>

ከመስጊድ ቃጠሎው ጀርባ!!! (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

ከመስጊድ ቃጠሎው ጀርባ!!!
ሞሀመድ አሊ መሀመድ
ዶ/ር አምባቸው በጎንደር – እስቴ መስጊዶች መቃጠላቸውን ተከትሎ ፈጥነው በቦታው በመገኘት ነገሩን ለማረጋጋት የወሰዱትን እርምጃ በበጎ ጎኑ ማዬት ያስፈልጋል። የአካባቢው ክርስቲያንና ሙስሊም ማህበረሰብ በመካከሉ ችግር እንደሌለና ሀዘኑንም ሆነ ደስታውን የመጋራት ልምድ እንዳለው መረጋገጡም አዎንታዊ ነው። የአካባቢው ሙስሊምና ክርስቲያን ማህበረሰብ የተቃጠሉትን መስጊዶች በጋራ ለመገንባት ያሳዬው አብሮነትና ትብብርም አበረታች ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ; “መስጊዶቹን ያቀጠላቸው ማነው?” የሚለው ጉዳይ ተድበስብሶ መታለፉ ግን ምቾት አይሰጥም። ዋናው ነገር መስጊዶቹን ያቃጠሏቸውን ሰዎች ማንነት ማወቅ ሳይሆን ከዚህ ጀርባ ያለውን ድብቅ ሴራና ተልዕኮ አንጥሮ ማውጣት ነው። ተልዕኮና ሴራው በአማራው ማህበረሰብ ውስጥ የሃይማኖት ግጭት ለመቀስቀስና እርስ በርስ እንዲተላለቅ ነው? ወይስ በራሱ በአማራው ውስጥ የተደበቀና አደገኛ አስተሳሰብ ያለው ኃይል አለ?
ይኸ ጉዳይ ነጥሮ መውጣትና በማያዳግም ሁኔታ መፍትሔ ማግኘት አለበት። ህዝቡ የዚህን አደገኛ ድርጊት ፈፃሚዎች ሊደብቅ የሚችልበት ምክንያት አይታየኝም። ወትሮም ቢሆን ወንጀለኞች በተለይ እንዲህ ዓይነት አደገኛ ድርጊቶችን የሚፈፅሙት ለህዝብ አሳውቀው አይደለም። ወንጀልን በመከላከልና የህብረተሰቡን; ብሎም የእምነትና የሌሎችንም ተቋማት በመጠበቅ ረገድ የማይተካ ሚና ያለው የአካባቢው አስተዳደር; በተለይም የፀጥታ ኃይሉ ነው።
አስተዳደሩና የፀጥታ ኃይሉ ወንጀል ሊፈፀም እንደሚችል ጠቋሚ ሁኔታዎችንና አዝማሚያዎችን ቀድሞ በማወቅ ወንጀሉን መከላከል እንደነበረበት እሙን ነው። ያን ማድረግ አለመቻሉ እንደተጠበቀ ሆኖ; ቢያንስ ወንጀሉ ከተፈፀመ በኋላ ወንጀለኞችነ ተከታትሎና ለይቶ በመያዝ ለህግ ማቅረብ ይጠበቅበታል። ከዚህ በፊት በአፅንኦት ለመግለፅ እንደሞከርኩት ይኸ ከተራ ወንጀል የተለዬና በማህበረሰቡ ሰላምና አብሮነት ላይ ያነጣጠረ አደገኛ ሴራ/አዝማሚያ ነው ማለት ይቻላል።
ለማንኛውም ሴረኞች/ክፉዎች በዘረጉት ወጥመድ ውስጥ ላለመግባት ጉዳዩን በትዕግስትና በጥንቃቄ መያዝና በማያዳግም ሁኔታ መፍታት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የሁሉም ወገን አስተዋይነት; ትብብርና አንድነት ያስፈልጋል። በዚህ መንገድ ይህን አደገኛ ወንጀል የፈፀሙት ሰዎች/ኃይሎች ተለይተው ለህግና/ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።
የአካባቢው ህዝብ ያሳየውን ቅን ተነሳሽነትና አብሮነት አድንቀን ሳናበቃ ሌላ ቃጠሎ? ወይ ነዶ!!!
ከዚህ ጀርባ ያለው ማንና/ምንድነው?
Filed in: Amharic