>

አዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም፤ የአስተዳደር ጉዳይ ወይስ የባለቤትነት? (ያሬድ ሀይለማርያም)

አዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም፤ የአስተዳደር ጉዳይ ወይስ የባለቤትነት?
ያሬድ ሀይለማርያም
የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 49(5) “የኦሮሚያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ የአስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል።”
=========
ይህ አንቀጽ በተወሰነ ደራጃ ግልጽነት የሚጎድለው እና አንዳንድ አሻሚ የሚመስሉ ሃሳቦችን በውስጡ የያዘ ቢመስልም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ እንጂ ከባለቤትነት የመነጨ እንዳልሆነ በማያሻማ መልኩ አስቀምጧል። አሻሚው ጉዳይ ልዩ ጥቅም የሚባሉት ነገሮች ከምን ተነስቶ የት ይደርሳል፤ ምን ምን ጉዳዮችን ያካትታል፤ የማያካትታቸውስ ነገሮች ምንድን ናቸው የሚለው ነው። እነዚህ ጉዳዮች በዝርዝር ሕግ ይወሰናሉ ስለሚል ዝርዝር የውጡ ሕጎችን ማገላበጥ ይቻላል። ሆኖም ዋናው በሕገ መንግስቱ የሰፈረው ሃሳብ ስለሆነ እሱ ላይ ብቻ ልናተኩር እንችላለን።
የዚህን አንቀጽ የመጀመሪያዎቹን አራት ንዑስ አንቀጾች በደንብ የተመለከትን እንደሆነ አዲስ አበባ የፌዴራል መንግስቱ መቀመጫ እንደሆነች፣ የከተማ አስተዳደሩ እራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው፣ መስተዳድሩም ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስቱ እንደሆነ እና የከተማዋ ነዋሪዎችም እንደማንኛውም ክልል ሕዝብ በፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚወከሉ በግልጽ ይደነግጋል። ይህ ማለት አዲስ አበባ እንደ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ አማራ ወይም ደቡብ ክልል እራሷን የቻለች አስተዳደራዊ ግዛት ነች ማለት ነው።
የከተማዋ አቀማመጥ ዙሪያዋን በኦሮሚያ ክልል የታጠረ ስለሆነ የከተማዋ የውሃ፣ የመብራት፣ የመንገድ ትራንስፖርት፣ የደረቅ እና የፍሳሽ ቆሻሻዎች እና ሌሎች አገልግሎቶች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ዙሪያዋን የሚገኙ ከተሞችን እና መንደሮችን የሚነካ በመሆኑ በዙሪያዋ የሚገኙት እነዚህ ከተሞች ቀጥተኛ ተጎጂዎች ወይም ተጠቃሚዎች ናቸው። በመሆኑም የከተማዋ እድገትም ሆነ መስፋፋት በቀጥታ በመሬት ይዞታቸው፣ በከባቢ አየር፣ እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የእለት ተዕለት ኑሮዋቸውን ስለሚነካ የኦሮሚያ ክልል በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ጥቅማቸው እንዳይነካም ሆነ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት ስላለበት ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በእነዚህ ልዩ ጥቅሞች ዙሪያ አብሮ እንዲሰራ መብት እና ግዴታንም ጭምር የሚጥል ድንጋጌ ነው።
1. ይህ አስተዳደራዊ ልዩ ጥቅም በአግባቡ ተተግብሯል ወይ?
የዚህን ድንጋጌ አፈጻጸም የተመለከትን እንደሆነ ሦስቱም የመንግስት አካላት፤ የፌዴራል መንግስቱ፣ የኦሮሚያ ክልል እና የአዲስ አበባ መስተዳደር በሕገ መንግስቱ የተጣለባቸውን ታላቅ ኃላፊነት በአግባቡ ያልተወጡ መሆኑን መሬት ላይ ያለውን እውነታ በማየት ለመረዳት ይቻላል። ባለፉት አሥርት አመታት በአዲስ አበባ ዙሪያ ይኖሩ የነበሩ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የኦሮሚያ ክልል ገበሬዎች በከተማዋ የማስፋፊያ ማስተር ፕላን ሰበብ ሲፈናቀሉ እና መሬታቸው ለባለሃብት ሲቀራመት እነዚህ ሦስት የመንግስት አካላት የዚህ ሕገ ወጥ ሥራ ዋና ተዋናይ ነበሩ።
በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን ባሉበት ማልማት እና የአካባቢው ነዋሪም የልማቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ይቻል ነበር። የመጀመሪያው ስህተት እነዚህን አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ እንዲካለሉ ማድረጉ ላይ ነው። ሁለተኛው ስህተት ደግሞ መንግስት ለገበሬዎቹ እፍኝ የማትሞላ ገንዘብ በካሳ መልክ እየሰጠ መሬታቸውን በብዙ ሚሊዮኖች መቸብቸቡ እና አንዳንዱንም ቤቶች እየሰራ በከፍተኛ ገንዘብ መሸጡ ነው። ሶስተኛው ስህተት እነዚህ ከቅያቸው የተነሱ ገበሬዎች የት ወደቁ ብሎ የሚጠይቅ የመንግስት አካል አለመኖሩ ነው። በተለይም የክልሉ መንግስት።
እርግጥ ነው ከተማ ሲዘምን ብዙ መፈነቃቀሎች፣ መጉላላት እና ኪሳራዎች ይኖሩታል። ይሁንና የመጨረሻ ግቡ እና በልማቱ የሚገኘው ትርፍ ግን የሁሉም ስለሚሆን በሂደቱ ውስጥ የተጉላሉ ሰዎች የፍሬው ዋና ተጠቃሚ ስለሚሆኑ ለተሻለ ጥቅም የተከፈለ ዋጋ ተደርጎ በሁሉም ዘንድ ይወሰዳል። ብዙ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ከተሞችም ሲዘምኑ ዋጋ እያስከፈሉ ነው። ግን የመጨረሻ ፍሬው ሁሉንም ስለሚያስደስት ማህበራዊ ፍትሐዊነትንም አብረው እያረጋገጡ ነው የሚሄዱት። እኛ ዘንድ ይህ አይነቱ ነገር ፈጽሞ አይታሰብም። መፈናቀሉ ዳር ዳሩን ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ መሃሉንም በደንብ ነክቷል።
ሰዎች ለዘመናት ከኖሩበት ሥፍራ እየተፈናቀሉ ሜዳ ላይ ሲጣሉ ተስተውሏል። በአዲስ አበባ እምብርት የሚገኙ ቁልፍ ቁልፍ ስፍራዎች ዛሬ ያላቸውን የገበያ ዋጋ ሊያወጡ የቻሉት ለዘመናት በሥፍራው ላይ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ገንዘባቸውን አፍሰው በገነቡት መልካም የአካባቢ ዝና (good will) እና ለንግድ እና ለሌሎች እንቅስቃሴዎች ተፈላጊነትን እንዲያፈራ ባደረጉት ነባር ነዋሪዎች ነው። ፒያሳ ላይ የአንድ ሄክታር መሬት እና ለገጣፎ ያለ አንድ ሄክታር መሬት ዋጋ መካከል ያለው የሰማይ እና የምድር ያህል የዋጋ ልዩነት ዋናው መንስዔ ይሄው ነው። የመሬቱ መጠን ሳይለያይ የዋጋ ልዩነት የሚታየው የማይዳሰሰው እና የማይጨበጠው የአካባቢው መልካም ዝና ዋጋ ነው። ያ ዝና ደግሞ እየተፈናቀሉ በየሜዳው እና ጥጋጥጉ የተጣሉት ሰዎች ልፋት ዋጋ ነው።
እነኚህን ሰዎች አፈናቅሎ እና በየጥጋጥጉ ሌላ ያለማ ስፍራ እንዲያለሙ በማድረግ እነሱ በካቡት የአካባቢ መልካም ስም አትራፊ የሆኑት መሬቶቹን የቸበቸበው መንግስት እና የዘመኑ ጥቂት ባለሃብቶች ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ቱባ ባለሃብት ዋጋ በስንት ደሃ ህይወት እንደሚተመን ለማወቅ ወደ የከተማዋን ዙሪያ ቀኝ ማየት በቂ ነው።
2. ልዩ ጥቅሙ የከተማው ባለቤትነትን ይጨምራል ወይ?
አዲስ አበባ እራሷን የቻለች እና በማንኛውም ክልል ባለቤትነት ወይም ሞግዚትነት ያልተያዘች ከተማ መሆኗን ከላይ የተጠቀሰው አንቀጽ በግልጽ ይደነግጋል። በእርግጥም አዲስ አበባ የማንኛውም ክልል ልዩ ግዛት ወይም ሃብት ተደርጋ ልትቆጠር አትችልም። ኦሮሚያ ክልል በከተሟዋ ዙሪያ ባሉ ተዋሳኝ ከተሞች ምክንያት አስተዳደራዊ ልዩ ጥቅም ማግኘቱ ባለቤትነትን አሳያይም፤ አያረጋግጥምም። አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሁለት እና ሦስት ክልሎች ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ የምትዋሰን ቢሆን ኖሮ ልክ እንደ ኦሮሚያ ክልል ሌሎቹም ተዋሳኝ ክልሎች የልዩ ጥቅም ባላቤት ይሆኑ ነበር።
ከዚህ በዘለለ ግን ጅማም ሆነ መቀሌ፣ ነቀምት ሆነ ባህርዳር፣ ሐሮማያ ሆነ ጋምቤላ፣ አፋር ሆነ አርሲ፣ ኦጋዴን ሆነ መቱ ሁሉም በአዲስ አበባ ላይ ያላቸው ጥቅም እንደ ርዕሰ ብሔር ከተማነቷ እኩል ነው። አንድ ነቀምት ያለ የኦሮሞ ተወላጅ መቀሌ ካለ የትግራይ ተወላጅ ወይም ጎንደር ካለ የአማራ ተወላጅ ወይም ኦጋዴን ካለ የሶማሌ ተወላጅ ወይም ጋምቤላ ካለ የአኝዋክ ተወላጅ ወይም አርባ ምንጭ ካለ የጋሙ ተወላጅ የተለየ መብትም ሆነ ጥቅም በአዲስ አበባ ላይ የለውም፤ ሊኖረውም አይችልም።
የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም የሚያያዘው በአዲስ አበባ ዙሪያ እና አቅራቢያ ካሉ እንደ ሰበታ፣ ለገጣፎ፣ ሱሉልታ፣ ሰንዳፋ እና ሌሎች አጎራባች ከተሞች እና መንደሮ ጋር በተያያዘ ነው። ነቀምት፣ ሐረር፣ አርሲ፣ ባሌ፣ ጅማ ወይም ሌሎች ከአዲስ አበባ በብዙ እርቀት የሚገኙ የክልሉ ከተሞች በአዲስ አበባ ላይ ከደሴ፣ ከመቀሌ፣ ከባህር ዳር፣ ከድሬደዋ፣ ከአሳይታ፣ ወይም ከአዋሳ የተለየ የኦሮሚያ ክልል አካል ስለሆኑ ብቻ ልዩ ጥቅም የላቸውም፤ ሊኖራቸውም አይችልም። ሁሉም እኩል ጥቅም ነው የሚኖራቸው።
እንዲሁም፤ ሰበታ ወይም ሰንዳፋ ላይ ያለ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ በእነዚሁ አካባቢዎች ካሉ ሌሎች ብሔር ተወላጆች ጋር በአዲስ አበባ ላይ ያለው የልዩ ጥቅም ተጠቃሚነት እኩል እና የማይበላለጥ ነው። ሰበታ ያለ አንድ ውራጌ ወይም ትግሬ ወይም ከንባታ ወይም አማራ፤ ሰበታ ካላ አንድ ኦሮሞ ጋር በአዲስ አበባ ላይ በሚነሱ ልዩ ጥቅሞች ላይ ያለው መብት እና ድርሻ እኩል ነው። ምክንያቱም የልዩ ጥቅሙ ዋናው መስፈርት አካባቢያዊ አቀማመጥ እና አስተዳደራዊ ግንኙነት እንጂ የብሔር ማንነት አይደለም። ሰበታ ከተማ በአዲስ አበባ አጎራባችነቷ በሚደርስባት ማንኛውም አስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሌሎች ጫናዎች የሚጎዳው ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ ነው እንጂ አንድ ዘር ወይም አንድ የህብረተሰብ ክፍል ብቻ አይደለም።
ስለዚህ ነቀምት ላይ ያለ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ አዲስ አበባን በግዛት ባለቤትነት ወይም የተለየ ልዩ ጥቅም አለኝ ብሎ የሚጠይቅበት አግባብ ብቸኛ ምንጩ ሊሆን የሚችለው በታሪክ ወደ ኋላ ብዙ መቶ አመታትን ተጉዘን የዛሬዋ አዲስ አበባ በማን እጅ ነበረች የሚል ጥያቄ ስናነሳ ነው። ይህ አይነቱ ሙግት የፖለቲካ ጡዘቱን ከማስፋት እና አዲስ አበባን የመሻኮቻ ሜዳ ለማድረግ ከማለም ያለፈ ብዙ የሚያስኬድ መሟገቻ ሊሆን አይችልም። በተመሳሳይ ሁኔታ ብዙ የአገሪቱ ክፍሎች በታሪክ አንዱ ከሌላው ሲወርስ፣ ሲያፈናቅል እና ሲሰፍር የመጣ ስለሆነ የግዛት ይገባኛል ጥያቄው ማቆሚያ አይኖረውም።
ባጭሩ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ነች። በዙሪያ ያሉ አዋሳኝ ከተሞች አስተዳደራዊ ልዩ ጥቅም አላቸው የሚለው የሕገ መንግስቱ አንቀጽ በአግባቡ ቢተረጎም እና በሥራ ላይ ቢውል መልካም ነው።
ኦሮሚያ ክልል ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ልዩ ጥቅም ሊኖረው አይገባም የሚለውም ሆነ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ነች የሚለው ሙግት ሁለቱም ጠርዝ የረገጡ እና መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘቡ ይመስለኛል። በምንም መንገድ አንድ ሰው ከጅማ መጥቶ አዲስ አበባ ላይ ከአዲስ አበቤውም ሆነ ከሌላው ኢትዮጵያዊ በተለየ መልኩ የባለቤትነት መብት አለኝ ሊል አይችልም። በተመሳሳይ ሁኔታ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖሩ እና በከተማዋ መስፋፋት እና ሌሎች ጥቅሞች የተነሳ የመኖር ዋስትና እስከማጣት የደረሱ የኦሮሞ ገበሬዎችን አንተ በአዲስ አበባ ጉዳይ አያገባህም፤ ልዩ ጥቅምም የለህም ልንል አንችልም።
የአዲስ አበባ ዘመናዊነት፣ መስፋፋት እና ሌሎች የከተማ ጣጣዎችን የተሸከመውን አጎራባች ከተማ እዳ ተሸካሚ ብቻ አድርጎ ከመብት እና ከጥቅም ማግለል አይቻልም። የአዲስ አበባ ቆሻሻ የት ነው የሚጣለው? የአዲስ አበባ ውሃስ ከየት ነው የሚቀዳው? የአዲስ አበባ ወጪና ገቢ ንግድ በማን ደጃፍ ነው የሚያልፈው? አዲስ አበባ ከሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች የሚያገናኛት ጉሮሮዋ ከወዴት ነው ያለው? ወደ አዲስ አበባ የሚጎርፍ መኪና የነ ማንን ደጃፍ እያበሸቀጠ ነው ወደ ከተማዋ የሚገባው?
ስለዚህ ስለ አዲስ አበባ ጥቅም ሲሰላ አብሮት የሚነሳውን ግዴታም አብረን እናስብ። ይህቺን የአዲስ አበባን ጉዳይ የፖለቲካ ማጠንጠኛ በማድረግ በአገሪቱ ውስጥ ሊያገግም እየዳኽ ያለውን የዘር ልዩነት እና የጥላቻ ፖለቲካ ለማስፋፋትና ዳግም እንዲያገረሽ ለማድረግ የአዲስ አበባን የቅርጫ ስጋ አድርጎ ማቅረብ ነውር እና የማያዛልቅ ነው። ጉዳይን ከአስተዳደር ልዩ ጥቅም አንስቶ ወደ ባለቤትነት ጥያቄ ማሸጋገርና የአንድ ብሔረሰብ የህልውና ጥያቄም አድርጎ ማቅረብ ሌላ ደም አፋሳሽ ግጭትን ከመጋበዝ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም።
የአዲስ አበባ ጉዳይ በጥንቃቄ ቢያዝ ጥሩ ነው። በስሜት እና በድብቅ የፖለቲካ ሸር አዲስ አበባን የፍልሚያ ማዕከል ለማድረግ ከተለያዩ አግጣጫዎች የተጀመሩቱ የቃላት ውንጨፋዎች እና ዛቻና ማስፈራሪያው ይቁም እና የጥሞና ውይይት ይጀመር።
በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic