>
9:14 am - Saturday December 10, 2022

“ትግራይ ተከባለች!!!" (በፍቃዱ ኃይሉ)

“ትግራይ ተከባለች!!!”

በፍቃዱ ኃይሉ

አገር ሲንቀሳቀስ በዚህ “ትግራይ ተከባለች፣ ልንጠቃ ነው” ፕሮፓጋንዳ የተነሳሳው ሕዝብ መንገድ ዘግቶ ሠራዊቱን አላሳልፍም እስከማለት ደርሷል። (ተቃዋሚዎቹን ባለመታገስ የሚታወቀው የትግራይ መንግሥትም ወጣቶቹን ባለማስቆሙ፣ ምንም እንኳን የኋላ ኋላ ለማስተባበል ቢሞክርም ሕወሓት ራሱ ያስተባበረው የመንገድ መዝጋት እንደሆነ ተገምቷል።)

በተመሳሳይ፣ በታኅሣሥ ወር 2011 የሱዳኑ መሪ ከኢትዮጵያ መሪ ጋር ጅማ ላይ በተገናኙበት ወቅት ላይ ባደረጉበት ወቅት፣ በትግራይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ለመቃወም በርካታ ሰልፎች እየተካሔዱ ነበር። ሰልፈኞቹ ከያዙት መፈክር መካከል “አልበሽር እናመሰግናለን” የሚል ይገኝበታል። አልበሽር እና ኢሳያስ ከፌዳራሉ መንግሥት ጋር ያላቸውን ግንኙነትነት በአንድ በኩል በቅናት፣ በሌላ በኩል በማባበል ለመሳብ የሚሞክሩት የትግራይ መሪዎች ሕዝባቸውን ተከበናል እያሉ ከሚያሳምኑበት ጉዳይ ውስጥ እነዚህ የውጭ ግንኙነቶች ይገኙበታል።

ትግራይ እና ሕወሓት

ሕወሓት ማዕከላዊው መንግሥት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበረውን የትግራይ ሕዝብ ወደ ዳር (periphery) እንዲገፋ ምክንያት ሆኗል። ሆኖም በዚህ ራሱ ተወቃሽ ሊሆን በሚገባበት ጉዳይም ድጋፍ መሰብሰቡን አላቆመም። “በትግራይ ሕዝብ እና በሕወሓት መካከል ልዩነት የለም” የሚል አቋም የሚያራምደው ሕወሓት፥ በፖለቲካ ጫወታ ሲሸነፍ ሕወሓት ላይ የተወሰደውን እርምጃ በሙሉ የትግራይ ሕዝብ ላይ የተወሰደ እርምጃ ነው እያለ ይናገራል። በዚህም ምክንያት ከአዲሱ አመራር መምጣት በፊት ሕወሓት ላይ ምሬት የነበረው ብዙኃን ትግራዋይ፥ አሁን ክልሉን በመከላከል ሥም የሕወሓት ደጋፊ ወደ መሆን እየተሸጋገረ እንደሆነ እየተነገረ ነው። ለዚህም በትግራይ ክልል የሚካሔዱት የፌዴራል መንግሥቱን የሚቃወሙ ሰልፎች ማሳያ ናቸው። ሌላው ቀርቶ የሑመራ ድንበር በተከፈተበት የገና ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን “ሌባ ሌባ” እያሉ ይሰድቡ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ይህንን የትግራይ ማኩረፍ የሚያሳዩ ምልክት ናቸው።

ከድጡ ወደ ማጡ

የፖለቲካ ኩርፊያው እና እሰጥ አገባው እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ በመግለጫዎች እና በቴሌቪዥን ፕሮፓጋንዳዎች ብቻ ነበር የሚስተዋለው። ባለፈው ሳምንት፣ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ ምክር ቤት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ያቋቋመውን የማንነት እና አከላለል ጥያቄዎች አጣሪ ኮሚሽን በመቃወም አቋም ሲወስድ፥ ኩርፊያው ኦፊሴላዊ ዕውቅና አግኝቷል። በመሠረቱ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በድምፅ ብልጫ የሚወስነውን ውሳኔ “እኔን ካልተስማማኝ” ብሎ የመሻር መብት አንድም ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለክልሎች አልተሰጠም። ይሁንና አሁን የትግራይ ክልል አቋም አዋጁን በክልሉ ተፈፃሚ እንዳይሆን እስከማድረግ ድረስ ይዘልቃል።
የትግራይ ክልል ኩርፊያ የኢትዮጵያን ኅልውና አደጋ ላይ ከሚጥሉ ፈተናዎች አንዱ ነው። ይሁን እንጂ የኩርፊያው አንድ አካል የሆነው የፌዴራል መንግሥትም የሚገባውን ትኩረት የሰጠው አይመስልም። አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል አንፃራዊ የለውጥ ንፋስ እየተነፈሰ ባለበት ወቅት፥ የትግራይ ሕዝብ ግን የተለየ የጭቆና ደሴት ውስጥ ሆኖ ቀጥሏል። በዚህ መካረር መሐል ቀጣዩን ምርጫ በትግራይ እንዴት ማካሔድ ይቻላል? ሕወሓትስ ከኢሕአዴግ ጋር አብሮ የሚሠራው (ወይም አብሮ ሳይሠራ አብሮ የሚኖረው) እስከመቼ ነው? የሚሉት ጥያቄዎች ገና ብዙ ትርምስ እንደሚኖር አመላካቾች ናቸው።

Filed in: Amharic