>

ከሀሳብ ይልቅ ማንነት ላይ የተንጠለጠለ ፖለቲካ!!! (ወንድወሰን ሽመልስ)

ከሀሳብ ይልቅ ማንነት ላይ የተንጠለጠለ ፖለቲካ!!!

 

ወንድወሰን ሽመልስ

 

ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን የዘለቀ የመንግሥት ሥርዓት ቢኖራትም፤ የስልጣን ጉዞው ግን ዛሬም ድረስ ከሃሳብ ይልቅ የሸፍጥ ፖለቲካ የበዛበት መሆኑን ምሑራን ይናገራሉ። ሂደቱ መቋጫ ካላገኘም ችግሩ እየከፋ ሊሄድ ይችላል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሑር የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ እንደሚሉት፤ በአንድ አገር ፖለቲካ ውስጥ የመጠባበቅ ሂደቶች በማንኛውም የሽግግር ወቅት የሚነሱ ችግሮች ናቸው። በተለይ በአፍሪካ አገራት አንድ ህዝብ በፖለቲካ ሽግግር ወቅትና ነጻ በሚሆንበት ጊዜ የተደራጁ ቡድኖች መሳተፋቸው የተለመደ ነው። ይሄን መሰል አካሄድ አሁን በኢትዮጵያ እንደሆነው ሁሉ ህዝብ ምርጫ ሲያጣ የሚያካሂደውን ትግል ለመቆናጠጥ እያንዳንዱ የፖለቲካ ቡድን ሌላውን ቡድን ይጠብቃል። በዚህም ያ ቡድን ወዴት ነው የሚሄደው፤ አቅጣጫው ምንድን ነው፤ ያ ቡድን አሸናፊ እንዳይሆን እኔ ምን ማድረግ አለብኝ፤ ወዘተ. የሚል አካሄድ ይታያል።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አቶ እንዳለ ንጉሴ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር ያለውከመነሻው ነው።  ምክንያቱም አንድ ሰው ለፖለቲካ ስልጣን የሚወዳደረው የአብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ጥቅም ከፍ ለማድረግ፤ ወይም የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ አይደለም። የህዝብን ብሎም የአገርን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅም ለማስጠበቅና ለማሳደግም አይደለም። የግልና የቡድን ጥቅምን ለማስጠበቅ ሲባል የመንግሥት ስልጣን ለመያዝ ነው። ይህ ደግሞ፣ አንድም ስለ ውድድር ባለ የግንዛቤ ክፍተት ሲሆን፤ በሌላም በኩል ከዴሞክራሲ አረዳድ ጋር ይያያዛል።

ለምሳሌ በንጉሱ ዘመን በንጉሳዊው ቤተሰብ ውስጥ እንኳን የተወሰኑ መተነኳኮሶች ነበሩ፤ ከዛ በኋላ ያለውም የመጠባበቅ ጉዞው በግልጽ የሚታይ ነው። ይህ ደግሞ ወደ ፖለቲካው የቀረቡ ሰዎችና ግለሰቦች ተንኮል የሚታይበት አካሄድ እንጂ ሳይንሱን ተከትሎ አገርን ለማሳደግ ሲሉ ወደ መንግሥት ስልጣን የሚወጣበት አልነበረም። ሌላው ቀርቶ መንግሥትን ሲፈልግ አገርን ሊያጠፋ የሚነሳና የሚያጠፋ ግለሰብ ጭምር ያለበት ነው። አንድ ሰው የተሻለ ሆኖ ሲመረጥም፣ የኔም ጥቅም ይጠበቃል ብሎ የማሰብ ሂደቱ አልዳበረም፤ የለምም።

አቶ እንዳለ እንደሚሉት፤ ሁሉ ነገር የማይነገርና ሂደቶች በምስጢርና ሸፍጣዊ አካሄድን የመከተል ባህሉ የጎለበተ በመሆኑም ግልጽ ሆኖ መነጋገር እንደ ሞኝነት የሚቆጠርበት ባህል ሰፍኗል። ህዝቡም ቢሆን በደርግ የነበረው የመግፋት፣ ከዚያም በኋላ በነበረው የማሸማቀቅ የፖለቲካ ባህል ተጽዕኖ ምክንያት በስልጣን ላይ ያለውን የመጠየቅ፤ ከስልጣን የወረደውን የማክበር፤ እንዲሁም የተሻለ ሀሳብ ይዞ የሚታገልን አካል ሸፍጠኞች ሲያንቋሽሹት ሲያይ የመከላከሉ ባህሉ ስለሌለው ፖለቲካን ሙጥኝ የማለትና በሸፍጥ የተሞላ ጉዞን ለማድረግ የራሱ ድርሻ አለው።

እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ ደግሞ፤ በሃሳብ ልዕልና ልቆና የህዝብን ስሜት ገዝቶ በምርጫ የማሸነፍ ትክክለኛው መንገድ ሳይሆን፤ አንዳንዴ የፖለቲካ ቡድኖች ሂደቱን ወደ ሽብር ስራ የሚያስገቡበትና አገሪቱ ውስጥ ነውጥ እንዲፈጠር የሚያደርጉበት መንገድ ነው። በዚህ መልኩ አለመረጋጋትን በመፍጠር የበላይነትን ለመያዝ የሚደረግ ጥረት ደግሞ የሚፈጥረው ትልቅ ችግር አለ። በኢትዮጵያም ይሄ ችግር ለመፈጠሩ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚባሉት የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፊ ባልነበረበት ወቅት እንዲሁ በትግል የቆዩ መሆናቸው አንዱ ምክንያት ሲሆን፤ ለውጥ መጥቶና የፖለቲካ ምህዳሩም ሰፍቶ ወደ ዴሞክራሲያዊ አሰራር እንግባ በሚባልበት ጊዜ ተደራጅተው የቆዩ ጥቂት ፓርቲዎች ብቻ መሆናቸውም ሌላው ችግር ነው።

ይህ ደግሞ እነዚህ ቡድኖች የሌሎችን ሁኔታ እየተጠባበቁ እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል። የህዝቡ የዴሞክራሲ ምርጫ ባህል ያለመጎልበት እና የዴሞክራሲ ተቋማት ብሎም የመንግሥት አካላት እንደ አንድ ተደራጅተው የፖለቲካ ፓርቲን ሲያገለግሉ የነበሩ መሆን ደግሞ ይሄን መንገድ እንዲመርጡ መንስኤ ከሚሆኑ ነገሮች መካከል ይጠቀሳሉ። እነዚህ ተቋማት አሁንም ቢሆን በአዋጅና በመንፈስ ተቀየሩ እንጂ በሰው ሃብት ይዞታቸውም ሆነ በአሰራራቸው አለመቀየራቸው ደግሞ ተቃዋሚ ቡድኖች ሂደቱን በአንክሮ እንዲመለከቱት ያደርጋል።

ይህ አካሄድ ደግሞ የፈጠረውና የሚፈጥረው የራሱ የሆነ ችግርና ተጽዕኖ አለ። ከእነዚህ መካከል አንዱ በየቦታው የሚታየውና የብሔር ግጭት ገጽታን ለመላበስ እየሄደ ያለው ችግር ሲሆን፤ ይህ ደግሞ በአጋጣሚ በሚያገኙት ቀዳዳ የፖለቲካ ስልጣን እንያዝ ብለው በየቀዬው ያለውን ህዝብ እየቀሰቀሱ ለጥፋት የሚዳርጉ ሰዎች መኖር ውጤት ነው። በዚህም አገሪቱ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለች ትገኛለች። ለምሳሌ፣ እ.አ.አ በ2018 በዓለም ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የተፈናቀለ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ ስትሆን፤ ይህ ደግሞ ህዝቡ ከስደት አልፎ ህዝብ ለከፋ ጉዳት እንዲዳረግ አድርጎታል።

እንደ አቶ እንዳለ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አጥፍቶ የወረደ እንኳ መልሶ የሚያጠፋበትና ሸር ሚሰራበት ነባራዊ ሁኔታን ፈጥሯል። አሁን ላይ በየቦታው የሚታዩ ግጭቶችና መፈናቀሎች የተወሰኑ ሰዎችና ቡድን ጥቅም ስለተነካ የተወለዱ ናቸው። ምክንያቱም ለዘመናት ተጋብቶ ጭምር አብሮ የኖረና ዘሩን ቁጠር ቢባል እንኳ ከአምስትና ስድስት ብሔር የሚቀዳው ህዝብ ከዚህ ከሸፍጥ ፖለቲካ በዘለለ ሌላ ሊያጣለው የሚችል ምንም ነገር የለም። ሀሳብን በነጻ ለመግለጽ ዋስትና ያለው የሲቪክ ማህበረሰብ እንዳይፈጠር፤ ህዝቡ የሚፈልገው ሰው እንዲመታና ህዝቡም እምነት እንዲያጣ፣ እየፈራና እየደነገጠ እንዲሄድ አድርጓል።

አቶ እንዳለ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ  ከ3ሺ ዓመት በላይ መንግሥት ሥልጣን ያላት ቢሆንም፤ በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ ውድድር የማድረግ ባህሉን አላዳበረችም። ለምሳሌ፣ ደርግ ሶሻሊዝም ነኝ ቢልም እጅጉን ማዕከላዊነት የበዛበትና ጭራሽ በስልጣኑ መደራደር የማይፈልግ፤ ስልጣን የሚያስነካ አልነበረም። ከዛ በኋላም ከደርግ ለመሻል የተወሰነ ቢኬድም ከኢህአፓ ጋር ተያይዞ ላለፉት 40 ዓመታት ግራ ዘመሙ ያመጣው በሽታ አላፈናፈነም። ምክንያቱም ኢህአፓ እንኳን የአገር ጥቅም ሊያስጠብቅ በቃላት ስለሚጣላ አንዱ አንዱን የሚያጠፋበትና ወንድም ወንድሙን የሚገድልበት ነበር። ይሄን ደግሞ ኢህአፓ ውስጥም ሆነ ህወሃት ውስጥ ከነበሩት፤ እንዲሁም አሁን ኦነግ ውስጥም ከሚታየው ክፍፍል አኳያ ማየት ይቻላል።

በመሆኑም ከመጠባበቅ ፖለቲካ ወጥቶ በሃሳብ ለማሸነፍ እንዲቻል ግልጽ የውይይት ባህል ማዳበር ይገባል። ተንኮል መስራት ሳይሆን የሕዝብና የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስቀደም እንደ ችሎታ ሊታይም ያስፈልጋል። መንግሥትም የአስተዳደር ሚናውን መወጣት፤ በየደረጃው ባሉ የትምህርት ተቋማት፣ በእድርና እቁብ ማህበራት ጭምር ሀሳብን በነጻ የመግለጽ ባህል መዳበር አለበት። መገናኛ ብዙሃንም የመንግሥትና ህዝብ አገናኝነት ድልድይነታቸውን በኃላፊነት መከወን ይኖርባቸዋል። የገዳ እና መሰል የባህል እሴቶችን አጎልብቶ መጠቀም፤ ፓርቲዎችም ተደብቆ ከመተኮስ እንዲወጡና በግልጽ እየተናገሩ ማንነታቸው እንዲታወቅ ማድረግ፤ የሀሳብ አንድነትንም መፍጠር ይገባል። ይህ ካልሆነ ነገም ባቋራጭ ወደስልጣን ለመሄድ መጓዝና መልሶ ወደ ማፋጀት መኬዱ አይቀርም።

በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደሚሉትም፤ ኢትዮጵያ ዕድገቷን ለማስቀጠል አንደኛ፣ ከይድረስ ይድረስ የምርጫ ጉዳይ ባለፈ ህዝቡ ነቅቶ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊውም ሆነ በፖለቲካው ምን አይነት ጥቅም አገኛለሁ ብሎ የሚያስብበትን ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል። አገሪቱ አሁን ያለችበትን ሁኔታ (መልካሙንም ችግሩንም) የሚገነዘቡ፤ አገሪቱ ታሪክ እንዳላትም የሚያውቁ አዳዲስ ፓርቲዎች ከህብረተሰቡ ሊፈልቁ ይገባል። መንግሥትም አካሄዱን በሕግ ማገዝ ይኖርበታል። ለምሳሌ፣ እንደ ጋና በብሔር፣ እንደ ግብጽ ደግሞ ሃይማኖት መደራጀትን መከልከል ይገባል። ይህንንም ሰፋ ባለ ውይይት ማገዝ ካልተቻለ ውጤቱ የከፋ ሊሆን ይችላል።

Filed in: Amharic