>

ከኢሕአዴግ ፌዴራሊዝም ወደ መደመር ፌዴራሊዝም እንሻገር (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

ከኢሕአዴግ ፌዴራሊዝም ወደ መደመር ፌዴራሊዝም እንሻገር

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

የኢሕአዴግ ፌዴራሊዝም በብሔር ወይም በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ነው እንዳልል ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔሮች ሆኑ ሁሉንም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ማካተት ቀርቶ ባብዛኛው እንኳን የማያሳትፍ ስለሆነ በተለምዶ የዘር (ethnic) ፌዴራሊዝም የሚባለውን አጠራር መጠቀም አልችልም። አሁን ያለው ፌዴራሊዝምን “የኢህአዴግ ፌዴራሊዝም ” ከማለት በቀር ሌላ ቃል ላገኝለት አልቻልኩም። በዚያው መልክ ወደፊት እንዲኖረን የምሞግተው ፌዴራሊዝም በዓይነቱ አዲስ መሆን ያለበት ስለሆነ “የመደመር ፌዴራሊዝም ” በማለት ለመግለፅ ወድጃለሁ።

በኢትዮጵያ ከ 80 በላይ ብሔረሰቦች ወይም ጎሣዎች እንዳሉ እናውቃለን። የኢሕአዴግ ፌድራላዊ መንግስት ጥቂት ጎሣዎችን አግንኖ እና ብዙ ጎሣዎችን ጨፍልቆ በክልል መንግስታት አደራጀን። በእውነት ሁሉንም ጎሣዎች በእኩልነት የሚዳኝና የሚያስተናግድ ስርዓት አይደለም። ከዚያም በላይ የኢትዮጵያን አንድነት ጥያቄ ውስጥ የሚከትና እርስ በርስ በማጋጨት የሚያፈናቅል ስንክሳር ሆኖ እየተገለጠ ይገኛል። ይህንን ውጥረት ለመፍታት የብሔር ፖለቲካና የዜግነት ፖለቲካ በሚያደርጉት ሩጫ፥ መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ ራሳቸው የእርስ በርስ ውጥረት ውስጥ ገብተዋል። ያም የሆነው የኢሕአዴግ ፌዴራላዚም በሚያመጣው ተፅዕኖ ምክንያት ነው። ለዚህም ነው ይህ የኢሕአዴግ ፌዴራሊዝም ራሱ ችግር መሆኑ ብቻ ሳይሆን፥ ሌላ መፍትሔም እንዳይመጣ ጭምር የሚያስረንና የማይድን የኢትዮጵያ በሽታ መስሎ የሚታየው።

በብሔር ፖለቲካ እና በዜግነት ፖለቲካ መካከል ያለውን ፍጥጫ በስኬት ለመፍታት፥ መደመር ላይ ከተመሰረተው ሀገር በቀል የኢትዮጵያዊነት ርዕዮተ ዓለም ውስጥ አስታራቂ የመደመር ፌዴራሊዝምን ፈልቅቆ ማውጣት ያስፈልጋል። ይህ መደመር ብሎ ነገር፥ ከስሜታዊ ትርክቶች አልፎ መሰረታዊ የሆኑ የማንነት ጥያቄዎቻችንን የሚመልስና በብዝሃነት አንድነት አያይዞ ወደፊት የምንሄድበትን አቅጣጫ ማመላከት መጀመር ያለበት ወቅት አሁን ይመስለኛል።

በአንድ በኩል ለእውነት እኩልነትና የማንነትን ጥይቄ በፍትሀዊነት ለመመለስ የመደመር ፌዴራሊዝም ስሌት መፍትሔ አለው። ደግሞም በልዩነት የማይበጣጠስ ግን በልዩነት የሚደምቅና የሚሰምር እውነተኛ አንድነት እንዲኖረን የመደመር ፌዴራሊዝም ፋይዳ ያመጣል። ይህም የሚሆነው የመደመር ፌዴራሊዝም የብሔር ፖለቲካንና የዜግነት ፖለቲካን አቻችሎ ሁለቱም አብረው እንዲያሸንፉ የመፍትሔ መውጫ አቅጣጫ ስለሚያስቀምጥ ነው። በዚህም ምክንያት እንድንነካከስና እንድንጠፋፋ ከተጠመደልን ወጥመድ ሰብረን በብልሃትና በትልቅ ጥንቃቄ አንድ ላይ ተያይዘን እንድናመልጥ የመደመር ፌዴራሊዝም አቅም ይሰጠናል።

በአንድ በኩል ጎሣዎች የራሳቸውን እድል በራስ በማስተዳደር እንዲወስኑ እንፈልጋለን። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ጎሣዎች ስብጥርና በጂኦግራፊ አቀማመጥ ድብልቅ እንደሆነ እናያለን። ደግሞም 80 በላይ የሆኑ ጎሣዎች በእኩልነት እንዲወከሉና ሁሉም ድምፅና ተሰሚነት እንዲኖራቸው እንፈልጋለን። ለዚህ አንደኛው መድሓኒት ጎሣን በዞን ደረጃ መከለል ነው። ይህ አናሳ ጎሣዎች ሁሉ የየራሳቸው የዞን ክልል እንዲኖራቸው ዕድል ይሰጣቸዋል። ትላልቅ የሆኑት ጎሣዎች ደግሞ በየአቅራቢያቸው ዙሪያ በየቀጠናቸው እየሆኑ ከአንድ በላይ የዞን ክልሎች እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል። እያንዳንዱ ዞን ራሱን እንዲያስተዳደርና ለሕዝብ ተወካዮችም ከዞናቸው በመላክ በፓርላማ መሰየም ይችላሉ።

ከዚያ ባለፈ እነዚህ በጎሣዎች የተዋቀሩት ዞኖች በመንግስታት ስር የሚከለሉት በጂኦግራፊ ይሆናሉ። ያ ማለት የደቡብ ክልል መንግስት፥ የሰሜን ክልል መንግስት፥ የምዕራብ ክልል መንግስት፥ የምስራቅ ክልል መንግስት፥ የደቡብ ምስራቅ ክልል መንግስት፥ የሰሜን ምዕራብ ክልል መንግስት፥ ወዘተ በማለት ማዋቀር ይቻላል። እያንዳንዱ መንግስት በውስጡ የተለያዩ ዞኖች ይዞ “ትንሿ ኢትዮጵያ” በመሆን የገለጣል። ፓርላማ በዚህ ዓይነት የብሔር ማንነትን እና የዜግነት እኩልነትን ባስታረቀ መልኩ በሕዝባዊነት መሠረት ላይ ቢታነፅ መካከለኛ ቦታ ላይ ሁላችንንም ያገናኘናል ብዬ አስባለሁ።

ይህን ዓይነት በጂኦግራፊ የተመሰረተ መንግስታት እንዴት ማድረግ እንችላለን እንዳንል፥ በፍርደ ገምድልነት አንዱን ብቻ ነጥለን የደቡብ ክልል መንግስት ብለን አናሣ ጎሳዎችን አንድ ላይ ደምረን መንግስት እንዲኖራቸው ለ 27 ዓመት ያደረግን ጉደኞች ነን። ያንን ለደቡብ ሕዝብ አድርገን ስናበቃ “ትንሿ ኢትዮጵያ” ስንል፥ በዚያው መስፈርት ራሳችንን መዝነን በሁላችንም ላይ በፍትሀዊነት ለምን አላደረግንም? የሞራል ልዕልና ካለንና ራሳችንን ከሌላው በላይ አድረገን በእውነት ማየት የማንፈልግ ከሆነ፥ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ የመደመር ፌድራላዊ መንግስት ስር ያሉ የደቡብ፥ የሰሜን፥ የምዕራብ፥ የምስራቅ ወዘተ መንግስታት እያልን በፍትሀዊነት ማስተካከል ይጠብቅብናል።

ይህን ስናደርግ መደመርን በተፈጥሯዊ (organically) እንዲያድግ እንፈቅዳለን። በመጀመሪያ ደረጃ በጂኦግራፊ በተመሰረቱት ክልል መንግስታት ውስጥ ያሉ የተለያዩ በጎሣ የተዋቀሩ ዞኖች መደመርን አቅራቢያቸው ካሉት ኢትዮጵያውያን ጋር ይለማመዳሉ። በሁለተኛ ደረጃ በኢትዮጵያ የመደመር ፌድራላዊ መንግስት ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ መደመርን በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሳልጣሉ። በሶስተኛ ደረጃ መደመርን ለአፍሪካ በመሸጥ ምስራቅ አፍሪካ ብሎም መላው አፍሪካ ወደ አንድነትና አብሮነት በመጠቅለል መደመር በጥቁር ሕዝብ ላይ ብሩህ ብርሃን ያበራል። በአራተኛ ደረጃ ለዓለማችንም ይህ የመደመር ህሳቤ ገፀ በረከት ሆኖ ይተርፋል።

የኢትዮጵያ የመደመር ፌድራላዊ መንግስትን ደግሞ የሚመራ (ጠቅላይ ሚኒስቴር ወይም ፕሬዚዳንት) ሕዝቡ ራሱ እንዲመርጥ በማድረግ፥ የሚልቅ አሳብ የያዘ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከአናሣ ጎሳም ጭምር ለመመረጥ ፍትሀዊነት ያለው ዕድል ይኖረዋል።

በኢህአዴግ ፌዴራሊዝም ጣጣ ምክንያት ብዙ ቁጥር ያላቸው ጎሣዎች ሊሂቃን የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ተመልከተውና ለአናሣዎቹ ብሶት ጆሮ ዳባ ብለው የራሳቸው የሆነውን ለማግነን ተገደው ደፋ ቀና ይላሉ። ዛሬ እኩልነትን ስናቀነቅን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲሆን ሆኖ እንዲሰራ ሳይሆን፥ ብዙ ቁጥር ያለው ሕዝብ ሊሂቃን በየፊናው ራሳቸውን የበላይ የሚያደርጉበትን ስሌት ለመቀመር በራሳቸው ዘር ላይ እንዲያጠነጥኑ ይገደዳሉ። እነዚሁ ሰዎች ድሮ ድሮ ለጭቁን ሕዝብ ብለው ታግለው ንጉሱን የገረሰሱት በሰው መሆን ስብዕና ላይ ተመሰርተውና ተያይዘው እንጂ፥ እንደ ዛሬ በየግል ጎሣ አጥር ውስጥ ሆነው እየተራኮቱ አልነበረም። ከዚህ ከያዘን አባዜ የምንነቃው የኢህአዴግ ፌዴራሊዝም ለሁላችንም የተለያየ መነፅር ሰጥቶንና በማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ ከቶን የጭቅጭቅ ድራማ እንድንከውን ያደረገን መሆኑን አውቀን ራሳችንን ከዚህ ወጥመድ ስንፈታ ነው።

መደመር ስሌት ላይ አተኩረን ተደምረናል ስንል የድምራችን ውጤት ዜሮ እየሆነ ያሳብቅብናል። መደመር ውጤታማ የሚሆነው ተደምረናል የምንለው ቀናሽ ቁጥር (negative number) እስካልሆንን ድረስ ብቻ ነው። አንዱ ሲተክል ሌላው እየነቀለ የደቦ ድምር ሆነን በዜሮ እንዳንጨርሰው እንጠንቀቅ። ከመደመራችን በፊት ቀናሽ ቁጥር (negative number) ከመሆን ራሳችንን እናፅዳ። ቀናሽ ቁጥር ላለመሆን ደግሞ ለራስ መቆም ብቻ ሳይሆን የወንድሞቻችን (በተለይ የተረሱትና አናሣ ለሆኑት) ፍፁም ፍትሀዊ የመሆን እሳቤ ያስፈልጋል።

ኢ+ት+ዮ+ጵ+ያ = ፍቅር። ኢትዮጵያዊነት የፍቅር ቤት ነው።

1ኛ/ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር ቤት መሰረት የጥቁር ሕዝብ አንድነት ፋና ወጊነት ሆኖ መገኘታችን ነው። ኢትዮጵያዊነትን ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የጎሣዎች ስብስብ በላይ ነው። ይህም የሆነው ኢትዮጵያዊነት በውስጡ የአፍሪካን አንድነት ያረገዘ ራዕይ ሰንቆ እንዲንቀሳቀስ ታሪክ ግድ የሚለው ስለሆነ ነው።

2ኛ/ የኢትዮጵያዊነት የፍቅር ቤት የማዕዘን ምሶሶዎቹ ብዙ ቁጥር ያላቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ጎሣዎች ናቸው። እነዚህም የኢትዮጵያዊነትን ግዙፍ ራዕይ ክብደት የሚሸከሙና በመስዋዕትነት ኢትዮጵያዊነትን የሚያቆሙ ናቸው።

3ኛ/ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር ቤት ግድግዳው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት አናሣ ጎሳዎች ናቸው። እነዚህም እርስ በርስ በመያያዝና ከምሶሶዎቹ ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያዊነትን የፈጠሩ ናቸው።

4ኛ/ የኢትዮጵያዊነት የፍቅር ቤት ጣሪያው የኢትዮጵያ አምላክ ነው። ፈሪሃ ፈጣሪ ያለው ሕዝብ እርስ በርስ ሰላምታ በሰጠና በተቀበለ ቁጥር የፈጣሪን ስም የሚጠራ ሲሆን በረከትን ከሰማይ ይለምናል። ከስንት ጉድ እያወጣን ለዛሬው ብሩህ የተስፋ ጭላንጭል ቀን ያደረሰን ፈጣሪም ዳር ሳያደርሰን አተወንምና በስጋት ከመሽመድመድ ይልቅ ተስፋ በማድረግ መደሳሰት ይቀናናል።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ።
እግዚአብሔር አፍሪካን ይባርክ።
ኢሜል፦ Z@myEthiopia.com

Filed in: Amharic