>

ይድረስ ለትግራይ ልጆች!!! (ሳምሶን ጌታቸው)

ይድረስ ለትግራይ ልጆች!!!
ሳምሶን ጌታቸው
*አማሮችና ትግራዮች እንዲታረቁ፤ ጠ/ሚ ዓብይ ከኤርትራ ጋር እርቅ ያወረዱበትን መንገድ ብንከተልስ?!?
ውድ የትግራይ ሰዎች ከአማራ ክልል ጋር የገባችሁበትን ፍፁም አላስፈላጊ ኩርፊያና ፍጥጫ ከዚህ በላይ ሥር ሳይሰድ በቶሎ መቋጨት ያለበት አይመስላችሁም? “አዎ” ካላችሁ ከማንም በላይ ቀላሉ መፍትሔ ያለው በእጃችሁ ነው። በሁለታችሁ መካከል የተፈጠረውን አሳዛኝ ፍጥጫ ማንም ለሀገሩ ቅን አሳቢ የሆነ ሁሉ ሳያሳስበው አይቀርም። ችግሩ፣ አንድ ሰው ላስታርቅ ብሎ ቢነሳ አንድ ከባድ ቅድመ ሁኔታ ከአማሮቹ በኩል ከፊቱ መጋረጡ የማይቀር ጉዳይ መሆኑ ነው። በቅድሚያ በህወሓት የፖለቲካ ውሳኔ የተወሰዱብን መሬቶቻችንን ወደነበሩበት ይመለሱ የሚል። ይኼ እናንተንም አይጠፋችሁም።
ይኼን ነጥብ ነው እንግዲህ በእጃችሁ ያለውና በእናንተ በኩል የሕሊና ሚዛን ላይ እንድታስቀምጡ የሚጠበቅባችሁ። ከእልህ እና ከማያዛልቅ የፖለቲካ ብሽሽቅ ወጣ ብላችሁ፣ ዘላቂ ትርፍና ኪሳራን ማስላት አለባችሁ። ህወሓት ይከተለው በነበረው የጎሰኝነትና የአንበርካኪነት ፖለቲካ የተነሳ፣ ራሱንም የትግራይ ሕዝብንም ይዞ ከቀረው የሀገራችን ሕዝብ ጋር በጅምላ ከባድ ቅያሜ ውስጥ ገብቷል። በተለይ ደግሞ ትግራይን ከአማራ ሕዝብ ጋር የሁለት ጠላት ሀገራት ስሜት እስኪፈጠር ድረስ በትግራይ ስም ተከልሎ ብዙ ጥፋቶችን አድርሷል። በዚህም በአማራ ሕዝብ ላይ ፖለቲካዊ ውንብድናዎችና ኢኮኖሚያዊ ድቀቶችን፣ ሰብአዊ ውድመቶችንና ስነልቦናዊ ኪሳራዎችን እንዲደርስበት ጥሯል፣ አድርጓል።
አሁን ያ ሁሉ አልፏል። ህወሓት ጊዜያዊ የሰዎች ስብስብ ናትና በጊዜዋ አብቅቶላታል። ጠባሳው ግን ሊሽር አልቻለም። ቢሆንም በፓርቲው የተነሳ የተፈጸመው ጥፋት፣ ሕዝባዊ መልክ ይዞ ወደ ቀጣይ ትውልድ ከመተላለፉ በፊት፣ ቂምና ኩርፊያው ይበልጥ ስር ሰዶ፣ ብዙ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኪሳራዎች ሳይከሰቱ፣ በአላስፈላጊ መጠባበቅና ማድፈጥ ምክንያት ብዙ ዕድሎች ሳያመልጡ፣ ችግሩ ቶሎ መልክ ቢይዝ ለሁለቱም ክልሎች ብሎም ለሀገር ይበጃል። የትግራይ እና የአማራ ሕዝብ የደም ወንድማማችነቱም በጥሩ መንፈስ ወደፊት መቀጠል አለበት። ስለዚህ ብዙ ኪሳራ የማያደርስ፣ ገንዘብ የማይጠይቅ፣ ደም የማያፋስስ፣ #ቅን_ልብ ብቻ የሚጠይቅ አንድ ሀሳብ አለ።
በእርግጥ የትግራይ ሰዎች በወያኔዎች ለተፈፀሙ ጥፋቶች እናንተ እንደ ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅም ሆነ ኃላፊነት መውሰድ አይጠበቅባችሁም። ነገር ግን ፓርቲዋ ከትግራይ እንደመውጣቷ፣ ጥፋቶቿን ሁሉ ከሕዝቡ ጋር የተሳሰረ ለማስመሰል ስትጥር እንደመኖሯ፣ ‘ያሳደጉት በሬ ቢወጋ ሰው፣ ባለቤቱ ይዋሰው’ ነውና፣ ስለ ፍቅር ብላችሁ ለምን ከአማራ ሕዝብ ጋር ለመታረቅ ተነሳሽነቱን ወስዳችሁ፣ እጃችሁን ቀድማችሁ አትዘረጉም? ዋነኛው የወቅቱ ያለመግባባት ችግር የሆነው የወሰን ጉዳይ ነው። ውዝግብ ያስነሱት የአስተዳደር ወሰኖች በየትኛውም ክ/ሀገር ስር ቢሆኑ ችግር አይኖረውም ነበር። ግን የወሰን አከላለል የሽንፈትና የድል ምልክት ጭምር እንዲሆኑ አድርገው የቃኙት የእናንተው ህወሓቶች ናቸው። ስለዚህ የአስተዳደር ወሰኖቹ የተላበሱትን አላስፈላጊ ፖለቲካዊ ትርጉም ለማርከስ ዋናው ዕድል ያለው በእናንተ እጅ ነው። ህወሓቶች የራሳቸውን ሒሳብ ራሳቸው ያወራርዱ። እናንተ በሕዝብነት የሚጠበቅባችሁን የሠላም እና የእርቅ ርምጃ ከተራመዳችሁ፣ የይቅርታውና የእርቁ ፍሬ ለእነሱም መትረፍረፉ አይቀርምና አስቡበት።
ለምሳሌ በቀላሉ የጠ/ሚ ዓብይን ዘዴ ተመልከቱ። ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዴት አድርገው ከኤርትራ ጋር እርቀ ሠላም እንዳወረዱ አስተውሉ። ጠ/ሚ ዓብይ ለኤርትራውያኖቹ አይደለም ባድመ አዲሳባም፣ ቦረናም፣ አዋሳም፣ ጅማም የእናንተ ናቸው አሏቸው። እነሱ ደግሞ በምላሹ ኧረ አሰብም፣ ምፅዋም፣ አሥመራም የእናንተ የወንድሞቻችን ኢትዮጵያውያን ናቸው አሉ። ስለዚህ እናንተም ለአሰራርም ሆነ ለፖለቲካ በሚያመች መልኩ ተነጋግራችሁ፣ አሁን የሚያወዛግቡት የአስተዳደር ወሰኖች ቀርቶ ለምን መቀሌም፣ አክሱምም፣ አድዋም፣ ተንቤንም፣ ሽረም፣ አዲግራትም ወዘተ ኧረ እንደውም ራሷ ትግራይ በሙሉ የአማራ እና የኢትዮጵያ መሆናቸውን አታውጁም? ያኔ የጎንደሮችን፣ የጎጃሞችን፣ የወሎዬዎችን የፍቅር ምላሽ ታዩታላችሁ። ያኔ እንኳን መንገድ ሊዘጋባችሁ፣ እንኳን በጠላትነት ልትታዩ ይቅርና “ኧረ ደሴም፣ ወልድያም፣ ጎንደርም፣ ባሕርዳርም ወዘተ የእናንተ የወንድሞቻችን ናቸው፣ እኛ ድሮም እልህ ነው እንጂ ወንድሞቻችን ናችሁ” ብለው አማሮቹ በእጥፍ ድርብ የሠላምና የፍቅር ምላሽ ሲያቅፏችሁ ታያላችሁ። እንኳን እናንተን ያ ሁሉ ስድብ፣ የጥላቻ ንግግሮችን አስተላልፈውና አንፈልግም ብለው የሄዱትን ኤርትራውያንን እንዴት በፍቅር እንደተቀበሏቸው አይታችኋል። ሕዝብ ቂም አይዝማ።
ጠ/ሚ ዓብይ ለማንም አይመለሱም የተባሉትን ሻዕቢያዎች፣ በቃ እናንተ እንዳላችሁ በማለታቸው ምን ከሰሩ? ምን ተዋረዱ? ከሀገራቱ አልፎ በአለም የተደነቀ ተግባር ሆኖ በስማቸው ተመዘገበላቸው እንጂ። አስቸጋሪ ናቸው ተብለው በአለም ሳይቀር የተፈረጁትን ኢሳይያስ አፈወርቂን ሳይቀር በይቅርታ እና ሁሉን እሺ በማለት በፍቅር አንበረከኳቸው። ስለአከራካሪዎቹ የባድመና ሌሎች የድንበር ጉዳዮች ተረስቶ የዕርቁ መንፈስ ጭራሽ ወደ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ሊያመራ የሚችል መልክ ይዞ ተገኘ። እናንተም ከዚህ ምሳሌ ተማሩ። በማይረባ እልህ የሀገራችሁ ባለ ሙሉ መብት ባለቤትነታችሁን አሳልፋችሁ አትስጡ። ኤርትራዎች ከእናንተ የበለጠ ለአማሮችም ሆነ ለኢትዮጵያ ሊቀርቡ አይችሉም። እየሆነ ያለውን ግን ተመልከቱ። ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል የሚለውን ሀሳብ ይዘት መዝኑ። በፖለቲካ ጉዳይ እልህ በፍፁም ከእውነታ በላይ ሊመዝን አይገባምና ንቁ።
ውድ የትግራይ ሰዎች የተወሰኑ እምቡር እምቡር የሚሉ፣ ጀግንነት በጦርነት ብቻ እንደሚለካ የሚያምኑ፣ በየሚዲያው ጦር የሚሰብቁ ጎረምሶቻችሁ፤ ከጥፋት፣ ከኪሳራ እና ከማያባራ ውድቀት ሌላ ለእናንተም ሆነ ለሀገራችን ምንም ትርፍ አያመጡልንም። እነሱን ተዉ በሏቸው።  ዘመኑም ያን አይፈቅድምና አትስሟቸው። ይልቅ ትንሽ ዝቅ ብሎ ብዙ ከፍ ማለት እንደሚቻል አስታውሱ። ነገ ዛሬ ሳትሉ፣ ይቺን ሀሳብ ለአፈፃፀም በሚመች መንገድ አጎልብታችሁ ተጠቀሙባት። ጊዜው ካለፈበት የእንዋጋ ፉከራ ይቅርና ለእርቅ ለሠላም እጃችሁን ዘርጉ። ልክ እንደ እናንተው ሐይማኖተኛውንና ደጉን የአማራ ሕዝብ ስነልቦና አስታውሱ። ለእርቀ ሠላም እጃችሁን ከዘረጋችሁ በምላሹ እጅግ አስደሳች ውጤት ታተርፋላችሁ። #ስህተቶች_የተጠነሰሱት ከእናንተ መንደር ነውና ተነሳሽነቱን እናንተ ውሰዱ። ትግራይና አማራ በድንበር፣ በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ ቢዋሃዱ ለሁለቱም አካባቢዎች ብሎም ለሀገራችን ላቅ ያለ ጥቅም አለውና በቅንነት ይታሰብበት። ስለ ሁሉም ፈጣሪ ይርዳን።
Filed in: Amharic