>

ጀግኖቻችን እና የፈረሶቻቸው ስሞቻቸው!!  (ዳዊት ከበደ ወየሳ) 

ጀግኖቻችን እና የፈረሶቻቸው ስሞቻቸው!! 
(ዳዊት ከበደ ወየሳ)
የአንዳንዶቹን ታሪካዊ ሰዎች ስም እነሆ ላካፍላቹህ ወደድኩ።
በቀደመው ዘመን የነበሩ አባቶቻችን ለሚዋጉበት ፈረስ ስም ይሰጠዋል። ስም ሰጪው ህዝቡ ሊሆን ይችላል፤ የጀግናውን ባህሪ በሚያንጸባርቅ መልኩ፤ ለፈረሱም ተመሳሳይ ስም ይሰጡታል። ብዙዎች የአጼ ቴዎድሮስን – አባ ታጠቅ፤ ወይም የቀዳማዊ ኃይለስላሴን – አባ ጠቅል… ፈረሶች እንደምታውቁ ይታመናል። የአጼ ቴዎድሮስ ፈረስ ስያሜውን ያገኘው፤ ንጉሡ እና ሰራዊታቸው ሁሌም በተጠንቀቅ ሆኖ ለዘመቻ ስለሚጠራ፤ ስንቅና ትጥቁን ዝግጁ አድርጎ ስለሚጠብቅ – ፈረሳቸው አባ ታጠቅ ተባለ።
ከነገሥታቱ ፈረሶች በተጨማሪ… የልጅ እያሱ፣ የበላይ ዘለቀ፣ የራስ ሃጎስ፣ የራስ ደረሶ፣ የደጃች ገረሱ ዱኪ፣ የደጃች አያሌው ብሩ ፈረሶች ስም ተጠቃሽ ነው። እንደው እንደዋዛ ለመጨዋወት ያህል ‘ያንዳንዶቹን ጀግኖች ስም ሳንጠቅስ ላለማለፍ ስንል  ይቺን ማስታወሻ አዘጋጀሁ። በነገራችን ላይ… ስያሜው “የፈረስ ስም ይባል” እንጂ፤ አንዳንድ የፈረስ ስም ዘመኑን ወይም የፈረሱን ባለቤት ባህሪ ጭምር ያንጸባርቃል። ለምሳሌ የምኒልክ ፈረስ አባ ዳኘው ሲባል፤ በዘመኑ አጼ ምኒልክ የዳኝነት እና የፍትህ ስርአት መዘርጋታቸውን ለማሳየት ጭምር ነው።
ሌላም ምሳሌ ልስጥ። ደጃች አያሌው ብሩ የፈረሳቸው ስም አባ ይርጋ ይባል ነበር። ከምኒልክ ዘመን ጀምሮ በልጅ እያሱም፣ በንግሥት ዘውዲቱም፤ ደጃዝማች ተብለው ከፍም ዝቅም ሳይሉ በዚህ ማዕረግ ብቻ ረግተው ብዙ ቆዩ። “የራስነት ማዕረግ ይሰጥዎታል” ተብለው ቤጌምድርን ሲያስተዳድሩ ቆይተው ከጣልያን ተዋግተው እና ታስረው ወጥተውም፣ በ1940 እስኪሞቱ ድረስ የደጃዝማችነት ማዕረጋቸው እንደረጋ ነበር የቆየው። እናም የፈረሳቸው ስም እንደሳቸው የደጃዝማችነት ማዕረግ በዚያው ረግቶ ስለቆየ፤ “አባ ይርጋ” ተብሎ ቀረ። ሚያዝያ 13፣ 1940 ዓ.ም በ60 አመታቸው እስከሚያርፉ ድረስ ደጃዝማችታቸው እንደረጋ አለፉ – አባ ይርጋ።
የጎጃሙ ራስ ደረሶ ደግሞ ጸብ ወዳድ ነበሩ። ከእምባቦ ጦርነት በፊት ከራስ ጎበና ጋር ጭምር ተዋግተዋል። ፈረሳቸውንም የሳቸውን ባህሪ ተከትሎ፤ “አባ ጠቦ” ተብሎ ይጠራ ነበር። አንዳንዴ ከፈረስ ስም ውጪ ህዝቡም የሚሰጠውን የፈረስ ስም መዘንጋት የለብንም። ለምሳሌ የእውቁ ጀግና ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የፈረስ ስም አባ መቻል ሆኖ ሳለ፤ በፍርድ አዋቂነታቸውና በጦርነት ግዜ መላ ስለማያጡ ህዝቡ እስካሁን “አባ መላ” በሚለው የፈረስ ስም ይጠራቸው ነበር።
በላይ ዘለቀ በፈረስ እየጋለበ ጦርነት ሲያካሂድ የነበረበትን ታሪክ ብዙም አናውቅም። ሆኖም የበላይ ዘለቀን ኮስታራነት የተመለከተው ህዝብ በላይ ዘለቀንም “አባ ኮስትር” ነበር ብሎ የሚጠራው – በ1937 አዲስ አበባ ውስጥ፡ በስቅላት መገደሉ ሳይዘነጋ።
አባ ፈንቅል ደግሞ የትግራዩ ራስ ሃጎስ ፈረስ ስም ነው። (አንዳንዶ ይህንን ስም ለጄ/ል ኃየሎም አርአያ ሲጠቀሙበት ታዝበናል) ብዙዎች በታሪክ የምታውቋቸው ራስ አሉላ አባነጋ በዶጋሊ እና ሰሐጢ ላይ ዬሩትን ታላቅ ገድል እንጂ ስለአሟሟታቸው ብዙም አናውቅም። ራስ አሉላ አባ ነጋ – ከአባ ፈንቅል ጋር በተራ የድንበር ጸብ ምክንያት ጦርነት ገጥመው ነው የሞቱት። የሞቱትም ጥር 10፣ 1891 ነበር።
የኦሮሞው ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ የፈረስ ስም ደሞ አባ ቦራ ነበር። በነገርዎ ላይ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፤ በአምስቱ አመት የጣልያን ወረራ ወቅት ከሸዋ እስከ ጅማ፤ ከጅማ እስከ ኢሉ አባ ቦር ድረስ እየተዘዋወሩ ብዙ ጀብዱ የፈጸሙ ጀግና ናቸው። እንደአያሌው ብሩ በደጃዝማችነት ማዕረግ መቅረታቸው ቅር እንዳላቸው ነው የሞቱት። ታዲያ እሳቸው የ’ራስነት ማዕረግ እንዲሰጣቸው ሳይሆን የፊታውራሪነት ማዕረግ ነበር የፈለጉት። ፊታውራሪነት በተለይ ለጦር መሪ የሚሰጥ ማረግ ሲሆን፤ የፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ፈረሰኛም ሆነው በጦር መሪነት ብዙ የሰሩ ነበሩ – ደጃዝማች ገረሱ በ1958 ነው የሞቱት።
አንዳንድ ግዜ ደሞ የፈረሱን ስም እንደ አባት ስም ሲጠሩበት እናያለን። ለምሳሌ የራስ አሉላ ፈረስ – አባ ነጋ ነው። ህዝቡ አሉላ ቁምቢ ማለቱን ትቶ – አሉላ አባ ነጋ ይላቸዋል። የራስ ባልቻ አባት ስም ሳፎ ሲሆን፤ የፈረሳቸው ስም አባ ነፍሶ ነው።  አንዳንድ ሰዎች “ባልቻ አባ ነፍሶ”ይሏቸዋል። ታዲያ ዘፋኙ ሳይቀር – “ባልቻ አባቱ ነፍሶ” ብሎ ሲያንጎራጉር ሰምተናል።
ጨዋታችንን ለማጠቃለል ያህል የአንዳንዶቹን ፈረሶች ስም ልንገራቹህ። የጀግናው ፊታውራሪ ገበየሁ ፈረስ – አባ ጎራው፤ የእውቁ ጀግና አቶ በዛብህ ፈረስ – አባ ድክር፤ የራ መንገሻ ዮሃንስ – አባ ገድብ፤ የራስ ጎበና ዳጨ ፈረስ – አባ ጥጉ፤ የደጃዝማች በየነ መርድ ፈረስ አባ ሰብስብ ይባላል። እንዲሁም የልጅ እያሱ አባት – ንጉሥ ሚካኤል፤ ለፈረሳቸው የሰጡት ስያሜ “አባ ሻንቆ” የሚል ነበር።
እንዳላሰለች በማለት… በመጨረሻ የልጅ እያሱ ፈረስን አስታውሼ በዚሁ ላብቃ። ልጅ እያሱ በነገሱበት ወቅት አገሩ ሁሉ ከዳር እስከ ዳር ሰላም ሆኖ ነበር። አገር ሰላም ሲሆን ደግሞ ስለፍቅር እና ስለጤና ነው የሚወራው። እናም በዚህ የሰላም እና የጤና ዘመን ላይ የደረሱት ልጅ እያሱ፤ ፈረሳቸውም አባ ጤና ተባለ። አባ ጤና ጋራ ሙለታ ታስረው ከቆዩ በኋላ ህዳር 12 ቀን 1928 ዓ.ም. ሲገደሉ 39 አመታቸው ነበር። የአባ ጤናን ነፍስ ይማር – ለናንተም ጤና ይስጥልን።
Filed in: Amharic