>
7:20 am - Wednesday December 7, 2022

ጥቅል እውነቶች እና ሽፍንፍን የበዛበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክር ቤት ንግግር!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ጥቅል እውነቶች እና ሽፍንፍን የበዛበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክር ቤት ንግግር!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት ምክርቤት ቀርበው በቀረቡላቸው ጥያቄዎች ላይ የሰጧቸውን ማብራሪያዎች በጥሞና ለመከታተል ሞክሬያለው። እንደተለመደው ንግግራቸው ከሞላ ጎደል ጥሩ የሚባል እና አቀራረባቸውም አስደማሚ ነው። ይሁንና ብዙ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡዋቸው ማብራሪያዎች በጥቅል እውነታዎች (General truth) የተመሰረቱ፣ ግልጽነት የጎደላቸው እና የአገሪቱ የበላይ ለሆነው አካልም የሚቀርብ ሳይሆን በሎሎች መድረኮች ላይ የሚሰጡ ማብራሪያዎች ነው የሚመስሉት።
በርካታ ጥያቄዎችን በመለሱበት ማብራሪያቸው ውስጥ በርካታ እና ትልቅ ግምት ሊሰጣቸው የሚችሉ ነገሮችን ያነሱ ቢሆንም ምላሻቸው ግን በዝርዝር መረጃዎች የተደገፉ አልበነሩም። እንዲ ያሉ ንግግሮች ብዙ ሰዎችን ሊያግባቡና ማንንም ሊጎረብጡ የሚችሉ ባለመሆናቸው ለአቅራቢውም ሆነ ለሰሚው ጥሩ መስለው ይታያሉ። ነገር ግን እንደ አገር በግልጽ በስም፣ በጊዜ እና በቦታ ተጠቅሰው ሊነገሩ የሚገባቸው እውነታዎች ከላይ ከላዩ እየተነካኩና በጥቅል ዳሰሳ መታለፋቸው ግን የማይበረታታ አጉል አካሄድ ነው።
ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል በንግግራቸው ላይ በወንጀል ተጠርጥሮ በመንግስት እየተፈለገ ያለ ነገር ግን ያልታሰረ ሰው የለም የሚለው ንግግራቸውን መውሰድ እንችላለን። በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጡት ማብራሪያ ሁለት መሰረታዊ ግድፈቶች አሉበት። የመጀመሪያው እነዚህን ማንነታቸው የሚታወቅ እና ጉዳይም የአደባባይ ሚስጥር የሆነውን ነገር  በጥቅል መግለጻቸው በእኔ እምነት ትክክለኛ አካሔድ አይደለም። ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ሰማቸውን ጠቅሶ እና የፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ አውጥቶ ሊይሳቸው ካልቻላቸው ሰዎች መካከል አንዱ እና ግንባር ቀደቡ አቶ ጌታቸው አሰፋ መሆናቸው ይታወቃል።
እኚህ ሰው ተደብቀው ሳይሆን የክልሉ መንግስት አሳልፌ አልሰጥም በማለቱም እንደሆነ የአደባባይ ሃቅ ነው። ጭርሱኑ እኙህ ሰው የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ተደርገው መሾማቸውም ይታወቃል። ይህን ሃቅ በገደምዳሚት ለምክር ቤት ማቅረብ ምን ይሉታል። መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ለምክርቤቱ የገጠሙትን ችግሮች በግልጽ ማስረዳት ነበረበት። ከክልሉ መንግስት ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ያደረጋቸው ውይይቶች እና የተወሰዱ እርምጃዎችም ካሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዝርዝር ማስረዳት ይጠበቅባቸው ነበር። የትግራይ ክልል ግለሰቡ አሳልፌ አልሰጥም ብሎም ከሆነ በግልጽ ተነግሮ ምክር ቤቱ የውሳኔ አቋም እንዲወስድበት መደረግ ነበረበት። የፌደራል መንግስቱም አቅም አንሶት ከሆነ ምክር ቤቱ ሁኔታውን በግልጽ ሊነገረው ይገባ ነበር። ከዛ ይልቅ ጠቅላይ ሚንስትሩ በስላቅ መልክ የሰጡት ምላች ደረጃውን ያልጠበቀ እና ተቀባይነት የሌለው ነው።
እኛ ባናስራቸውም ግለሰቦቹ የመንቀሳቀስ ነጻነታቸው ስለተገደበ እንደታሰሩ ነው የሚቆጠረው የምትለዋ አገላለጽ ውሃ የምትቋጥር አይደለችም። አንድም የፌደራል መንግስቱ በመላ አገሪቱ ተንቀሳቅሶ ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር አቅም ያነሰው መሆኑን ነው የሚያሳየው አለያም ግለሰቡን ለፍትሕ የማቅረቡ ጉዳይ ከፖለቲካ እንድምታ የዘለለ የሕግ አስከባርነት ቁርጠኝነት በፌደራሉ መንግስት በኩል ጉድለት ይታይበታል ማለት ነው። ሌላው ቢቀር የትግራይ ክልላዊ መንግስት እኚህን ሰው ከሰጣቸው ስልጣን ማንሳት እና ከአባልነት ማሰናበት ይጠበቅበት ነበር። ይህ አለመሆኑ በራሱ ከግለሰቡ መታሰር ባሻገር በክልሉ እና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለው ጡዘት እልባት አለማግኘቱን ነው የሚያሳየው። ይህም ሆነ ከሆነ ነገሩ ለፓርላማው እና ለሕዝብ በይፋ ሊገለጽ የሚገባው ጊዜ አሁን ይመስለኛል።
ሁለተኛው የጠቅላይ ሚንስትሩ ግልጽነት የጎደለው እና በቂ ማብራሪያ ሊሰጡበት ይገባው የነበረው ጉዳይ በምዕራብ ወለጋ ከኦነግ ጋር በተያያዘ የሚታዩት ችግሮች ላይ ነው። በጥቅል ንግግራቸው ውስጥ በቀጥታ ኦነግን የሚመለከቱ ነገሮችን ጠቃቅሰዋል። ጠንከር ባሉ ቃላትም ወርፈዋል። ይሁንና ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ግልጽ ጥያቄዎች አንዳንድ ፓርቲዎች፣ አንዳንድ ቡድኖች፣ አንዳንድ  …… የሚጠቅሷቸው ስም አይጠሬዎች በማንነት፣ በጊዜ እና በቦታ ተጠቅሶ ያለው ሁኔታ በግልጽ ለምክር ቤቱ መቅረብ ነበረበት። መንግስት ከኦነግ ጋር የገባው እሰጥ አገባ በምን መሉ እንደተፈታ፣ የተደረጉ ድርድሮች ምን መልክ እና ይዘት እንዳላቸው፣ በክልሉ ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል በቂ ማብራሪያ ይሰጣሉ ብዮ ጠብቄ ነበር። በየመገናኛ ብዙሃኑ የኦነግን ነገር ለክልሉ መንግስት የተተወ የሚመስል አካሄድም አግባብ አይመስለኝም። ከየትኛውም ድርጅት ጋር የሚደረጉ እና የአገርን ልዑአላዊነት እና ጸጥታ የሚመለከቱ ጉዳዩች መያዝ ያለባቸው በፌደራል መግስቱ በኩል ነው።
ሦስተኛው የመሳሪያ ዝውውርን በተመለከተ ከየትኛውም ክልል በከፋ ሁኔታ መሳሪያ በአደባባይ ሰንቀሳቀስ እና ሲዘዋወር የሚታየው በአማራ ክልል ነው። ይህንንም በተመለከተ መግስት ጥብቅ የሆነ እርማጃ ለመውሰድ የሚያስችል ዝርዝር የመፍትሔ ሃሳብ ያቀርባሉ ብዮ ጠብቄ ነበር። ነገሩ ከኮንትሮባንድ ንግድ በላይ እና አሳሳቢ ደረጃም ላይ እየደረሰ ያለ ስለመሆኑ ብዙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያ እና ተደረጉ ያሏቸው የእስረኞች አያያዝ ሁኔታ እጅግ የሚያስመሰግን እና ሊደገፍ የሚገባው የመንግስት ትልቅ የመሻሻል እርምጃ ስለሆነ እሱን ሳልጠቅስ ማለፍ አልወድም።
በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic