>

የመቀሌው ቡድን ሴራ!?!  (የአግ7 ከፍተኛ አመራር አቶ አበበ ቦጋለ)

የመቀሌው ቡድን ሴራ!?!
 የአግ7 ከፍተኛ አመራር አቶ አበበ ቦጋለ
#Ethiopia : ከሥልጣን ተባሮ መቀሌ የመሸገው ወንጀለኛው የህወሃት አመራር የአገራችንን ሠላምና መረጋጋት ለማደፍረስ ተግቶ እየሰራ እንደሆነ ከህዝብ የተሰወረ ጉዳይ አይደለም። ይህ ቡድን ዛሬ የትግራይን ክልል ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ እንደሚያስተዳድር በይፋ ባይነገረንም ብዙዎቻችን የምናውቀው ሃቅ ነው። የማዕከላዊውን መንግሥት ቁልፍ ሥልጣኖችን በሞኖፖሊ ተቆጣጥሮ በኖረባቸው አመታት በፈጸመው የሰብአዊ መብቶች ጥሰትና የሃብት ዘረፋ በወንጀል የሚፈለገው ይህ ቡድን በሌላው የአገሪቱ አንድ ክፍል ማለትም በትግራይ ሥልጣን በእጁ አስገብቶ በመሪነት መታየቱ የሚገርም ነገር አለው።
ሰሞኑን ከህወሃት አመራር በይፋ መልቀቁን ያሳወቀው ዛዲግ አብረሃ በመለቅቂያ ደብዳቤው ላይ በግልጽ አዳሰፈረው ( https://www.ethiopianreporter.com/article/14705 ) ህወሃት እንደ ድርጅት አሁን በአገራችን እየተካሄደ ያለውን ለውጥ አጥብቆ የሚቃወም ብቻ ሳይሆን ለመደበቂያ ዋሻነት እንዲመቸው የትግራይን ህዝብና ክልል ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ነጥሎ በጉልበት አፍኖ ለመያዝ የወሰነ ድርጅትም ሆኖአል።
የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ባለፈው ታህሳስ ወር ለህወሃቶች አዘጋጅቶት በነበረው ወቅታዊ የአገራችን ፖለቲካ ውይይት መድረክ ላይ በአብላጫው ህዝባችን ከፍተኛ ድጋፉ የተቸረውና በዶር አቢይ መንግሥት የሚመራው የለውጥ ሂደት “በበርካታ ሰማዕታት ውድ ህይወት መስዋዕትነት የተገኘውን አብዮታዊ ዲሞክራሲ የቀለበሰ ነው” የሚል አቋምና የጋራ መደምደሚያ የተያዘበት እንደሆነ እናስታውሳለን። “ቅልበሳ” ነው የተባለውን የለውጥ ጅማሮ ለመታገልና አቢዮታዊ ዲሞክራሲ መልሶ እንዲያንሰራራ ለማድረግም ህወሃት ባለ በሌለ ሃይሉ እንደሚታገል በበረከት ስሞኦን አንደበት ግልጽ አድርጎአል። ለዚህ አላማው ማሳፈጸሚያ የሚሆን በሥልጣን ዘመኑ ሙሉ በዘረፋና በኮንትሮባንድ ንግድ የሰበሰበውን መጠነ ሰፊ ሃብት ከተጠቀመ በተለያዩ ክልሎች የዘረጋውን የጥቅምና የስለላ መረብ አንቀሳቅሶ አላማውን ለማሳካት ወይም እስከመጨረሻው ለመፍጨርጨር የሚገታው ነገር እንደማይኖር መገመትም ቀላል ነው ።
አቶ ለማ መገርሳ በቅርቡ በክልላቸው አንድ የምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደገለጹት ከህወሃት ጋር ተመሳጥረው ሲዘርፉ ፤ ፍትህ ሲያዛቡና ህዝብ ሲያሰቃዩ የኖሩ በየቦታው አኩርፈው የተቀመጡና ባገኙት አጋጣም ለውጡን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ “ትናንሽ ሜቴኮች” በየቦታው ስላሉለትም ከባዶ ሜዳ እንደሚነሳ ጀማሪ ታጋይ ሊታይና ሊያደርሰው የሚችለው ጉዳት መጠን ችላ ሊባል የሚገባ ሃይል እንደሆነ ይታወቃል። እነዚህ ትናንሽ ሜቴኮች ኦሮሚያን ጨምሮ በተለያዩ የአገርቱ ክልሎች ከህወሃት ሥርዓት ጋር ወግነው ያገኙትን የኢኮኖሚና የሥልጣን ጥቅም ዘላቂነት ለማረጋገጥ የህወሃትን የቅልበሳ አጀንዳ ለማስፈጸም ምን አይነት እምቅ ጉልበት እንዳላቸው በተለያዩ ወቅቶች አሳይተዋል ፤ እያሳዩም ነው። የእነዚህ አይነቶቹ ትናንሽ ሜቴኮች በብዛት በአማራም ፤ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችም ፤ በቤኔሻንጉል ጉሙዝም ፤ በሱማሌም ፤ በአፋርም ክልሎች ውስጥ አሉ። ዋና ተግባራቸውም የአንድ እግራቸውን ጫፍ የለውጡ ሜዳ መስመር ውስጥ አስገብተው በተቀረው እግራቸውና መላው ጉልበታቸው የለውጡ ትሩፋቶች ከላይ ከክልል እስከ ወረዳና ቀበሌ እንዳይወርድ በዘዴ ሂደቱን አንቆ መያዝ ነው። ኢትዮጵያ በአለም ዙሪያ በከፈተቻቸው የኤምባሲና የቆንሲላ ጽ/ቤቶች ውስጥ ተመድበው የሚያገለግሉ አብዛኛው ዲፕሎማቶችና ሰራተኞቻቸውም ይህንን ዘዴ በመጠቀም የመቀሌው ቡድን አሸንፎ እስኪመጣ ጊዜ መግዛት እንደሆነ በግልጽ ይታይባቸዋል።
አዛውንቱ ስብሃት ነጋ፤ አባጸሃይ፤ ጌታቸው አሰፋ፤ ስዩም መስፍንና አለም ገብረዋህድ ከመቀሌ መሽጎ የቅልበሴ ሴራ እንቅስቃሴውን የሚመራው ቡድን መሪዎች እንደሆኑ የሚያረጋግጥ መረጃ አለ። እነዚህ 5ቱ ጎምቱ ህወሃቶች ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ናቸው በሚባሉት የማዕከላዊ ኮሚቴውና የሥራ አስፈጻሚው አባላት ይሁንታን ያገኙ እንደሆነም ይነገራል። ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በዚህ ቡድን ውስጥ እንዳልተካተተና ከትግራይ አስተዳዳሪነቱም ተገፍቶ በነዚ ሰዎች ቁጥጥር ስር የታዘዘውን ብቻ የሚፈጽም ሆኖአል ነው የሚባለው። ዛሬ በአገራችን የተለያዩ ቦታዎች የሚፈነዳዱትን የግጭት ፈንጂዎችና ሰላምና መረጋጋትን የሚያውኩ የሥረአተ አልበኝነት ተግባራት የሚመሩትና ፋይናንስ የሚደርጉት በእነዚህ 5ቱ ግለሰቦች በሚመራው ኮሚቴ ነው ። በረከት ስሞኦን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር እስከዋለበት ጊዜ ድረስ ዋና አማካሪና ስትራቴጂስት ሆኖ ከቡድኑ ጋር ይንቀሳቀስ እንደነበር በእርግጠኝነት የሚመሰክሩ አሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ እየተካሄደ ያለውን ህገወጥ የመሣሪያና የገንዘብ ዝውውርን በዋናነት የሚያንቀሳቅሰውም ይሄው ቡድን እንደሆነ ይታወቃል። የቡድኑ የአጭር ጊዜ ዕቅድ ተብሎ እየተሰራ ያለው ከአገር አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ በዚህ አጭር ጊዜ እውቅናና ዝና የተቸረውን የዶር አቢይ መንግሥት ለማሳጣት ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር ማድረግ ነው። ዩኑቨርሲቲዎች፤ ቤተእምነቶችና የሃይማኖት ተቋሞች፤ የማንነትና የድንበር ጥያቄዎች ያሉዋቸው ዞኖችና ወረዳዎች በቀላሉ የግጭት መቀስቀሻ መሣሪያ ለመሆን የተመቹ ናቸው ተብለው የተለዩና በእጅ አዙር ከፍተኛ ገንዘብ እየፈሰሰባቸው የሚገኙ ፕሮጄክቶች ናቸው።
መንግሥት ፈጣን እርምጃ በመውሰድ አከሸፈው እንጂ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን የዘረጉትን የጥቅምና የሥልጣን ሰንሰለት ተጠቅመው የኢትዮጵያ ሱማሌን ክልል ወደ ስኦልነት ለመቀየርና ከኢትዮጵያ ራሷን የምታገል የመጀመሪያዋ ክልል እንድትሆን ለማድረግ ከፍተኛ እቅድ እንደነበረም በመንግሥት ሚዲያ ጭምር የተገለጸ ጉዳይ ነው። በአፋርና በቤነሻንጉል ክልሎችም ቀብረውት የነበረው ፈንጂ በጊዜ እንዲመክን መደረጉ እንደ አገር በጅቶናል። መሣሪያውን አውርዶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል በመቀሌ በኩል ወደ አገሩ የተመለሰው የአቶ ዳውድ ኢብሳ ኦነግም በትግል ወቅት ያልነበረውን ትጥቅና የሰራዊት ብዛት አንቀሳቅሶ ምዕራብና ምሥራቅ ኦሮሚያን የግጭትና የሁከት መናሄሪያ ለማድረግ የቻለበት አቅም ምንጭ ምን እንደሆነ ገና መልስ አላገኘም። ተጋብቶና ተዋህዶ የሚኖረውን የቅማንት ህዝብ ከአማራ ወገኑ ጋር ለማጋጨት ሲጎነጎን ከቆየው ሴራ በተጨማሪ ሰሞኑን ደግሞ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር ውስጥ ቤተእምነቶችን በኢሳት በማጋየት አንዱን ሌላው ላይ ለማስነሳት እየተሰራ ያለ ወንጀል እየተመለከትን ነው።
ሌላው የቅልበሳ ሃይሉ በተጠናከረ መንገድ እየሰራበት ያለው ማህበራዊ ሚዲያዎችን ነው። እንደ ግሪሳ ወፍ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሰፍረው የሚውሉትና የሚያድሩት ደመወዝ ተከፋዮቹ አክቲቪስቶቹ ነጋ ጠባ የሚፈበርኩት የሃሰት ዜናዎች ፤ የስም ማጠልሼት ዘመቻዎች ፤ ዘርን ከዘር ለማጋጨት የሚጻፉ የጥላቻ መልዕክቶች ፤ ስድብና ዛቻዎች በሚገባ የታሰበበት ፤ በታቀደና በተቀናጄ ሁኔታ ከአንድ ማዕከል  በሚሰጥ አመራር እየተከናወነ ያለ የቅልበሳ ሴራው ዘመቻ አካል ነው። ግሪሳው በተለይ ልዩ ትክረት ያደረገው ለህወሃት አገዛዝ ዕድሜ ማጠር በጋራ የተንቀሳቀሱትን የአማራና የኦሮሞ ማህበረሰብን እርስ በርስ ማጋጨት ይሁን እንጂ አብዛኛው ማህበረሰብ ለትግራይ ህዝብ የተለየ ጥላቻና ቂም ያለው በማስመሰል ለህሊውናው ሲል ተሸማቆ በፍርሃት ከህወሃት ጉያ ተወሽቆ እስከመጨረሻው ጸንቶ እንዲቆም ማድረግንም ይጨምራል።
ሃፍረትና ይሉኝታ ያልፈጠረባቸው የቡድኑ አባላት በሰጡዋቸው አመራር ለኦሮሞና ለአማራ ተቆርቋሪ መስለው የለውጥ ሃዋሪያት የሆኑትን የሁለቱን ማህበረሰብ አመራር አባላትን ሲያብጠለጥሉ ይውላሉ። አቢይና ለማ ለኦሮሞ ህዝብ አልቆሙም ፤ ገዱና ደመቀ አማራን አይወክሉም በማለትም ነጋ ጠባ ያብጠለጥሉዋቸዋል። በስሜት ለሚነዱትና የነርሱን ተንኮል ለመረዳት አቅም ያነሳቸውን ዜጎች ስሜት በሚኮረኮር አጀንዳ ይሰጡዋቸዋል።
ይህ ሁሉ ሲሆን መንግሥት ዝም ብሎ የሚመለከተው እየሆነ ያለውን ነገር የማያውቅ ወይም እርምጃ ለመውሰድና ለማስቆም አቅም የሚያጥረው ሆኖ እንዳልሆነ መገመት ከባድ አይደለም። ታዲያ ምንድነው ችግሩ ፤ ምን እስኪሆንስ ይጠበቃል? እነዚህን ሰዎች መናቅና የትም አይደርሱም ብሎ ጊዜ መስጠት ሊያደርሱት የሚችለውን ጉዳት መፍቀድስ አይሆንም ወይ ? የሚሉ ጥያቄዎች ለውጡ እንዳይቀለበስ የምንጨነቅውን ሁሉ የሚያሳስብ ነው።
በእርግጥ ለውጡ የመጣውና የሚመራው በዋንኛነት በራሱ በኢህአደግ እንደመሆኑና ኢህአደግን እንደፈለገው ሲያሾረው የኖረው ህወሃት አሁን ምሽግ ያደረገውን ትግራይ ክልል ላለፉት 40 አመታት ያለምንም ተቀናቃኝ አፍኖ የያዘና ከላይ እስከ ታች ቁርኝት የፈጠረ በመሆኑ በቀላሉ ከህዝቡ ነጥሎ እርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል እንረዳለን። ሆኖም ግን ህወሃት በሌሎች ክልሎች የዘረጋውን የጥቅም ሠንሰለት ተጠቅሞ ትግሉን ለመቀልበስ ወይም የትግሉ ትሩፋቶች እስከ ታቺኛው የወረዳና ቀበሌ መዋቅሮች እንዳይዘልቅ እንቅፋት የሆኑትን ግለሰቦች አንድ በአንድ ነቅሶ በማውጣት በቁጥጥር ሥር ማዋልና የመቀሌውን ቡድን ሴራ የማክሸፍ እርምጃ መውሰድ ይህን ያህል አስቸጋሪ መሆን አልነበረበትም ብለን የምናምን ብዙዎች ነን። በወረዳና በዞን ደረጃ ባሉ አስተዳደራዊና አገልግሎት ሰጪ እርከኖች ላይ ተቀምጦ ለውጡ ሥር እንዳይሰድ የሚያደናቅፉትን በቀላሉ መለየትና ከያዙት ሃላፊነት ማንሳት ይቻላል። መንግሥት በተለይም የለውጥ ሃይሉ ይህንን ሃላፊነቱን እንዲወጣ አጥብቀን እያሳሰብን ለውጡን እንደብቸኛ የአገር መዳኛ መፍትሄ የምንመለከት ሁሉ በያለንበት የሚከተሉትን ተግባራት በማከናወን መቀሌ ከመሸገው ወንጀለኞች ቡድን እየተጠነሰሰልን ያለውን እርስ በርስ የመጠፋፋት አደጋ ማመከን እንችላለንና የየድርሻችንን እነወጣ ኣላለሁ። በይቻላል መንፈስ !
1. በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰማሩት ግሪሳዎች የሚበትኑትን የጥላቻና የክፍፍል ማቴሪያሎችን ተቀብለን ከማስተጋባት መቆጠብ
2. በየትኛውም የቋንቋና ባህል ማህበረሰብ ወይም ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የሚሰነዘር የጥላቻ ወይም አንዱን አሳንሶ አንዱን ከፍ የማድረግ እሰጣ ገባ ውስጥ አለመግባት ፤ ከተቻለ ያንን አይነት መልዕክት የሚያሰራጩትን የፌስቡክ ጓደኞቻችንን ከጓደኝነት ማባረር ወይም ብሎክ ማድረግ
3. ላይ ላዩን ሲታይ ከመብት መቆርቆር የመነጨ የሚመስል ነገር ግን በደንብ ከቃኘነው እኛን ለመከፋፈልና ለማበጣበጥ ያለሙ አጀንዳዎችን በጥንቃቄ መለየትና ከማራገብ መቆጠብ
4. ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የዘመናት ችግራችንንና በነርሱ ምክንያት ታፍኖ የኖረው መብት ወይም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በወራት ዕድሜ ውስጥ መልስ ማግኘት እንደማይችል ተገንዝበን ይህ የተጀመረው ለውጥ ተጠናክሮ ከቀጠለ ብቻ ጥያቄዎቻችን መልስ እንደሚያገኙ ማመንና ለተግባራዊነቱ በንቃት መሳተፍ
5. በትምህርት ቤቶች፤ በእምነት ቦታዎች ፤ ማህበረሰቡ ተሰባጥሮ በሚኖርባቸው መንደሮችና በሥራ ቦታዎች የሚደረጉ አፍራሽ ቅስቀሳዎችን ወይም ወደ ግጭት የሚያመሩ ትርክቶችን በተቻለ አቅም ለማክሸፍ መጣር ፤
6. ህገወጥ የመሣሪያና የገንዘብ ዝውውር እንቅስቃሴን ለማስቆም ሲባል ዕቃ የሚጭኑትንና የሚያራግፉትን ተሽከርካሪዎች በንቃት መከታተልና ጥርጣሬ የሚጭር ነገር ከተገኘ ወዲያውኑ በአቅራቢያው ለሚገኝ ፖልስ በማሳወቅ ትብብር ማሳየት፤
7. ህወሃት ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ወደ ትግራይ የተካለሉ የጎንደር ፤ የወሎና የአፋር ይዞታዎች ላይ የተነሱ ህጋዊ ጥያቄዎች ወደ ግጭት እንዳያመሩ በቂ ጥንቃቄ ማድረግ (መንግሥት ከሰሞኑ ያቋቋመው የማንነትና የወሰን ኮሚሽን ጥናት ተጠናቆ ለመንግሥት እስኪቅርብና በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ወደ ቦታ እስኪመጣ መታገስ )
8. የአዲስ አበባ ይዞታ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችንም እንዲሁ በምርጫ የሚቋቋመው መንግሥት እስኪመጣ ማዘገየት (የድረደዋና የሀረርንም ጉዳይ እንዲሁ)፤
9. ከፖለቲካ አመለካከቶቻችን የሚመነጩ ልዩነቶች በሠለጠነና በሰከነ መንገድ በውይይት ፤ በድርድርና ከፍም ካለ በህዝበ ውሳኔ ለመፍታት እራስን ማዘጋጀት (መሰልጠን) ፤
10. ማንም ግለሰብ ፤ ቡድን ፤ ፖለቲካ ድርጅት ወይም ተቋም አሁን አገራችን በደረሰቺበት ተጨባጭ ሁኔታ እምነቱን ፤ ፍላጎቱን ወይም ምኞቱን በሃይል አስፈጽማለው የሚል አመለካከት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በቅንነት ለማየትና ከዚያ ለመራቅ መወሰን ፤
11. በማንግባባቸው የታሪክ ምዕራፎች ላይ ሙጉትና ክርክር ለመግጠም አለመፍቀድ
12. የቀረውን እናንተ ጨምሩበት
ይህ ሃሳብ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በግሌ የሚሰማኝ ሃሳብ እንጂ በአባልነት የምሳትፍበትን የፖለቲካ ድርጅት አመለካከት ወይም አቋም የሚያንጸባርቅ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ (የድርጅት አቋምንና በድርጅት ውስት ጉልህ ሚና ያላቸውን ግለሰቦች የግል እይታ ለመለየት የሚቸገሩ ወገኖቼን ለማሳሰብ ነው)) ።
Filed in: Amharic