>
10:51 am - Sunday May 22, 2022

ምኞትን ማመን!!! (የሽሀሳብ አበራ)

ምኞትን ማመን!!!
የሽሀሳብ አበራ
* ” አቶ ለማ መገርሳ መታወቂያ ላይ ብሄር የሚለውን አሰረዙ፡፡”፣” ጠሚዶ አብይ  ሀገሪቱ በፕሬዝዳንታዊ ስራዓት እንድትመራ አዘዙ፡ “፣ የብሄር ልዮነት ሙቶ  ምስራቅ አፍሪካ በፍትሃዊነት አንድ ላይ ልትደመር ነው፡፡”  እያሉ የምኞት ህልም ከማኘክ ገሃዱን  ማጣጣም ይሻላል!!!
—-
 ከድህረ ትህነግ (post tplf) በኃላ ያለውን ጊዜ ብዙው ህዝብ የሚመኘውን እንደሚደረግለት አምኗል፡፡ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ህዝቡ  በምኞት ቀውስ ውስጥ ወድቋል የሚል ገራሚ መረዳታቸውን ለቢቢሲ አቅርበዋል፡፡ አዎ፡፡ትናንትም  ሆነ ዛሬ ህዝብ ምኞቱን እያመነ ራሱን ለአምባገነን መሪዎች አመቻችቷል፡፡
….
የዜግነት አቀንቃኞች ጠሚዶ አብይ ያላሰቡትን፣ሊያስቡትም የማይችሉትን፣ሊሆን የማይችለውን የዜግነት ፖለቲካ ጠሚው ሊያስጀምሩ ነው እያሉ የመልካዓምድራዊ አከላልን ካርታ ሲሰሩ ከርመዋል፡፡ ጠሚዶ  አብይ የብሄር ፌዴራሊዝምን  ያስቆማሉ እያሉ  በምናብ ሲወናጨፉ  ባጅተዋል፡፡  ምኞት እና ምናባዊነት የኢትዮጵያ  ፖለቲካ ህመሞች ናቸው፡፡ ጠሚዶ አብይ የብሄር ፌዴራሊዝሙን ከመቀየራቸው በፊት በድሬድዋ ያለውን የ 40:40:20 አፓርታይድ  ስራዓት፣በሀረር የተዋቀረውን 50:50 ፍፁማዊ አፓርታይዳዊነት እንዲቀየር የወተወተ ብዙ የለም፡፡ ሰው ምኞቱን አምኗልና፡፡ በ 21 ኛው መቶ ክፍለዘመን በዓለም  የገነነ አፓርታይድ የሰፈነባት  ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ ህዝቡ ግን ተደላድሎ  በምኞቱ ያድራል፡፡  በኢትዮጵያ  ያለው አፓርታይድ  ስራዓት በደቡብ አፍሪካ እና በእንግሊዞች  መካከል እንደነበረው የቅኝ ግዛት ዘመን ነው፡፡ግን ህዝብ ምኞቱን አምኖ ባሪያነቱን   ይክደዋል፡፡
 …
ለዚህ ነው ኦዴፓ በብሄር ፌዴራሊዝሙ አልደራደርም ሲል ብዙዎች የደነገጡት፡፡በእርግጥም ከብሄር ፌዴራሊዝሙ ይልቅ የአፓርታይድ  ስራዓቱ እንዲወገድ መሞከር ይሻል ነበር፡፡ ጠሚዶ አብይ  የኦዴፓ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኝነት አቀንቃኝ ናቸው፡፡ የኦዴፓ ባህሪ የጠሚዶ አብይም መገለጫ ነው፡፡ ጠሚዶ አብይ የኦሮሞ ብሄርተኛ ካልሆኑ የኦዴፓ ሊቀመንበር አይሆኑም፡፡ ግን ሰው ምኞቱን አመነውና የዜግነት  ፖለቲካ አቀንቃኝ ናቸው አለ፡፡
 ደርግ ጨቋኝ ስለነበር ትህነግ ሲገባ ህዝቡ ወዶ ተቀበለ፡፡ ትህነግ ጨቋኝነቷን ያየ ህዝብ ደግሞ ትህነግን ያጣጣለውን መሪ ሁሉ ወደደ፡፡  የፖለቲካ መለኪያው ትህነግን መጥላት ብቻ ሆነ፡፡ ትናንትም የደርግ ሰው ለመሆን ጃንሆይን፣ የትህነግ ኢህአዴግ ሰው ለመሆን ደርግን መጥላት ግድ ነበር፡፡
 “ህዝብ የሚወደውን እየተናገርክ፣ አንተ የምትወደውን አድርግ፡፡” በሚለው የማካቬላዊ የሴራ ፖለቲካ  መርህ መሰረት ህዝብን ለመንዳት ቀላል ነው፡፡ ህዝብ የሚመኘውን እየተናገሩ የሚመኙትን መስራት   ለሴራ ፖለቲከኞች አዋጭ ነው፡፡
 …
በእርግጥ ህዝብ በጅምላው  የተለየ ነገር አያስብም፡፡ ህዝብ በሊሂቃን -elite  ይመራል፡፡ይቀረፃል፡፡ ክፋቱ ግን ሊሂቃኑም ምኞቱን ያምናል፡፡ ምኞትን ማመን ትልቁ ክፋቱ አንተ ሳትሰራ፣ ለውጥ ከሌላ እንድትጠብቅ ማድረጉ ነው፡፡ ብዙው ፖለቲካዊ ለውጥን ይመኘዋል እንጂ ራሱ ለመለወጥ አይሰራም፡፡ ስለዚህ የህዝቡ የስልጣን እና የፖለቲካ አረዳድ በሊሂቃኑ ሊሞረድ ይገባል፡፡ ለአፓርታይድ እና ለፀረ ዲሞክራሲ የተመቸ ህዝብ ሁሉ ምኞቱን ያምናል፡፡ ወዳጀ ምኞትህን አትመነው!! ምናባዊ ያደርግሃል፡፡ የምኞትህን  አንተ ስትሰራው ብቻ እመነው፡፡ የምኞት ቀውስ እና ቁስለት ደግሞ ቶሎ አይፈወስም፡፡
 …
 ” አቶ ለማ መገርሳ መታወቂያ ላይ ብሄር የሚለውን አሰረዙ፡፡”፣” ጠሚዶ አብይ  ሀገሪቱ በፕሬዝዳንታዊ ስራዓት እንድትመራ አዘዙ፡ “፣ የብሄር ልዮነት ሙቶ  ምስራቅ አፍሪካ በፍትሃዊነት አንድ ላይ ልትደመር ነው፡፡”  እያሉ የምኞት ህልም ከማኘክ ገሃዱን  ማጣጣም ይሻላል፡፡ በአዲስ አበባ እንደ ሀረር እና ድሬድዋ የአፓርታይድ  ስራዓት እንዳይገነባ ከመታገል ይልቅ ደግ ምኞትን ብቻ  እያኘኩ ማደር  መፍትሄ አይሆንም፡፡
….
ተግባርህ እንጂ ምኞትህ እውነት አይደለምና ምኞትን አትመነው፡፡ ተጠራጠረው !!
Filed in: Amharic