>
8:11 am - Tuesday August 9, 2022

ግብግብን ምን አመጣው ጁሃር? (ዳንኤል በቀለ)

ግብግብን ምን አመጣው ጁሃር?
ዳንኤል በቀለ
የአዲሳባ እጣ ፈንታ በሰላም፥ በድርድርና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈታ እፈልጋለሁ ለሚል እንደ ጁሃር አይነት ፖለቲከኛ፥ ጁሃር እራሱ በሚመራው ሚዲያ ቀርቦ የሰጠው አስተያየት ይህንን አቁዋሙን የማይንጸባርቅ ጠንከር ያለ የአቁዋም መግለጫ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ሙሉውን ቃለ መጠይቅ ከዚህ በታች መመልከት ትችላላችሁ። ቆንጽሎ ማቅረቡ ለጁሃርም፥ ለአድማጭም ፌር አይመስለኝም።
ሌላ ቃል ጠፍቶኝ ነው እንጂ ይህንን ውይይት ቃለ መጠይቅ ያልኩት፥ ይህንን ትእይንት interview/ቃለ መጠይቅ ማለት ይከብዳል።
ጋዜጠኛው ጁሃርን የመሰለ አንደበተ ርቱእ እና አስተዋይ ፖለቲከኛ ቻሌንጅ እያረገ ፥ ታዳሚዎቹን ሰለሚያወያይበት ርእስ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከማረግ ይልቅ ውይይቱን ሙሉ የጨረሰው በአሟሟቂነት ነው።
ጋዜጠኛው አለቃውን አያክብር ማለቴ አደለም። ጋዜጠኛ ግን ታማኝነቱ ለእውነትና ለታዳሚዎቹ መሆን አለበት።
ለዚህ አይነት ቃለ መጠይቅ ጥሩ ምሣሌ ካስፈለገ ከጥቂት አመታት በፊት የኢሳቱ ሲሳይ አጌና የግንቦት ሰባቱን መሪ ብርሃኑ ነጋ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ይመለከቷል።
 ኢሳት ለግንቦት ሰባት የቀረበ ድርጅት እንደሆነ ይታማል። ግንቦት ሰባትም ለኢሳት የገንዘብም ድጋፍ አንደሚያደርግ ይነገራል። ይህ ሁኔታ ግን ሲሳይ አጌና ብርሃኑ ነጋን በእያንዳዱ የፖለቲካ አቁዋማቸውና አስተያየታቸው ከመፈታተን አላገደውም።
ይህ የትልቅ ጋዜጠኝነት ማሰመሰከሪያ እድል አቶ ደጀኔን ትላንት አምልጡዋቸዋል። የጎዱትም ድርጅታቸውንና አለቃቸውን ይመስለኛል።
እኔ፥ ጁሃር በዚህ “ቃለ መጠይቅ” ላይ እንዳለው የቀድሞው የህወሐት ከንቲባ አቶ አረከበና ያሁኑ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ ለአዲሳባ ትልቅ ሥራ እንደሰሩ አምናለሁ።
 ምክትል ከንቲባው በከተማው የሚታየውን የተንዘራፋ ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ጥረትና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመክፈት ተፍ ተፍ ማለታቸውን አደንቃለሁ።
ብዙም ያዲሳባ ነዋሪም ፥ጋዜጠኛውና ጁሃር በይጠቅሱትም፥ በዚህ ሥራቸው ምክትል ከንቲባውን ያከብራቸዋል።
አቶ ታከለ ላይ የሚነሳው ተቃውሞ ከሶሰት ጉዳዮች ያጠነጠነነ ይመስለኛል።
አንደኛው ኦዲፒ/ኢሕአዴግ እሳቸውን ለመሾም ሲል የድሮ ሕገ ወጥ አሰራር ተጠቅሞ፥ የሸንጎ አባላትን እጅ ጠምዝዞ፥ ሕግ አስቀይሮ ፥ ለሳቸው መሾም ጥርጊያ መንገድ አዘጋጅቶ በማሾሙ ነው። የተሾሙት በድሮ አምባገናናዊ የመሪዎች አስተዳደር ስታየል ነው።
ጋዜጠኛው ይሄንን ለምን ሳተው?
ሁለተኛው ተቃውሞ ደግሞ አቶ ታከለ በተሾሙበት ወቅት የከተማው ንዋሪ አለመሆናቸው ነው።
ምክትል ከንቲባው ያዲሳባ  ተወላጅ (native) አደደሉምና ከንቲባ መሆን አይችሉም የሚሉ አንዳንድ መደዴዎች ቢኖሩም፥ ዋናው ተቃውሞ ግን ያዲሳባ ከንቲባ ያዲሳባ ነዋሪ (resident) መሆን አለበት ከሚል መርህ የተነሳ ነው።
ጋዜጠኛው ይሄን አላነሳም፥ ጁሃርም የተቃዋሚዎችን arguments አንድም ሳይነካ፥ እራሱ በምናቡ በፈጠረው የተቃዋሚዎች መከራከሪያ ነጥብ ላይ መልስ ሰጥቷል።
ሶሰተኛው ተቃውሞ ደሞ የከተማው ነዋሪ ላልሆኑ ዜጎች የከተማ ንዋሪነት ማስታወቂያ እየታደለ ነው የሚል ነው።
 በዚህ ርእስ ላይ ሸገር በቅርቡ አንድ ጥሩ ፕሮግራም መሥራቱን አውቃለሁ። ጋዜጠኛው እንዲህ አይነት ሥራዎችና ጥናቶች ላይ ተመርኩዞ እንግዳውን በመጠየቅ ፈንታ፥ አንዳንድ ተቃዋሚዎች፥ አማርኛ በደንብ ለማይናገሩ ሰዎች የከተማው አስተዳደር መታወቂያ እየሰጠ ነው የሚል ቅሬታ ያሰማሉ ስለዚህስ ምን ትላለለህ የሚል ‘ጥያቄ መሰል ማጣጣያ’ መጠቀምን መርጥዋል።
እንደዚህ አየተባለ ብዙ መዘርዘር ይቻላል። ጊዜ መፍጀት ሰለሆነ አንድ ሁለቱን ብቻ ለምሳሌ ላንሳ።
ካልተሳሳትኩ ጁሃር ያዲሳባ ጥያቄ ለ50 አመታት የኦሮሚያ ዋናው ጥያቄ ሆኖ  ቆይቷል ብሏል። ይሄ እውነት ነው?
 የኦሮሞ ሕዝብ ትልቁ ጥያቄዎች የመሬትና ራስን የማስተዳደር ጥያቄዎች እንደነበሩ ነው የማሰታውሰው። የመሬቱን ጥያቄ ደርግ በከፊል ሲመልሰው፥ ራስን በራስ ለማስተዳደሩ ደግሞ ሕዝቡ እስካሁን ሲታገል ቆይቷል።
ያዲሳባ ጥያቄ በልዩ ጥቅም ሰም የገባው የኦነግና ህወሐት ኮሚኒሰቶች ከኮሚኒስት ዮጎዝላቪያ ልምድ ወሰደው በሸረቡት አንቈቀጽ 49 ነው።
ይህ የኮሚኒስቶች ሕግ ለዮጎዝላቪያም አልበጀም ለኢትዮጵያም አይበጅም።
በዚህ ርእስ ላይ ከዚህ በፊት የሄድኩበት ሰለሆነ አልመለስበትም። ማንበብ ለሚፈልግ ሊንኩ ይሄው፥
በመጨረሻም ጁሃር አዲሳባ የተመሠረተችው የየካና ጉለሌ ሕዝቦችን በማጽዳትና በመጨረስ ነው ብሏል።
እንዲህ አይነት ውንጀላ በማሥረጃ ካልታገዘ ተራ ወሬ ሆኖ ነው የሚቀረው። የሚታመን ማሥረጃ የማቅረቡ ግዴታ የጁሃር ነው።
በዚሁ ይብቃኝ። ቸር ይግጠመን።
Filed in: Amharic