>
1:57 pm - Thursday December 8, 2022

የሜንጫ ዛቻ እና የዲሞክራሲያዊ ለውጥ ፍጥጫ! (ሀይለገብርኤል አያሌው)


የሜንጫ ዛቻ እና የዲሞክራሲያዊ ለውጥ ፍጥጫ!
ሀይለገብርኤል አያሌው
ሊገል የመጣ ጠላት ጌታ ቢሉት አይሰማም እንዲሉ: በበታችነት ደዌ የተጠቃ አንገት የመቅላት መፈክር ስር የዋለው ግዜ ያነሳው የአረቦች የጡት ልጅ የሆነው ጁሃር በበለጬ ምርቃና የሽብር አቋሙን አንጸባርቋል:: ይህ የጎረምሳው ድፕሎማሲ የጎደለው  ድንፉታ   ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን በየጫቱ መደብና በየዋርካው ስር ሲዶለት የቆየው ሴራ አካል ነው::
ጁሃርና ጭፍራው የአዲስ አበባ ሕዝብን በማሸበር የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ሊጭኑበት ከፖለቲካ ሴራ እስከ ሕዝብ ዲሞግራፊ ለውጥ በግልጽና በስውር እየተንቀሳቀሱ ነው:: የዶር አብይ አመራር ይህንን ደባ አውቆ በይሁንታ አልያም በፍራቻ አልፎት ካልሆነ በቀር መረጃው የለውም ማለት አይቻልም:: ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚያሳፍረው የሚያሳዝነው ማህበራዊ መሰረታቸውን የአዲስ አበባ ሕዝብን ያደረጉ የዜግነት ርዕዮት አራማጅ ተብዬ ድርጅቶች የከተማውን ሕዝብ  አጀንዳ ይዘው ሊሟገቱለት ሲገባ ፖልሲና  እቅድ ነድፈው ለመብቱ ሊቁሙ ሲችሉ ማፈግፈጋቸውና ምርኮኛ ይመስል መሽኮርመማቸው ትዝብት ላይ እንዲውቁ አድርጏቸዋል::
የአዲስ አበባ ሕዝብ የሚከራከርለት ተቋም አለመኖር የፈጠረው ክፍተት ዘመኑን በሙሉ ያለ እረፍት መራራውን የግፍ ጽው ሲጎነጭ የቆየው እስክንድር ዛሬም ሕዝብን ሲል የግንባር ስጋ ሆኗል:: ጉሮወሸባዬ የተዘፈነላቸው ወዶ ገቦች በዝምታቸው አፍረን ሳንጨርስ አርበኛችን እስኬውን ለመጎንተል ሲቃጡ አስተዋልን::
እስክንድር ወንድሜ ነው:: ለጨዋና ለሰላማዊ ፖለቲካዊ እይታው ፍርሃትና ይሉኝታ ሳይኖረው ሃሳቡን ለመግለጽ የሚደፍር  ጀግና ነው:: ሰሞኑን ስለ አዲስ አበባ በተናገረው አቋሙ ከያቅጣጫው ብዙ የአረፉ ፍላጻዎች ተወርውረውበታል:: ስለብዙዎቹ የስኒ ማዕበል ቀስቃሾች በሱ ዘንድ አይታወቁም:: እንኳን በመከኑ ቃላት በታንክ መትረየሱ ያልተረታ የጀግኖች ጀግና ነው:: እነሜንጫና እነበርጫ ለሱ የትንኝ ያህል የማይከብዱ ተራዎች ናቸው::
እስኬው በሃሳብ ሙግትና  በሰለጠነ ውይይት የሚያምን የሰላም ሰው ነው::  የደፈረ የሰለጠነ ታሪካዊ ፖለቲካዊና ሎጅካዊ ንድፈ ሃሳቦችን ይዞ ሊሞግተው ሊከራከር ሊያምን ወይ ሊያሳምን ከተሳሳተም ይቅርታ ለመጠየቅ ብርቱ ሞራል ያለው ዘመናዊ ሰው ነው::
ከእስኬው ጋር ባለፈው ሰሞን ለሰአታት በሃገራችን ፖለቲካ ዙሪያ ሰፋ ያል ውይይት እድርገን ነበር:: በዛም አጋጣሚ ላልተወሰነ ግዜ የሽግግሩ ሂደት መልክ  እስኪያገኝ ከጠባብ የኦሮሞ ፖለቲከኞች  ጋር ሊያነካኩ ከሚችሉ ርዕሶች ሚድያው ሊቆጠብ ቢችል  ጭር ሲል የማይወዱ መረሳት ውስጥ የወደቁ የሚመስላቸው የጁሃር ብጤ ጽንፈኞች ሚና አጥተው ተራማጁ ወገን የተሻለ ተደማጭ የመሆን እድል ያገኛል የሚል ሃሳብ  አካፍዬው ነበር:: እስኬው ሕዝብ የማወቅ መብት አለው በሚለው መርሁ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እስከሆነ ምንም ቢሆን መታለፍ የለበትም በሚል  ሃሳቡን አጋራኝ ::
የገመትኩት አልቀረም ይሄው ሃገር ምድሩን የሚያነጋግር አጀንዳ ተፈጠረ:: ከጠባብ የኦሮሞ ፖለቲካ አቀንቃኞች እየተላለፈ ያለው ፀብ አጫሪና ጦርነት ቀስቃሽ ቅስቀሳ የሕግ ስርዐቱ አቅመ ቢስ በመሆኑ ጎረምሶቹ ሊጠየቁ አልቻሉም:: እስክንድር በዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲሆን ያስቀመጠውን አቅጣጫ እነጃዋር በአመጽም ቢሆን እንደሚለውጡት ሲያቅራሩ ሰምትናል::
ይህ የተደበቀ የሴራ አላማ እንዲገለጥ ሕዝቡም ከወዲሁ እንዲያስብና እንዲዘጋጅ የእስክንድር ግልጽ አቋም እረድቷል:: የአዲስ አበባ ጉዳይ የአንድ ወይም የሌላ  ብሄር ችግር ሳይሆን መላው ኢትዮጵያውያንን የሚመለከት ጥብቅ ጉዳይ በመሆኑ የፌዴራል መንግስቱን ግልጽና ጠንካራ ውሳኔም ይፈልጋል:: የማንም ወጠጤ እየተነሳ የሚያደርገው ፋከራ ከድንፋታ ባያልፍም የመንግስትን አቅም ጥያቄ ላይ የሚጥልና የልማትና ኢንቨስትመንት እድሎችንም የሚያሳጣ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል::
በመላው ሕዝባችን ወደር የለሽ ተጋሎ የተገኘው ለውጥና አንጻራዊ ሰላም እንዳይደፍርስ ; በጋራ ለሰላማችን ዘብ እንቁም:: ትግሉ በሽብርና በሁከት ሳይሆን በዲሞክራስያዊ አግባብ እከሆነ ድረስ የሕዝብን ውሳኔ ለመቀበል ከተዘጋጀን ምንም ሊያጋጭ የሚችል ችግር አይኖርም:: ይህንን የሕዝብ መብት ተላልፎ ሻጋታና ተሸናፊ ሃሳቦችን በጉልበት አሳካለው የሚሉ ጮርዎች ሊመከሩ ይገባል:: አለያ ፍጻሚያቸው አያምርም:: ዲሞክራሲን መተግበር እንጂ ያቃተን ቃታ መሳብማ ለሺ ዘመን ኖረንበታል:: ከጋርዮሽ  አተሳሰብ ወጥተን እንደ 21 ክፍለ ዘመን ለመኖር እንሞክር::!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!
Filed in: Amharic