>
6:46 am - Tuesday December 6, 2022

መከራዋ ያላለቀላት ናት እናት ምድር – ጎንደር!!! (ሲሳይ ዋኘው)

መከራዋ ያላለቀላት ናት እናት ምድር – ጎንደር!!!
ሲሳይ ዋኘው
* የዕብሪት – የጥጋብ ደጀን  በሆነው ጠብ-መንጃ ጎንደር እየታመሰች ነው !!!
ዛሬ ሀገር መሪ አልባ፤ ዛሬ መከራ ተጠሪ አልባ፤ ዛሬ ህዝብ እረኛ አልባ፤ ዛሬ ህይወት ሙሴ አልባ ወና ላይ የወለሌ ገበታ ሆኗል በምድረ ናራ ጭልጋ። ገና መከራዋ ያላለቀላት ናት እናት ምድር – ጎንደር። ይህን እልባት ሊሰጥ ወይንም ሰብስቦ በአንድ ማህለቅ ሥር ማስተዳደር ከሚችል መቋጫ መድረስ አልተቻለም – ፈጽሞ።
ተስፋ የሰነቁ፣ አድገው ያልጨረሱ ነገ የኛን የታላላቆቻቸውን ፍልግ ተክልትለው ህዝብን አገር ምቅየር ሚችል ህልም የሰነቁ ህጻናት በየቦታው ተፋናቅለው እያንዳንዷን ቀን በስጋት እየኖሩ ነው። ጭብጥ እህል መደፋት እንደነውር በሚታይበት አገር ሙሉ አዝመራ በእሳት ጋየ። ክቡሩ የሰው ልጅ በእሳት ሃሩር ነደደ። ገበና ከታች ቤት ዶግ አመድ ሆነ። ከብቶች በቁማቸው ተጠበሱ። ሀገር መረን አልባ ሆነ። የእናቶች ለቅሶ፣ የህጻናት ፍርሃት የሽማግሌዎች ጭንቀት ሰማየ ስማያት ደረሰ።  የተጀመረው የቃላት ጦርነት ወደተግባር ተቀየረ። ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፤ ከምራዕብ አስከ ደቡብ፤ ከደቡብ እስከ ስሜን ጎንደር ልይ ዋይታ ተበራክቷል።
ግፍ በዛ፤ ዕንባ በረከተ፤ መከራ ጠና፤ ፍዳ አና አለ። ሃይማኖት ተጣሰ። ሱባኤ ተረገጠ። ክህንት ተደፈረ። ጠኔ የነፃነት ቤቱን ሁሉን ቃኘው። ድምጽ ተዘጋ። ውሸት እና ማዳዳጥ የመንግሥት መኩሪያ ፖሊሲ ሆነ። ጥዋት የተነገረው በዛው ፍጥነት ተደምስሶ ወይ ተደመርምሶ ይደመጣል። ዝግጠት። ዝገት። ብላሽነት። ቃልአባይነት ነገሠ። ተፈጥሯዊ ሰዋዊነት መተንፈስ ታገደ። መንቀሳቃስ ተከተረ። ሰው ለሰው ይገናኝ ዘንድ እንደ ወንጀል ተቆጠረ። ሁሉም ተከረቸመ።
ዛሬ ከዛም አልፎ መንገድ ላይ የተገኘ ሁሉ በመትረዬስ ይታጨዳል። ሽዎች ተፈናቅለው ለስደት ተዳርገዋል። የተገኘው ሁሉ ይታሠራል። መሬት ያፈራው የታዬው ሁሉ ይወረራል፤ ይጋፈፋል። መታበይ ነግሷል፤ ንቀት ጣሪያ ነክቷል፤ ጥጋብ ዙሪያ ገባውን ትጥቁን አሳምሮ በጎንደር ላይ ዘምቷል። እኛን ይሳደጉን መተማመን- መደማማጥ – መከባባር – መቻቻል – መፈቃቀድ ሁሎችም ጠወለጉ፤ ፊትም ተነሱ። ጠበንጃ ንጉሥ ሆነ። ጠበንጃ ተመለከ። ጠበንጃ ገዢ ሆነ። ጠበንጃ የማንነት መለኪያ ሆነ። ጠበንጃ የትምህክት – የትዕቢት – የጥጋብ ደጀን ሆነ። ጠበንጃ መፎከሪያ የሰው ልጅ ረቂቅ ተፈጥሮ ማሸነፊያ ሆነ። ሰው ረከሰ ከእንሰሳም በታች ታዬ። ደጉ፤ ገራገሩ የናራ ጭልጋ ሰው እንደ ምናምንቴ ታዬ።
የሰው ልጅ መስፈሪያው ሰብዕናው መሆኑ ቀረ። በናራ ጭላጋ ምድር የሰው ልጅ ተፈጥሮን ጨምሮ እንደሌለ ተቆጠረ። መኖር ተሰበረ። የነበረው ጎንደሬ ዜጋ እንዳልነበረ ታዬ። ሁሉም በተለያዬ ሁኔታ ከፈጣሪ ቃል ወጥቶ ሰዋዊነቱን በደቦ ሰረዘ። ሰው እያለ የለህም፤ ማህበረሰብ አይደለህም ተባለ። ሰው አልተፈጠረም እስከ ማለት መንጠራራቱ አንቱ አስባለ። መለኪያው፤ መሥፈርቱ፤ ልቅናው፤ ዕውቅናው ሌላ እና ሌላ ሆነ። መለኪያው ሰው ከተፈጠረ በኋላ በሚገኙ ሰብዕና ተኮር ተሆነ። ሰውነት ከተፈጥሮ በታች ቀርቶ ሰውነት ስለመፈጠሩ የሚገድቡ ድንጋጌዎች ሁሉም በእጁ ሥራ እንደ ዳንቴል ተፈበረኩ። ድንጋጌው በድንጋጌ ላይ ዘምኖ ሰው ሆይ! በጎንደር ምድር በመንፈሱ ተሰቃይቶ ሰውኛ ጠረኑን ይለቅ ዘንድ፤ ታፍኖ ይፈናቀል ዘንድ ፍርድ ተገመደለበት።ጎንደር በጠና ታመመች። በናራ ጭልጋ ምድር ቁና ሆነች።
እኛስ?
ያኔ በደጉ ዘመን ያደግን፣ የድህነት ብርድ እንዳይሰማን በፍቅር ተጅቡነን ያደግን፣ የማነህ ልጅ ነው እንጅ ከየትኛው ብሄር ነህ? እምነትህ ምንድነው? ሳንባል ያደግን…ይህን ሁሉ ጉድ ስንሰማ ምን አልን? ለዚህ ነው ዛሬ በተለዬ ሁኔታ ጆሯችን እና ልባችን ከፍተን እንነጋገር ዘንድ በአድራሻችን የጻፍኩት።
ጭልጋ፣ መተማ፤ ቋራ፤ ደምቢያ፣ አርማጭሆ መተዳደሪያ ጥማዱን ሸጦ ጠበንጃ ሲገዛ፣ ህዝብ ሲጠቃ፣ ህዝብ ሲደፈር፣ ህዝብ ተጠላልፎ ሲወድቅ እኛ የት ነበርን። ይህ ምልክት የሁላችን የእኛዊነት መግለጫ መፈታተሻ ነው። ይህ ምልክት ነገን ያመተረ ነጋሪተ – ምልክት ነው። ይህ ምልክት አቅጣጫ የጠቆመ የሰማይ መለከት ምልክት ነው። ይህ ምልክት የሳትነውን ነገር በፍጥነት እናስተካከል ዘንድ በጽሞና የመከረም ነው። ይህ ምልክት ልቦናችን እንመረምር ዘንድ በተደሞ ብሄራዊ ህብራዊ ጥሪ አስተላልፏል። ይህ ምልክት ለውጥ ፈልገን ለውጥ ለምንፈራ ሁሉ የተላለፈ የፈጣሪ ድምጽ ነው፤ ጎንደርን እያዳረሰ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ።
አሁን እኔ የሚጨንቀኝ ለጎንደር እናቶች እና ህፃናት እና ምስኪን ገበሬዎች ነው። እነሱ ቅዱስ ናቸው። ዛሬን አያውቁትም። እኛ በምን እንደምንተራመስ አይገባቸውም። ግን ዕዳ ከፋዮች እነሱ ናቸው። ለነገሩ መቼ የኢትዮጵያ እናቶች ሁነኛ ሃሳባችን ሆነው ሲውቁ ነው? ነገ እኮ ታስቦም አያውቅም። ተራ ዜና አድርጋችሁ እንደማታዩት እምነቴ ነው። … ሞት ህዝባችን ደጅ ላይ፤ ጥፋት ወንድሞቻችን አናት ላይ ነው ያለው። ይህ ፌስ ቡክ ላይ አቲካራ ምንገጥበት ጊዜ አይደለም። የእንካ ሥላንትያ በመንትያ የውርርድም ጊዜም አይደለም። መተማመን መትረፍ አለበት። ሰው ያፈርሰውን አንድነት ሰው ሊጠግነው ይችላል። ያልተገባ ሞት ራሱ መሞት አለበት። ለዛ ደግሞ ባለጉዳዮች እኛው ራሳችን ነን። ከእኛ አልፎ ማን ሊመጣ? ( If not us, then who? If not today then when?)
የክልሉ መንግስት አንዲህ አድርጎ፤ ወያኔ እንዲህ አድርጎ፤ አብን፤ የቅማንት ኮሚቴ እንዲህ አድርጎ እያሉ መነታረኩ…ለምስኪኑ ህዝባችን ዳቦ አይሆንም። ከላይ የጠቀስኳቸው አካላትን መኮነንም ሆነ ማጽደቅ በየግላችን ምናደርገው ሆኖ፤ የጋራ ሃለፊነታችን የሆነውን ምስኪኑ ህዝባችንን ከፖለቲከኞች መንጋጋ ለማስጣል በጋራ መረባረብ ግን ጊዜው ሚጠይቀው ሃቅ ነው።
Filed in: Amharic