>

"....እግዚአብሄርም ኢህአዴግ አርባ አመት ይመራል ብሏል ወይ?..." (ሸንቁጥ አየለ)

“….እግዚአብሄርም ኢህአዴግ አርባ አመት ይመራል ብሏል ወይ?…”
ሸንቁጥ አየለ
አቢይ ሆይ የህዝቡን ጩህት ብትሰማ ይሻልሃል::ህዝብ እየጮህ አጠገብህ ያሉ ደጋፊዎች ጩህት የለም የሚሉትን እና አንተን ለመከላከል የሚወራጩትን እያደመጥህ ገደል እንዳትገባ!!
ይሄ ትንቢት መሰል ቀልድ ለዛሬዎቹ ኦህዴዶችም ይሰራል::ኦህዴዶች ግን ህዝብ ሲጮህባቸዉ እንደ ህዉሃት ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዉ በህዝብ ጩህት ላይ ያላግጣሉ::
ለደጋፊዎቻቸዉ እና ለአባላቶቻቸዉም ምርጥ ምርጡን ማቅረብ እና መስጠት ብቻ ሳይሆን ሌላዉ ህዝብ ተገፋሁ ብሎ ሲጮህ ለምናባክ ተገፋሁ ትላለህ ማለት አብዝተዋል::
———————
ከአምስት አመታት በፊት አቶ ወርቁ ከሚባሉ ሰዉ ጋር በአንድ ድርጅት ዉስጥ እሰራ ነበር::እኝህ ሰዉ የድርጅቱ ሹፌር ናቸዉ::አቶ ወርቁ ቀልድ ይችላሉ:: አንዳንዴ መጀመሪያ በኦሮምኛ ይቀልዱና መልሰዉ በአማርኛ ይፈትቱታል:: አንድ ሰዉ ሲናገር ዝም ብለዉ ያደምጣሉ::ሰዉዬዉ በተናገረዉ ንግግር ላይ ግን እጥር ያለች አስተያዬት ይሰጣሉ::አንዳንዱ አስተያዬታቸዉ ለዘላለም በሰዉ ዉስጥ የመኖር ጉልበት አለዉ::
—————–
እናም አንድ ቀን በመኪና ዉስጥ የነበርነዉ ሰዎች የግል ጋዜጣ እያነበብን በበረከት ንግግር እየተናደድን እንንጫጫለን:: በረከት እነ አላሙዲን እና ሌሎችም ባሉበት መጽሀፉን ሲያስመርቅ የተናገረዉን ንግግር በጋዜጣ ላይ እያነበብን ነበር:: በረከት ከዘባረቀዉ በርካታ ሀሳብ ዉስጥ አንዱ “ኢህአዴግ ገና አርባ አመት ይገዛል” የሚል ሀሳብ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር እና በጋዜጦችም ላይ ሀሳቡ ይሽከረከር ነበር::
———————–
እናም በዚህ ሀሳብ ላይ እየተነጋገርንም እየተበሳጨንም ሳለ አቶ ወርቁ በቀልድ አንድ ጥያቄ ጠየቁ:: ” አቶ በረከት ካሁን ብኋላ ኢህአዴግ አርባ አመት ይመራል አለ?” ሲሉ ጠዬቁ:: ሁላችንም “አዎን” አልናቸዉ::
አቶ ወርቁ አስከትለዉ በኦሮምኛ የሆነ ነገር ተናገሩ:: በኦሮምኛ የተናገሩትንም ንግግር አስደግፈዉ በአማርኛ አንድ ቀልድ የመሰለ ጥያቄ አቀረቡ:: እንደ ነቢይ ነባቢነት የተለበሰ ግን ለጊዜዉ ቀልድ የመሰለን ጥያቄ::
“ማለቱንስ አቶ በረከት ይበል::ግን እግዚአብሄርም ኢህአዴግ አርባ አመት ይመራል ብሏል? እግዚአብሄር በበረከት ሀሳብ ተስማምቷል?”  ሲሉ ጥዬቁ::
እኛም ሁላችን ስቀን ዝም አልን::አሁን የኝህን ሰዉ ንግግር ሳስበዉ ሁሌም ያስገርመኛል:: አሁን ይሄ ጥያቄ ለኦህዴዶች/ኦዴፓዎች ሊጠዬቅ ይገባዋል::
የአዲስ አበባ ህዝብ ተገፋሁ እያለ ሲንጫጫ: በድሬዳዎ ብዙ ጩህት ሲሰማ የኦዴፓ ደጋፊዎች እያንዳንድሽ ዝም በይ::ምንም አታመጭም::ካሁን ብኋላ ስልጣኑን ተቆጣጥረንዋል የሚል ፉከራ ላይ ናቸዉ::የወያኔ ደጋፊዎችን እና አባላትን ያስናቀ ብሎም ስድብ እና ዛቻ ይዥጎደጎዳል::
በደቡቡ ኢትዮጵያ ትንንሽ ቁጥር ያላቸዉ በርካታ ነገዶች በጎጄ ኦሮሞ ከፍተኛ መገፋት ደረሰብን እያሉ እየጮሁ ነዉ:: ማዕከላዊ መንግስትም ሆነ የኦሮሚያ መንግስት ግን ማላገጥ የመረጠ ይመስላል::
ስልጣኑን በረከት ለአርባ አመት ሲመኛት ስልጣንን እግዚአብሄር ያስገባት አቢይ መሃመድ እጅ ነዉ::ስልጣን ከኢህአዴግ ወደ ኢህአዴግ ብትዘዋወርም የበረከትን ተንኮል እግዚአብሄር ሰብሮበታል::
አቢይ አህመድ የህዝቡን ጩህት ብትሰማ ይሻልሃል::ህዝብ እየጮህ አጠገብህ ያሉ ደጋፊዎች ጮህት የለም የሚሉትን እና አንተን ለመከላከል የሚወራጩትን እያደመጥህ ገደል እንዳትገባ::
የከበበህ ሙሰኛ ባለስልጣናት ነዉ: የቆምከዉ የጎሳ ድርጅት ላይ ነዉ: አንተ የምትናገረዉ ግን ኢትዮጵያዊነት ነዉ::
ኢትዮጵያዊነትን ስትናገረዉ ማንም ይማልልሃል::ግን ኢትዮጵያዊነትን መኖር ታላቅ ወኔ እና የርዕዮተ አለም ለዉጥ ያስፈልገዋል::
በጎሰኛዉ ኦዴፓ/ኢህአዴግ የፖለቲካ ራ ዕይ እየተመራህ: በሙሰኞች ተከበህ: የኛ ጎሳ አባላት ብቻ ሁሉን ይዋጡት በሚሉ ሰዎች ተወረህ: ወገናዊነት ሀገሩን ሲያጥለቀልቀዉ እያስተዋልክ ዝም ብለህ: ሌላዉ ሲጮህ እና ሲንጫጫ የሚሳደቡ ባለጌ ደጋፊዎችን አሰለፈህ የኢትዮጵያን ህዝብ አታሸንፈዉም::የአዲስ አበባ ህዝብ የጠላዉን ታከለ ኡማን አለ ህዝቡ ዉዴታ እህዝቡ ላይ ጭነህ የትም አትደርስም::
አሁን ይሄን ሁሉ ሀሳብ በመናቅ ህዝቡ ምንም አያመጣም ስልጣን የኛ ነች የሚል ታሳቢን በመንገብ የራስን ጎሳ ብቻ ለመጥቀም የመገስገስ አሰራር ከተከተልክ የአቶ ወርቁ ጥያቄ ትከተላለች::
 “…ኦዴፓ/ኢህአዴግ ካሁን ብኋላ ስልጣን የእኔ ናት እና ህዝብ ቢጮህ አያሳስበኝም ብሏል:: ግን እግዚአብሄርም በኦዴፓ ሀሳብ ተስማምቷል ወይ?…”
በየቦታዉ የሚጮህዉን ዜጋ ድምጽ ቶሎ ካልሰማችሁ የሚመጣባቹን ህዝባዊ ማዕበል እዚህ ማብራራት አይጠበቅብኝም::ህዝብ ባትፈሩ እምነቱ ካላችሁ እግዚአብሄርን ፍሩ::ምክንያቱም እግዚአብሄር ሁሌም ከተገፉት ጋር ነዉና::
Filed in: Amharic