>
5:18 pm - Saturday June 16, 7291

ይድረስ ለክቡር ዶክተር አብይ አህመድ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር (ዳግማዊ ሲሳይ - ከቤልጂግ ሄል ከተማ)

ይድረስ ለክቡር ዶክተር  አብይ አህመድ

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

አዲስ አበባ

 

 

 

              ጉዳዩ፦ኢትዮዽያ ከሰላም ሚኒስቴሯ ይልቅ የመቻቻል ሚኒስቴር እንዲኖራት ስለመጠየቅ

መግቢያ

በእርሶ የሚመራው ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ በሀገሪቱ እየታየ ያለው የመልካም ጅማሬ ለውጥ ይበል የሚያሰኝና የወደፊቷን ያደገችና የዜጎቿን መብት የምታከብር ሀገር እንደምትሆን ተስፋ ያደረጉና ያደረግን ኢትዮዽያውያን ብዙዎች እየሆንን ነው።እንደሚታወቀው እየተካሔደ ያለው ለውጥ የብዙዎችን ህይወት የበላና እየበላ ያለም ነው።ይህ ከአዝጋሚነቱ ይልቅ በሰበር ዜናዎች የተጥለቀለቀው ፈጣን ለውጥ ይዞት የመጣው በረከት የመኖሩን ያክል እርግማኑንም እያየነው ነው።ታፍነው የነበሩ የዘርና የሀይማኖት ችግሮች ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው በየቦታው እየታዩ መሆናቸው የምርቃት እርግማን ሆኖብኛል። እነዚህን በየቦታው ብቅ ብቅ እያሉ ያሉትን ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ለማስወገድ ማዕከላዊ መንግስቱ በሆደ ሰፊነት ምክኒያት ተገቢውንና አፋጣኙን እርምጃ እየወሰደ ባለመሆኑ ጥፋቶቹና ውድመቶቹ የሚያስደነግጡ እየሆኑብኝም ነው።

በመከባበርና አብሮ በመኖር የሚታወቀው ህዝባችን ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የተለያዩ አስፀያፊና አስነዋሪ ድርጊቶችን ሲፈፅም መመልከቱ በተለይም በሰው ሀገር ላይ ሆነው ሲያስቡት ያማል!ያቆስላል። ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ከእነ ህይወቱ ዘቅዝቆ ሰቅሎ መግደል አረመኔ እየተባለ የሚወገዘው አዶልፍ ሂትለር እንኳ ያልፈፀመው ዘግናኝና አስነዋሪ ድርጊት ነው።ከዚህ በተቃራኒው በደቡብ ክልል የሆነውን ስናይ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ህዝባችን አስነዋሪ ድርጊትን ይፈፅማል ብለን እንዳናስብ ያደርገናል። እርጥብ ቄጤማ ይዞ ተንበርክኮ ወጣት ልጆቹን ከጥፋት የሚመልስ የመልካም አባት ስብስብም እንዳለን የሚያሳይ ነው።በርግጥ ነው ያለፉትን ሀያ ሰባት አመታት ዊዝደም /ጥበብ/ የሌለው ትውልድ ተፈጥሯል። ታላላቆቹን የማያከብር፣ የሀገር ፍቅር ማለት ምን ማለት እንደሆነ የማይገባው፣በመሰደዱ ኩራት እንዲሰማው የሆነ፣ እውቀት ማለት ዲግሪና ዲፕሎም ከመጫን ባለፈ ክህሎት የሌለው፣ በአቋራጭ መክበር ስልጣኔ የሚመስለው እና የመሳሰሉት ፀባይ ያለው ትውልድ ተፈጥሯል። በተጨማሪም ከሀገራዊ ማንነቱ ይልቅ በጎጡ እንዲያስብም የተደረገ ትውልድ ተፈጥሯል። እውነት ነው እርሶም ኢትዮጵያን ደጋግመው ስሟን እያወደሱ ያክብሯት እንጂ የሚመሩት የጎጥ ፓርቲ ነው። ለእኔ የለውጡ ትልቁ ቁልፍ አሁንም በእርሶ እጅ ያለ ቢሆንም እስከ አሁን ላደረጓቸው የመልካም ጅምር ለውጦች ምስጋና ቢገባዎት ነው እንጂ አያንስቦትም።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

እንደው ዝም ብዬ በጥሞና ኢትዮጵያ ምንድነው የጎደላት የሚለውን ሳስብ አንድ ድሮ የነበረን አሁን ግን ያጣነው መቻቻልን ነው። መቻቻል የሚጀምረው ከቤት ነው። ባል ሚስቱን፤ሚስትም ባሏን፤ወንድም እህቱን፤እህትም ወንድሟን፤እናትና አባት ልጆቻቸውን፤ልጆቻቸውም እናትና አባቶቻቸውን የመቻል ተፈጥሯዊ ስጦታ የተሰጣቸው ይመስለኛል፤ ምክኒያቱ ባይሆን ኖሮ አይደለም ለአመታት ይቅርና ለአንድ ሰከንድም ቢሆን አብረን ልንቆይ አንችልም። እርሶና ባለቤቶ ስንት ጊዜ ተጋጭታችኋል? ስንት ጊዜስ አስቀይመዋቸዋል?እርሳቸውስ ስንት ጊዜ አስቀይመዎታል? መቼም ሁልጊዜም ከልጆችዎ ጋር ሰላም እንደማይሆኑም አምናለሁ። ሁሉንም ግን ያለፉት ስለ ፍቅርና ሰላም ሲሉ በመቻልዎ ነው። ህዝባችን የሀይማኖት ልዩነት ሳይገድበው፣ የዘርና የፖለቲካ ልዩነት ብዙም ሳይረብሸው በእድርና እቁቡ፤በበዓልና ሀዘኑ እየተደጋገፈና እየተጋገዘ እዚህ ደርሷል። አሁን ግን ይህንን መቻቻል አጥቷል፤ስለሆነም መንግስቶ መቻቻል ላይ ቢሰራ እመክራለሁ።

 

የመቻቻል ሚኒስቴር  /Ministry Of Tolerence/

ሁላችንም እንደምናውቀው እርሶ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሀገሪቱ ሰላም እንዲመጣ በማሰብ የሰላም ሚኒስቴር ማቋቋሞ ይታወቃል። በስሩ የተለያዩ የህግ አስከባሪ አካላትን የያዘው ይህ ሚኒስቴር በዋናነት በሀገሪቱ ውስጥ ሰላም እንዲመጣ በትብብር ይሰራል። በርግጥ ስለ ዓላማው ማቋቋሚያ አዋጁ በድረ ገፅ ላይ ለማንበብ ፈልጌ ባለማግኘቴ ሳይሳካልኝ ቢቀርም፤ ሰላምን ከማስፈን በዘለለ ሊኖረው የሚችል ግብ እንደሌለ ግን እገምታለሁ።

ተቋሙ ግብና ተልዕኮው እንዲሁም አላማው ከተቀመጠለት ማዕቀፍ ውጪ ሊሔድ እንደማይችልና የተገደበ እንደሆነም ግልፅ ነው። በመሆኑም የመቻቻል ሚኒስቴር ቢቋቋም ግን ሰላምን ግቡ ያደረገ ስራው ደግሞ ከቤት የሚጀምር በዘላቂነት በመላው ሀገሪቱ ሰላምንና መከባበርን የሚያመጣ ይሆናል የሚል ዕምነት አለኝ። አሁን በሀገራችን እየተከሰቱ ያሉት ችግሮች የሰላም ማጣት ሳይሆን የመቻቻል እጦት፣ የብሶት ድምርና ብዜት ውጤቶች ናቸው። ሰላም ለአንድ ሀገር መሰረቷ ብቻ ሳይሆን ህልውናዋም ጭምር ነው። ይህንን ሊጠብቁላት የሚችሉ በርካታ የጎንዮሽ ስራዎች መሰራት አለባቸው። አንዱ ብሔር ከሌላው፣ አንዱ ሀይማኖት ተከታይ ከሌላው እንዴትና በምን አግባብ አብሮ መኖር እንዳለበት፣ የጋራና የወል እሴቶችን እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል፤ አብሮ በመኖር ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ መሰናክሎችንና ፈተናዎችን በጥበብ እንዴት መኖር እንደሚቻል በመቻቻል ውስጥ በግልፅ ይታያል። መቻቻል ግለሰባዊ፣መቻቻል ቡድናዊ፣መቻቻል ብሔራዊና አገራዊ ነው።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

ሁለት መቶ በላይ ብሔረሰቦች የሚኖሩባት የተባበሩት አረብ ኤመሬት ዜጎች አንድም ቀን በዘር፣በሃይማኖት፣ በቋንቋም ይሁን በፖለቲካ ልዩነት ሲጋጩም ሆነ ሲጋዳደሉ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። በርግጥ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ይህንን ካላት የነዳጅ ሀብት ጋር ቢደምሩትም ከእርሷ ጋር ስትወዳደር ምንም የሌላት ኢንዶኔዢያ በስድስት መቶ ብሔረሰቦች አንድም ቀን ስሟ በክፉ ተነስቶ አያውቅም፤ምናልባት የዛሬ አንድ አመት ግድም ሁለት ከመቶ በሚሆኑት ክርስቲያኖች ላይ ጥቂት እስልምና አክራሪዎች ከፈፀሙት ጥቃት በስተቀር ይህ ነው የሚባል በሀገር ደረጃ ስጋት የሚፈጥር ግጭት ተከስቶ አያውቅም።ታዲያ እኛ ሰማንያ ብሔር ብሔረሰቦች ሆነን እንዴት መቻቻል አቃተን? ትላንት ነበረን የምንለውን የበጎነት መልካም ባህሪያቶቻችንን ማን ወሰደብን? ትናንትናም የነበሩት የእኛ ወላጆች ዛሬ ደግሞ ያለነው እኛ የወላጆቻችን ልጆች!!!

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ያጣነውና የጠፋብን መቻቻል ነው። ቤታችን ያለውን መልካምነት ወደ ጎረቤቶቻችን ከማጋባት ይልቅ በንፉግነት በክፋት ተስፋፍተናል። የሰላም ሚኒስቴርን እርሶ ለምን ዓላማ እንዳቋቋሙት ጠንቅቀው ቢያውቁትም ለእኔ በግብ ደረጃ የሰላም ሚኒስቴርን አቋቁሞ ሰላምን ለማስፈን መሞከር መድረሻን መሳት ይመስለኛል።

የመቻቻል እሴቶችና ጥቅሞች

* በመቻቻል ውስጥ ወጣቶች ከተለያዩ ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ማድረግ፣

* ባህላዊና ሳይንሳዊ የመቻቻል ፍልስፍናዎችን በመቻቻል ሚኒስቴር ውስጥ በጥናትና ምርምር እንዲዳብሩ ማድረግ፣

* ቤተሰብ ለአንድ የተረጋጋ ሀገር መሰረት በመሆኑ ለመቻቻል የመሰረት ድንጋይ መሆኑን ማስተዋወቅ፣

* መቻቻልን በሀገር ውስጥ ለማስፈን የመንግስትን ሚና ከማህበረሰቡ ጋር በማስተጋበር ማጉላት፣

* መቻቻል የስብጥር ባህሎች ስብስብ፣አብሮ የመኖር ውብ ዜማ፣የመከባበርና አንዱ የሌላውን መብት የማክበር ድምርና ብዜት ውጤት መሆኑን ማስገንዘብ፣

*መቻቻል ከአንድ ማህበረሰብ የዕለት ከዕለት የኑሮ መስተጋብር የሚመነጭ፣ በጋራ ለጋራ ጥቅምና አብሮነት ዜጎች የሚያዳብሩት ከማህበራዊ እሴቶቻቸው ውስጥ አንዱና ዋነኛው ማድረግ፣

*ማህበረሰቡን ከሚያለያዩት ነገሮች ይልቅ የጋራና አንድ በሚያደርጉት ነገሮች ላይ እንዲያብር  ማድረግ፣

* የመቻቻልን ጥቅምና መርሆች የህዝብ እንደራሴዎች በሚገባ እንዲያውቋቸው አድርጎ ሀገሪቷ የምታወጣቸው ህጎች በዚህ ማዕቀፍ እንዲቃኙ ማድረግ፣

* የመቻቻል ሚኒስቴር ከሰላም ሚኒስቴርነት በተሻለ ችግሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ከመሰረታዊ ፍልስፍናው በመነሳት የተሻለ ተደራሽነት ያለው መሆኑ፣

* በአንድ ወቅት ሔለን ኬለር እንዳለችው የትምህርት የመጨረሻው ውጤት መቻቻል ነው” ብላ ነበር እናም ማህበረሰባችን ስለመቻቻል የሚኖረውን ግንዛቤ መሰረት ለማስያዝ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ቢሰጥ፤

* ሮበርት ግሪን ኢንገርሶል በበኩሉመቻቻል ማለት አንተ እንዲሆኑልህ የምትፈልጋቸውንና የምትጠይቃቸውን ነገሮች ለሌሎችም አለመንፈግ ነው” እንዳለው ይህ ማለት መቻቻል ግለሰቦች ለእኔ ብቻ በሚል ከንቱ ስግብግብነት ታውረው ሌሎችን ማዳከሚያ እንዳያደርጉበት ንቃተ ህሊናን የማሳደግ ስራ ሊሰራበት እንደሚገባ ያመለክታል።

ብሔራዊ የመቻቻል ቀን ፌስቲቫል /The National Festival Of Tolerence/

ይህንን ሀሳብ ወደ ማህበረሰባችን ለማስረፅ ብሔራዊ የመቻቻል ቀን ፌስቲቫልን በሀገር አቀፍ ደረጃ ማክበር ብንጀምር፦

* የተጀመረውን ለውጥ ከማስቀጠል አንፃር መሬት የሚያስረግጥ መሆኑን፣

* ዜጎች የጋራ የሆነ እሴታቸውን ለማሳደግ እድል የሚሰጥ መሆኑን፣

* አብሮ የመኖር ይትባህላችንን ከሚደርሱብን መገዳደሮች ለመጠበቅና በተቀዳጀናቸው መልካም የለውጥ ጅማሮዎች ላይ በጋራ እንድንፈትሽና የተሻለ ነገን ለማመለከት፣

* አንደኛው ባህልና አኗኗር የሌላኛውን ባህልና አኗኗር እንዲያውቅና እንዲጠብቅ፣

* የአብሮነት፣ወንድማማችነት፣እህትማማችነትና ቤተሰባዊነት ስሜትን በዜጎች መካከል ለመፍጠር ቁልፍ ሚናን

ስለሚጫወት፤

የአከባበሩ ይዘት

ከዚህ ቀድምም ሆነ እስከ አሁንም ድረስ ኢትዮዽያችን የብሔር ብሔረሰቦች ቀንን ስታከብር ከርማለች። በየዓመቱ እስከ አርባ ሚሊየን ብር የሚደርስ ውጪ ሲበላ የከረመው ይህ ቀን፤ ግለሰቦች ኪሳቸውን ሲያደልቡበት ከመክረማቸው በቀር ፍፁም አላማውን ስቶ የተጓዘ መሆኑም ለማንም ግልፅ ነው። ይህ ቀን ዓላማውን አሳክቶ ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ዕልቂት በዜጎች ላይ ባልደረሰ ነበር፤

አንደኛው ብሔር በሌላኛው ብሔር ላይ እጁን ለማንሳት የሞራል ልዕልናንም ባላገኘ ነበር። ስለሆነም ከትናንት

ስህተት በመማር እንዳይደገም ይህንን ጠባሳ የሚሽር ብሔራዊ ቀን ያስፈልገናል።

*ይህንን ቀን በአሸሼ ገዳሜ ከማሳለፍ ይልቅ፦

*ጥናታዊ ፅሁፎች፣

* የየብሔሩ ባህላዊ ጭፈራዎችና አመጋገቦች፣

*በተማሪዎችና በትምህርት ቤቶች መካከል የጥያቄና መልስ ውድድሮች፣

*ሲምፖዚየሞችና ወርክሾፖችን  ለተከታታይ ሶስት ወይም አራት ቀናት በማካሔድ የተሻለ መቻቻልን ያሳየ ክልል የሚሸለምበትና እውቅና የሚሰጥበት፣ በበጀትም በድጎማ መልክ ለክልሉ ማጠናከሪያ የሚሰጥበት ቢሆን፤ክልሎች የተሻለ የመቻቻል ዓላማን ለማሳካት ትልቁን ሚና ይጫወታሉ።

 

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

እዚህ ድረስ ከደረሱ የፅሁፌን ሙሉ ሃሳብ አግኝተውታል ብዬ እገምታለሁ። ስለ ውድ ጊዜዎትም ከልብ አመሰግናለሁ። እንደቃልዎ ተገኝተው ስልጣን ሳያጓጓዎ በምርጫ ተሸንፍው መንበርዎን ለማስረከብ ያብቃዎ እላለሁ!!

 

የሲሳይ ተድላ ልጅ ዳግማዊ

ከቤልጂግ ሄል ከተማ

ግልባጭ

በኢትዮዽያና ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚገኙ ብዙሃን መገናኛዎች

Filed in: Amharic