>
6:01 pm - Friday August 19, 2022

"በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ላይ ድርድር አይኖርም!!!"  (ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ)

“በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ላይ ድርድር አይኖርም!!!”
 ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ
በአብርሃም ፈቀደ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው እለት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።
 
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ላይ ከማንም ጋር ድርድር እንደማይኖር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
በምላሻቸውም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ላይ ድርድር እንደማይኖር አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላማዊ መንገድ እንታገል ብለን እንደጠራነው ሁሉ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የሚደራደር ኃይል ጦርነት ማወጁን ሊያውቅ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም የሃገሪቱን ሰላም የሚነሳና ልማቷን የሚያደናቅፍ ጉዳይ ላይ መንግስት ህግን በተከተለ አግባብ የማያዳግም እርምጃ ይወስዳልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ይህ ማለት ግን መንግስት ሲሳሳት አይወቀስ ማለት ሳይሆን ህግን መሰረት ባደረገና የኢትዮጵያን አንድነት በማይፈታተን መልኩ መቅረብ ይኖርበታልም ነው ያሉት።
በማብራሪያቸው ውጭ ሀገር ለነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደረገው ጥሪ የሠላምን መርህ የተከተለ እና ከፓርቲዎቹ ጋር የተደረገው ድርድርም ልዩነት የሌለውና አንድ ዓይነት መሆኑንም አብራርተዋል።
ባለፉት ወራት ከ20 በላይ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ገልጸው ይህ ሂደት ለፓርላማውም ድል ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ምንም አይነት ፓርቲም ሆነ ሚዲያ ከውጭ ሆኖ እንደማይታገልም በምላሻቸው ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደራደሪያ መርሁ ከሁሉም ጋር አንድ ዓይነት የሆነበትን ምክንያት ሲያብራሩም፥ መንግስትን መንግስት የሚያደርገው አንዱ ተግባር ይህ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ ጥሪውን ተከትለው ከገቡ ፓርቲዎች መካከል የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና ቢሮ ችግር እያለባቸው ዴሞክራሲውን ለማጠናከር የሚሰሩ ፓርቲዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ከዚህ በተጻራሪ የሚንቀሳቀሱና አንድ እግራቸውን አዲስ አበባ አንድ እግራቸውን ውጭ ሀገር ያደረጉ ፓርቲዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፤ ይህም ወደ ጸረ ዴሞክራሲያዊ ልምምድ ውስጥ እንደሚከት በመጥቀስ።
አሁን ላይ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን ጠቅሰው ፓርቲዎቹም ከዚህ ጋር ልምምድ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፤ ከዚህ በተጻራሪ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ህግን ተከትለው እንዲሄዱም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
አሁን የሚያስፈልገው አንድነቷን፣ ሰላሟን እና ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ የሚያስችል ሀሳብ ያለው ፓርቲ ነውም ብለዋል በሰጡት ምላሽ።
ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ፓርቲዎችም ከጊዜው አጭር መሆን አንጻር ምርጫ ቦርድ በተገኘበት ማሟላት የሚገባቸውን ሁሉ እንዲያሟሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ፓርቲዎቹ በራሳቸው ያልተለማመዱትን ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ላይ ሳይሆን መጀመሪያ ከራሳቸው መጀመር አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው የሚፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተም፥ ሁኔታው ከባህል ያፈነገጠ መሆኑን አንስተው ከማሻሻያው በኋላ ከተፈናቀሉት ውስጥ 90 በመቶዎቹ ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ተግባር ውስጥ ለተሰማሩ ኃይሎችም ሉዓላዊ ሀገር እንጅ ሉዓላዊ የሚባል ክልል የለም ብለዋል።
ግጭትን ማስቆም፣ እምቅ የግጭት አቅሞችን ማክሰም እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ይገባልም ብለዋል በማብራሪያቸው።
በወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎችን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ሰርቶ ያልታሰረ ሰው የለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፤ ሁሉም ክልሎች ወንጀለኛ ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችን አሳልፈው መስጠታቸውን በመጥቀስ።
ሆኖም ተጠርጣሪዎችን አሳልፈው የማይሰጡ ቡድኖችም ይሁኑ ግለሰቦች ተጠያቂ ይሆናሉም ነው ያሉት።
በሙስና ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎችን አያያዝ በተመለከተም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ አያያዛቸውን መመልከቱን ጠቅሰው፥ ቤተሰብ እንደሚጠይቃቸው፣ እንደሚያነቡና ሰብዓዊ አያያዛቸው መጠበቁንም ነው ያነሱት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚደግፈንም ይሁን የሚቃወመን ኃይል በህግ አግባብ መሰረት መሆን አለበት ሲሉም ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ገልጸዋል።
የክልል እንሁን ጥያቄን በተመለከተ ጥያቄው ህገ መንግስታዊ መብት፣ የዴሞክራሲ ልምምድና መደመጥ ያለበት ጥያቄ መሆኑን ጠቅሰው፥ ጥያቄው በሰላማዊ መልኩ ከቀረበ በዚህ መደናገጥ እንደማይገባ አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችንም በማብራሪያቸው ውስጥ ያካተቱ ሲሆን፥ የፖለቲካ ኃይሎች መጠቀሚያ አለመሆን የተማሪዎች ኃላፊነት ነው ብለዋል።
እንዲሁም ከተማሪዎች የሚጠበቀው ሀሳብና ሀሳብን አጋጭቶ የተሻለ ሀሳብ ማውጣት እንጅ ድንጋይና ድንጋይን አጋጭቶ እሳት ማውጣት አለመሆኑንም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጨረሻም መገናኛ ብዙሃን መጫወት የሚገባቸውን ሚና እየተጫቱ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ ውስጥ ጤነኛ የሚባል ሚዲያ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚኖሩበት ክልል ተሻግረው ኢትዮጵያን ያማከለ ሲሆኑ አይታይም ነው ያሉት።
በዚህም የመንግስት ሚዲያዎችን ማስተካከልና ለግል ሚዲያዎች ደግሞ የጋራ መድረክ ማዘጋጀት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
Filed in: Amharic