>

የህጋዊ ስደት ትሩፋቶች (ከአሸናፊ በሪሁን)

የህጋዊ ስደት ትሩፋቶች

ከአሸናፊ በሪሁን

የባሪያ ንግድ ከቆመ ከክፍለ ዘመናት በኃላ ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካውያን ውንድሞቻችን አንገታቸውን በገመድ ታስረው እንደ እንስሳ ሲሸጡ እንደ ማየት ልብን የሚሰብር አሳዛኝ ድርጊት የለም ፡፡ ባለፈው 2017 ሲኤንኤን የተሰኘው የአሜሪካ የቴሌቪዝን ጣቢያ ሊቢያ ውስጥ በሰራው ድብቅ የምርመራ ሪፖርት አንድ አፍሪካዊው ወጣት በአራት መቶ የአሜሪካ ዶላር ሲሸጥ የሚያሳየውን ምስል መታየቱን ተከትሎ ብዙ አፍሪካውያንን ቢያስቆጣም ወቅታዊ የከበሮ ምቱ ጎልቶ ከመሰማት ውጪ ያስከተለው ለውጥ አለ ለማለት አያስደፍርም ፡፡

ይህ ህገ ወጥ ስደት የወለደው እና በአፍሪካ ሰማይ ስር በአፍሪካውያን ላይ እየደረሰ ያለው የዜጎች ስቃይ ማሳያ ቢሆንም ዛሬም ይህን እየሰሙ አና እያዩ የስደት በርን የሚያንኳኩት አፍሪካውያን ቁጥር አልቀነሰም፡ ዛሬም እኛም ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ሁሉንም እያነጋረ ያለው እና ማህበራዊ ቀውስ እያስከተለ ያለው ጉዳይ ህገ ወጥ ስደት ያስከተለው መዘዝ እና ችግር ነው፡፡ ዛሬም በህገ ወጥ መንገድን ተከትለው ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ የሄዱ በህይወት የተረፉት ስደተኞች አገራቸውን ጥለው የወጡበትን ቀን እየረገሙ ና ቤተሰቦቻአውን እየናፈቁ «እያነቡ እስክስታ» በሚሉት አይነት ፈሊጥ ኑሮቸውን እየገፋ ነው፡፡ በህጋዊ እና ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድን መሄድ እያለ ህገወጥ እና ደህንነነቱ ባልጠጠበቀ መንገድን መርጦ የመሄድ ትሩፋቱ ጥቃት፣ ስቃይ እና ሞት ነው፡፡ በአንፃሩ በህጋዊ መንገድ የሚሄዱ ስደተኞ ች ግን ደህንነታቸው ተጠብቆ እና መብታቸው ተከብሮ የሚሰሩት ስራ የራሳቸው እና የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ከማሳደግ አልፎ ለሀገርም ያለቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡

አፍሪካውያን ስደተኞች የአህጉሩን ኢኮኖሚ እድገት ለመጨመር አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆናቸውን በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያመላክታል። እንደ ሪፖርቱ በአፍሪካ ውስጥና ከአህጉሩ ውጭ የሚንቀሳቀሱ 41 ሚለዮን የተመዘገቡ የአፍሪካ ስደተኞች ከሚያገኙት ገቢ 85 በመቶውን ወደ አገራቸው ፈሰስ ያደርጋሉ።ከእነዚህም መካከል 19 ሚሊዮኑ ማለትም (53 በመቶ ) ያህሉ በአፍሪካ ውስጥ የሚደረግ ፍልሰት ሲሆን 17 ሚሊዮኑ ደግሞ አፍሪካን ለቀው ወደ ሌላው አለም የተሰደዱ ናቸው።

ስደተኞቹ የራሳቸውን ዕውቀት ከማሳደግ ባለፈ ከሚገኙበት አገር በሚልኩት ገንዘብ፣ ኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጅ ሽግግርና ያገኙትን ልምድ በማካፈል አገራቸውን ኢኮኖሚ በመደገፍ የድህነት ምጣኔ ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋኦ እያደረጉ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም በሚሄዱበት አገር የስራ ቦታ ክፍተትን በመሙላት ያግዛሉ። በውጭ የሚኖሩ ስደተኞች የአፍሪካን ባህልና ልዩ ምርቶች ለመላው አለም በማስተዋወቅም ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ ኮትዲቭዋር፣ ጋና፣ ርዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ ከስደተኞች በሚመነጭ ገንዘብ ተጠቃሚ የሆኑ አገሮች መሆናቸውን በምሳሌነት ይጠቀሳል።

3 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የዓለም አገራት ውስጥ እንደሚኖሩ መረጃዎቹ ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው በሚልኩት ገንዘብ( Remittance) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ 2010 ከሪሚታንስ 1 .9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያገኘች ሲሆን በ 2017 ገቢው ወደ 4.6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ብሏል። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ሪሚታንስ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አለው፡፡ከውጪ የሚላከው ገንዘብ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 5% የሚሆነውን የሚሸፍን ነው፡፡በርግጥ ይህ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው፡ ለምሳሌ ላይቤሪያ በስደት በውጭ ከሚገኙ ተወላጆቿ የምታገኘው ገንዘብ ከአገሪቱ ጠቅላላ ምርት 26 ነጥብ 7 በመቶውን ሲይዝ ሌሴቶም 18 ነጥብ 2 በመቶ የሚሸፍን ነው፡፡ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ የሚላክላቸውን ዜጎች ከፍተኛ መሆኑ የኢትዮጵያ ከሪሚታንስ የሚጠበቀውን ያህል እንዳታገኝ አድርጎል ፡፡

አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ከሚኖሩባቸው ሀገራት ቀዳሚዎቹ አሜሪካ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ጣልያን ሲሆኑ ከፍተኛ ገንዘብ የሚላከውም ከእነዚሁ አገራት ነው። ባለፈው 2017 ከአፍሪካ ናይጄሪያ 21 እንዲሁም ግብፅ 20 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በማግኘት ከአፍሪካ ቀዳሚ አገራት መሆናቸው የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል። ሕንድ 69 ቢሊዮን ዶላር፣ ቻይና 64፣ ፊሊፒንስ 29 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከሪሚታንስ ገቢ በማግኘት ከዓለም ከአንድ እስክ አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።ይህም በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ህጋዊ በሆነ መንገድ ከተሰማራ ሀገራቸው ከ’ሪሚታንስ’ ከፍተኛ ገቢ እንደምታገኝ በጥቂቱ ማሳያ ነው ፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ አገር የስምሪት አዋጅ ተመርቶ በህዊ መንገድ ወደ ውጭ የስራ ስምሪት ማድረግ ራስን ከአደጋ ቤተሰብን ደግሞ ከሃሳብና ከሰቀቀን ይታደጋል ።ይህም ለራስ፣ ለቤተሰብ እና ለሀገር ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው፡፡

(አሸናፊ በሪሁን seefar በተሰኘ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጀት ውስጥ የሚዲያ ባለሙያ ናቸው)

Filed in: Amharic