>

ፖለቲካችን ከድርቀት ወደ ልምላሜ ተሸጋግሯል !! (አሰፉ ሀይሉ)

ፖለቲካችን ከድርቀት ወደ ልምላሜ ተሸጋግሯል !!
አሰፉ ሀይሉ
* በፖስተሩ ላይ የሚታየው ያ የህወሃት የቁም ቅዠት 4ሚሊየኑ ትግሬ  ሳይፈጅ ማለፉ ይገርማል!!!
* ያለ ለህወሃቶችና ህወሀታውያኑ ብቻ መሽቶ በነጋ ቁጥር የሚታያቸው ፕሮፓጋንዳ የወለደው ክፉ ህልም የቀን ቅዠት ነበረ….??!! 
ወዝ የሌለው ደረቅ ፖለቲካ አልወድም። ለጨዋታ አይሆንም። ለጨዋታ ይቅርና ለቁምነገርም አይሆንም። ፖለቲካ ሰብዓዊ ሳይንስ ነው። ከሰው፣ በሰው፣ ለሰው የተበጀ። ፖለቲካ የሰውን የዕለት ተዕለት ህይወት መዘወሪያ ነው። የዜጎች ህይወት ነው። እና ሰው ሰው የሚል ለዛ ሲኖረው ነው ደስ የሚለው። ከሌለው እንኳ ፖለቲካህ ውስጥ ከየትም ፈልገህ ትንሽ ሰው ሰው የሚሸት ቅመም ጠብ ማድረግ ይኖርብሀል።
ይህ ሰብዓዊ ንጥረነገር የሌለው ፖለቲካ – በእኔ አመለካከት – በቃ ስትጠጋው ከሩቅ የሚገፈትረህ – ማላታይን ማላታይን (ወይም ጋዝ ጋዝ) የሚል ፖለቲካ ነው።
ምናልባት ከሳለፍነው የግማሽ ክፍለዘመን (የ50 ዓመታት) ያገራችን ፖለቲካ – አሁን በቅርቡ በእነ ዶ/ር አብይ የሥልጣን ዘመን ያየሁት የመጀመሪያው ለውጥ (የመጀመሪያው & ትልቁ) – ለሰው ችክ እና ድርቅ ከማለት አልፎ – እጅ-እጅ ያለውን ያገራችንን ሮቦት የመሰለ ፖለቲካ – ሰው ሰው በሚል በሰብዓዊ ቅመም የወረዛ ሰብዓዊ ፖለቲካ የመቀየሩ ነገር ነው። ወይም በበኩሌ ለውጡ የጀመረው ከዚያ ወይም እንደዚያ ነው ባይ ነኝ።
/ፖለቲካችን እንደዚያ አልሆነም የሚል ካለ ግን ምንም ማድረግ አልችልም። ፖለቲካና ህልም እንደፈቺው ነው። በቃ እንደ ማንኛውም የዕለት ተዕለት ህይወታችን ሁሉ ከምሬቱ መካከል ጣፋጭ ነገርን የያዘ ሰውኛ ፖለቲካ መሆን አለበት – በሚለው ተስማምተን አብረን እንዝለቅ። ይህ ያልጣመው ካለ ግን ሳይሻገር ጫፉ ላይ ቢወርድልኝ – እና ትንሽ ፖለቲካዬን ቀለል ቢያደርግልኝ .. ደስ ይለኛል። የምን ድርቅና ነው?!!! በቃ ፖለቲካችን ከድርቀት ወደ ልምላሜ ተሸጋግሯል። ስድስት ነጥብ።/
አሁን ከፅሁፌ ጋር ወደተለጠፈው የግድግዳ ላይ ፖስተር ተሸጋገርኩ። ፖስተሩን ከግድግዳ ላይ ፎቶግራፍ ያነሳሁት እኔ አይደለሁም። ያነሳሁት ከመፅሐፍ ገፅ ላይ ነው። ያነሳሁት ከታዋቂው የግራሃም ሀንኮክ “The Sign and the Seal” በእኛ አቆጣጠር በ1984 ዓ.ም. ላይ ከታተመው መፅሐፍ ከገፅ 92 ላይ ነው። እርሱ ደግሞ ይሄን ፖስተር ፎቶ ያነሳው በ1982 መጨረሻ ላይ ታቦተ ፅዮንን ፍለጋ ለንደን ላይ መቀመጫውን ያደረገውን የህወሀት ከፍተኛ አመራር አስፈቅዶ ወደ ከክሱም ባቀናበት ወቅት የያኔው ህወሃት ከሚቆጣጠረው አንድ የትግራይ ከተማ ግድግዳ ላይ በትልቁ ተስሎ አግኝቶት ነው።
በፖስተሩ ላይ በ”ፋሺስት/ናዚ” የተመሰለው ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም የጦር ጄቶቹን በአናቱ፣ ሠራዊቱን በፊቱ፣ ቢኤሞቹንና ታንኮቹን ከግራና ከቀኙ አሰልፎ – በጥፍራም እጁ ታላቅ ጎራዴ ጨብጦ – “ትግሬ ገዳይ! ትግሬ ገዳይ!” እያለ እያጓራ – “አራት ሚሊዮን ወንበዴዎችን ለመደምሰስ!” የሚል ለዘር ፍጅት ቆርጦ መነሳቱን የሚገልፅ የመፈክር ባነር እንደ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ እያውለበለበ – በትግራይ ህዝብ ላይ እንደ ወልደ-ነጎድጓድ ሲተምም ይታያል። ወ……..ቸ ጉድ!!!!
ያ የህወሃት የቁም ቅዠት 4ሚሊየኑ ትግሬ  ሳይፈጅ ማለፉ ይገርማል። አይደል??!! ማን ነው ህዝቡን ከፍጅት ያዳነው???!! ከገበሬ ወጣቶች የተመለመለ ጦር ያሰለፈው ህወሃት ይሆን??!! ወይስ ከግራና ከቀኛቸው አናብስትና አናብርት ከበላያቸው የቁራ መላዕክተኛ ያሰለፉት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ (አቡሄ ቀዳማዊ) ይሆኑ የትግራይን ህዝብ በፖስተሩ እንደሚታየው ካለው ከታወጀበት የዘር ፍጅት የታደጉት??!! ወይስ ዘንዶን በመስቀላቸው የገዘቱት የ14ቱ አቡነ አረጋዊ (አቡሄ ፃዲቁ) ይሆኑ??!! ወይስ ይሄ የመፈጀት ሥር የሰደደ የህወሃታውያኑ ሥጋት ራሱ ምናብ የፈጠረውና በቀን ተፈጥሮ በቀን እልም ያለ ለህወሃቶችና ህወሀቶች ብቻ መሽቶ በነጋ ቁጥር የሚታያቸው የቀን ህልም (ወይም የቀን ቅዠት) ነበረ….??!! ወይስ ምን?!!
የሚገርመው ፖስተሩና በፖስተሩ ለትግራይ ህዝብ በተደጋጋሚ የታሪክ ምዕራፎች መቀመጫቸውን በለንደን ምድር፣ አውደ ግንባራቸውን በሀማሴን ምድር ባደረጉ የህወሀት የፖለቲካ መሪዎች እየተሰበከ የኖረው ይህ በፖስተሩ ላይ በግልፅ ቋንቋ የሰፈረ ከህወሀት ጋር አብሮ ለበርካታ አሰርት ዓመታት የኖረ ይህ ዘግናኝ (አፖካሊፕቲክ) የመጥፋትና የመጠፋፋት ሀሳብና ሥጋ የለበሰ ሥጋት ብቻ አይደለም።
ከዚህ ይበልጥ የሚገርመው – በህወሃት መሪዎች ዓይን ሲታዩ – ኮሎኔሉ መንግሥቱ ኃ/ማርያምም፣ ንጉሡን ከነሚኒስትሮቻቸው የረሸነው የበታች መኮንኖች ስብስብ ደርግም፣ ንጉሡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ራሳቸውም፣ ኢጣልያንን እስከ መረብ አባረው ሸኝተው ወደአዲሳባቸው የተመለሱት አፄ ምኒልክም፣ ኧረ ጎራው ብሎ የባህሉን የሚያንጎራጉረው የጎንደር ባለማሲንቆም፣ በእድሜ ዘመኑ የጀማን ወንዝ ተሻግሮ የማያውቀው የመራቤቴ ባልደራስም፣ የበግ ቆዳ እያስጫነ ከጅሁር ማዶ የሚመላለስ የመንዝ ባላባትም – በቃ ሁሉም – እነዚህ ሁሉ – በአንድ ወይም በሌላ መንገድ – ለተመሳሳይ ዓላማ – በትግሬ ህዝብ ላይ ፍጅት ለማድረስ – በየዘመናቱ የተሰለፉ፣ የሚሰለፉ፣ አሊያም ለመሰለፍ አድፍጠው አመቺ የጥቃት ጊዜ (የትግራይ ህዝብ የበላይ ጠባቂ የሚዳከምበትን አመቺ ወቅት) የሚጠባበቁ – “ፀረ-ትግራይ” ነፍጠኞች (ወይም ባለነፍጦች) – አድርገው – በአንድ የዘመነ ስብስቴ-ነጋሲ የጦርሜዳ መነፅር ሲመለከቱ የመኖራቸው፣ ያንን እውነት ነው ብለው መቀበላቸውም፣ ያንኑ “እውነታቸውን” ደግሞ ለሚከተላቸው እና ሲሞትላቸው ለኖረው ምስኪን ህዝባቸው እመነን ብለው ሲሰብኩ መኖራቸውም ነው። ያ ነው እጅግ ገራሚው። How come!!??!!
እጅግ የሚገርመኝ፤ ወይም እጅግ የሚገርመው፤ ይህ የህወሃት ቀዳሚ ፖለቲከኞች ቋሚ ሥጋትን እና ቋሚ ጠላትን የህልውና መሠረቱ አድርጎ በትግራይ ምድር ቅቡል ሆኖ ለረዥም ዓመታት ለመኖር የመብቃቱ ተዓምር ነው – ከሁሉ ከሁሉ እጅግ የሚገርመው በእውነቱ።
ሌላ ቀርቶ ታሪክ ዘጋቢው ግራሃም ሀንኮክ ራሱ ያን የህወሃቶችን ቅዠታዊ ትርክት በሚያስተጋባ መልኩ ያንን የአክሱም ፅዮንን የሙሴ ታቦት ኃይል ሊመረምር በወጣበት በመንገድ ግድግዳ አግኝቶት ፎቶ ያነሳውን በኃይል የተሞላ ሣጥናዔላዊ ፀረ-ፅዮናዊ የናዚ ፍጅት ፖስተር በመፅሐፉ ሲያካትት፣ … ለፖስተሩ ካፕሽን ያሰፈረው መግለጫ፦ “A poster showimg the brutaluty of the Emperor’s successor, President Mengistu.” የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። በንጉሡ እግር የተተካው – በጭካኔው አቻ ያላገኙለት – ፕሬዚዳንት መንግሥቱ (ዓይነት የህወሃቱ ከላይ የጠቀስኩት ስብከት ቅንጫቢ ያወረዛው መልዕክት)!!!
ይሄ የግራሃም ሃንኮክ (እና የየኔው ህወሃት) በኢትዮጵያ የመሪነቱን በትረሥልጣን የጨበጠውን (እና የተጨበጠውንም) ሁሉ ያው አንዱ የሌላኛው ወራሽና ተተኪ – ወይም በራሳቸው ቋንቋ ተተካኪ – አድርጎ የማቅረብ አነጋገር አንድ ከዚያ ቀደም የተሰማን ተመሣሣይ ዜና አስታወሰኝ። ሶማሌ ኢትዮጵያን ስትወር ፕሮፓጋንዳዋን በተለያዩ የሀገራችን ቋንቋዎች የምትነዛበት የራዲዮ ሥርጭት ጀምራ ነበረ።
/እንዲያውም ሳስበው – በሀገራችን ከደርግም፣ ከህወሀቶችም ቀድሞ በተለያዩ የሀገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋ በአየር ሞገድ ማሰራጨት የጀመረ የመጀመሪያው የጭቁን ብሄር እንባ ጠባቂ – የሞቃዲሾው ኮ/ል ሞሀመድ ዚአድባሬ ሳይሆን የሚቀር አይመስለኝም!!/
እና በወቅቱ የእኛው ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም በአብዮት አደባባይ ላይ ቪምቶ ከነጠርሙሱ መዝዘው በመሰባበር ለተቃጣባቸው ነጭ ሽብር – በመልስ ምት ቀይ ሽብርን መንዛታቸውን ባወጁበት ጊዜ – ያ የሞቃዲሾ ራዲዮ የአማርኛ ዜና ዕለታዊ ስርጭት የኮ/ሉን ድርጊት እንዲህ ብሎ ነበረ የዘገበው (በተሰባበረ አንደበት አማርኛዋን ለማሰካካት በምትጣጣር የሶማሌ ዜና አንባቢ አንደበት) ፦
“የሚኒሊክ የሊጅ ሊጅ፣ የኃይለ ሢላሴ ሊጅ፣ የሆኑት ኮሎኔል መንጊሥቱ ኃዪለ ማሪያም፣ በዛሬ ኢለት፣ ሂዝብ በተሰበሰበበት አዴባባዪ፣ በደም የተሞላ ጠርሙስ አምጢተዉ አፈነዱ..!!!” እና ግራሃም ሃንኮክም ከያኔው ህወሃት አፍ ልቅም አደረገና በአፄው እግር የተተካው …መንጊሥቱ…ተረረረረረ
ኡኡኡ….ይይይይ !!!??? አቦ አሁንስ የት ሄጄ ሊፈንዳ??!!!
ጠብቁኝ። ተመልሼ እመጣለሁ። የህወሃት የከረረ የሥጋት (እና የተቃውሞ) ፖለቲካ ወደየት ሊያመራ ይችላል? – በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የታዩኝን 6 ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሥጋቶች – ከነመፍትሄ ሃሳባቸው – ፍንትው አድርጌ – አወርዝቼ – የእንትን…አበባ አስመስዬ – ለእናንተ ለማቅረብ።
ለሁላችን በያለንበት የቸሩ ፈጣሪያችን ፍቅር እና ጥበቃ አይለየን።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ።
Filed in: Amharic