>
1:32 am - Saturday December 10, 2022

የሰሜኑ የመገለል ፖለቲካ እና ወቅታዊ የፖለቲካ ሥጋቶች!!! (አሰፋ ሀይሉ)

የሰሜኑ የመገለል ፖለቲካ እና ወቅታዊ የፖለቲካ ሥጋቶች!!!
አሰፋ ሀይሉ
“Right actions in the future are the best apologies for bad actions in the past.”
                      –  Tryon Edwards
 
* “አንድም ሁለትም ሆናችሁ ስሜን ብትጠሩ ፥ እነሆ ታጣፊ-ክላሼን ይዤ በመካከላችሁ እገኛለሁ!” ባይ ነበረ ህወኀት-መሩ መንግሥታዊ ፀረ-ነፃነት ፖሊሲ!
ቀደም ባለው ፅሁፌ በሀገራችን ሠፍኖ የቆየውን ያለፈውን ዘመን የመጥፋትና የመጠፋፋት ፖለቲካ ከህወኀታውያኑ “ደርግ በዘራችን ለይቶ ጠራርጎ ሊፈጀን ነው!” ከነሚለው ሥጋ የለበሰ ሃሳብና የግድግዳ ፖስተር ጋር ለአንባቢዎቼ እውነታውን አዋዝቼ ለማሳየት ሞክሬያለሁ።
አሁን በፖለቲካው ሜዳ ላይ ትልቅ ለውጥ አለ ከተባለ – በመጀመሪያ ተርታ የምጠቅሰው – ያ ችክ ያለ በረሃ-ወለድ ህወኀት-መራሹ የቀደመው ዘመን ፖለቲካ – ሰው ሰው በሚል – የእነ ዶክተር አብይ ፖለቲካ የመቀየሩ – መሆኑን፤ ሽግግር አለ ከተባለም ሽግግሩ በቀዳሚነት ፖለቲካችን ከድርቀት ወደ ልምላሜ የመምጣቱ ሽግግር – ከወዝ-አልባ ፖለቲካ ወዝ ወዳለው ሰዋዊ ፖለቲካ የተደረገ ታላቅ ሰብዓዊ ሽግግር መሆኑ እንደ ትልቅ ለውጥ መጠቀስ ያለበት መሆኑን በወፍራሙ አስምሬ አልፌያለሁ።
ለዛሬ ተመልሼ ልመጣ ቀጠሮ በያዝኩት መሠረት ይኸው መጣሁ። ስለ ወቅታዊው ህወኀታዊ የመገለል ፖለቲካ አካሄድ (ያገነገነ ተቃውሞ) እና ያ ስለሚያጭራቸው 6 ሀገራዊ ሥጋቶች ነገር ሳላበዛ እንደወረደ ባጭር ባጭሩ ለመጠቆም።
ወደዛሬው ፅሁፌ ከመሻገሬ በፊት ፖለቲካችን ሰው-ሰው ወደሚል ፖለቲካ ከመሻገሩ በመቀጠል – በእኔ ዕይታ – በሀገራችን የታየ ሌላው “ታላቅ!” ሊባል የሚችል ለውጥ – የዒላማ ለውጥ ነው። ወይም መንግሥታዊ የሆነ የሀገራዊ ፖለቲካዊ ግብ የተገላቢጦሽ ለውጥ (political auto reverse)  ልንለውም እንችላለን ይሄን ለውጥ።
ሀገራችን በቀደመው የህወኀት-መር የፖለቲካ ሜዳ – በበረሃም ሆነ በከተማ – የህወኀታውያኑ ጠብመንጃ ተነጣጥሮ የኖረው በተቃውሞ ብዕር ላይ ነበረ። “አንድም ሁለትም ሆናችሁ ስሜን ብትጠሩ ፥ እነሆ ታጣፊ-ክላሼን ይዤ በመካከላችሁ እገኛለሁ!” ባይ ነበረ ህወኀት-መሩ መንግሥታዊ ፀረ-ነፃነት ፖሊሲ።
እግዜርን በኮሚኒስትነታቸው ዘመን እርግፍ አርገው የጣሉ የህወኀት የጊዜ ጀግናዎች – አፍ አውጥተው እግዜርን እንሁን ማለት ነበር የቀራቸው። የአንድን ትልቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር – በውጭ ሀገር ሄደህ አብረህ አትታይ ካልኩህ ሰዎች ጋር ቁጭ ብለህ አይቼሀለሁ – ብሎ እስርቤት አጉሮ የሚያሰቃይ – ፀረ-ዕውቀት፣ ፀረ-ብዕር የሆነ የክላሽኒኮቭ ጌታ ነበረ ሀገሪቱን የሚመራት። ያ ሁላችንም የምናውቀው የአንድ የፖለቲካችን ዘመን ጥቁር ሌጋሲ ነው።
አሁን ያ ሽግግር መጥቷል ከተባለ – በቃ – ያ አፈሙዝ አሁን የለም። (ምንም እንኳ ከኢህአዴግ ማህፀን ቢወጡም!) – አሁን – በእነ ዶ/ር አብይ የመሪነት ዘመን ግን – አፈሙዞች በብዕርና ብዕረኞች ላይ አልተነጣጠሩም።
አሁን – አንተ ከፈለግከው ሰው ጋር እየተጨባበጥክ መግለጫ ልትሰጥ ትችላለህ። አሁን (ይኸው አሁን እየሰማን እንዳለነው!) “የአብይ መንግሥት እኔን አይወክለኝም ብለህ ቃልህን ለሚዲያ መላክ ትችላለህ። ማንም በሃጃህ አይገባብህም።
አሁን ነብርና ፍየል ሆነን እንዳልተፈጠርን – ሁላችንም በአንድ መስክ በነፃነት ለመቦረቅ የምንችልና የሚገባን የሰው ልጆች – በሀገራችን ከቆላ እስከደጋ ካሻን ወገናችን ጋር እፍፍፍ ክንፍፍፍፍ ለማለት የምንችል ነፃ የአንዲት ሀገር ወንድማማችና እህትማማች ዜጎች መሆናችንን – ቢያንስ በፕሪንሲፕል ደረጃ የተቀበለች የኢትዮጵያ ሀገራችን የፖለቲካ መሬት ላይ ነው እየተመላለስን ያለነው። ይኸው አሸባሪና ተሸባሪ አብረን አለን። ሳንጠፋፋ። ሳንፋጅ። የምን ፍጅት ነው???
እና በቃ – ሁለተኛው ለውጥ – ለእኔ – እንዲያ አፈሙዞች ብዕር ላይ ከሚያነጣጥሩበት የአዳፍኔ ዘመን ተሸጋግረን – እነሆ – በተገላቢጦሽ – እንዲህ ብዕሮች በአፈሙዞችና በጠብ-ነጂዎች ላይ ወዳነጣጠሩበት የምህረት ዘመን መሸጋገራችን ነው።
ያኔ ጠብ-መንጃዎቻችንን ብዕሮች ላይ አነጣጥረን እናቶችን ስለልጆቻቸው ተስፋ በማድረግ ፋንታ የብዙዎችን እናቶች የሀዘን እንባን አስነባናቸው። አሁን ደግሞ የእናቶቻችንን ለቅሶ የሰማ አምላካችን – የእናቶቻችንን እምባ በምህረት እጆች አበሰልን። የታሠሩ ተፈቱ። የተያዙ ተለቀቁ። የተጨነቁ እፎይ አሉ። የተሰደዱ ሀገራቸውን ረገጡ። የታገቱ ወዳሰኛቸው ሄዱ።
እነሆ የእኔ ትውልድ በዓይኖቹ እያዬ – ብዕር – ከ60ዎቹ የዘመነ ኢህአፓ ዋዜማ ወዲህ – ለመጀመሪያ ጊዜ – በኢትዮጵያ ምድር ላይ የነፃነት ነፍስ ዘርታ – በጠብ-መንጃዎች ላይ ፉከራዋን አሰማች!!! ብዕር አሁን ራሱ እልልታዋን አላቆመችም። ይኸው እልልልልልልልልልል….!!! ስትል አብሮ “እልልልልልል..!!!” ማለት ነው እንጂ ደሞ። ይሄ ታላቅ ለውጥ – ለውጥ ካልተባለ – ታዲያ ምን ነገር ለውጥ ሊባል ነው???!!
አቦ እንዲያውም – በቃ ለዛሬ – ስለ ወቅታዊ ሥጋቶች ያጋጀሁትን ሀሳብ ለነገ አሸጋግሬዋለሁ። ምክንያቱም የዚህን ዓይነት ታላቅ ሽግግር አውርቼ  በቀጥታ ወደ መዓትና ሟርት ማምራት የእምዬ ኢትዮጵያችንን አምላክ ማስቀየም ሆነብኝ። አለማመስገን። ለምስጋና እና ለደስታ የራሱን ጊዜ አለመስጠት። እና አሁንም ቀጠሮዬን ወደ ቀጣዩ ቀን አሻገርኩት።
አየህ። ደስ የተሰኘ ሰው ስትፈጥር – ክፉ ነገርን እንዳያመነጭ የምትከለክለው አንተ አይደለህም። እርሱ ራሱ ራሱን ይከለክለዋል። አምላክ በመልካም ይሉኝታው ከክፋት ሀሳብ የሚከለክለንን መንግሥት በምድራችን ያፅናልን።
በነገራችን ላይ – አንዴ ላለፈ ክረምት ያፈሰስከውን ውሃ እኮ – መልሰህ ያቺኑ ውሃ እፍስ አርገህ ውለዳት የሚልህ ማንም ወገን የለምኮ!!! ያለፈውን መመለስ አይቻልማ። ላለፈው ጥፋትህ ግን ቢያንስ አንድ ታላቅ የይቅርታ አማራጭ በእጅህ ተሰጥቶሀል። ዛሬህን እና ነገህን መልካም በመሥራት ለማሳለፍ ከወሰንክ – በቃ – ያ እኮ ነው ትልቁ ይቅርታ!!! ከዚያ በላይ ምን የይቅርታ መንገድ ይኖራል??
“Right actions in the future are the best apologies for bad actions in the past.” (- Tryon Edwards)
እስቲ ሁላችንን ክፋቱ ይብቃን። እና ጥሩ ለመሆን እየሞከርን እንኑር። እና እንሙት። ሞት እንደሁ አይቀር?! ታዲያ መልካምን መርጠን ብንሞትስ?! – አባቴ ይሙት .. በስንት ጣዕሙ!!!
ሁላችንን የነገ ሰው ይበለን። ትላንትን ተሻግረን ዛሬን፤ ዛሬን ተሻግረን ደግሞ ነገን ተነገወዲያን የምናይ ባለራዕይ ትውልዶች ያድርገን ፈጣሪ አምላካችን!!
አምላክ እምዬ ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር።
Filed in: Amharic