦምብ ከበስተጀርባ ሆኖ ነገሮችን ያቀነባበረው ተመስገን ገብሬ ነው ተብሎ ቀንደኛ ተፈላጊ ሆነ። የገባበት ሁሉ ገብተው ጣሊያኖች ያድኑት ነበር። በመጨረሻም በእጃቸው ገባ። ግን ተመስን ጣሊያኖችን አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው።
“ማንን ነው የፈለጋችሁት?” አላቸው።
“ተመስገን ገብሬን ነው!” አሉት።
“እኔ ተመስገን ገብሬን አውቀዋለሁ፤ አብሬያችሁ ብዞር እናገኘዋለን” አላቸው።ጣሊያኖቹም እውነት መስሏቸው ተመስገንን ይዘው ተመስገንን መፈለግ ጀመሩ። አዲስ አበባ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ በአይኑ ተመለከተ። በመጨረሻም በራሱ ተመስገን ላይ የሞት ፍርድ ፈርደውበት ከሌሎች እስረኞች ጋር አብሮ ይረሸናሉ። ነገር ግን ተመስገን በጅምላ ርሸና ውስጥ ወደቀ። ይሁን እንጂ ጥይት አልመታውም ነበር። እንደ ሞተ ሰው ከሟቾች ጋር ተኛ። ጣሊያኖቹም አስክሬኖቹን ጥለዋቸው ሔዱ። የዚህን ጊዜ ተመስገን ገብሬ ከሟቾች መሐል ተነስቶ ይጠፋል። በመጨረሻም ወደ ሱዳን ተሰደደ። ሱዳን ውስጥ ሆኖ ዋነኛው የአርበኞች ትግል አቀጣጣይ ነበር። ጃንሆይ ጄኔቫ ላይ የሊግ ኦፍ ኔሽን ስብሰባ ንግግር ሲያደርጉ የንግግራቸው አብዛኛው ሃሳብ ተመስገን ገብሬ ከሱዳን ሆኖ የፃፈላቸው ደብዳቤ ነበር።ይሔ ታላቅ የኢትዮጵያ አርበኛ ጣሊያኖች ከተሸነፉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ከጃንሆይ ጋር መጥቶ በወቅቱ የምትታመው “የኤርትራ ድምፅ” የምትባለው ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ይሰራ ነበር። ይህ ሰው በ1941 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሥነ-ፅሁፍ ታሪክ የመጀመሪያዋ አጭር ልቦለድ የምትባለውን መፅሐፍ “የጉለሌው ሰካራም” የተሰኘችውን የፈጠራ ስራውን አሳትሟል።
ተመስገን ገብሬ ከዚህ አለም በሞት የተለየው በ1941 ዓ.ም በአርባ አመቱ ነበር። ይሁን እንጂ ቀደም ብሎ “ሕይወቴ” በሚል ርዕስ መፅሐፍ አዘጋጅቶ እቤቱ ቁጭ አድርጎት ነበር። ከሞተ ከ60 ዓመታት በኋላ ይህ መፅሐፍ ታተመ። በውስጡ የተመስገን ገብሬ የሕይወት ታሪክ ብቻ ሳይሆን የያዘው፣ የኢትዮጵያንም ታሪክ ነው። በተለይ እንደልቦለድ አድርጎ የፃፈው “የካቲት 12 ቀን” የተሰኘው ፅሑፉም በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው አጭር ልቦለድ እየተባለ ተነግሮለታል።
Filed in: Amharic