>
10:42 am - Tuesday July 5, 2022

የቀ.ኃ.ሥ. ቴምብሮች ...  (አሰፋ ሀይሉ)

የቀ.ኃ.ሥ. ቴምብሮች –  H.S.I Stamps.
አሰፋ ሀይሉ
የዓለም ህዝብ ሁሉ በፖስታ ይላላካል፡፡ ፖስታ ብቻ ሳይሆን ፖስትካርድ ራሱ ያለፖስታ ይላላካል፡፡ ሲላላክ ደግሞ ሁሉም ቴምብሮችን ይጠቀማል፡፡ ደግሞ የሚገርምህ ቴምብሮቹ ሁልጊዜም ሃገር እያቆራረጡ ነው የሚሄዱት፡፡ በብዙ ሰው እጅም ያልፋሉ፡፡ እና በቃ አንተ ላገኘኸው የመልዕክት ማስተላለፍ አገልግሎት ቀረጥ ለመክፈል ብለህ እንደተመኑ ገዝተህ.. ቤትህ ከሆነ በምላስህ ምራቅ.. ፖስታ ቤት ከሆነ ደግሞ በስፖንጅ ውሃ እያራስክ እንደቀልድ የምትለጥፈው ቴምብር ለካንስ በብዙዎች እጅና ዕይታ አልፎ ነው ተቀባዩ ዘንድ የሚደርሰው፡፡ ስለዚህ… ማሳየትና ማስታወስ የምትፈልገውን የሃገር ገጽታ ሁላ በቃ በየቴምብርህ ላይ መለጠፍ ነው፡፡ እና ቴምብር በቃ ለ ‹‹ኢሜጆሎጂ›› ቀላል የመገናኛ አውታር አይምሰልህ፡፡ ይህን ሁሉ ለማለት ያነሳሳኝ ባጋጣሚ ዓይን-ጥሎኝ (እግር-ጥሎኝ) የጃንሆይን ቴምብሮች ለማየት በመታደሌ ነው፡፡ የምር በቃ እኒህን ቴምብሮች ያየ ሰው ሁሉ.. በቀኃሥ ዘመን በጥቅም ላይ ውሎ በነበረው ሃገርን (እና ዘውድን ጭምር) ለራስህና ለዓለም ህዝብ የማስተዋወቅ ችሎታቸው መደመም አይቀርለትም፡፡ ለካንስ ቴምብሮች ራሳቸው ኃይለኛ አቅምን የተላበሱ የማስተዋወቂያ መሣሪያዎች (communication tools) ኖረዋልና ትላለህ፡፡
ከአንዱ የአንድ ብር ቴምብር ስትጀምር ቀኃሥ በውሃ-ሰማያዊ ሱፍ.. የምታምር ሰማያዊ ነጭ ነጠብጣብ ጣል ጣል ያረገባትን ክራቫት ሸብ እንዳረጉ ገጭ ብለው ታገኛቸዋለህ (ፀጉራቸውን በሙድ ትንሽ ሎጨጭ ማድረጋቸው ታዲያ ይያዝልኝ)፡፡ ደግሞ የሚገርምህ ይህንኑ ፎቶ የያዘው ቴምብር ሁሉም ሰው እጅ እንዲገባ ነው መሰል.. በርካሽ ዋጋ 10ሣ ቀንሶ በ90 ሳንቲም እና 70ሣ ታላቅ ቅናሽ ተደርጎለት በ30ሣ ቴምብርም ተዘጋጅቶለታል፡፡ ስትቀጥል ደሞ ጃንሆይ.. በሃበሻ የእጅ ጥበብ ወርቀ-ዘቦው የተጠለፈ ካባቸውን እንዳደረጉ.. (አሁንም ከነሉጫ ፀጉራቸው) ከጎን በኩል በቀይ የአንበሳ መደብ ላይ.. በወርቅ ፅሁፍ የጃንሆይ 75ኛ ዓመት ልደት መታሰቢያ የሚል ፅሁፍ በእንግሊዝኛ በፈዛዛው ተጽፎ.. አንበሳቸውም በፈዛዛ መስመር በቀዩ መደብ ከጀርባቸው ሆኖ የሚያሳይ ባለ አንድ ብር ቴምብር አለ፡፡ (እንዴ! ጃንሆይ.. ከዚህ በኋላ ልደታቸውን ለማክበር አልታደሉም፤ ደሞኮ ቀይ መደብ መምረጣቸው… ምናልባት ሊመጣ ያለው የኮሚኒስት-ሶሻሊስት እንቅስቃሴ ታይቷቸው ይሆን እንዴ? ያሰኝሃል)፡፡ ደግሞ እልፍ ስትል… በገብስ ጥምዝ ላይ በቀኝ በኩል የቀኃሥ ፎቶ በግራ ደግሞ ከዓለም ካርታ ስር.. ‹‹ኢትዮጵያ፡ ስለ፡ ሰላም፡ ያደረገችው፡ ጥረት›› ‹‹ETHIOPIA’S STRUGGLE FOR PEACE›› የሚል ሎጎ ያለበት ባለ 1ብር ቴምብር ታገኛለህ፡፡  አለፍ ደግሞ ስትል… በግራና በቀኝ ከታች በኩል በአማርኛና እንግሊዝኛ ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚል ያለበት…ከላይ በኩል ግን በአልማዝ ቅርፅ፡- ‹‹አበበ ቢቂላ›› ‹‹MARATHON WINNER›› የሚል ያለበት ባለ 50ሣ ቴምብር አለልህ፡፡ ደሞ የገረመኝ ይሄኛው ቴምብር የዲዛይነሩ ስም ከስር በትንንሹ በሁለቱም ቋንቋዎች አለልህ፡- ‹‹ሠረቀ የማነ ብርሃን›› የሚል፡፡ ምናልባት ታዋቂ አርቲስት ይሆን ይሆን? እኔንጃ ብቻ፡፡ ግን ይህ ሠረቀ የሚባል ሰውዬ.. ደግሞ ስሙ በሌላም ቴምብር ላይ አለ፡- ‹‹ኢትዮጵያ›› ከሚለው በላይ ባህላዊ ጨዋታችን ‹‹ጉግሥ›› ‹‹GUKS›› የሚል የሚጫወቱ ጉግሰኞችን የያዘ ቴምብር ላይ ነው፡፡ ደሞ ሌላኛው አረንጓዴ ቀለም የተላበሰ ቴምብር.. በቃ ‹‹ዝቋላ›› የሚል ነው፡፡ ዝቋላን በቃ አረንጓዴ መስክ አስመስሎታል፡፡ ደግሞ የሚገርምህ.. ከዝቋላ በላይ በአረንጓዴ ቀለም የተመሰለ.. አውሮፕላናችን ሲሄድ ይታያል፡- በቃ ከዝቋላ የእሣተ ገሞራ ጉድጓድ እስከ ሰማይ ጫፍ የደረስንበትን ‹‹የአረንጓዴ ልማት›› ግሥጋሴ ውጤት ለማሳየት ይሆን የሚል ሃሳብ ይመጣብሃል፡፡
የቴምብር ጉዟችን ይቀጥላል፡፡ አንዱ የሠረቀ የማነ ብርሃን ቴምብር ላይ ምን ታገኛለህ መሠለህ፡- በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ላይ ትልቅ ዋንጫ አለ፤ ተጫዋቾችም በክብ መስመር ውስጥ ይታያሉ፤ ከዚያ በአልማዝ የአግድም አቅጣጫ በግራና በቀኝ፡- ‹‹ኢትዮጵያ፤ አፍሪቃ ዋንጫ፤ 1962›› ‹‹ETHIOPIA. AFRICA CUP. 1962›› የሚል ታገኛለህ፡፡ ይህ ቴምብር 30 ሣንቲም ነው ዋጋው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ፖስታ ፈጣን›› ‹‹POSTES ETHIOPIENNES – Addis Ababa Bureau Des Postes›› ከሚል የፈረንሣይኛ ፅሁፍ ጋርም የያዘ ባለ 50ሣ ቴምብር አለልህ፡፡ በፈረንሣይኛ የተጻፈበት ሌላ ቴምብር ደግሞ ‹‹የኢትዮጵያና የፈረንሣይ ምድር ባቡር የአምሣኛ ዓመት መታሰቢያ›› ‹‹CINQUANTENAIRE ARRIVEE DU CHEMIN DE FER A ADDIS-ABEBA›› ከሚል ፅሑፍ ጋር.. በቀኝ የቀኃሥ ፎቶ 1967 ከሚል ዓ/ም ጋር፤ በግራ ደግሞ የአፄ ምኒልክ ፎቶ 1917 ከሚል ጋር፤ በመሃ ደግሞ ባቡሩ.. ሼ መንደፍር.. በሃዲድ ላይ ሲሄድ የሚያሳይ ቴምብር አለልህ… በ30 ሣንቲም ብቻ፡፡ በነገራችን ላይ የሁሉም ቴምብሮች ዋጋ በአማርኛ አኃዝ አፃፃፍ ነው የተጻፉት እና እነሱ ከተሣቱህ.. በ123 የተፃፈልህን አይተህ ከስህተት ትድናለህ፡፡ ግን የራሳችን ነገር ምንም ቢሆን ደስ ማለቱ አይቀርም  – ባናነበውም መቼስ! እና ብቻልህ.. የዩ.ኤን.ን UN ሄልሜት ቆብ ከደፋ ሰላም ማስከበር “COLLECTIVE SECURITY” የሚል ቴምብር አንስተህ.. እስከ ቱራኮ ሊየኮቲስ ‹‹TURACO LEUCOTIS››  የምትሰኝ ጅራተ ራጅም ያገራችን ወፍ ድረስ፤ ከወንጂ ይሁን ከመተሃራ ስኳር ፋብሪካ እስከ ድሬዳዋ ይሁን ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፤ ወላ ጣሊያን የሰራው የአባይ ድልድይና በምፅዋ ላይ የተገነባ መስጊድ ሳይቀር..፤ ጭራሽ፡- ‹‹ከረሐብ ነፃ የመውጣት ተጋድሎ›› ‹‹FREEDOM FROM HUNGER CAMPAIGN›› የሚልና ‹‹AFRICAN SOLIDARITY›› የሚሉ ቴምብሮች ሁሉ ታገኛለህ፡፡ ምን የሚል ድንገተኛ ትርጉም እንዳመጣልኝ ታውቃለህ? አፍሪካውያን ረሃብን ከምድራቸው ለማጥፋት.. በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘው ታላቁን ተጋድሎ ያደርጋሉ››!! የሚል ትንቢት ሁሉ መሰለኝ.. ከቴምብሮቹ የማየው፡፡ በመጨረሻ ለስንብት.. አንድ የሚያሥቅህ የ‹እንቁልልጬ› ቴምበር አለልህ፡፡ የታተመው የመን ነበር፡፡ ስለዚህ ጃንሆይ.. ቴምብሩ ላይ ያሳተሙበት ምስሎች ምን ቢሆን ጥሩ ነው? መዓት ባለሻኛ ከብቶች.. እዚህም እዚያም ቆመው ሲንጎማለሉ!! (ሃሃሃ..!) ታዲያ ከዚህ በላይ ‹‹እንቁልልጬ!›› ከወዴት ልታገኝ ኖሯል??!! እና ብቻ.. ቀኃሥን የምር በቃ ታላቅ የዲፕሎማሲና የፕሮሞሽን ሰው ቢሏቸው ለካንስ ምን ያንስባቸዋል? እኔ ደግሞ ለኮሙኒኬሽን… ለኢሜጆሎጂ.. ለሃገር ገፅታ ግንባታ.. ትንንሿን የተቆራረጠች ቴምብር.. ከየቤታችን በምላሳችን አርሰን የምንለጥፋትን ቴምብር ሁሉ ሣትቀር ሣይንቁ በሥራ ላይ ያዋሉ.. ታላቅ የብዙሃን (የብዝሃነትስ ቢባሉ!) መገናኛ ሰው ብላቸው ቅር የሚለው ሰው ይኖር ይሆን?? (ካለ.. ወንድሜ.. በቃ ከላይ ያላካተትኳትን የማሞ ካቻን አውቶብስ የያዘ ቴምብር ጋብዤሃለሁ… ለእጅ መንሻ!)፡፡
እንደ ምርቃት :- 
የአጼ ኃይለስላሴ ታሪክና የሀውልት መሰራትን በተመለከተ አዲስ ቴቪ የካቲት 3/2011 ዓ.ም ያቀረበውን የንጉሱን ፖለቲካዉ ህይወት የዳሰሰ  ሪፖርታዥ ላስቃኝዎ:-
 
 ‹‹ትዝታ በፖስታ ልኬልሃለሁ.. መልሱን በቶሎ እጠብቃለሁ›› በሚለው ቆየት ያለ.. ዜማ ብንሰነባበትስ! መልካም ጊዜ፡፡ ቻው፡፡
Filed in: Amharic