>
10:47 am - Sunday May 22, 2022

ካሳ ሲገባው እስር...  ኤርሚያስ ዛሬም ለውጥ አልመጣም!?! (መስከረም አበራ)

ካሳ ሲገባው እስር…
ኤርሚያስ ዛሬም ለውጥ አልመጣም!?!
መስከረም አበራ
ኤርሚያስ መአመልጋ እንዲፈታ ስንጠይቅ ግለሰቡ ሊታሰር ቀርቶ ካሳ ሊከፈለው የሚገባ ሰው ነው ብለን ስለምናምን ነው፡፡ ለዚህ ምክንያታችን ደግሞ
1. ኤርሚያስ ከአሜሪካን ሃገር ወደ ሃገሩ መጥቶ የሃገሩን የኢኮኖሚ እድገት ለማገዝ ሲወስን ሲኖርበት በነበረበት ሃገረ-አሜሪካ ጥሩ ገቢ እና ኑሮ የነበረው ሰው ነበር፡፡ ወደ ሃገሩ የመጣው ራሱን ከመጥቀም ይልቅ የሃገርን ኢኮኖሚ በተለይ የአገልግሎቱን ዘርፍ ለማዘመን ነበር፡፡ ለዚህ ማመሳከሪያው ሰውየው ከሃይንድ ውሃ ጀምሮ የተለያዩ አሻጥሮች ሲሰሩበት አልተመቼኝም ብሎ ወደ አሜሪካ አለመመለሱ፤ይልቅስ ለቁጥር የሚታክቱ ከየአቅጣጫው (ከመንግስት ባለስልጣን፣እስከ ማስታወቂያ ባሙያ) የሚመጡበትን ተግዳሮቶች (እስርን ጨምሮ)ተቋቁሞ እስካሁን መቆየቱ ነው፡፡ለምሳሉ ሆላንድ ካርስ የተባለው ኢትዮጵያዊ ኢንቨስተር፣የኢትዮጵያ አማልጋሜትድ ሊሚትድ በለቤት አቶ ገብረየስ ቤኛ በዚህ ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ምክንያት ስራቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ ኤርሚያስ ግን እየተሰቃየ የተቀመጠ ፅኑ ሰው ነው፡፡ ይህ አርዓያነቱ ዘመን ሲቀየር የሚያስመሰግነው እንጅ የሚያሳስረው መሆን የለበትም፡፡
2. አክሰስ ሪል ስቴትን አስመልክቶ ለተከሰሰበት ክስ ምክንያቱ መንግስት ድንገት  ግንባታን ማገዱ ሆኖ (ይህን ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄ ያለው ሰው ካለ ለማብራራት ዝግጁ ነኝ፤ወይም ኤርሚያስ ከሸገር ጋር ያደረገውን ቆይታ ማዳመጥ ይቻላል)  የእርሱ ጥፋት ተደርጎ፣ደባን እየወለደ መልካም ስሙ ጠፍቶ ጭራሽ ለእስር ተዳርጓል፡፡ ለእስር የተዳረገውም መንግስትን አምኖ መጥቶ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የእሱን ስም ከማጥፋት ጀምሮ የመንግስት ስልጣናቸውን እና ከባስልጣን ጋር  ያላቸውን ዝምድና ተጠቅመው ያለመውን የቤት እጥረት የመቅረፍ አላማ ዳር እንዳይደርስ ያደረጉ ሰዎች አሉ፡፡ ኤርሚያስ እነዚህን ሰዎች በስም ጠርቶ ተጠያቂ ለማድረግ የህግ ከለላ ስለሌለው ውንጀለኞችን ለመጠየቅ አልቻለም፡፡ አሁን ዘመን ተቀየረ ከተባለ እነዚህ ሰዎች ላጠፉት ጥፋት ተጠያቂ መሆን ሲገባቸው ጭራሽ እሱው ራሱ ለድጋሚ እስር መዳረጉ እጥፍ ድርብ ግፍ ነው፡፡
3. ከለውጡ በፊት በነበረው የኢህአዴግ አስተዳደር የተበደሉ ምሁራን ወደ ስራቸው ተመልሰዋል፣ማዕረግ የተወሰደባቸው ወታደሮች ማዕረጋቸው ተመልሶላቸዋል፣ጋዜጠኞች የተዘጋባቸውን ሚዲያ ከፍተው እንዲሰሩ ተደርገዋልን፡፡ ወደ ኤርሚያስ ሲመጣ ግን ይህ ነገር ሲደረግ አልታየም፡፡ለኤርሚያስ ለውጥ አልመጣም፡፡ የጠፋው መልካም ስሙን እንዲያድስ፣ ህልሙም እውን እንዲያደርግ፣ልምድ እና እውቀቱ የሚፈቅደለትን ያህል ሃገሩን እንዲያገለግል አልተፈቀደለትም፡፡ ዘመን ባንክ ያልከፈለው ገንዘቡ አልተከፈለውም፣የተጎዳው ሞራሉ አልተካሰም ጭራሽ ወደ እስርቤት ተወርውሯል፡፡
4. ኤርሚያስ ከዘመን ባንክ በመስራችነቱ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም አለማግኘቱ አንድ ነገር ሆኖ ባንኩን ለመመስረት ሲነሳ በርካታ ዘመናዊ አሰራሮችን አቅዶ ነበር፡፡ እነዚህ የአእምሮ ንብረቶቹ ተዘርፈው ሌሎች ባንኮች እንዲጠቀሙበት ሆኗል፡፡ ኤርሚያስ ዘመን ባንክን ለመመስረት አቅዶ አዳዲስ አሰራሮችን ከማሰቡ በፊት ባንኮች ለምሳ ሰዓት ይዘጉ ነበር፣ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ የውስጥ ስራ ለመስራት በሚል ለደንበኞች ይዘጉ ነበር፣ቅዳሜ አይሰሩም ነበር፡፡ ይህን ሁሉ የሚያስቀር ሃሳብ ያመጣው ኤርሚያስ ነበር፡፡ በተጨማሪም አሁን ባንኮች ሚጠቀሙባቸው የተለያዩ የክፍያ አይነቶች ለምሳሌ ኤም ብር አይነት ሃሳቦች ያመጣው ኤርሚያስ አመልጋ ነው፡፡ ነግር ግን ሃሳቡም ተዘርፎ፣ ገንዘቡንም እጥቶ ሞራሉ ተነክቶ እስርቤት ተወረወረ፡፡ ኤርሚያስ ከእስር ተፈትቶ ለዚህ ሁሉ አበርክቶው ምስጋና ሊሰጠው ይገባል፡፡
Filed in: Amharic