>
9:40 pm - Tuesday July 5, 2022

"መስጂዳችንን መጠበቅ የምንችለው በመስጂድ አጀንዳ ከመታጠር ስንወጣ ብቻ ነው!" (አህመዲን ጀበል) 

“መስጂዳችንን መጠበቅ የምንችለው በመስጂድ አጀንዳ ከመታጠር ስንወጣ ብቻ ነው!”
አህመዲን ጀበል 
“ሁሉንም ነገር ለናንተ ትተናል መስጂዳችንን ብቻ ተዉልን” የሚል አስተሳሰብ ባለቤት የሆነ ህዝብ   እንዳሰበው መስጂዱንም የራሱ ማድረግ አይችልም። ሰዎች ሀገር እየገነቡ፣ ሀገርና ሥልጣን እየተጋሩ ባመኑበት መንገድ ተደራጅተው ሲታገሉ፣ ሊታገሉ ከጊዜ ጋር ሲሮጡ አብዛኛው ሙስሊም ደግሞ በሃይማኖታዊ አጀንዳ ላይ ብቻ ታጥሮ በመስጅድ አጀንዳ ዉስጥ  ቀረ።ዓሊሙም ምሁሩም ዓይኑን በመስጊድና በመጅሊስ ጉዳይ ላይ ተክሎ በመቅረቱ  እየተገነባ ባለው ሀገር ዉስጥ የኛ ሚናና ስፍራ የቱ ጋር ነው? ብሎ የሚጠይቅ ጠፋ። በሀገሪቱ እየተሻሻሉ ባሉ ህጎች፣ እየተቋቋሙ ባሉ ተቋማት፣ እየተሾሙ ባሉ ግለሰቦች፣  ሌላም የህዝበ ሙስሊሙ መብትና ጥቅም ታሳቢ በማድረግ ማን ምን አለ? ምንስ አደረገ? የጠየቀ አካልስ አለ? እንጃ።
እስከመች በመስጂድ አጀንዳ ብቻ ታጥረን ስለመስጂድና ሃይማኖታዊ መብት ጥሰት እየተማረርን እንዘልቃለን? እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከመስጂድ አጀንዳ ወጥተን ሀገርንና መንግሥትን ወደ መጋራት የምናድገው መች ነው? “መስጂዱን እንኳ ተዉልን?” እያሉ በአካልም በሀሳብም በፍላጎትም በመስጂድ ዉስጥ ብቻ መኖር አግባብ እና የሚያዛልቅ ነውን? ለመስጂድና መጅሊስ የሰጠነውን ትኩረትና ስፍራ ያክል ለሀገርና ለመንግስት ብንሰጥ ኖሮ ሀሳባችን ወደ መስጊድና መጅሊስ እንዲመለስ ለማድረግ ሲሉ የመጅሊስ አጀንዳ ቶሎ ምላሽ ያገኝ ነበር። የኛ ትኩረት በመስጂድና በመጅሊስ ላይ ቆሞ ስለቀረ የሴረኞች ሚና ደግሞ አጀንዳ እየፈጠሩ እኛን ከዚያው የማቆየት ቀላል ተግባር ብቻ ሆነ።
እንደሙስሊም ዜጋ ለህዝበ ሙስሊሙ ችግሮች መፍትሄ መራቅ ሌሎችን በመውቀስ ጊዜ ማባከን አልሻም። የችግሮቻችን ምንጩና ዋንኛው ማእከሉ እኛው ሙስሊሞች ራሳችን ነን። ራሳችንን ፈትሸን ችግሮቻችንን ነቅሰን በማውጣትና ዘላቂ መፍትሄ እንደመፈለግ ጣታችንን በሌሎች ላይ እየቀሰርን የኛን ችግሮች ዘነጋን። የዉስጥ የቤት ሥራችንን በመቋጨት እና የጋራ ሀገራዊ ጥቅሞቻችንን በጋራ ለማስጠበቅ ከመትጋት ይልቅ የጀመዓንና የቡድንን ፍላጎትን በማስቀደም ጠርዝ ይዘን ለመጓተት ፀንተን እየተጋን  እንዴትስ ሌሎችን እንወቅሳለን?
የኛን ባህሪ፣ ስነልቦና ፍላጎትን የተረዱ አካላት በተደጋጋሚ ባዘጋጁልን ወጥመድ ዘው ብለን ገብተናል። ዓላማቸውን በዉል በመለየት ለዓላማቸው ተገቢውን ምላሽ እንደመስጠት በተደጋጋሚ  ለተግባራቸው በስሜት ምላሽ በመስጠት ዳግም ድርብ ችግር ሰለባ ሆነናል።
በተለያየ ጊዜ ሆነ ብለው ስሜታችንን በሚነካ መልኩ ነካክተውን ስሜታዊ ምላሽ ሰጥተን ጥፋተኛ ተብለን ስማችን ጠፍቷል። የኛን የተለመደ ምላሽ የሚጠብቁ አካላት ገና ብዙ ይተነኳሱናል። በስሜት ምላሽ ከመስጠትና በዝምታ ከመብከንከን ወጣ ብለን ከተለመደው መንገድ በተለየ ሁኔታ ቆም ብሎ በመነጋገር የተለየ አቅጣጫ መፈለግ ይሻል። ችግራችን ዉስጣዊና ዉጫዊ ነው። ስለራሳችን ከማንም በላይ ማሰብና መትጋት ያለብን እኛ እንጂ እነእገሌ አይደሉም። ሚናቸውን አልተወጡም ከምንላቸው እነእገሌ በፊት እኛ ሚናችንን መች ተወጣን? የምንወቅሳቸው ሌሎች ሁሉም የየራሳቸው ዓላማና ፍላጎት አላቸው።
  መንግሥትስ ቢሆን አስተሳሰቡና ፍላጎቱ የተበታተነ ያውንም ያልተደራጀ ህዝብ ጥያቄዎቹን ቶሎ ካልመለስኩ ችግር ይገጥመኛል ብሎ ምን እንቅልፍ  ይነሳዋል? ምኑስ ያስፈራዋል? መንግስት የህዝበ ሙስሊሙን መብትና ጥቅም ማዕከል ያደረገ ጠንካራና ተደራሽ የሆነ ህዝቡን ይቀሰቅስብናል ብለው መንግስትም ይሁን ሌሎች የሚፈሩት ሚዲያ የሌለው ህዝብ ብዙ ነን እያለ ቢደነቅ ምን ሊያመጣ?  ተማሩ፣ “ምሁራን”፣ ዓሊሞች  የሚባሉቱ የህዝቡን ችግሮች ነቅሰው በማውጣት የመፍትሄ ሀሳብ  አፍልቀው መንገድ ማሳየት ካልቻሉ፣ ከዘላቂ መፍትሄ ይልቅ ጊዜያዊና እሳት የማጥፋት ተግባርን እየመረጥን ችግሮቻችን እንዴት በዘላቂነት ሊፈቱ ይችላሉ?
ብዙ ሰው በቀጥታ ከፊትለፊቱ የሚያሳስበውና የሚያሰጋው ነገር ካልተደቀነበት በቀር ከዱዓም ከተግባራዊ ሥራም ይዘናጋል። ይህ ባህሪ ደግሞ ህዝበ ሙስሊሙን ዘወትር ችግሮች ሲከሰቱ ብቻ በመከላከል ላይ እንዲጠመድ አስገድዶታል። መከላከልን የመረጠ አካል ደግሞ ችግሮች ዘወትር በርሱ መንደርና ሜዳ መደጋገማቸው አይቀሬ ነው። ምክንያቱም ችግሮቹ እንዳይከሰቱ ከማድረግ ይልቅ ሲከሰቱ ለማስወገድ መንቀሳቀስን መርጧልና።
እኔ በግልፅ ለህዘበ ሙስሊሙ የማስተላልፈው መስጊድ ከዉስጣችሁ እንዲቆይ አድርጉ። እናንተ ግን ከመስጊድ ዉጡ። መስጊድን ለመስገጃና ለመማማሪያ እንጂ በመስጂድ ዉስጥ ብቻ አትኑሩ። በመስጂድ ዉስጥ ብቻ ከመኖር ወደ ትክክለኛ ኢትዮጵያዊነትና የሀገር ባለቤትነት ከፍ በሉ። ይህን እስካላደረጋችሁ መስጂዳችሁም ሆነ መጅሊሳችሁ  በኢትዮጵያ ዉስጥና የኢትዮጵያን መንግስት በሚመራው አካል ፍላጎት ስር  እንደሚወድቁ ለሰከንድም  ቢሆን አትርሱ። የሰፊዋን ኢትዮጵያን ባለቤትነት መብት ያረጋገጠ አካል የመስጂድና የመጅሊስ ባለቤትነቱን አያጣም። ስለሆነም ከመስጂድ ጥያቄ ወደ መንግስት ባለቤትነት፣ ከመጅሊስ ወደ ሀገር ባለቤትነትን ማረጋገጥ አጀንዳን ማሳደግ ግድ ይላል። ይህ ደግሞ በግልፅ የሃይማኖትንና የፖለቲካን ልዩነት አውቆና ድንበሩን አክብሮ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በህጋዊ መንገድ በመደራጀትና በመታገል በዘላቂነት የሁላችንና ለሁላችን የምትመች የተሻለች ሀገርና በልበ ሙሉነት “የኛ” የምንለው የተሻለ መንግሥት በጋራ ወደ ማረጋገጥ ማሰብና መታገል የዘወትር አጀንዳችን ወደ መሆን ማደግ ይገባናል። ለዚህ በሃይማኖታዊ አጀንዳ ንቁ ማህበረሰብ እንደሆንነው ሁሉ በሀገራዊና በፖለቲካ ጉዳይም ንቁ ማህበረሰብ ወደመሆን ማደግ ይገባናል። ይህ እዉን እንዲሆን ለዚህ ዓላማና መስመር ራሳቸውን የሰጡ፣ መስመራቸው ከሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ የለዩ  ራሳቸውን በማብቃት ተግባራዊ ሚናቸውን በግልፅ የሚወጡ ሊኖሩ ይገባል። ስለችግሩ ብቻ ከመነጋገር እስቲ ወደ መፍትሄ አቅጣጫ እንነጋገር። ከችግር ሜዳ ወደ መፍትሄ ሜዳ እናቅና።
Filed in: Amharic