>

በመካሄድ ላይ ያለውን ለውጥ ለምን እደግፋለሁ? (ፍሬነህ ደረጀ - አትላንታ)

በመካሄድ ላይ ያለውን ለውጥ ለምን እደግፋለሁ?

(የዶ/ር ዐቢይን መንግሥት ለምን እደግፋለሁ?)

ፍሬነህ ደረጀ (አትላንታ)

(ማስታወሻ፦ ይህንን ፅሁፍ የምፅፈው ከአገሩ ርቆ እንደሚኖር አንድ ዜጋ ከሩቅ ሆኜ ከሰማሁት፣ ከአየሁትና ከታዘብኩት፣ እንዲሁም ከአነበብኩት ብቻ ተነስቼ የደረስኩበት የግል ድምዳሜ መሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ።)

  በአገራችን ኢትዮጵያ ዶ/ር ዐቢይ ጠ/ሚኒስትር ከሆነበት ሰዐት አንስቶ ሁሉንም በሚያስደንቅ ፍጥነትና ቀልብን በሳበ መልኩ ያከናወናቸውን ተግባራት አይተናል። እስካሁንም እያየን ነው። ይህ ከግራም ከቀኝ ብዙ እየተባለበት ሥለሆነ በዚሁ እንተወው። የኔ ትኩረት በኦሮምያ ክልል የተነሣው የቄሮ የህዝባዊ እምቢተኝነትና የ’ቲም ለማ’ ግኑኝነት ላይ ይሆናል።

  በኦሮምያ ክልል የተቀሠቀሠው የቄሮ ህዝባዊ ዓመፅና ከፍተኛ ተጋድሎ በኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ ግፊት ፈጥሮ የዶ/ር ዐቢይን መንግሥት ወደ ስልጣን እንዳመጣው ይነገራል። ወይም የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት የቄሮ ከፍተኛ ትግልና መሥዋዕትነት ውጤት ነው ማለት ነው። የቄሮ ተጋድሎ በግልፅ የታየ ስለሆነ ለክርክርም አይቀርብም። ነገር ግን ያለ ‘መሪ ድርጅት’ የተነሣው የቄሮ አመጽ እንደተባለው ‘መሪ የሌለው ግን በደንብ የተናበበ’ ብቻ ከሆነ እንዴት ተሣካለት?  የትግሉስ አላማ ምን ነበር?ዶ/ር ዐብይስ እንዴት የቄሮን ይሁንታ አገኘ? ( አቶ ለማ መገርሣና ዶ/ር ዐቢይ ለኦሮሚያ ክልል እንደተመረጡ የአመጹን መርገብ ስናስታውስ፥ እንዲሁም በአንዳንድ ቦታዎች ቀጥሎ የነበረ ቢሆንም በዶ/ር ዐቢይ ተግሣፅ መቆሙን ስናስታውስ።) ዶ/ር ዐቢይስ ምን ተማምኖ ነው ከመጀመሪያ ቀን ንግግሩ ጀምሮ የኢትዮጵያን ሥም ከፍ ከፍ ያደረገው? (በአንዳንድ ተቃውሞ ሰልፎች ላይ ‘ኦሮምያ ኬኛ’ የሚል መፈክር ያስቷውሷል።)

  እዚህ ላይ በአለማችን ውስጥ የተካሄዱን የሠላማዊ ትግል ውጤቶችና ስኬቶቻቸውን/ ውድቀቶቻቸውን ማየት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ እንደ ዶ/ር ጂን ሻርፕ በጉዳዩ ላይ ከ 40 ዓመታት በላይ በቅርበት ያጠና፣ የተመራመረ እና በርካታ ፅሁፎችን ያዘጋጀ አናገኝም። (ከ1928-2018 ነፍሱን በገነት ያኑርልን) በ20ኛው ክፍለ ዘመንና በ21ኛው ክ/ዘ የተደረጉ ከአምባገነን ስርዐት የተደረጉ ሠላማዊ ትግሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የእርሱ አሻራ አለባቸው። በትግሉ ውስጥ ምንም ተሣትፎ ባይኖረውም( አንዳንዶቹን በአካል ቀርቦ በቅርብ ታዝቧል) የሱን ጽሁፎች እንደ የትግል መመሪያ በመጠቀም ውጤት አግኝተውበታል። ዝነኛውን ‘ከአምባገነን ስርዐት ወደ ዲሞክራሲ’ ጨምሮ በመጠቀም። (በአማርኛም ተተርጉሟል) በአጭሩ የዘመናዊው የሰላማዊ ትግል አባት፤ የሠላማዊ ትግል ማኪያቬሊ ተብሎ በተለያዩ ቡድኖች  የተጠራና በተለይ በዓለም ላይ ባሉ አምባገነኖች በጣም የተጠላ ምሁር ነበር።

  እንደ ዶ/ር ጂን ሻርፕ ገለፃ፦ ሰላማዊ ትግል ማለት( ከአምባገነን ስርዐት ለመላቀቅ የሚደረግ) አንድ ቅሬታ ወይም ተገፍቻለሁ ብሎ የሚያምን የህብረተሰብ ክፍል ይህንኑ መነሻ በማድረግ መልዕክቱን ወደ ሰፊው  ህዝብ፣ የተለያዩ የሰላማዊ የትግል ዘዴዎችን በመጠቀም፣ በማዳረስና ለህዝባዊ እንቢተኝነት በማነሣሣት ከአንባገነኑ ላይ የፖለቲካ ሥልጣኑን መንጠቅ ማለት ነው። ስለሆነም የተሳካ ትግል ለማድረግ ትግሉን የሚመራው አካል በሰላማዊ ትግል ብቻ የሚያምን(  ነን ቫዮለንት)፣ በደንብ የተደራጀ፣ የጠራ ስትራተጂ ያለው፣( ከውጤት በኋላ የሥልጣን ክፍተት እንዳይኖር የተዘጋጀ) መሆን ይኖርበታል።

  በኦሮሞ ክልል የተነሣውንን የቄሮ ትግል ስናይ ከላይ ከገለፅነው የተለየ ነገር አናይበትም። ትግሉን ወደተቃራኒው መንገድ ለመውሰድ የነበረው ግብግብ እንደ ተጠበቀ ሆኖ። በነገራችን ላይ የሰላማዊ እንቢተኝነት በአገራችን በተደጋጋሚ ተሞክሯል። አይሳካ እንጂ። በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ፣ የአላማ ፅናታቸውም ሆነ ድፍረታቸው ፈፅሞ የሚደነቅ ቢሆንም የአንባገነኑ ሰለባ ከመሆን አላመለጡም። የአለመሣካቱ ምሥጢር የተበታተነ እና በደንብ የተደራጀ መሪ ቡድን ያለመኖር ነው። የቄሮ ትግልም ከዚህ ተለይቶ አይታይም። የስኬቱ ሚስጢር፣ እንዲህ አይነት ትግል ህዝቡ መሀከል መሆንና በአካል መሣተፍን ስለሚጠይቅ፣ ከጀርባ ሆኖ የሚመራው ቡድን ነው። ካለው የቄሮ ይሁንታና ተደማጭነት ስናየው በቅርበት የምናገኘው ‘ቲም ለማ’ ነው። ስለሆነም ‘መሪ የሌለው ግን በደንብ የተናበበ ህዝባዊ እንቢተኝነት’ ሲሰሙት ቃሉ ደስ ቢልም በቀላሉ ተግባራዊ መሆን አይችልም። ባይሆን ከገዢው ፓርቲ መሀከል ወጥቶ፣ ህዝብ አንቀሣቅሶ፣ አንባገነን ስርዐትን ማፍረስ አዲስ ዘዴ ይመስላል።  ይህንኑ ተከትሎ የታወጀው ‘የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት ፕሮግራም’ የሚያሣየው የዚሁ አካል መሆኑን ነው።

  ‘ቲም ለማ’ በኦሮሚያ ብቻ አላቆመም በመቀጠልም ከ’እህት ድርጅቱ’ የሚተባበራቸውን በማካተት፣ ምናልባትም ሥልጣን ላሉት ዋስትና በመስጠት፣ በድርጅቱ ውስጥ አብዛኛውን ድምፅ በማግኘት አጥፊውን ስርዐት ላይመለስ ሸኝቶታል። ለዚያውም በተደጋጋሚ የተጋረጡበትን ብዙ ደም አፋሣሽ ሊሆኑ የሚችሉ ትንኮሳዎችንና አደጋዎችን በዘዴ አልፎ።

  ጠ/ሚርነቱን ከያዘ በኋላ ያንን ሁሉ ግዙፍ ውሣኔዎች በፍጥነትና ያለእንከን ያከናወነበት ሚስጢር፤ በቡድኑ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ውስጥ ተቀምጦ ይጠባበቅ የነበረ መሆኑ አያጠራጥርም። ‘ቲም ለማ’ የህግ የበላይነት የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ለመመስረት የወሰነ፤ ይህንንም ለማስፈፀም ሰላማዊውን የትግል ዘዴ ወስዶ የተጠቀመ/ እስከአሁንም  እየተጠቀመ ያለ፤ በዚህም ያልተነገሩ ብዙ መሥዋዕትነት የከፈለ/ እየከፈለ ያለ፤ በደንብ የተደራጀ፤ ጥሩ ጥሩ ስትራተጂስት ያሉበት፤ ያለጥርጥር ደግሞ አገሩን አጥብቆ የሚወድ ነው። (ፍፁም ነው እያልኩ አይደለም) በአሁን ሰዓት እያንዳንዱ የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር እያንዳንዱ እርምጃ የሚያሣየን ከላይ የተገለፀውን ነው። ስለሆነም በአሁን ሰዓት ለአገራችን ከዚህ የተሻለ አስተዳደር የለንም (ወደ ፊት አይኖረንም ማለት አይደለም)።

  ይህ ከሆነ እኛ እንደዜጋ ምን ማድረግ እንችላለን? የማይፈለግ የትብብር ዐይነት የለምና፦ የመንግስት ሚ/ር መስሪያ ቤቶችና አገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤቶችን ስራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩና ግልፅነት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ይሄ በትግል፤ በስብሰባ (ግምገማ)፤ ወይም በተደጋጋሚ ስልጠና አይሣካም። የእያንዳንዱን ሠራተኛ የእያንዳንዱን ባለጉዳይ የእያንዳንዱን ዜጋ ትብብር ይጠይቃል። በተለይ ቢሮክራሲው የተቀኘው በፊውዳል አስተሣሰብ (የጌታና ሎሌ) በመሆኑና ላለንበት ክ/ዘመን በፍፁም የማይመጥን ስለሆነ መቀየር አለበት። ይሄንን ማነቆ የሆነ አሰራር መቀየር የሚቻለው አንድ ላይ በመተባበር ነው። በመንግስት ውሳኔ ብቻ የሚለወጥ አይነት አይደለም። የመንግስት ድርሻ የሚሆነው ለተገቢው የህብረተሰብ ጥያቄ ተገቢውን መልስ  መስጠቱን ብቻ ነው (ግልፅነት)። አሰራራቸውን መከታተሉ እንደተጠበቀ ሆኖ። ይሄ ግን ያለ ብዙሀኑ ተሣትፎ አስቸጋሪ ነው።

  ከላይ የተጠቀሰው በአገር ውስጥ ላሉት ሲሆን እኛ ከውጭ የምንኖር ደግሞ ማድረግ ያለብን፦ አገር ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ አቅም ያለው ኢንቨስት ማድረጉ፤ እውቀት ያለው እውቀቱን መጠቀሙ፤ ጠ/ሚሩ ለጉብኝት ሲመጣ በድምቀት መቀበሉ፤ እንደተጠበቀ ሆኖ ‘ይህንንም ሳትተዉ ያንንም አድርጉ’ እንዲል መጽሐፉ፤ አገሪቱን ለማልማት በእጅጉ ይረዳል ተብሎ ታምኖበት በተከፈተበት ‘የትረስት ፈንድ’ ውስጥ የበኩላችንን ማድረግ ይገባናል። ይሄ ለአገር የሚደረግ የውዴታ ‘ግዴታ’ ጥሪ ነው። እዚህ ላይ ጎልቶ መታየት ያለበት የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት አይደለም። የትረስት ፈንዱ አባላት ማንነትም አይደለም። (እኛ ኢ/ያን ተጠራጣሪዎች ስለሆንን) ጎልቶ መታየት ያለበት አገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ ነው። መጪውን የአድዋ ድል ስናስብና እያጣጣምን ያለውን ነፃነት የተከፈለበትን መስዋዕትነት ስንዘክር ማስታወስ ያለብን አገራችን ዳግም ፈተና ውስጥ መሆኗን ነው። እያልኩ ያለሁት የተከማቸውን የዕዳ ቁልል ነው። ይሄ ብሄራዊ አደጋ ነው። ድሮ ‘ብድር ተሰረዘ’ እንደሚባለው አይደለም። እንደ አባ/እማዎቻችን ቀና ብለን ለመሄድ ያለን ይሄ አንድ ዕድል ነው። እንጠቀምበት። ‘ሌሎች’ ያዋጣሉ እኔን አይመለከትም አንበል። የእያንዳችን ሰርቶ የሚገባ ሁሉ ግዴታ ነው። እኔ ምን አገኝበታለሁ አንበል፤ በተለይ በተለይ ቆይ ነገ አንበል። የአገራችንን የወደፊት ዕድል ራሳችን እንወስን (አበዳሪዎች ከመወሰናቸው በፊት፤ ምንም እንኳን አሁንም እየወሰኑልን ቢሆንም የከፋ ነገር በይፋ ሳይመጣ)። በብድር የተማረረ ነው እንዳትሉኝ¡ ለየትም አገልግሎት ቢውል ውጤቱ አንድ ነው። በመደምደምያው ለአገር የሚደረግ ነገር ሁሉ ክብር አለው። ቸር እንሰንብት።

ፍሬነህ ደረጀ (አትላንታ)

(ምስጋና፦ ለብራና.ካም የአማርኛ ፅሁፍ ለመተየብ ያስቻለኝን)    

Filed in: Amharic