>

የአንድነት ፓለቲከኞች ! (ሳምሶን ሚሀይሎቪች)

የአንድነት ፓለቲከኞች !
ሳምሶን ሚሀይሎቪች
* ብሄረተኛን ሚኖሶታ ፣ ኮሎራዶ አልያም ሲያትል ብቻውን ስታገኘው ኦሮሞነቱ ፣ ትግራዋይነቱ ፣ አማራነቱን ረስቶ አሜሪካዊ ዜጋ ሆኖ ነው የምታገኘው (የዜግነት መብቴ አላለም ለራሱ ሲሆን ?) ። ሸገር ላይ ፊንፊኔ ኬኛ እያለ መፈክር የሚሰብቀው ኦሮሞ ጎንደር ላይ በቴዲ አፍሮ
 ” ኢትዮጵያ ሀገሬ ባንች አይደል ወይ ክብሬ ” ዘፈን ጨፋሪ ነው!! የጎንደሩም ሌላ ስፍራ ሲሄድ እንዲሁ!!!
*
ብዙው ሰው የብሄረተኞች ጫጫታ ሲበዛ የአንድነት ፓለቲከኞች ትንሽ ይመስሉታል። በሰው መፍረድ አይቻልም ጮክ ብሎ የተናገረ ሁሉ አዋቂ ሰብሰብ ብሎ ያጫበጨበ ሁሉ ብዙ ቢመስል አይደንቅም። የሆነ ሆኖ የዜግነት መብት ይከበር ባዮች ከአንድነት ውጪ ሌላ የማይገባን ሰዎች ብዙ እልፍ ነን።
፩ መምህራን ፣ መምህራን ከሙያቸው ባህሪ የተነሳ ከምልአተ ብዙ ተማሪዎች ጋር ከአድማሰ ሰፊ መጻህፍት ጋር ይውላሉ። መምህር ምን ቢደድብ ጎበዝ ተማሪው ኦሮሞ ይሁን አማራ ፣ ከምባታ ይሁን ወላይታ ግዱ አይደለም። የመምህር ትኩረት ከተማሪው የማወቅ ጉጉት ከመመራመር አድማስ ጋር ነው። መምህር የዘመን ጎርፍ ካልወሰደው በቀር እጠረጴዛቸው ቁጭ ብለው የሚያደምጡት ተማሪዎቹ ለእርሱ ዜጎች ብቻ ናቸው ፣ ብሄሮች ሆነው አይታዩትም። እናም መምህር በሙያው ሰበብ የአንድነት ፓለቲከኛ ነው የተማሪዎቹን ዘር ሳይቆጥር ትልቅ ቦታ እንዲደርሱለት የሚሻ ባለሙያ።
፪ ነጋዴ ፣ ድሮም በዘመነ ሲራራ ነጋዴ ዛሬም በቴክኖሎጂው ዘመን ነጋዴ ድንበር ፣ ዘውግ ፣ ኬላ የለውም። ነጋዴ ምርት ወይም አገልግሎቱን ይዞ ገዥ ነው የሚፈልገው ባለፈራንካ ! ለነጋዴ የደንበኛው ብሄርና የትውልድ ስፍራ የመስፈርቶች ሁሉ መጨረሻ ነው። ምናልባትም ከሁላችንም በላይ ብሄረተኝነት/ዘረኝነት ግራ የሚገባው ፍጡር ቢኖር ነጋዴ ነው። ከጨንቻ ሸቀጥ ይዞ የመጣ ነጋዴ ፣ ሻሸመኔ ከኦሮሞው ጋር ምሳ በልቶ እግረመንገዱንም ገበያ አፈላልጎ መርካቶ እስኪደርስ ምናልባትም ሰላሳ ምናምን ብሄሮች አግኝቶ ይሆናል ግን ልብ አይላቸውም ዜጎች እልፍ ካለም ደንበኞች እንዳገኘ ብቻ ነው ወደ አዕምሮው የሚመጣው። እናም ነጋዴ የአንድነት ‘ፓለቲከኛ’ ነው ብንል ይበዛበት ይሆን ?
፫ ብሄረተኛ : ብሄረተኛ ምን ጽንፈኛ ቢሆን ከክልሉ ሲወጣ የዜግነትና አንድነት ፓለቲካ አራማጅ ነው። ብሄረተኛ በተፈጥሮው ከቡድን ውስጥ ወጥቶ ብቻውን ሲሆን ራቁታም ነው ይበርደዋል ፣ እናም አንድነትን አልብሱኝ የዜግነት መብቴን አክብሩልኝ ባይ ነው። ብሄረተኛን ሚኖሶታ ፣ ኮሎራዶ አልያም ሲያትል ብቻውን ስታገኘው ኦሮሞነቱ ፣ ትግራዋይነቱ ፣ አማራነቱን ረስቶ አሜሪካዊ ዜጋ ሆኖ ነው የምታገኘው (የዜግነት መብቴ አላለም ለራሱ ሲሆን ?) ። ሸገር ላይ ፊንፊኔ ኬኛ እያለ መፈክር የሚሰብቀው ኦሮሞ ጎንደር ላይ በቴዲ አፍሮ ” ኢትዮጵያ ሀገሬ ባንች አይደል ወይ ክብሬ ” ዘፈን ጨፋሪ ነው። የጎንደሩም ሌላ ስፍራ ሲሄድ እንዲሁ።
እናም በብሄረተኞች ጩኸት የተዋጥን ቢመስልም ሹፌሩን ፣ ከሀገር ሀገር የሚዞረውን መሀንዲስ ፣ ወታደሩን ወዘተ ስንጨማምረው የአንድነት ‘ ፓለቲከኞች’ ብዙ ነን ለማለት ነው። ብሄረተኞቹ አብሮ መኖር ፋይዳ ሲገባቸው ደግሞ ‘ እልፍ’ እንሆናለን።
Filed in: Amharic