>
5:16 pm - Sunday May 23, 3976

አንድ ጊዜ ቀኝ እጃችሁን ወደፊት ዘርጉና ተመልከቱልኝ! (ግርማ በላይ)

አንድ ጊዜ ቀኝ እጃችሁን ወደፊት ዘርጉና ተመልከቱልኝ!

ግርማ በላይ

 

የግራችሁንም ይሁን የቀኛችሁን ግዴለኝም፡፡ ብቻ አንዱን እጃችሁን ዘርጉና ለአፍታ ተመልከቱልኝ፡፡ አምስቱም ጣቶቻችሁ መኖራቸውን ደግሞ አረጋግጡ፡፡ የአካል ጉድለት ያለበትና ከጣቶቹ አንዱ ወይም የተወሰኑት ቀድሞውን የጎደሉበት ሰው የምናገረውን ተምሣሌታዊ  ንጽጽር በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ ሙሉ ጣቶች ያሏችሁ ግን የምነግራችሁን ንጽጽር የምታደርጉት በምናብ ነው፡፡

ከጣቶቻችሁ መካከል አውራ ጣታችሁን ወይም ትንሽዋን ጣታችሁን ወይም የቀለበት ጣታችሁን ወይም መሀል ጣታችሁን ወይም አመልካች ጣታችሁን በሃሳብ ደረጃ አጉድሉና ተመልከቱ፡፡ አንዱ ሲጎድል የሌሎቹ ውበት ምን ያህል እንደሚደበዝዝ አስተውሉ፡፡ ትንሹም፣ ትልቁም፣ አጭሩም፣ ረጅሙም፣ ወፍራሙም፣ ቀጭኑም በጋራ በሚሰጡት የልዩነት ኅብረት እጃችን ከማማሩም በተጨማሪ የተለያዩ ተግባራትን በአግባቡ ያከናውናል፡፡ አንዳቸው ቢጎድሉ ምናልባት አንዱን በሌላው ቦታ ለመተካት በሚደረግ የማሰልጠን ሂደት በተወሰነ ደረጃ ይተካኩ እንደሆነ እንጂ ተፈጥሯዊ ውበትና ፀጋቸው አይኖርም፡፡ የእግዚአብሔርም እንበለው የተፈጥሮ ህግና ሥርዓት በአመዛኙ እንደዚህ ነው – እንከን የለሽ የተቃርኖዎች ኅብረት፡፡

 የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥሪቱ ከተለያዩ ጎሣዎችና ነገዶች ነው፡፡ የውበታቸው ምንጭም ይህ ልዩነታቸው ነው፡፡ ይህን የኅብረ ቀለማት ውበት ለማስገኘት ሲባል በየትኛውም የዓለም ሀገር እንደተደረገውና እንደሚደረገውም ብዙዎች ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ጠላ ሲጠጣ፣ ዳቦ ሲገመጥ ደስ ይላል፡፡ ነገር ግን መብልና መጠጡን ወደዚያ ደረጃ ለማድረስ የተደረገውን ድካምና ልፋት፣ የፈሰሰውን ጉልበት ማሰብ ካልተቻለ የሰውን ውለታ ሜዳ ላይ መጣል ነው፡፡ የሀገራችን ሁኔታም እንደዚሁ ነው፡፡ የወቅቱ ፖለቲካዊ ቅኝት በአባቶችና በእናቶች ድካም የተገኘ ፀጋ ላይ የጠነባ የአስተሳሰብ ክምር በመቆለል ለዘመናት የተሠራውን የአብሮነት ሕይወት ማፍረስ ነው፡፡ የሚሊዮኖችን የተረጋጋ ሕይወት በመናጥ ወዳልነበሩበት የጥፋት ዘመን መመለስ፡፡

የዱሮ አባትና እናቶቻችን “አንተ አማራ፣ አንተ ኦሮሞ፣ አንተ ትግሬ፣ አንተ ጉራጌ፣ …” ሳይባባሉ ቆላ ደጋ ወጥተውና ወርደው ከውጭ ጠላትና ከውስጥ ሤረኛ ጋር ታግለው ደማቸውን በማፍሰስና አጥንታቸውን በመከስከስ ይህችን ውብ ሀገር ባያቆዩልን ኖሮ ይሄኔ ሰማንያው ብሔረሰብ ሰማንያ ሀገር መሥርቶ ሰማንያ ቁጫጭ መንግሥታት በወረሱን ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ዕድገትና ልማት ማየት የማይፈልጉ ኃይሎችና ብሔራዊ ኩራቷ ዕንቅልፍ የነሣቸው ወገኖች ሊያጠፏት ለዘመናት ቢማስኑም ፈጣሪዋ ያልተለያት ኢትዮጵያ ብትወድቅ እንደምትነሣ፣ ብትከሳ እንደምትወፍር በተደጋጋሚ በተግባር አስመስክራለች – አሁንም ያንኑ ሞቶ የመነሳት ነባር ልምዷን ባለመርሳት ትንሣኤዋን ልታበስር ከወደቀችበት ማንሠራራት ጀምራለች – “ጀምራለች” ነው ያልኩት – “ሀ” ሳይባል “ሁ” አይባልም –  “የአንድ ሽህ ማይል ርቀት”ም “በአንድ እርምጃ ይጀመራል”ና፡፡ በብዙ ምሣሮች ስትጨቀጨቅና በብዙ መዶሻዎች ስትቀጠቀጥ የነበረችዋን ኢትዮጵያን የመሰለ አሳዛኝ ፍጡር ይቅርና ለበርካታ ዓመታት ወድቆ የነበረን አንድ መኪና እንኳን ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ብዙ እንደሚያለፋ ግልጽ ነው፡፡ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ቢመስልም የምናየው ተጨባጭ ሀገራዊ ሁኔታ የሚጠቁመውም ይህንኑ ነው፡፡

በፈጣሪ ረድኤትና በብዙ ወጣቶች የዘመናት ገድል ምክንያት ዋናው የሀገራችን ዘንዶ – ለሰማይ ለምድር አስፈሪ ይመስል የነበረው ሕወሓት የተባለ ጭራቅ – ተሰብስቦ በአንድ ቦታ ላይ ተቀምጧል፡፡ ይህን ያደረገው ማን እንደሆነ ያለማወቅ ብዥታ ያስከተለው ሌላ ብዥታ እንዳለ ደግሞ እየተረዳን ነው፡፡ ድልን በመከፋፈል ረገድ በተፈጠረ ችግር አንዳንድ ሞኞች “ተራው የኛ ነው” ከሚል ግብዝነት በመነሣት የሚሠሩትን አጥተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ አያ እንደልቡ ወያኔ እንኳን ሊያደርገው ያልደፈረውን በአዲስ አበባ ውስጥ ሥራ ለመቀጠር አመልካቹ  “እንዲህ ያለ ቋንቋ ማንበብና መጻፍ ይኖርበታል” የሚል አስገዳጅ መሥፈርት ማስቀመጥ እንደተጀመረ እየሰማን ነው – በዚህ ዘመን ጆሮ የማይሰማው፣ ዐይንም የማያየው የለም፡፡ “መቼ መጣሽ ሙሽራ፣ መቼ ቆረጠምሽ ሽምብራ” እንዲሉ ወያኔ በጥይት የተባረረና ያንንም ጥይት እነሱ የተኮሱት የመሰላቸው ገልቱዎች ከታሪክና ከራሱ ከወያኔ ባለመማርና ለመማርም አእምሯዊና ኅሊናዊ አቅም በማጣት የሚሠሩትን ሥራ ስንመለከት “ወይ ሰው መሆን ከንቱ!” እያልን መደመማችን አልቀረም፡፡ የብልጠትንና የሞኝነትን፣ የትግስትንና የፍርሀትን ድንበር ለማወቅ እስኪቸግረን ድረስ ብዙ ነገር እያየንና እየተገረምንም እንገኛለን፡፡ መጥራቱ ግን እርግጥ ነው፡፡

በሌላም በኩል የፖለቲካ አዛውንት አሁንም የፖለቲካ መድረኩን ተቆጣጥረው ባረጀ ባፈጀ ባህላዊ አካሄድ የዚህችን ድንቅ ሀገር የወደፊት ዕጣ ፋንታ እንወስን ብለው ሲወራጩ ማየት አንዱ አስገራሚ ነገር ሆኗል፡፡ ሀገራችን ብዙ ሰው እያላት ምንም እንደሌላት ቆጥረው የሰማንያዎችና የዘጠናዎች ዕድሜ ትውልድ ሊያውም አንዲት ጣት የተቆረጠችበትን የፖለቲካ እጅ (መድረክ) ሲያንቀራብጡ ማየት ማሳዛኑ በታሳቢነት ተይዞ ማሳቁ በሚያደላ ሁኔታ ፈገግታን እያጫረ እያዝናናን ይገኛል – ጋኖች ያለቁ በሚመስሉባት ሀገር ምንቸቶች ጋን እየሆኑ ትያትሩ ቀጥሏል – “ቀጥ ያለ ሲጠፋ ይመለመላል ጎባጣ” ይባል ነበር ዱሮ – አሁን አሁን መልማዩም እንደተመልማዩ ጠፋ እንጂ፡፡

ከደነቆሩ አይቀር እንግዲህ እንደዚህ ነው፤ ዕድሜ የማያለዝበው የሥልጣን ጥም፣ ዕድሜ የማይበግረው ዝነኝነትን የመሻት ልክፍት፣ በዕድሜ የማይረግብ የግትርነትና የትዕቢት አባዜ፡፡ ጉድጓዱ በተማሰበትና ልጡ በተራሰበት የመጨረሻ የዕድሜ ጫፍ ቢገኙም ከዚያች ዘውዳዊ የራስ ቁር ፍቅር ላለመፋታት የቆረጡት እነዚህ ጎምቱዎች የዛሬ 30 እና 40 ዓመታት የተጠናወታቸው የሥልጣን አራራና የስመጥርነት ፍቅር አሁንም ያነሆልላቸው ይዟል፡፡ ዶ/ር አቢይም አላቻ ጋብቻ መሥርቶ ከነዚህ ያረጡ ሰዎች – ከነዚህ ዲሞክራሲ ሲያልፍ ከማይነካቸው አእሩግ ምን ሊያገኝ እንደፈለገ ግልጽ ሊሆንልን አልቻለም – በተለይ ከነዚህ የሥልጣን ሱሰኞች አንዱ “ሊ/መንበር፣ ሰብሳቢ፣ፕሬዝደንት” በሚሉ የድርጅት ሹመቶች ላይ ተጎልቶ አረጀባቸው፡፡ … እነሱ ባያፍሩና አለማፈርንም ከወያኔ ወንድማቸው ቢወርሱ አቢይ እንዴት ከዚያ የተሻለ አሠራር አጣ? በውክልና ደረጃስ ቢሆን የጊዜው ወረርሽኝ ሆኖ ሕዝብ በነገድ ከተወከለ ዘንዳ አማራው ሳይወከል እንደዚህ ያለ “ፌዴራላዊ” ጉዳይ እንዴት ይታሰባል? የሚመጥነኝ አባባል ሆኖ አላገኘሁትም እንጂ “አማራን መናቅ ያዋጣል?” ብዬ መጠየቅ አሰኝቶኝ ነበር፡፡ ለነገሩ ከዚህ ሸፋፋ ሂደት አማራ የሚያጣውም የሚያገኘውም የለም፡፡

የበቀደሙን የተፎካካሪዎች ስብሰባ እንደተከታተልነው ብዙ ያናግራል – እንደሰውና እንደዜጋም፡፡ አማራ በአማራነቱ እንዳልተወከለ አይተናል፤ መድረኩ በምን ስሜት እንደተዋጠ ታዝበናል፡፡ በሌላ በኩልም በዚህ ዘመን አማራ እንደማይወከል ካለማወቅ በመነጨ ብዙዎች በቁጭት ሲናደዱ አስተውለናል፡፡ ሁሉም ዘመን የራሱ አሻራ አለው፡፡ ይህ ዘመን የአፈንጋጮች እንጂ የመደበኞች አይደለም፡፡ አፈንጋጭ ቦታውን በያዘበት ሁኔታ “እኔ አልተወከልኩም” ወይም “የኔ ጎሣ አልተወከለም” ብሎ መናደድ ንዴትን ከማባከን ባለፈ “ራሷ ሄዳ ጣፊያ የከለከሏት ምላስ ሰምበር ላኩልኝ አለች” እንደሚባለው መሆን ነው፡፡ ዘመንንና የዘመንን ቅኝት መረዳት ከዚህ ዓይነቱ የማይረባ ንዴት ይታደጋል፡፡ ቻይኖች የእንጨት፣ የብረት፣ የቆርቆሮ፣ የብር፣ የወርቅ፣ የአልማዝ፣… ዘመን አላቸው – በያመቱ የሚያከብሩት፡፡ የኛ የአሁኑ የቡቃያ ዘመን ይመስለኛል – ያለፈው የወያኔው ዘመን ደግሞ የሲዖል ትል ዘመን እንደነበር ብገምት አልተሳሳትኩም፡፡(ቡቃያ ጥንቃቄን ይጠይቃል – በእንጭጩ ሊደርቅ ወይም አድጎ ሊያፈራ -ባግባቡም ላያፈራ – ይችላል፡፡)

ከዶ/ር አቢይ በስተቀር በዚያ ስብሰባ ላይ የተገኙት አብዛኞቹ – ይህ ግምቴ ምናልባት በላንቲካነት እንደገባ የተነገረለትን አንድ ወጣት መሳይ ሽማግሌ (ወመሽ) ላይጨምር ይችላል – ፀረ አማሮች እንደሆኑ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል – የትግላቸው የተጻፈም ይሁን ያልተጻፈ ማዕከላዊ ዓላማ ፀረ-አማራነት ነው – መነሻና መድረሻቸው በአማራ መቃብር ላይ የተከፋፈለች ኢትዮጵያን መሥርቶ ዘመነ መሣፍንትን በተለዬ ገጽታው መመለስና የየጎራው አፄ መሆን፡፡ እናም ከነዚህ የአስተሳሰብ ድውያን ምንም ነገር አይጠበቅም፡፡ ሀገራችን አርጅታ አርጅታ በመጨረሻዋ ስታርጥ የወለደቻቸውን እነዚህን ጉዶች ከማየት የበለጠ መጥፎ ነገር ባይኖርም ሀገር እንዳረጀችና እንዳረጠች አትቀርምና በቅርቡ አመዛዛኝ ኅሊናና ሁለገብ ዕውቀት ያላቸው ምርጥ ዜጎች ወደ ኃላፊነት ቦታዎች እንደሚመጡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እነዚህ ግን እንድንማርባቸው ፈጣሪ የላካቸው ከቀን ጅቦቹ እምብዝም የማይሻሉ ናቸው፡፡ ከአሁኑ የሀገራችንን ውሱን ሀብት በየሆቴሉ የሚጨርሱ የሆድና የሥልጣን ፍቅር ያናወዛቸው ናቸው፡፡ ለምን እንደባበቃለን? ይሉኝታስ ምን ይሠራል? ከወያኔ የሚሻሉት ሥልጣን አለመያዛቸውና በዚያም ሥልጣን እንደፈለጉ አለመሆናቸው ብቻ ነው፡፡ ከሌሎች ወንድምና እህቶቹ ጋር በመተባበር አገር ባቀና በባለጊዜዎች የሚጨፈጨፈው አማራ “ሲያዩት ያላማረ ሲበሉት ያቅራል” የሚለው ወዶ አይደለም፡፡

አማራ የሚባል ሕዝብ ራሱን ችሎ ሊኖር አለመቻሉ ለብዙ ችግር ዳርጎታል፡፡ አማራ በሁሉም ውስጥ ገብቶ ስለቀለጠና የአማራዊነት ሥነ ልቦናም ባለማዳበሩ፣ በሚደርስበት ግፍና በደል ሳቢያ አሁን አሁን “የአማራነት ስሜትን ማዳበር ጀምሯል” ከተባለም ያ ስሜት እያቆጠቆጠ የመጣው ገና በቅርብ በመሆኑ ይህን ሕዝብ “የኔ ነው” የሚለው እንደሕወሓት ወይም እንደኦህዴድ ያለ ወገን አልነበረም – የነበረከትን ጥፍጥፍ ብአዴን ትተነው፡፡ በዚያም ምክንያት ማንም ቀን የሰጠው ወሮበላ ሁሉ እየተነሣ እንደባብ አናት አናቱን ሲቀጠቅጠው ኖሯል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ታሪክ ይቀየራል፡፡ ኢትዮጵያም ከወደቀችበት ትነሳለች፡፡ ከሁሉም ነገድ የሚወለዱ ነብሮችና አንበሦች የጊንጦችንና የሸለምጥማጦችን፣ የእስስቶችንና የፍልፈሎችን እግርና ራስ ይቀጠቅጣሉ፡፡ የተሸሸገው ደራጎንም አንገቱ ተቆርጦ የሚጣልበት፣ በመያዣነት የያዛቸው ነፍሳትም ከእስር የሚለቀቁበት ጊዜ ቀርቧል፡፡ ቤተ እምነቶችም የሚፀዱበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፤ እነሱም ተፊዞባቸዋል፤ መሠሪ እረኞች በበጎች ላይ ቀልደዋል፤ በተኩላም አስበልተዋል፡፡ ብዙ አየን፤ ብዙ ታዘብን፡፡

ወደፊታችን ግን በፖለቲካው ረገድ ባጭር ታጥቀው ቀን ከሌት ለሕዝቸው የሚፋትሩ ሀገር ወዳድ መሪዎችና በሃይማኖቱም ለሁለት መንግሥት የማያድሩ ብፁዓን አባቶችና ወንድሞች ይላኩልናል፡፡ ይህ ፉርሽካ ጊዜ ማለፉ የውዴታ ሳይሆን የግዴታ ነው፡፡  የሆኖ ሆኖ በርትተን መጸለይ ይገባናል፡፡ ድል ያለ መስዋዕትነት የለም፡፡ ምንም እንኳን ሌባና አጭበርባሪው በዝቶ ያለ ሥራ፣ ያለ ድካምና ያለ ላብ መክበር ፋሽን የሆነበት ጊዜ ላይ ብንገኝም ዘመናችን በወዝና በላብ የሚኖርበት እንጂ ተዓምራዊው ዘመነ ኅብስተ መና እንዳልሆነ መርሳት የለብንም፡፡

ውድ በአማራነታችሁ የምታምኑ ወገኖቼ! አደራ የምላችሁ ነገር ቢኖር አማራነትን ከኢትዮጵዊነት እንዳታስበልጡና ይህችን ሀገር ወደ ኋላ እንዳትጎትቷት፣ የነፃነት ዘመኗንም እንዳታዘገዩት ነው፡፡ በመሠረቱ የጨነቀ ባይጨንቀው አማራ የሚያምርበት በኢትዮጵያዊነቱ እንጂ በጎሣ መደራጀቱ አይደለም፡፡ የተጎዳ ተጎድቷል – ከአሁን በኋላ ግን ይህን አማራ አማራ የሚባል ነገር ላልተወሰነ ጊዜ እንደትግል ሥልት ከመጠቀም ውጪ በዘላቂነት ብታራምዱት ለሀገርም ለሕዝብም ጎጂ ነው፡፡ ማነስ ነው፤ መኮራመት ነው፡፡ ይህ የመጨማደድ አባዜ በሌሎች እንዳላማረ ታውቃላችሁ፡፡ ኢትዮጵያ ያለ አማራ አንድ ጣት የጎደለበት እጅ ናት፤ ኢትዮጵያ ያለ ኦሮሞ ሁለት ጣት የጎደለበት እጅ ናት፤ ኢትዮጵያ ያለ አፋር ሦስት ጣት የጎደለበት እጅ ናት… ተጠየቃዊ አካሄዱ በዚሁ ይቀጥላል፡፡ አንዱ ለሌላው ጌጡና መድኃኒቱ ነው፡፡ አንዱ ያለ ሌላው ጎደሎ ነው፡፡ የጂማው ቡና ያለ ጎጃሙ ጤፍ ባዶ ነው፡፡

እነዚህን ጉዶች ተዋቸው፤ አምላክ የክቶቹን እስኪልክልን እነሱ ይጃጃሉበት፤ የሀገሪቱን አንጡራ ሀብትም ይምነሽነሹበት፤ የቀራቸው ጊዜ አጭር ስለሆነ ይዘባነኑ፤ በምኞት እየራዡ ለዘመናት ምራቃቸውን ስለዋጡ አሁን በልቅምቃሚው ይዝናኑ፡፡ ሀብት ይተካል፤ የማይተካው የሰው ሕይወት ነው፡፡

በነገራችን ላይ ተሰብሳቢዎቹ አማራ ጠል መሆናቸውን ለመረዳት ይሄ ነው የሚባል ሰው ከአማራው ወገን አለማከተታቸው ራሱ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ በዚያም ላይ ከነዚያ ሰዎች መሀል ስለአማራ ክፉ ነገር የተናገሩ አሉ፤ በታሪክ መዝገብ ተቀምጦላቸዋል፡፡ ሕዝቡም ያውቀዋል፡፡ መልካም የከሃዲዎች ኅብረት! ግን ልብ እንበል – እየነጋ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ትንሽ ጨለማ አለች እንጂ ቁልቁለት ነው፡፡ ያቺ ጨለማ እንድትለዝብልን እንጸልይ፡፡

የሚታየኝን አንድ ማኅበረሰብኣዊ ክፍተት በግልጽነት ልናገር – ለጠላቶቻችን ጅራፍ ከሚያጋልጡን እንከኖቻችን አንዱ እርሱ ነውና፡፡ ወገኖቼ በተለይም ወጣቶች መጻሕፍትን እያነበብን ራሳችንን በዕውቀትና በግንዛቤ እናሳድግ – ሀብት ማካበት ላይ ብቻ ያተኮራችሁ ወጣቶች ትንሽ ሶበር በሉና ወደ ኅሊና ምግብ ቤቶችም ጎራ በሉ፡፡ ሥጋ ብቻውን ነጠላ ነው፤ ነፍስም አለች፤ ኅሊናም አለ፡፡ ለሥጋ ብቻ ስንራወጥ ኅሊናችንና ነፍሳችን በርሀብ አለንጋ ይገረፋሉ፡፡ አንጎልን በእልህና በበቀል ስሜት ሳይሆን በዕውቀትና በጥበብ እንሙላው፡፡ ማወቅ ኃይል ነው፤ የጦር መሣሪያን ለመተኮስ ምንም ዕውቀት አይጠይቅም፤ በሥልጣን ሰክሮ አንድን ዘር ለመጥላትና እያሳደዱ እንደዐይጥ ለመጨፍጨፍ ሰይጣንነትን እንጂ ዕውቀትንና ጥበብን አይጠይቅም፡፡ በሀብት አምሮት ደንዝዞ የሰውን ገንዘብና መሬት መቀማትና በአንድ አዳር መክበር ድፍረትንና አጃቢውን ድንቁርናን እንጂ ዕውቀትን አይጠይቅም፡፡ ስለዚህ ባዶ ጭንቅላት ይዘን መጪውን ወርቃማ የለውጥ ዘመን መቀበል ይከብደናልና ራሳችንን በዕውቀት ለማበልጸግ እንትጋ – እግዚአብሔር ከኢትዮጵያ ጋር ይሁን – ነውም፡፡

ለገምቢ አስተያየት – gb5214@gmail.com

Filed in: Amharic