>
10:30 pm - Tuesday August 16, 2022

በ31 የራያ ታዋቂ ሰዎች ላይ የሽብር ክስ ተመስርቷል!!  29 ራያ የልዩ ሀይል አባላት ታስረዋል!!! (ዶችቬሌ)

በ31 የራያ ታዋቂ ሰዎች ላይ የሽብር ክስ ተመስርቷል!!  29 ራያ የልዩ ሀይል አባላት ታስረዋል!!!
ዶችቬሌ
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በራያ ወረዳዎች እና አካባቢው ካሰማራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ልዩ ኃይል ሠራዊት መካከል 29ኙ ለመጥፋት በዝግጅት ላይ እያሉ ደርሼባቸዋለሁ በሚል የትግራይ ክልል መስተዳድር ወታደራዊ እስር ቤት አስሯቸዋል ሲል የራያ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አስታወቀ ።
የኮሚቴው የህዝብ ግንኙነት ዋና አመራር አቶ ደጀኔ አሰፋ በተለይ ለ DW በሰጡት ቃለ መጠይቅ የራያ ተወላጅ የሆኑት የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት የተያዙት በራያ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት እና ግድያ በመቃወም ለማምለጥ ሲሞክሩ ነው ብለዋል። ኢሕአዲግ ለውጡን ተከትሎ በሽብር ህጉ አማካኝነት በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰት በአገሪቱ መፈጸሙን አምኖ በይፋ ይቅርታ ቢጠይቅም የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ግን የማንነት ጥያቄን  በህብረተሰቡ ውስጥ ያነሳሳሉ ብሎ በጠረጠራቸው 31 ታዋቂ የራያ የአገር ሽማግሌዎች መምህራን እና ነጋዴዎች ላይ የሽብር ወንጀል ክስ ሰሞኑን መመስርቷል ይህም የፌደራል መንግሥቱን ሕግ የሚጻረር ነው ሲል ኮሚቴው አውግዞታል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በራያ ሕዝብ ላይ በደል እየተፈጸመ ነው ያሉ ተጨማሪ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ በሳውድ አረቢያ እና በግብጽ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለት ተጨማሪ ዲፕሎማቶች ከሕወሃት አባልነት በፈቃዳቸው መልቀቃቸው ታውቋል።የራያ ሕዝብ ያለፍላጎቱ በግዳጅ ወደ ትግራይ እንዲካለል ተደርጓል ያሉ የአካባቢው ተወላጆች የማንነት ጥያቄያቸውን ማስተጋባት ከጀመሩ ዓመታት መቆጠሩን የማንነት አስመላሽ ኮሚቴው አመራሮች ይገልጻሉ። ጥያቄያቸው በሕጋዊ መንገድ በሕዝበ ወሳኔ እንዲፈታም ሕገ መንግሥቱ ከሚጠይቀው 5 ፐርሰንት የሕዝብ ድምጽ በላይ ይኸውም ከ28 ሺህ የአካባቢው ተወላጆች ከ8 በመቶ የሚልቁ ነዋሪዎችን የድጋፍ ፒቲሽን በማስፈረም ለክልሉ መንግሥት እና ለፌዴሬሽን ምክርቤት ማቅረባቸውን ነው የሚያስረዱት። ይሁን እንጂ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በራያ የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር እንጂ የማንነት ጥያቄ የለም በጥቅም የተገዙ በውጭ ኃይል የሚደገፉ እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎች ክልሉን የብጥብጥ ቀጠና ለማድረግ የሸረቡት ሴራ ነው የሚል ተደጋጋሚ ተቃውሞ ሲያሰማ ቆይቷል። የማንነት አስመላሽ ኮሚቴው የሕዝብ ግንኙነት አመራር አቶ ደጀኔ አሰፋ ግን ሕወሃት እስካሁን ሕዝባዊ ትግሉን በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ለማፈን የተጓዘበት መንገድ እንደማያዋጣው የተረዳበት ጊዜ ላይ ደርሷል ነው የሚሉት።
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በራያ ወረዳዎች እና አካባቢው አሰማርቷል ከሚባለው በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ልዩ ሃይል ሰራዊት መካከል 29ኙ ከአላማጣ ኮረም እና ዙሪያው ካሉ ወረዳዎች ለመጥፋት በዝግጅት ላይ እያሉ ደርሼባቸዋለሁ በሚል የትግራይ ክልል መስተዳድር ወታደራዊ እስር ቤት አስሯቸዋል ሲሉ የራያ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ዋና አስተባባሪ አቶ አገዘው ህደሩ ይናገራሉ። ከልዩ ኃይሉ አባላት ጦርነት ማካሄድ ፍትሃዊ ነው ብለው ያላመኑ እና ለማምለጥ የቻሉት ወደ ቆቦ እና ሌሎችም አጎራባች አካባቢዎች ከእነ ትጥቃቸው በመግባት ላይ ይገኛሉም ብለዋል። ኢሕአዲግ ለውጡን ተከትሎ በሽብር ህጉ አማካኝነት በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰት በአገሪቱ መፈጸሙን አምኖ በይፋ ይቅርታ ቢጠይቅም የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ግን የማንነት ጥያቄን  በህብረተሰቡ ውስጥ ያነሳሳሉ ብሎ በጠረጠራቸው 31 ታዋቂ የራያ የአገር ሽማግሌዎች መምህራን እና ነጋዴዎች ላይ የሽብር ወንጀል ክስ ሰሞኑን መመስረቱንም የፌደራል መንግሥቱን ሕግ የሚጻረር ነው ሲሉ አቶ ደጀኔ አውግዘውታል።
አቶ ደጀኔ  እንደሚሉት ሕወሃት በአሁኑ ወቅት በራያ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን ግድያ እስር እና የሰብአዊ መብት ጥሰት በመቃወም በርካታ የአካባቢው ተወላጆች ከድርጅቱ መልቀቃቸውን ተስፋ ስላስቆረጠው የራያን ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በጠመንጃ አፈሙዝ ለማፈን እና አካባቢውን ጭምር የጦር ቀጣና ለማድረግ ምሽግ በመቆፈር እና በከባድ የጦር መሳሪያዎች ጭምር ራሱን በማደራጀት ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጀምሯል። በአሁኑ ወቅትም ከ 37ሺህ በላይ የሚሆን የክልሉን ልዩ ታጣቂ ኃይላት በዎፍላ ወረዳ በራያ አላማጣ እና በራያ አዘቦ ወረዳዎች እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች ማስፈሩን ለማረጋገጥ መቻላቸውን የማንነት አስመላሽ ኮሚቴው አመራር ጠቅሰው የፌደራል መንግሥት በአፋጣኝ ለጉዳዩ ትኩረት ሰቶ መፍትሄ እንዲፈልግ አሳስበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በራያ ሕዝብ ላይ በደል እየተፈጸመ ነው ያሉ ተጨማሪ የአካባቢው ተወላጅ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረቦች የሆኑ በሳውድ አረቢያ በዲፕሎማትነት የሚያገለግሉት አቶ ሚስባህ ማህመድ እና በግብጽ የኢትዮጵያ መንግሥት ዲፕሎማት አቶ አሊ መሀመድ ከሕወሃት አባልነት በፈቃዳቸው መልቀቃቸው ታውቋል። በቅርቡም በሚኒስትር ዴኤታነት እንዲሁም በቅድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚድያ እና ህዝብ ግንኙነት ሃላፊነት ያገለገሉትን አቶ ዛዲግ አብርሃ ጨምሮ 6 የራያ አካባቢ ተወላጅ የሕወሃት አባላት ከለውጡ በተቃራኒው ተሰልፏል በራያ ሕዝብም ላይ ግድያ እና አፈና ይፈጽማል በማለት ከድርጅቱ ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል።

እንዳልካቸው ፈቃደ

አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ

Filed in: Amharic