>
5:13 pm - Sunday April 20, 5975

“ክሱ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ውሸት መሆኑ ገብቶኛል!!!”  (አቶ አብዲ መሐመድ ኢሌ)

“ክሱ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ውሸት መሆኑ ገብቶኛል!!!” 

አቶ አብዲ መሐመድ ኢሌ

 

ፍርዱ አስረስ

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሐመድ የቀረበባቸው ክስ “የተቀነባበረ ውሸት ነው” አሉ። አቶ አብዲ ይህን ያሉት ጉዳያቸውን እየተመለከተ ላለው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት ነው።

ችሎቱ ለዛሬ ቀጠሮ ይዞ የነበረው አቶ አብዲን ጨምሮ በ47 ተጠርጣሪዎች ላይ የቀረበባቸውን ክስ በንባብ ለማሰማት ነበር። የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በይፋ ክስ የመሰረተው ባለፈው ረቡዕ ጥር 22 የነበረ ቢሆንም የተከሳሽ ጠበቆች በችሎት ባለመገኘታቸው የክስ ንባቡ ለዛሬ ተላልፏል። ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተከሳሾቹ በሐምሌ 2010 ዓ. ም. በሶማሌ ክልል 59 ሰዎች እንዲገደሉ እና 412 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት እንዲወድም አድርገዋል በሚል ነው ክሱን ያቀረበው።

በዛሬው የችሎት ውሎ ክሳቸውን ያደመጡት አቶ አብዲ ክሱን ተረድተውት እንደሆነ በመሐል ዳኛው ሲጠየቁ “ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ውሸት መሆኑ ገብቶኛል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የእርሳቸውን ምላሽ ተከትሎ ችሎቱን ሞልተው የነበሩ ታዳሚዎች በሹክሹክታ ሲጠያየቁ እንደነበር በስፍራው የተገኘው የጀርመን ራድዮ ዘጋቢ ታዝቧል። ፍርድ ቤቱ ከአቶ አብዲ ውጭ የሌሎችን ተከሳሾች ምላሽ ያላደመጠ ሲሆን ከክስ መቃወሚያ ጋር ደርቦ ለመስማት ለመጪው የካቲት 20 ቀጠሮ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎው የተከሳሽ ጠበቆች በክሱ ላይ ያቀረቡትን አቤቱታም አድምጧል። በክሱ ውስጥ የምስክሮች ዝርዝር አለመካተቱን ያነሱት የተከሳሽ ጠበቆች በተገቢው ሁኔታ “እንድንከላከል አያስችለንም” ሲሉ ተቃውመዋል። አቃቤ ህግ ምላሹን በጽህፈት ቤት በኩል እንዲያስገባ ያዘዘው ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለየካቲት 6 ቀጥሯል።

በዛሬው ችሎት አብዛኞቹ ተከሳሾች በአካል አለመቅረባቸውን ዘጋቢያችን ተመልክቷል። ፍርድ ቤቱ ባለፈው ሳምንት ባስቻለው ችሎት ፖሊስ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እንዲያውል የአምስት ቀናት ጊዜ ፈቅዶ ሰጥቶ ነበር። የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ለፖሊስ የደረሰው ከትላንት በስቲያ መሆኑን አቃቤ ህግ ዛሬ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። “ከቦታው ርቀት አንጻር በቂ ጊዜ ይሰጠን” ሲልም በዛሬው ችሎት አመልክቷል።

ምንጭ:- የጀርመን ድምፅ ራዲዮ

Filed in: Amharic