>

ሁሉን እዩ፣ የሚበጀውንም ያዙ (ምሕረት ዘገዬ)

ሁሉን እዩ፣ የሚበጀውንም ያዙ

ምሕረት ዘገዬ

መጽሐፍ ቅዱስ “ኩሎ አመክሩ ወዘሠናየ አፀንዑ” እንዲል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንም ሁሉንም አይተው የሚበጃቸውን ይይዙ ዘንድ ፈጣሪያቸው አለውድ በግዳቸው በየቀኑ ግለቱ እየጨመረ በሚሄድ እቶናዊ እሳት እንዲፈተኑ አድርጓቸዋል፡፡ “እግዚአብሔር ወዳጆቹን ይፈትናል/አይፈትንም” የሚለውን ክርክር ለጊዜው ወደ ጎን እንተወውና እኛ ግን ክፉኛ እየተፈተንን እንዳለን ዓለም በሞላ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡

የዮሐንስ ወንጌል 3፡18-20 – ልጆች ሆይ፤ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ። እኛ የእውነት ወገን መሆናችንን በዚህ እናውቃለን፤ ልባችንንም በፊቱ እናሳርፋለን፣ ይህም ልባችን በእኛ ላይ በሚፈርድብን ነገር ሁሉ ነው። እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉን ነገር ያውቃል።ወሬ የሚወድ ሰው አይጠድቅም፡፡ ከምሣ መልስ አንድ ወዳጄ ጋር ጭውውት ይዘናል፡፡ ነገዱን አትጠይቁኝ፡፡ ግን አማራም ኦሮሞም አይደለም፡፡ ለኅሊናው ያደረ ትልቅ ሰውና ጨዋም ነው፡፡ ቦሌ የሚሄድበት አጋጣሚ ብዙ ነው – አሁንም ከአንድ ዓመት በፊትም፡፡

የምንጫወተው ስለዘመኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነው – አሁን አሁን አፍ ማሟሻችን ይሄው የሀገር ጉዳይ ሆኗል፡፡ “እነዚያኞቹ ሰውነታችንን አረከሱ፤ በነፍስ በሥጋችን ተጫወቱ፤ እነዚህኞቹ ደግሞ ምን ያመጡብን ይሆን?” የሚለው ጥያቄ ብዙዎችን እያስጨነቀ ይገኛል፡፡ ነገሩ ሁሉ በርግጥም “አያያዙን አይተው ጭብጦውን ቀሙት” እንደሚባለው ሆኖ ነገረ ሥራችን ከእሳት ወደረመጥ፣ ከድጥም ወደማጥ እየሆነ ነው፡፡ ያ ወዳጄ ታዲያላችሁ በጣም ገርሞት “በፊት ከዘብ ጀምረህ የሚገጥምህ የአየር መንገዱ ሠራተኛ ትግሬ ብቻ ነበር – ሌላው ቢኖርም ቁጥሩና የኃላፊነት ደረጃው ጭምር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ አሁን ደግሞ ያ ተገልብጦ የምታገኘው ወታደርም በለው ፖሊስ በሙሉ ኦሮሞ ነው፡፡ ትንሽ ቸኮሉ፡፡ ዐይን እንዳይገቡ ፈራሁላቸው፡፡ ዐይን እኮ ድንጋይም ይሰብራል፡፡ ቋንቋ ደግሞ ስለማይችሉ …፡፡” ሲለኝ ጅምር ዐረፍተ ነገሩን እንኳን አላስጨረስኩትም፡፡ ምክንያቱም ቀድሞውንም አንዳች ነገር ለመጫር በቋፍ ላይ ነበርኩ፡፡ እንዲያውም ሳልዘነጋው ያን ላስቀድመው፡፡

ኢቲቪ ከወያኔ ይዞታነት በቀጥታ ዞሮ ወደ ኦህዴድ ይዞታነት ቦታ ቀይሯል፡፡ ብዙ ምልክቶችን መጥቀስ ቢቻልም ለአሁን አንድ ብቻ በቂ ነው፡፡ በኢሳት ላይ የደረሰውን አፈና፡፡ የኢሳትን ውለታ የኢትዮጵያ አምላክ ይመልሰው እንደሆነ እንጂ እንደዚሁ በቀላሉ “እናመሰግናችኋለን” በሚል የሚያበቃ አይደለም፡፡ ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ የሚጠላቸው ወገን ሁሉ በዚህ ረገድ ለሀገር ላበረከቱት አስተዋፅዖ ምሥጋናውን መሰሰት የለበትም፡፡ ፍርድ ለራስ ነው፡፡ አንድን ነገር በሆነ ምክንያት ልትጠላው ትችላለህ፤ ያለ ነው፡፡ ስትጠላው ውለህ ስትጠላው ብታድር ግን ጠንካራ ጎኑን መካድ አይገባም – ነግ በኔም ነው፡፡ እንደሰው መሳሳት ያለ ነው፡፡ ግን ሕጻንን ከነታጠበበት ውኃ የሚደፋ የልጅ ሞግዚት ወይ ወላጅ እንደሌለ ሁሉ በጠንካራ ጎናችን እንወዳደስ፤ በደካማ ጎናችን ደግሞ በሃቅና በአግባቡ እንወቃቀስ – የጎንዮሽ መልእክቴ ነው፡፡

ቅዳሜ የካቲት 9 ቀን 2011ዓ.ም የኢሳት ጋዜጠኞችን ለመቀበልና ውለታቸውን ለማስታወስ በሚሌኒየም አዳራሽ አንድ ታላቅ ዝግጅት ተካሂዶ ነበር፡፡ ያን ዝግጅት በምን መልክ እንደሚዘገቡት ኢቲቪዎችን እከታተል ነበር፡፡ ሲገቡ ቦሌ ላይ የነበረውን አቀባበል የመንግሥት ባለሥልጣናት ስለነበሩበት ይመስላል ቀንጨብ አድርገው አገባባቸውን ከማሳየታቸው በስተቀር ሌላውንና በሚሌኒየም የተካሄደውን ዋናውን ዝግጅት እንደነገሩ አድበስብሰው አለፉት፡፡ ይህ ቴሌቪዥን ጭርሱን ካልጠፋ በስተቀር ወደ እውነት ማዕድ ሊቀርብ እንደማይችል እያረጋገጠ ነው፡፡ አሁንስ እየባሰበት መጥቷል፡፡ ይህ የሚጠቁመው የኃላፊነት እርከኖች ላይ ማን እንደተቀመጠ ነው፡፡ ፀረ-አንድነትና ፀረ- ኢትዮጵያ ኃይል ወንበር ላይ ካለ የርሱን ትዕዛዝ መጣስ ዋጋ ያስከፍላልና የሚዳፈር የለም፡፡ ኢቲቪ የጎሣ ሣይሆን የመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ አንጡራ ሀብት መሆኑ ግን መታወቅ አለበት፡፡

በመሠረቱ በዘር የተቧደኑ በድኖች ሥልጣን በፈረቃ ሲይዙ ከዚህ የበለጠ ሀገራዊ ምስል ሊኖር አይችልምና ነገሩ አያስደንቅም፡፡ የሚያገስርመው ግን እነብጥለው ገለበጠኝ ከምንጊዜው በወያኔ ጫማ መራመዳቸውን መቀጠላቸው ነው፡፡
ባለፈው ለት ለሥራ ጉዳይ ወደ አንድ የግል ትምህርት ቤት ሄድኩ፡፡ ትምህርት ቤቱ የባለጊዜዎች ነው፡፡ በግቢው ያለ ኦሮምኛ ዘፈንና መዝሙር ሌላ አይከፈትም፡፡ ኢፊሴየል ቋንቋውም ኦሮምኛ ነው፡፡ ይህ በራሱ ምንም ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ቆንጆ ነው፡፡ ወደውና ፈቅደው የሚያደርጉት ከሆነ ችግር የለውም፡፡ ይሁንና የሌሎች ዘውጎች ልጆችም በዚያ ት/ቤት ውስጥ የሚማሩ ከሆነ ማዕከላዊነትና በጋራ የሚያግባባ ነገር ይጠፋና ባቢሎን በሣሎን ይሆናል ነገሩ ሁሉ፡፡ የገረመኝ ትልቅ ነገር ግና ይሄ አይደለም፡፡ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ወታደራዊ ተቋም ይመስል ማካሮቭ ሽጉጡን ወገቡ ላይ አገንድሮ ጎንበስ ቀና ሲልም ሆን ብሎ ለሰዎች ለማሳየት መፈለጉን በሚያሳብቅ ሁኔታ መታጠቁን ማየቴና ያም ትክክል አለመሆኑ ነው፡፡ መሣሪያ አይኑረው እያልኩ አይደለም – ግን ቦታ ቦታ አለው፡፡ እንኳንስ ባለጊዜ ሌላውም በፈቃድም ይሁን አለፈቃድና በድብቅ መሣሪያ ይይዛል፡፡ ይሁንና የትምህርት አመራር ቢቻል በግቢው መሣሪያ ባይዝ፣ ያ ባይሆን ደግሞ በድብቅ ይዞት ቢገባና መሣቢያው ውስጥ ቢያስቀምጠው ጥሩ ነው፡፡ ስለመሣሪያም አውቃለሁ – ነበረኝም፡፡ መሣሪያ እንደያዝክ ከታወቀ ባትይዝ ይሻልሃል፡፡ ለቀልድ ብለህ ፊትህን ብታኮሳትር እንኳ በሳይቀድመኝ ልቅደም በቢራ ጠርሙስ ወይም ውኃ በማያሰኝ ዱላ አናትህን ይበረቁስሃል፡፡ ስለዚህ መሣሪያ መያዝህ መታወቅ የለበትም፤ አላግባብም ማውጣት የለብህም፤ ካወጣህም በቁርጥ ወቅት ጥቅም ላይ ለማዋል እንጂ ለማስፈራራት ሊሆን አይገባም፡፡…

ባለጊዜዎች ለነገሩ እስኪጠነካከሩ ድረስ ሁሉም ነገር ብርቅ ይሆንባቸዋል፡፡ መሣሪያ ብርቃቸው፣ ሥልጣን ብርቃቸው፣ ሀብት ንብረትና ገንዘብ ብርቃቸው፣ ዝናና ዕውቅና ብርቃቸው፣ ብርቃቸው የማይሆን ነገር የለም – ልታይ ልታይ ማለትን እንደነሱ የሚወድ የለም – በኋላ ደብቁኝ ደብቁኝ ሊሉ፡፡ የነዚህ ነገሮች ሁሉ መጨናነቅ በሚፈጥርባቸው ቁንጣን “ምን እንሥራ?” እያሉ ሲቀብጡ አላግባብ ያገኟት ዕድል ከእጃቸው ታመልጣለች፡፡ እናም እነዚህን መሰል ቀትረ ቀላሎች ያሳዝኑኛል፡፡ ምን ይሻለን ይሆን ግን? ቀትረ ቀላልን ቀትረ ቀላል እየተካው ተቸገርን እኮ፡፡ ሰው ጠፋ፡፡

ሌላ ትዝብት ልንገራችሁ፡፡ በወያኔ ዘመን ግብዝ ትግሬዎች በየመዝናኛው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ትግሬነታቸው እንዲታወቅላቸው ባላስፈላጉጊ ሁኔታ በድምቀት ይናገሩ ነበር – የሚያስተዛዝበው ሊያስላልፉት የፈለጉት ዕብሪት የተሞላበት የዘረኝነት ትምክህት እንጂ ይህ በራሱ ምንም ማለት አይደለም፡፡ አሁን ደግሞ ዕድሜ ጥጋበኞችን ከመጎብኘት ለማይታቀበው የኢትዮጵያ አምላክ እነሱ ሰከን ሲሉ ግብዝ ኦሮሞዎች ልክ እንደትግሬዎቹ ሁሉ በየመዝናኛው የጆሮ ታምቡራችንን ሊበጥሱት ደርሰዋል – በዝቅተኛ ድምፅ ተነጋግረው መግባባት እየቻሉ ሆነ ብለው ያደነቁሩናል – አውቀናል እኮ ግን፤ እነሱና የነሱ እንደሆኑ በአንደበታቸው የሚመሰክሩ ወገኖች ሥልጣን ላይ መሆናቸውን በቃ አወቅን – ታዲያ አሁን ምን ይጠበስ? እነሱ በሚያዘወትሩበት ሥፍራ ካለኦሮምኛ ዘፈን አይከፈትም – ቢከፈት “ሃጣራው”ን ያስቀደመ “ጩፊ!” ይከተልና ሙዚቃው ይዘጋል፡፡ ድፍረታቸው ደግሞ ድፍረት እንዳይመስላችሁ፡፡ እነዚህ ሰገጤ የጃዋር ግርፎች ሰውን ሊያኖሩት አልቻሉም፡፡ በነዚህን መሰል ገልቱዎች መሣቅ እንጂ ማዘን አይገባም፡፡ ከሰማይ በንፋስ የሚወርድ ሲሳይ አንዳንዴ እንዲህ ያጃጅላልና በነሱ መከፋት ተገቢ አይደለም፡፡ ግዴላችሁም ዘመናቸው የጤዛ ያህል ነው፡፡ ታያላችሁ፡፡ ምን ይባላል መሰላችሁ – “ከአነጋገር ይፈረዳል፤ ከአያያዝ ይቀደዳል፡፡”

ይህን ስል ግብዝ ዜጎችን እንጂ መላውን ትግሬ ወይም መላውን ኦሮሞ ማለት እንደማልደፍርና እንደማልችልም ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ እጅግ በርካታ ኦሮሞዎች በአሁኑ አስጨናቂ ጊዜያዊ ሁኔታ እንደሚያዝኑ እረዳለሁ – አብረን ነዋ የምንውልና የምናመሽ፡፡ የጭንቅላታቸው ብሎን የላላባቸው የየጎሣው ዜጎች በተለዋዋጭ ሁኔታዎች እየተሞኙ ራሳቸውን ቢያዋርዱና ጠባያቸውን እንደእስስት ቢቀያይሩ አይግረመን፡፡ እስኪያልፍ ማልፋቱ ያለ ነውና ይህም ልክ እንደሕወሓት ዘመን ሁሉ አበቅቴውን ጠብቆ ጥርግ ይላል፡፡ መጠንቀቅ ያለብን እኛም እንደነሱ የጊዜን ንፋስ አይተን ለጥቅምም ይሁን ወንዝ ለማያሻግር ከንቱ ዓላማ ተታለን በደመነፍስ በመከተል እንደፔንዱለም ወዲያና ወዲህ እንዳንል ነው፡፡

ትንቢተ ‹ጦቢያ ካልዕ‹

ሦስት አንበሦች ከሰማይ ሲወርዱ አየሁ፡፡ ከሦስቱ አንበሦች ጋር ነብሮችም፣ ግሥላዎችም፣ ዝንጀሮዎችም፣ ጦጣዎችም አብረው ነበሩ፡፡ ከሦስቱ አንበሦች አንደኛው ግምባሩ ላይ ምልክት አለበት፡፡ ከቀሪዎቹ ሁለት አንበሦች መካከል አንደኛው አናቱ ላይ የዝንጀሮ ፀጉር የመሰል አክሊል ነገር ተደፍቶበታል፡፡ ሌላኛው አንበሣ ምንም ምልክት የለበትም፡፡ ነገር ግን ግምባሩ ላይ ምልክት ያለበት አንበሣ አዘናግቶ እግሩን ዘንጥሎት ኖሮ የሚራመደው እያነከሰ ነው፡፡ ፊቱና መላ ሰውነቱ ቅዝዝ እንዳለውና መላ ሰውነቱ በቁጭት እንደተሞላም ከአኳኋኑ መረዳት ይቻላል፡፡

አንበሦች እርስ በርስ የሚጣሉባቸው ወቅቶች አሉ፡፡ የጠባቸው መንስኤ በሴት ወይም በመኖሪያ ቦታ የወሰን መተላለፍ ወይም የአናብስታዊ የዘር ሐረግ ቆጠራ ሊሆን ይችላል፡፡

ባለአፋሮው አንበሣ ቆስሎ የተኛውን ጭምት የሚመስል ከተቆጣ ግን ጎራ የማይበቃውን አንበሣ በዐይኑ ቂጥ በንቀት እየገረመመ ግምባሩ ላይ ምልክት ያለበትን አንበሣ ያሳድድ ገባ፡፡ የሚሸሸውና ቀደም ብሎ ኃያል የነበረው አንበሣም ወደ ዋሻው ገብቶ በሩን በብረት አሎሎ ዘጋ፡፡ ነገር ግን የሚሮጥለትን አንበሣ ለማባረር ሲል በሰውነቱ የተነሳሳውን ከፍተኛ ኃይል (adrenaline enzyme) የሚያሣርፍበት ስላጣ ወደ ተኛው አንበሳ ዞሮ በተኛበት ይጎስመው ጀመር፡፡ ይህ የተኛ አንበሣ የቀድሞ ወዳጁና ምሥጢረኛው ነበር፡፡ ጥጋብ ግን ከኤደንም ገነት የሚያወጣ መጥፎ ነገር ነውና ወዳጆችን አራራቀ፤ ለጦርነትም ጋበዘ፡፡

ከቁስሉ ያላገገመው አንበሣ የጓደኛውን ግፍና በደል ያላዬና ምቱም ያልተሰማው እየመሰለ እንዲተወው ቢለምነውና ቢማጠነውም እንዲያውም የፍራቻ መስሎት በኩራት ተጀንኖ ጥቃቱን አባብሶ ቀጠለ፡፡ ያለው ብቸኛ አማራጭ ህመሙን እንደምንም ችሎ መግጠም መሆኑን በመገንዘብ የማይቀርለትን ፍልሚያ ገጠመ፡፡ … የነዚህ የሁለት አንበሦች ግጥሚያ ውጤት በመላው የእንስሳት ዓለም በጉጉት የሚጠበቅ ቢሆንም ለጊዜው የሚነገር አይደለም – ይህም የሆነው የመጨረሻው ውጤት ስለማይታወቅ ሳይሆን የላይና የታች ዳኞችን ፍትኃዊ ብያኔ በሰውኛ አንደበት አስቀድሞ ላለማራከስ ተብሎ ነው፡፡
Corinthians 13:10 – “But when the perfect comes, the partial will pass away.”

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ በነዶ/ር አቢይ የገባው መንፈስ የሌላ ሣይሆን የእግዚአብሔር ይሁንልን፡፡ የሞት ደብዳቤን ወደ ሕይወት የሚለውጠው የቅዱሣን መላእክት ተራዳኢነት በኢትዮጵያ ይንገሥልን፡፡ አሜን፡፡

Filed in: Amharic