>

እስክንድር ታላቅ ነው!!! (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

እስክንድር ታላቅ ነው!!!
ሞሀመድ አሊ መሀመድ
እስክንድር ነጋን በቅርብ አውቀዋለሁ ብዬ አስባለሁ። በተለይ የፖርላማ አገልግሎት ተርሜን ጨርሼ የጥብቅና ፈቃዴን ተከልክዬ በነበረበት ወቅት አብዛኛው ውሎዬ እንደኔው ሥራ ካልነበረው እስክንድር ነጋ ጋር ነበር። ይሁንና እኔና እስክንድር የማንግባባባቸው ጉዳዮች የነበሩ ሲሆን ሌሎች ወዳጆቻችንም ባሉበት ዱላ ቀረሽ ክርክሮችን እናደርግ ነበር።  ያም ሆኖ; እስክንድር ጋር ብዙ ከመከራከር ብዙ መረጃና ግንዛቤ ማግኘት ይቻላል።
እስክንድር አዋቂ ነው። በመረጃ ይሞግትሃል። እሱን የመሞገት ብቃት ካለህ ያደንቅሃል; እንጅ ቂም አይዝም። በልዩነታችን ስንከራከርና ስንጯጯህ ቆይተን አብረን ምሣ እንበላለን። መለስ ብለን ማኪያቶአችንን እየጠጣን የሆድ የሆዳችንን እንጫወታለን። እስክንድር ሲበዛ ደግና ሩህሩህ ነው። የሰው ችግር የሚገባውና ያለውን ተካፍሎ መብላት የሚወድ ነው።
እንዲያምሆኖ እስክንድር እውነተኛ አርበኛ ነው። የህወሓት/ኢህአዴግን ሥርዓት በብርቱ የፈተነ ጀግና ነው። አገሩን የምር ይወዳል። እሱ እንደሌሎቹ አትላንቲክን አቋርጧ በመሄድ ከባህር ማዶ ሆኖ የሚጮህና በሌሎች እጅ የጋለ ብረት ልጨብጥ የሚል አጉል ብልጣብልጥ አይደለም። እስክንድር እዚሁ እሳቱ ላይ ተጥዶ አደጋውን የተጋፈጠና በዚያም ዋጋ የከፈለ ነው።
እስክንድር በዲያስፖራውና ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ያላሰለሰ ጩኸት; በኋላም በሀገር ውስጥ በተቀጣጠለው ህዝባዊ ትግል ከእስር ከተፈታ በኋላ ብዙዎች ትግሉን እንዲመራ ጠይቀውት ነበር። እሱ ግን የፖለቲካ ሥልጣን መያዝን ግብ አድርጌ ከምንቀሳቀስ ይልቅ በምወደውና በምታወቅበት የጋዜጠኝነት ሙያ ሀሳቤን የመግለፅና ለሌሎች ወገኖችም መረጃ የማድረስ ተልዕኮዬን ብወጣ ይሻለኛል በሚል የሚታትር ብርቱ ዜጋ ነው።
እስክንድር እንደዜጋ ሀሳቡን የመግለፅ መብቱን ማንም ሊገድበው አይችልም። እስክንድር ምን መናገር እንዳለበትና/እንደሌለበት ማንም ሊነግረው አይችልም። እንዲህ ዓይነት ጨዋታ በእስክንድር ፊት አይሠራም። ደግሞኮ “አዲስ አበባ የማናት? የሚለውን አቋም መነሻ አድርገን በምርጫ ካርድ/በድምፃችን እንቀጣለን” አለ ነው የተባለው። እስቲ ይኸ ምኑን ያዙኝ ልቀቁኝ ያስብላል? ወይስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጨዋታ ይህን ያህል ባዕድ ነን?
እስክንድር ይኸን ስላለ ታከለ ኡማ አይመረጥም ማለት አይደለም። እኔ በበኩሌ ታከለ ኡማ አዲስ አበባን በምክትል ከንቲባነት መምራት ከጀመረ ወዲህ በሚያደርጋቸው ነገሮች ከሚደመሙት መካከል አንዱ ነኝ። እናም ዛሬ ላይ የታከለ ኡማ ደጋፊ መሆኔን መደበቅ አልችልም። ወደፊት “አዲስ አበባ የማናት?” የሚለው “ግራ” የሆነ አጀንዳ ወደመድረክ የሚወጣ ከሆነም የኔ ምላሽ “አዲስ አበባማ የአዲስ አበቤዎች ናት” የሚል መሆኑን ገና ዱሮ; የታከለ ኡማን ሥሙንኳ ሳላውቀው ግልፅ አድርጌያለሁ። ታከለ ኡማ ከዚህ የተለዬ አቋም ይዞ ከመጣም ያኔ መከራከሪያችንን አቅርበን እንሟገትበታለን። ዛሬ ላይ ግን ታኬን “በርታ” ላለማለት መነሻ የለኝም። ገና ለገና ወደፊት የተለዬ አቋም ይዞ ሊመጣ ይችላል በሚል እሱን ማበረታታቴን አላቆምም።
እስክንድር ግን መብቱ ነው። ደግሞም እንደጋዜጠኛ ቀድመው እጁ የገቡ መረጃዎች ሊኖሩት ይችላሉ። ያም ባይሆን በመላ ምትም (hypothetically) ቢሆን ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጨዋታ እንዳያወራ የሚከለክለው ህግም ሆነ የአሠራር መርህ የለም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ በአመፅ ከሚያስፈራራና “ቄሮን” ከሚጠራ ይሰውረን!
ቄሮ የተነሳለትን ክቡር ተልዕኮ ከግብ አድርሶ የተመለሰ ይመስለኛል። አሁን ጊዜው የተገኘውን ሰላም የምንጠብቅበትና የተጀመረውን ለውጥ አጠናክረን የምናስቀጥልበት ነው። ከዚያ ውጭ ያለው መንገድ ለነዳውድ ኢብሳም አልበጀ!
ክብርና ሞገስ ለጀግኖቻችን!!!
Filed in: Amharic