>

"ተወረናል" ከሚል ጭንቀትና ዛሬ ቀኑ የኛ ነው "መጤ" ን እናፈናቅል የሚል ትምክህት ነገ ላይ አደጋ አለው!!! (አቶ ሙሼ ሰሙ)

“ተወረናል” ከሚል ጭንቀትና ዛሬ ቀኑ የኛ ነው “መጤ” ን እናፈናቅል የሚል ትምክህት ነገ ላይ አደጋ አለው!!!
አቶ ሙሼ ሰሙ
——–
ለገጣፎ ዛሬ የደረሰችበት ቦታ ለመድረስና እንዲህ አነጋጋሪና አጓጊ ከተማ ለመሆን የበቃችው በርካቶች ገንዘባቸውን ጊዚያቸውንና ጉልበታቸውን አፍስሰውባት ነው።
በተለይ ደግሞ፣ ዛሬ ላይ ቤታቸው እየፈረሰ ያሉና የደም እምባ የሚያፈሱት የከተማዋ ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች ከቃለ ምልልሳቸው እንደተገነዘብኩት ካለፉት 10 ዓመታት ጀምሮ በተንጠባጠበ መንገድ ቦታ እየገዙ ግንባታ በማካሄድ የሚኖሩ ናቸው።
መንግስት የሾማቸውን የከተማዋ አስተዳዳሪዎች፣ ሕግን እና መንግስትን ተማምነው ቦታ ገዝተው፣ ቀን በጠራራ ጸሃይ ማታ በቁር ከአራዊት ጋር ታግለው አካባቢያቸውን በማልማት በሂደትም እውቅና አግኝተው ግብር እየከፈሉ፣ የመብራትና የውሃ አገልግሎት እየቀረበላቸው መለስተኛዋን ከተማ ለዛሬ ደረጃዋ ያበቁ ናቸው።
እነዚህ ነዋሪዎች ዛሬ ላይ በድንገት ጊዜ ፊቷን አዙራባቸው ንብረታቸው ሲፈርስ፣ ቢያንስ ቢያንስ ሃገራችን ፍትሕ ፊት ለመቅረብ እንኳን እድል መንፈጓ እና ንብረታቸው መፍረሱ ሳያንስ በየመገናኛ ብዙሃኑ ሕገ ወጥ እየተባሉ መወንጀላቸው ሁለት ሞት እንዲሞቱ አድርጓቸዋል ።
ሕጋዊና ሕገ ወጥ እነማን ናቸው።
በዚህ ድርጊት ውስጥ “ሕገ ወጥነት” ከተነሳ የአንድ ወገን ተግባር ብቻ እንዳልነበረ ተፈናቃዮች በቂ መረጃ አቅርበዋል። በርካቶች የተሳተፉበትና የተቀናጀ እንደነበረ መገመት ይቻላል። ግንባታ ፈቃጁ፣ ግንባታ ሲካሄድ በሙስና አይኑ በቸልተኝነት ሂደቱን የተመለከተው፣ ሻጭ፣ ውል አዋዋይ፣ የመብራትና ውሃ አገልግሎት እንዲያገኙ መረጃ የሰጠና የፈቀደው፣ መስመር የዘረጋው፣ አገልግሎቱን ያቀረበው፣ የነዋሪነት መታወቂያ የሰጠውን ጨምሮ በርካቶች እኩል ተጠያቂ ናቸው።
ማንኛውም ግብይት የተፈጸመበት፣ የገንዘብ ልውውጥ የተደረገበት፣ አግባብነት ባለው አካል የተመዘገበና እውቅና ያገኘ ቦታ ካርታ ኖረውም አልኖረውም ህጋዊ ነው።
በተለያየ ምክንያት ሕጋዊነቱ የማይጸና ቢሆን እንኳን ሕጋዊነቱን አምኖ እውቅና የሰጠውና ሽያጬን ያመቻቸው (በቸልተኝነትም ቢሆን) መንግስታዊ አካል ለገዢው ወጭውን መሸፈንና ለደረሰበት ውጣ ውረድም ተገቢውን ካሳ መክፈል ይኖርበታል።
ይህ እንግዲህ ተግባራዊ የሚሆነው ቀደምት ነዋሪ ነኝ በማለት ቦታውን የሽጠውና በገንዘቡ የተጠቀመው እንዲሁም ሃብቱን ያፈሰሰውና ”መጤ” የሚባሉት ዜጎች በእኩልነት የሚታዩባት አገር ከሆነች ብቻ ነው።
የዛሬ 10 ዓመት 50 ሺህ ብር የተሸጠ ቦታ፣ አካባቢው ሲለማና ሲለወጥ ዋጋው በእጥፍ ሊያድግ እንደሚችል ይታወቃል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ግሽበት በከፍተኛ ደረጃ በሚያጠቃቸው ሃገራት ደግሞ የገንዘብ የመግዛት አቅም ቆሞ የሚቀር አይደለም። ከዓመት በፊት የነበረ 100 ብር ዛሬ ላይ 1000 ብር ወይም ከዛ በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ፍትሕና ርትዕ ከሌለ፣ ውልና ስምምነትን ማስከበር ካልተቻል፣ ይህ ልዩነት እንደሚያጓጓና ማብቂያ የሌለው ቦታው ድሮ የኔ ነበረ። ያኔ የሸጥኩበት ገንዘብ ትንሽ ስለሆነ ክልሉ ቦታውን ያስመለስልኝ የሚል ውዝግብ እንደሚቀሰቅስ ግልጽ ነው።
ከተማው በዚህ ስሌት ውስጥ ሆኖ “ተወረናል” በሚል መንፈስ ወደ ማፈናቀል ከተገባ ከሕጋዊነት፣ ከገንዘብ የመግዛት አቅም ስሌት፣ ከሰብአዊነትም ሆነ ከካሳ ክፍያና ከሞራል አኳያ ሲታይ ፍጹም ፍትሐዊነት የሚጎድለው አሳፋሪ ተግባር ሊፈጸም እንደሚችል ጥርጥር የለውም።
መንስኤው ከሕግ አኳያ ተጠያቂነቱ አንዱ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ከሆነ፣ ከሞራልና ከፍትሕዊነት አኳያ ርህራሄ የሌለውና ካሳ ለመካስና ጊዜ ለመስጠት ንፉግ ወሳኔ ነው።
እነዚህ ዜጎችን በዚህ ሁኔታ ማፈናቀል ለምን አስፈገ ?
ግምቶች
1) የከተማው መስተዳድር እያወቀው ነዋሪዎቹ ግዢ ፈጽመው ተመዝግበው ፈቃድ ቢያገኙም “መጤዎች” በሚል በሕገወጥነት ስም በመንቀል እንደገና ነባር ለተባሉት ለመስጠት አሊያም “ለግሪን ኤርያ” ማዋል ስላስፈለገ።
2) ሰሞኑን አዲስ አበባን አስመልክቶ የተነሳውን ሁለ ገብና ጠንካራ ሙግት ለመበቀልና በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘንድ ፍርሃት ለማንገስ በማሰብ (መሰል ድርጊት ከዚህ ቀደም ተዘግቧል።)
3) ቀጣዮን ምርጫ ለማሸነፍ ሲባል ኦሮሚያ ውስጥ በሕዝብ ዘንድ ልዩ ስሜት በመፍጠር ተቀባይነትን ለማግኝት ሊሆን ይችላል።
4) ተወረናል ከሚል የመንፈስ ጭንቀትና ዛሬ ቀኑ የኛ ነውና “ለመጤ” መልስ ለመስጠት አንገደደም ከሚል ትምክህት የመነጨ ሊሆን ይችላል።
የዘር ፖለቲካ እንደ ሊስትሮ እቃ ኮተቱ የበ፤ በመኪና እንደተገጨ ሰው ድኖ የማይድን ልክፍት ነው።
ለማንኛውም፦ በንቃት
“ወደኃላ ሄደሽ በሃሳብ ከማለም
ቀኑ እንዳይመሽብሽ ትናንት ዛሬ አይደለም” ማለት ያስፈልጋል።
Filed in: Amharic